Tuesday, February 20, 2024

የፀጥታ ሥጋት ያጠላበት መጪው መርጫ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላላ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቅበት ይህ ዓመት ከመጀመርያውም በክስተቶች የተሞላ ሆኗል፡፡ በአብዛኛዎቹ ከፖለቲካው መንደር በሚፈጠሩ ክስተቶች ምክንያት እንዲህ ባለ ሁኔታ እንዴት ነው ጠቅላላ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችለው የሚለው ዓብይ ጥያቄ ጎልቶ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡

የፖለቲካው ተዋናዮች፣ ‹‹ጠቅላላ ምርጫው ከዚህ ዓመት ማለፍ የለበትም፤›› በሚለው፣ ‹‹አሁን ባለንበት አገራዊ አለመረጋጋት፣ እንዲሁም ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰን ሐሳባችንን ለመራጩ ኅብረተሰብ ሳናቀርብና ከመራጮች ጋር ሳንወያይ ማካሄድ የለበትም፤›› በሚሉ ሁለት ጎራዎች ተከፍለው በመነታረክ ላይ ናቸው፡፡

ይህ ምርጫ ‹‹በጊዜው ይካሄድ››፣ ‹‹የለም መራዘም አለበት›› የሚለውን ሙግት ምንም መፍትሔ ባላገኘበት በዚህ ወቅት ግን ምርጫው መቼ ይካሄድ የሚለው ላይ እንጂ መካሄዱ አይቀሬ መስሏል፡፡ ለዚህም እንደ ዋነኛ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ ለባለድርሻ አካላት ያቀረበው ጊዜያዊ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ነው፡፡

ምንም እንኳን የምርጫ ማከናወኛው ዕለት ጊዜያዊ መሆኑ ቢገለጽምና ወደ ፊት ቁርጡ እንደሚገለጽ ቢታወቅም፣ ምርጫው ‹‹አይካሄድ›› ለሚሉ ወገኖች ምርጫ ቦርድ ይህን ውሳኔ ማሳለፉ በአገሪቱ ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡  

አሁንም ቢሆን ግን ምርጫው ‹‹ይካሄዳል? አይካሄድም?›› የሚለው ጥያቄ መቋጫ መፍትሔ አላገኘም፡፡ ከዚህ አንፃር ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ማድረጉ ውይይቱን ወደ ምርጫው ማከናወኛ ዕለት መግፋቱን በመጥቀስና ቦርዱ ዘንድሮ ምርጫ እንደሚካሄድ የተሰጠ ውሳኔ አድርገው በመውሰድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ቦርዱን እየኮነኑ ሲሆን፣ አሁንም ለዝርዝር ውይይት በሩን ክፍት እንዲያደርግና ውሳኔውን እንዲያጤን በመወትወት ላይ ናቸው፡፡

ከዚህ በተቃራኒ የቆሙና ምርጫው ‹‹መካሄድ አለበት›› የሚሉ ወገኖች ደግሞ፣ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ መቼ እንደሚሻሻል የሚያረጋግጥ ነገር አለመኖሩን በማውሳት አገር እስኪረጋጋ ምርጫው ‹‹ይራዘም›› ወይም ‹‹ይዘግይ›› ማለት፣ ሕገወጥነትን ማበረታታት፣ ብሎም ቅቡልት የሌለው መንግሥት አገሪቱን እንዲመራ መፍቀድ በመሆኑ፣ ምርጫው ከዚህ ዓመት ማለፍ የለበትም በሚለው አቋማቸው በመፅናት ወይ ፍንክች ያሉ ይመስላሉ፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን በአብዛኛው ምርጫው ይራዘም በሚሉ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚነሳው መከራከሪያ፣ አሁን ያለው መንግሥት ‹‹ከየት ያገኘውን ቅቡልነት እንዳያጣ ነው የምንሠጋው?›› የሚል ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ምርጫ 2007 ዓ.ም. በተካሄደ ማግሥት ሕዝባዊ እንቢተኝነት አይሎ መቶ በመቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን የተቆጣጠረውን ገዥው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መፍረክረክን በማስታወስ፣ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው አካል ከመነሻው ቅቡልነት ያልነበረው በመሆኑ፣ አሁንም ምርጫ በማካሄድ የሚያገኘው ቅቡልነት ባለማካሄድም የሚመጣበት የቅቡልነት ቀውስ አይኖርም በማለት ሙግታቸውን ያጠናክራሉ፡፡

ከዚህ ባለፈም ኢሕአዴግን ወደ ደረሰበት ውስጣዊ ልዩነት፣ እንዲሁም አዲስ አመራር ከውስጡ እንዲወጣ ያደረገው ጉዳይ የተራዘመ የሕዝቦች መሠረታዊ የመብት ጥያቄዎች፣ ማለትም የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር፣ ሥር የሰደደ የወጣቶች ሥራ አጥነትና ተያያዥ ጉዳዮች እንጂ፣ ምርጫ ማድረግ ወይም አለማድረግ አይደለም በማለት ይሞግታሉ፡፡

በዚህም መሠረት ከ2007 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት ጀምሮ የተፈጠሩ ሕዝባዊ ጥያቄዎች የት ደረሱ? የተነሱት መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል ወይ? አግኝተው ከሆነ እንዴት? ካልሆነ ደግሞ ለምንና እንዴት መመለስ አቃተን? የሚሉትን መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች በቅጡ ሳንመልስ ወደ ምርጫ መግባት ችግሮቹን ከማባባስ ባለፈ፣ በአገሪቱ ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋን መጋበዝ ነው በማለት ሥጋት አዘል አስተያየታቸውን ይነዝራሉ፡፡

እነዚህን ዓይነት መሠረታዊ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን እያስተናገደ የሚገኘው መጪው አገራዊ ምርጫ የ‹‹መካሄድ›› እና ‹‹አለመካሄዱ›› ዕጣ ፈንታ ግን አሁንም ሾላ በድፍን ይመስላል፡፡ ምርጫው መካሄድ አለበት የሚሉት ወገኖች፣ ሁኔታውን ከሕጋዊነት ማዕቀፍ አውጥተው በመካሄዱ የሚገኘው ትሩፋትና አገራዊ ጥቅም ምን ሊሆን እንደሚችል ማብራራት ላይ እምብዛም ናቸው፡፡

በተለይ በአገሪቱ የሚታየው የሰላምና ፀጥታ መደፍረስ፣ እንዲሁም ደግሞ መንግሥት እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ላይ የሚወስደው ዕርምጃ የተለሳለሰ መሆንና ነገሮችን በትዕግሥት ለመፍታት የሚሄድበት ርቀት እያስተቸው በሚገኝበት ወቅት ላይ፣ ይህን ተዘዋውሮ መቀስቀስና ማደራጀት የሚጠይቀውን የምርጫ ጉዳይ እንዲሁ ዘው ብሎ መግባቱ አደጋው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል የሚያስጠነቅቁ በርካቶች ናቸው፡፡   

በምርጫ ምክንያት በሚፈጠር ቀውስ ሳቢያ የአገር ህልውና አደጋ ውስጥ ሊወድቅ፣ ባስ ሲልም ወደ መበታተን ያደርሰናል ብለው ከሚሠጉት ፖለቲከኞች አንዱ የኢዴፓው አቶ ልደቱ አያሌው ሲሆኑ፣ ይኼንን አቋማቸውን በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲያቀርቡ ተስተውሏል፡፡

ይኼንን ሐሳባቸውን ከማቅረብ በዘለለም በቅርቡ ከሌሎች ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ይህን ሐሳብ የሚሞግት፣ እንዲሁም ‹‹እውነተኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት›› መገንባት የሚያስችል አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰኘ የፖለቲካ ጥምረት አቋቁመዋል፡፡

አብሮነት የዛሬ ወር ገደማ በኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኅብር ኢትዮጵያ)፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) አማካይነት የተመሠረተው ጥምረት የዘንድሮ ምርጫ በምንም ዓይነት ሁኔታ መካሄድ የለበትም ብሎ የሚሞግት ስብሰብ ነው፡፡

ስብስቡ፣ ‹‹አገራችን ለገጠማት የፖለቲካ ቀውስ መነሻ ምክንያት ለሆኑ መዋቅራዊ ችግሮቻችን ትርጉም ያለው መዋቅራዊ መፍትሔ ለመስጠት ሙከራ ባልተደረገበት፣ በተካረሩ የጽንፍ አመለካከት ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ብሔራዊ ዕርቅ ሳያካሂዱና በብዙ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ባልተፈጠረበት ሁኔታ፣ በጥድፊያ ወደ አገራዊ ምርጫ ለመግባት እየተደረገ ያለው ሙከራ የተጀመረው የለውጥ ሒደት ተስፋ አስቆራጭ በሆነ መጠን የመክሸፍ አደጋ ውስጥ መግባቱን የሚያሳይ ነው፤›› በማለት ምሥረታውን ይፋ ባደረገበት ወቅት ገልጾ ነበር፡፡

የዚህ ስብስብ አቋም ወደ ምርጫ ከመግባት በፊት በአገሪቱ በተከሰቱ ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ ችግሮች ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት መፈጠር አለበት የሚል ሲሆን፣ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የሚካሄድ ምርጫ የሚያስከትለው ውጤት አገራዊ ደኅንነትን ከማናጋት ውጪ ጥቅም የለውም የሚል ነው፡፡

ይህ ስብስብ ረቡዕ ጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም ተመሳሳይ አቋሙን ያራመደ ሲሆን፣ በተለይ በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዕገታ የታየውን የመንግሥት አቅም ውስንነት በመጥቀስ፣ እንዲህ ባለ ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባት ምን ማለት ነው በማለት ይጠይቃል፡፡

የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዕገታ ጉዳይ ከምንም ጉዳይ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን የሚገልጸው አብሮነት፣ ‹‹መንግሥት ግን በጉዳዩ ላይ የሚጠበቅበትን ያህል አልሠራም፤›› በማለት ይወቅሳል፡፡

በቅርቡ ታፍነው የተወሰዱ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ በጣም አሳሳቢና አስጨናቂ ጉዳይ ሆኗል የሚለው አብሮነት፣ ‹‹መንግሥት የእነዚህ ተማሪዎች ጉዳይ እስካሁን መፍትሔ እንዲያገኝ ማድረግ ካለመቻሉም በላይ፣ ስለተማሪዎቹ የደኅንነት ሁኔታ ግልጽና ተጨባጭ መረጃ እየሰጠ አይደለም፡፡ በእኛ እምነት ለአንድ አገር መንግሥት ከዚህ በላይ አሳሳቢና ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ የዜጎች የሰብዓዊ መብትና የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ አለ ብለን አናምንም፡፡ ነገር ግን መንግሥት ለዚህ አሳሳቢ ጉዳይ ተገቢ ትኩረት እንዳልሰጠ በግልጽ እየታየ ነው፤›› በማለት መንግሥትን ክፉኛ በመተቸት፣ ከፊት ያለው ጠቅላላ ምርጫ ይህን መሰል ችግሮች መፍትሔ ሳያገኙ ለማካሄድ መወሰኑ ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት መሠረታዊ የአገሪቱ ችግሮች ላይ መወያየት ቅድሚያ ይሰጠው በማለት በመጠየቅ፣ ‹‹ምርጫ መካሄድ ያለበት መቼ ነው?›› በሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ላይ በቅድሚያ መንግሥትና ፓርቲዎች የጋራ ድርድርና ውይይት ሊያካሂዱ እንደሚገባ በድጋሚ አሳስቧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹አሁን ከምንገኝበት እጅግ አሳሳቢ የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት አንፃር ምርጫው መቼ መካሄድ እንዳለበት መወሰን ያለበት፣ በመንግሥትና በፓርቲዎች የጋራ ድርድርና ውይይት እንጂ በምርጫ ቦርድ መሆን የለበትም፤›› የሚል አቋሙንም አራምዷል፡፡

ምንም እንኳን አብሮነትን ጨምሮ ሌሎች ፓርቲዎችም ‹‹ምርጫው መካሄድ የለበትም›› የሚል አቋማቸውን ቢያራምዱም፣ አንዳንድ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ አከል እንቅስቃሴ በማድረግ ተጠምደው መሰንበታቸውን ማስተዋል ይቻላል፡፡

ከዚህ አንፃር አብሮነትም እየተካሄዱ ያሉ የምርጫ ቅስቀሳዎች አገሪቱን ቀውስ ውስጥ ሊከቱ እንደሚችሉ አሳስቧል፡፡ ‹‹የምርጫ የጊዜ ሰሌዳው ገና ባልፀደቀበትና የፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ማካሄድ ባልታወጀበት በአሁኑ ወቅት፣ ብልፅግናና አፌኮን የመሰሉ ፓርቲዎች ከሕግ ውጪ የምርጫ ቅስቀሳ መጀመራቸው እየታየ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሕገወጥ ተግባር ገና የምርጫው ሒደት ከመጀመሩ በፊት አገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የሚያስገባና አሉታዊ ውጤት ሊያስከትል ስለሚችል፣ ይህ ሕገወጥ የምርጫ ቅስቀሳ በአስቸኳይ ይቁም፤›› በማለት ጥያቄውን አቅርቧል፡፡

በዚህም መሠረት መጪው ጠቅላላ ምርጫን ማካሄዱ ለተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም፣ እንዲሁም ከምርጫው በፊት እንደ አገር ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉንን ተግባሮች በብቃት ማከናወን የሚያስችል አንድ የዕርቅና የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም በድጋሚ ሐሳብ በማቅረብ፣ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

‹‹ይህ የዕርቅና የሽግግር መንግሥት ለምንና እንዴት መቋቋም እንዳለበት፣ መንግሥትና የፖለቲካ ኃይሎች ተገናኝተው መወያየትና መደራደር በአስቸኳይ መጀመር አለባቸው፤›› በማለት አጥብቆ ጠይቋል፡፡

ምርጫው መካሄድ አለበት ብለው የሚያምኑ መንግሥትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች፣ ከምርጫው ጋር ተያይዞ በሚፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ለሚደርሰው የሰው ሕይወት መጥፋትም ሆነ የአገር ንብረት ውድመት ኃላፊነት እንዳለባቸውም አሳስቧል፡፡

በዚህ ሁሉ ጽንፍ የወጡና የተራራቁ ሐሳቦች የሚዋልለው ምርጫ መካሄድ አለመካሄዱ በውል ባይታወቅም ቅሉ፣ በመካሄዱ ሊደርስ ይችላል ተብሎ የሚሠጋውን አለመረጋጋት ለማስቀረት መከናወን የሚኖርባቸው ሥራዎች ላይ ፖለቲካዊ መፍትሔ ማበጀትና ማስቀመጥ ለነገ የሚባል የቤት ሥራ አለመሆኑን የሚጠቅሱ በርካቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የፖለቲካ ኃይሎች በዚህ ረገድ የሚያካሂዷቸው ድርድሮችና ውይይቶች በእጅጉ ተናፋቂና ተጠባቂ መሆናቸው ይሰማል፡፡        

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -