የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ማረጋገጫ ኬሚካል (ሪኤጀንት) ማስገባቱንና ምርመራ መጀመሩን፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ ኬሚካሉ መግባቱ የላቦራቶሪ ናሙናዎችን ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩን ያስቀራል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከቻይና የሚመጡና ኖቭል ኮሮና ቫይረስ በሽታ ምልክት ታይቶባቸዋል ተብለው የሚጠረጠሩ መንገደኞችን ናሙና፣ በላቦራቶሪ የመመርመር ሥራ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ (ዶ/ር) ኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ ማክሰኞ የካቲት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳብራሩት፣ የላቦራቶሪ ምርመራ ለማካሄድ የቻለው ለምርመራው የሚያበቁ ሪኤጀንት በዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ በመገኘቱ ነው፡፡
በዚህም የተነሳ በማቆያ ማዕከል የነበሩ ስድስት ተጠርጣሪዎች ባለፈው ቅዳሜ፣ እንዲሁም ከቻይና የመጣ አንድ ሌላ መንገደኛ የካቲት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በላቦራቶሪው ተመርምረው ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው በመረጋገጡ ከማዕከሉ እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት ተጠርጣሪ በማቆያ ማዕከላቱ እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ 25,000 የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ድጋፍ እንዳደረገ፣ ይህንንም ያደረገው ከአየር መንገዱ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት እንደሆነ፣ በዓለም ላይ ከፍተኛ የሆነ የፊት መሸፈኛ ማስክ እጥረት እንዳለ፣ አምራች ኩባንያውም እያመረተ የሚያወጣውን ማስክ ወደ ቻይና ብቻ እንደሚልክ፣ ከዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በአገር ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የቁጥጥር ሥራ የሚከታተል፣ ከፍተኛ የሆነ የመንግሥት አካላት የተሳተፉበትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ብሔራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑንም አመላክቷል፡፡ ብሔራዊ ግብረ ኃይሉ ባካሄደው በዚሁ እንቅስቃሴ የቁጥጥሩን ሒደት በመገምገም፣ ጠቃሚ የሆነ የሥራ አቅጣጫ መሰጠቱም ተገልጿል፡፡
በዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት መሠረት እስከ ማክሰኞ የካቲት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 43,108፣ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 4,053 ሲሆኑ፣ 1,018 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል፡፡ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በ25 አገሮች ውስጥ ሪፖርት መደረጉንም ነው የተመለከተው፡፡
ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ ለሆቴል ባለሙያዎችና ከክልልና ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለተውጣጡ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ከቻይና የሚመጡ መንገደኞችን የሙቀት ልየታና የበሽታው ምልክት የታየባቸው መንገደኞችን የጤና ሁኔታ የመከታተል ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል፡፡
በሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርክ ባለባቸው ክልሎች ውስጥ የለይቶ ማቆያ ማዕከልና የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከላትን ለምላሽ ዝግጁ ለማድረግ በተያዘው ዕቅድ መሠረት፣ በደቡብ ክልል በሐዋሳ ከተማ ድጋፍ ሰጪ የባለሙያዎች ቡድን በመላክ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን የዝግጅት ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሆነ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ዝግጁነትና ምላሽ እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ በሁሉም አቅጣጫ ባሉ የአገሪቱ መውጫና መግቢያ ድንበሮች ላይ ከጥር 14 ቀን 2012 እስከ የካቲት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የኮሮናና የኢቦላ ቫይረስን ዝግጁነት በጋራ በማጣመር፣ ከ172 ሺሕ በላይ መንገደኞች ላይ የሙቀት ልየታ መካሄዱን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡
የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ከታየባቸው አገሮች የመጡ መንገደኞች ወይም በዚህ ቫይረስ ከተያዙ ግለሰቦች ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ላይ የበሽታው ምልክቶች (ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥ፣ የመተንፈስ ችግር) ከታዩ፣ ማንኛውም የኅብረተሰቡ አካል በአስቸኳይ በ8335 ነፃ የስልክ መስመር ላይ በመደወል ሪፖርት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች በሚያስነጥሱበትና በሚያስሉበት ወቅት አፍና አፍንጫቸውን በሶፍት ወይም በክርን እንዲሸፍኑ፣ የተጠቀሙበትን ሶፍት እንዲያቃጥሉ፣ እንዲሁም እጃቸውን በሳሙና በመታጠብ የቫይረሱን ሥርጭት እንዲከላከሉ፣ በተጨማሪም ኅብረተሰቡ በኢትዮጵያ እስካሁን በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠ ሰው አለመኖሩን አውቆ ሳይዘናጋ የበለጠ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡