- የፕሮጀክቱን አሥር ቢሊዮን ዶላር በጀት በቦንድ ሽያጭ ለማሟላት ታቅዷል
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ፣ የአሥር ሺሕ ሜጋ ዋት የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡ ለፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስምንት አገሮች መታጨታቸውን አስታውቋል፡፡
ማክሰኞ የካቲት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በተካሄደውና ኮሚሽኑ ለሦስተኛ ጊዜ ባሰናዳው የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ላይ የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ዕቅድ ይፋ ሲደረግ፣ የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋዋ፣ የሞዛምቢክ ጠቅላይ ሚኒስትር ካርሎስ ኦጎስቲኖ ዶ ሮዛሪዮን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣናት በተገኙበት መድረክ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት ከፀሐይ፣ ከጂኦተርማል፣ ከንፋስና ከሌሎችም ታዳሽ የኃይል ምንጮች አሥር ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ያለመ ስለመሆኑ፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ቬራ ሶንግዌ (ዶ/ር) ይፋ አድርዋል፡፡
ስለፕሮጀክቱ ዓላማዎች ለሪፖርተር ያብራሩት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢነርጂ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ኦፊሰር ዮሐንስ ኃይሉ ናቸው፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የሚተገበረው ይህ የመጀመሪያው ምዕራፍ የኢነርጂ ፕሮጀክት፣ አሥር ቢሊዮን ዶላር በጀት ሊጠይቅ ይችላል፡፡
ለታዳሽ ኃይል ምቹ የሕግ ማዕቀፍ ያላቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከተቀመጡት የዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ፣ በተለይም በሰባተኛ ደረጃ የተቀመጠውን የንፁህ ኢነርጂ አቅርቦትን ለማስፈን ስምምነት የፈጸሙ አገሮች ቅድሚያው እንደተሰጣቸው ያብራሩት አቶ ዮሐንስ፣ ኢትዮጵያ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ከማሟላት ባሻገር በኃይድሮ ኢነርጂና ደረቅ ቆሻሻን ወደ ኃይል ምንጭነት በመቀየር ጭምር ያላትን ተሞክሮ በማውሳት ጭምር፣ በዚህ ፕሮጀክት ለመካተት ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየቷን ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ ባሻገር ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ዙምባቡዌ፣ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎችም ታጭተዋል፡፡
ከታዳሽ ምንጮች እንደሚመነጭ የሚጠበቀውን የፋይናንስ አቅርቦት ለማሟላት የቦንድ ሽያጭ ሊካሄድ መታቀዱን ባለሙያው አብራርተዋል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በአስተባባሪነት በሚሳተፍበት በዚህ ፕሮጀክት ሒደት የኃይል ማመንጨት ሥራውን የግል ኩባንያዎች እንደሚያከናውኑት ሲገለጽ፣ ለፕሮጀክቱ ትግበራ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ ፓስፊክ ኢንቨስትመንት ማኔጅመንት ካምፓኒ (ፒምኮ) የተሰኘውና ዋና መሥሪያ ቤቱን በአሜሪካ ያደረገው ድርጅት የተወሰነውን በብድር ለማቅረብ መስማማቱ ታውቋል፡፡ ኩባንያው በአብዛኛው በጡረታ ፈንድ ከሚሰበስበው የፋይናንስ ምንጭ በአፍሪካ ለታሰበው የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክት ኢንቨስት እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱን ለመተግበር ከወዲሁ ፍላጎት ያሳዩትና ቅድመ ምርጫ ተካሂዶ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት አገሮች፣ በሥራው ለሚሳተፉ ኩባንያዎች እንደ አገሮቹ ተጨባጭ ሁኔታ የብድር ሥጋት ዋስትና ሽፋን ከመስጠት ጀምሮ፣ የዋጋና የታሪፍ አወጣጥ ላይ ድርድሮችን ማካሄድ እንደሚጠበቅባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፒምኮ ከሁለት ትሪሊዮን ዶላር በላይ ፈንድ በማንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ግዙፍ የኢንቨስትመንት አስተዳደር ኩባንያ ሲሆን፣ ፍላጎት ያላቸውን ባለሀብቶችና ኩባንያዎች በማሰባሰብ በአፍሪካ የታሰበው ፕሮጀክት ላይ እንዲሳተፉ እንደሚያደርግ፣ በፒምኮ ቁልፍ የስትራቴጂ ክፍል ውስጥ ዋና የኢንቨስትመንት ኦፊሰር ስኮት ማተር ተስፋ ሰጥተዋል፡፡
የቀድሞ የናይጄሪያ ፋይናንስ ሚኒስትር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ እንዳወሱት ከሆነ በአፍሪካ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች መካከል በዓለም ካለው አቅም 40 በመቶው ከፀሐይ፣ ከ35 በመቶ በላይ ከንፋስ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ዕምቅ አቅም በአፍሪካ እንዳለ፣ ይህም ሆኖ በርካታ የአፍሪካ አገሮች በድጎማ ለሚያቀርቡትና በካይ ለሆኑ የኃይል አማራጮች ቅድሚያ ሲሰጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ቬራ ሶንግዌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በአፍሪካ በየዓመቱ 12 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ የሚውል ድጎማ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ድጎማ ውስጥም አብዛኛው ተጠቃሚ አቅሙ ያላቸውና በገቢ ምንጫቸውም ከደሃው የተሻለ ደረጃ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በመሆናቸው፣ መንግሥታት የሚያደርጉት ድጎማ ደሃውን እንደሚፈልገው ተጠቃሚ አላደረገም ብለዋል፡፡ በመሆኑም ከድጎማ ይልቅ አዋጭ፣ ለአካባቢ ብክለት አስተዋጽኦ የሌላቸውና ለዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል በርካሽ የታሪፍ ዋጋ ተደራሽ መሆን የሚችሉ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ማቅረብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
እንደ አቶ ዮሐንስ መረጃ እ.ኤ.አ. በ2017 በተመዘገበ አኃዝ መሠረት፣ በአሁኑ ወቅት ከ570 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት አልቻሉም፡፡ ይህ አኃዝ ከዚህ ቀደም ከነበረው ከ640 ሚሊዮን ሕዝብ ቁጥር አኳያ ቅናሽ ቢታይበትም፣ በተመድ የዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ በተቀመጠው መሠረት እ.ኤ.አ. በ2030 በመላው አፍሪካ ለሁሉም ተደራሽ የሆነ የኃይል አቅርቦት ማሳካት ከባድ ፈተና መሆኑ አልቀረም፡፡ በተቀሩት አሥር ዓመታት ውስጥ ይህን ያህል ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ ከሚያግዙ ጅምሮች አንዱ የሆነው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጅምር፣ ከአሥር ሺሕ ሜጋ ዋት ኃይል አቅርቦት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ 16 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች እንደሚፈጠሩ ታሳቢ ያደርጋል፡፡