የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሠራተኞች የጥር ወር ደመወዝ ስላልተከፈላቸው በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙ ገለጹ፡፡
ኮርፖሬሽኑ በበኩሉ የመንገድ ጥገና ዲስትሪክቶችን የመለየት ሥራ ውስጥ መቆየቱን ገልጾ፣ ደመወዛቸው ማክሰኞ የካቲት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ወደ ባንክ መላኩን ገልጿል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ለሪፖርተር እንደገለጹት ደመወዝ ሳይከፈላቸው ከአሥር ቀናት በላይ በመቆየታቸው የቤት ኪራይ፣ የልጆች ትምህርት ቤት ክፍያዎችና የቀለብ መሸመቻ ጭምር ችግር ገጥሟቸዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑን በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ተገቢ ምላሽ የሚሰጣቸው ማጣታቸውን የተናገሩት ሠራተኞች፣ ቀደም ብለው በነበሩ አመራሮች ወቅት የነበረ ውዝፍ የገቢዎች ሚኒስቴር ዕዳ (ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ሳይሆን እንዳልቀረ ተናግረዋል) ስለተከፈለ ገንዘብ አለመኖሩ እንደተነገራቸው አስረድተዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በርካታ ፕሮጀክቶች ያሉት መሆኑን የተናገሩት ሠራተኞች፣ በኃላፊነት ተመድበው ይሠሩ የነበሩ አመራሮች ከአስፋልትና ከተለያዩ ግዥዎች ጨረታዎች ጋር በተያያዘ ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጉን ጠቁመዋል፡፡ አሁን የተሾሙ የሥራ ኃላፊዎች ቁርጠኛ ሆነው የተቋሙን ሪፎርም በመሥራት ላይ ቢሆኑም፣ በነባር ኃላፊዎች ውስብስብ ሥራ ግራ እየተጋቡ ስለሆነና ሠራተኞችም በብዛት እየለቀቁ እንደሆነ ጠቁመው፣ ያሉትም ተረጋግቶ ለመሥራት የሚያስችል ምንም ዓይነት ዋስትና ስለሌላቸው፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ጣልቃ ገብቶ እንዲያስተካክል ጠይቀዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጥንፉ ሙጬ፣ ሠራተኞች ደመወዝ ስለመከልከላቸውም ሆነ ስለመከፈላቸው የሚያውቁት መረጃ እንደሌላቸው ቢናገሩም፣ የሰው ሀብት ዳይሬክተሩ አቶ ዋቅጅራ ይልማ ግን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ዋቅጅራ እንደገለጹት፣ በኅብረት ስምምነት መሠረት ደመወዝ የሚከፈለው በወሩ መጨረሻ ባሉ የሥራ ቀናት ነው፡፡ በመሆኑም ወሩ ካለፈ ገና ሁለት ቀናት እንደሆኑ በመግለጽ፣ ያም ሆነ ይህ ደመወዛቸው በባንክ ገቢ እንደተደረገላቸው ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ ደመወዝ የሚከፍለው እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር ስለመሆኑና እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ከአሥር ቀናት በላይ ስለማለፉ ሲጠየቁ፣ እውነት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ የዘገየበት ምክንያትም ኮርፖሬሽኑ ጠቅልሎ ይዟቸው የነበሩ የመንገድ ጥገና ዲስትሪክቶች በመንግሥት ውሳኔ ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በመተላለፋቸው ርክክብ ሲደረግ እንደነበር አብራርተዋል፡፡ አሁን ግን ለኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ከየካቲት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ደመወዛቸው በባንክ ገቢ እንደተደረገላቸው ገልጸዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ቀድሞ የውኃ ሥራዎች ድርጅት፣ ሕንፃ ኮንስትራክሽንና መንገዶች ተዋህደው የተመሠረተ ተቋም ሲሆን፣ በቅርቡ የመንገድ ጥገና ዲስትሪክቶች ወደ ኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን እንዲመለሱ ከመደረጉ በስተቀር ሌሎቹን ይዞ የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ በአጠቃላይ ከአሥር ሺሕ በላይ ሠራተኞች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል፡፡