Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትኩረት የሚሻው የሚጥል ሕመም

ትኩረት የሚሻው የሚጥል ሕመም

ቀን:

ኤፕሊፕሲ (የሚጥል በሽታ) እንደማንኛውም ክሮኒክ ከሚባሉና አንጎልን ከሚያውኩ በሽታዎች አንዱ ነው፡፡ ባደጉ አገሮች እስከ 0.8 በመቶ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ባሉት አገሮች እስከ 1.5 በመቶ፣ በተለይ በኢትዮጵያ እስከ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በበሽታው ተጠቅተዋል፡፡፡

የዓለም የኤፕሊፕሲ ቀን በኢትዮጵያ ከየካቲት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ‹‹እኔም የሚጥል በሽታ ሕመም ይመለከተኛል›› በሚል መሪ ቃል ለአምስተኛ ጊዜ እየተከበረ ነው፡፡ ቀኑን አስመልክቶ በመክፈቻው ዕለት በተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ ዓውደ ጥናት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ትምህርት ክፍል ስፔሻሊስት ያሬድ ዘነበ (ረዳት ፕሮፌሰር) እንደገለጹት፣ ለሕመሙ መከሰት ጎልተው የሚታዩት ምክንያቶች የጭንቅላት እባጭ፣ ዕጢና ጥሬ ዓሣን መመገብ ናቸው፡፡

በወሊድ ጊዜ በጨቅላው ላይ ከሚደርስ መታፈን፣ ከማጅራት ገትር (ሜኔንጃይትስ)፣ የአልኮል መጠጥ ከማዘውተር፣ አደንዛዥ ዕፆችን ከመጠቀም፣ ከባድ ትኩሳትና ለአንጎል የሚደረግ እንክብካቤ አነስተኛ መሆን ለኤፕሊፒሲ በሽታ እንደሚዳርግም ገልጸዋል፡፡

ባደጉ አገሮች ከ100,000 ሕዝብ መካከል 50 ያህሉ በየዓመቱ በሕመሙ እንደሚጠቁ፣ በማደግ ላይ ባሉና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ግን ይህን የሚያመላክት መረጃ እንደሌለ፣ በዚህም የተነሳ ለመገመት አዳጋች እንደሆነ አክለዋል፡፡

‹‹ኤፒሊፒሲ ብዙ ጊዜ በሕፃናትና በታዳጊ ወጣቶች ላይ ብቻ የሚከሰት የሚመስላቸው ወገኖች አሉ፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በተዛባ አመለካከትና ግንዛቤ ማነስ የተነሳ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኤፒሊፒሲ ዕድሜያቸው 60 እና ከዚያም በላይ በሆኑ አዛውንቶች ላይ ዘር፣ ፆታ፣ ቀለም ሳይለይ ሊከሰት ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር ያሬድ እንደሚሉት፣ በሽታው ካደረባቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ሕመሙ ሲጀምራቸው ልዩ ልዩ ምልክቶችን ያሳያሉ፡፡ ከምልክቶቹም መካከል አንዱና ዋነኛው መጫጫን ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምልክት መታየት በሽተኛው ድንገት እወድቃለሁ በሚል ሥጋት ከቆመበት ቁጭ እንዲል ዕድል ይሰጠዋል፡፡ መቀመጡም ድንገት ቢወድቅ ጉዳት እንዳይደርስበት ይረዳዋል፡፡

አብዛኞቹ ታማሚዎች ሕመሙ ሲጀምራቸው መላ ሰውነት የመንቀጥቀጥ፣ እጅና እግር መወራጨት፣ ያገኙበት ቦታ ላይ መውደቅ፣ ዓይንን ወደላይ መስቀል፣ ሽንት ማምለጥና ከነቁ በኋላ መደነጋገር እንደሚያጋጥማቸው፣ በዚህም ጊዜ አጠገባቸው ያሉት ሰዎች ሳይደናገጡ በተረጋጋ መንፈስ የበሽተኛውን አንገት ደገፍ አድርጎ መያዝ፣ ጉዳት ሊያደርሱበት የሚችሉትን ነገሮች ከአካባቢው ማንሳት፣ መንቀጥቀጡን ሲያበቃ ከወደቀበት አንስቶ በትክክል ማስቀመጥ፣ ምላሱን ከላንቃው እንዲወርድና ፈሳሽ እንዲወጣ በማድረግ የሕይወት አድን ሥራ ማከናወን እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የክብሪት እንጨት ማጨስና መንስዔው የስኳር ማነስ ነው በሚል ጣፋጭ ለስላሰ መጠጦችን ማቅረብ ሳይንሳዊ ድጋፍ እንደሌለው፣ ኤፕሊፕሲን በሕክምና ሊድን የሚችልና ብዙ ወገኖችም ድነው አምራች ዜጋ ለመሆን እንደቻሉ አስረድተዋል፡፡ ኤፕሊፕሲ በንክኪና በምራቅ እንደማይተላለፍ፣ መድኃኒቱን በየቀኑ ሳያቋርጡ ረዘም ላለ ጊዜ በመውሰድ በሽታውን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል መቆጣጠር እንደሚቻል፣ ረዳት ፕሮፌሰር ያሬድ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥርዓተ ጤናና የሥነ ተዋልዶ ምርምር ዳይሬክተር አቶ አበበ በቀለ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደ ጥናት መሠረት ከአጠቃላይ ሕዝብ መካከል 1.6 መቶ የሚሆኑት ከደም ግፊት እንዲሁም ስድስት በመቶ የሚጠጉ ከስኳር ሕመም፣ በሌሎች ምክንያቶች ከኤፒሊፕሲ ጋር አብረው እንደሚኖሩ ማረጋገጡን ገልጸዋል፡፡

የሚጥል ሕምምን ትኩረት አድርጎ የሚሠራና ‹‹ኬር ኤፒሊፕሲ ኢትዮጵያ›› መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ እናት የውነቱ ‹‹በድርጅታችን ውስጥ ለሚጥል ሕምም ተጠቂዎች ነፃ ሕክምና አገልግሎቶች በኒሮሎጂስቶች ይሰጣል፣ የካውንስሊንግ የእጅ ሥራ ትምህርቶችንም ያገኛሉ፤›› ብለዋል፡፡

በድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ የታቀፉ 280 የኤፒሊፕሲ ታማሚዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ገልጸው፣ በቀጣይ 393 የሚሆኑ የኤፕሊፒሲ ታማሚዎች የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን መመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡

ለአንድ ሳምንት የሚዘልቀው ብሔራዊ የሚጥል ሕመም ሳምንት በጤና ባለሙያዎች ሥልጠና፣ በጎዳና ላይ ትምህርትና በእግር ጉዞ እንደሚከበርና የመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱም እሑድ የካቲት 8 ቀን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ዋና ግቢ በራፍ ከጧቱ 2 ሰዓት ጀምሮ እንደሚሆን ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...