Thursday, May 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

​​​​​​​የንግድ ሥርዓቱን ያልደገፈ “የለውጥ ጉዞ” የት ይደርሳል?

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራ ታሪክ ከጥንታዊው ዘመን የሚነሳ ነው፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ የነበረው ንግድና ግብይት ከአገሬው ሰው ባሻገር ከባህር ማዶ የመጡ ነጋዴዎች ተሳትፎ የታከለበት ነበር፡፡

ገናናው የአክሱም ሥርወ መንግሥት በተነሳበት ወቅት የንግድ ሥርዓቱ የራሱ ገንዘብ የነበረውና በወርቅ፣ ብርና ነሐስ ይገበያይ እንደነበር ታሪክ መዝግቦታል፡፡ አክሱማውያኑ በምሥራቅ ሮማ ግዛተ አፄ (ኢምፓየር) እና በፋርስ መካከል የሚገኝ ኃያል መንግሥታቸውን መሥርተው የንግድ ልውውጥ ይፈጽሙ ነበር፡፡ በወደባቸው አዱሊስ በኩል ከግብፅ፣ ዓረቢያ፣ ፋርስ፣ ሕንድና እስከ ሲሎን ይገበያዩ እንደነበር ይታወቃል፡፡

በዘመናዊት ኢትዮጵያም አብዛኛውን የምጣኔ ሀብት ዘርፍ የያዘው የችርቻሮ ንግድ ሲሆን፣ በከፍተኛ፣ በመካከለኛና በአነስተኛ ንግድ የተሰማራውም ከፍተኛ የሰው ኃይል  መሆኑ ይታወቃል፡፡ አሁን የምንገኝበት ሁኔታም ሲታይ የንግድ ሥርዓቱ በነፃ ገበያ መርህ አገሪቱ በምትከተለው ፖሊሲና በዚሁ ላይ ተመሥርተው በሚወጡ ሕግጋት መሠረት የሚመራ ዘርፍ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ምንም እንኳን ባለፉት ሦስት አሠርታት የልማታዊ መንግሥት ስትራቴጂ ያጀበው አፈጻጸም የተተገበረ ቢሆንም፣ በተለይ በአምራች፣ አከፋፋይና የፍጆታ ተጠቃሚ የሆነው ነዋሪ መስተጋብር ረገድ የነበረው አተገባበርም ከነፃ ገበያና የውድድር መንፈስ የራቀ አካሄድ ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡

ይሁንና ሕግጋቱና የፍትሐዊ ንግድ ባህሉ፣ ብሎም መንግሥታዊ አሠራሩ በነጋዴውም ሆነ በሸማቹ ዘንድ ተገቢውን ግንዛቤ አላገኘም፡፡ ወይም ሆን ተብሎ እየተጣሰ ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው ዛሬም ድረስ ፍትሐዊውና ገበያ መር የሚባለው የሰለጠነ አካሄድ የንግዱን ኅብረተሰብ ከፀረ ውድድርና ተገቢ ካልሆኑ የገበያ ተግባራት ማውጣት አላስቻለም የሚል መከራከሪያ የምናነሳው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት አረም የወረረው አካሄድም፣ ሸማቹን ከሚያሳስቱ የገበያ ሁኔታዎች የሚከላከልና ለነፃ ገበያ ውድድር አመቺነት ያለው ሥርዓት ለማስፈን አላስቻለም፡፡

ቢያንስ የንግድ ሥርዓቱን ከአዘቅት ለማውጣት ይረዳል በሚል፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት የወጣው የንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ (ቁጥር 685/2002) የታሰበውን ያህል ካለመተግበሩ ባሻገር አሁን ከለውጥ በኋላ ደግሞ ይበልጥ ተዳክሞ ከሥራ የወጣ መምሰሉ አሳሳቢው የወቅቱ አጀንዳ ሆኖ ይገኛል፡፡

 አሁን በየአካባቢው የነጋዴው የንግድ አሠራር ባህርይ ከሸማቹ ፍላጐትና ሰብዕና ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም ነው፡፡ በተለይ በዕለት ተዕለት ፍላጐት የችርቻሮ ገበያ ላይ ያለው ነጋዴ አሠራር ለተጠቃሚው አመቺ አለመሆኑ ተባባሰበት እንጂ አልተቃናም፡፡ ነጋዴው ሲፈልግ ይሸጣል፣ ሲፈልግ አይሸጥም፡፡ ጋብ ያለ ቢመስልም አሁንም በተለይ ዋና ዋና አስመጭውና የጅምላ ቸርቻሪዎች በሱቅ ውስጥ ያለውን ዕቃ ይደብቃሉ፣ ‹‹ነገ ዋጋ ሊጨምር ይችላል›› በሚል ስሌት ይሸሽጋሉ፡፡ ‹‹የተሻለ ገንዘብ ያስገኝልኛል›› ወደሚለው ገበያ በሕገወጥ መንገድ ያሸጋግራሉ፡፡ ሚዛን ያጐድላሉ፡፡ የዋጋ ዝርዝር አይለጥፉም፡፡ ሸማቹ የሚፈልገውን መረጃ አይሰጥም፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ደግሞ ከአዋጁና ከንግድ ሕግጋት ጋር የሚጋጩ ናቸው፡፡

      ዛሬም ድረስ ሸማቹ ስለሚገዛው ዕቃ /ሸቀጥ/ ጥራት መጠየቅ አይችልም፡፡ ነጋዴ የሰጠውን ብቻ ተቀብሎ እንዲሄድ ሰብዕናን በሚነካ ሁኔታ ያንጓጥጣል፡፡ ሸማቹ በገዛ ገንዘቡ አማርጦ መግዛት አይችልም፡፡ ገንዘቡ በስንት ድካምና ልፋት እንደሚገኝ አይገነዘብም፡፡ መንግሥት ለሕዝብ እንዲደርስ ያቀረበውን መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጥ ባልተገባ ሁኔታ ለማይገባው ተጠቃሚ ይሸጣል፡፡ ዛሬ የገባውን ስኳር/ዘይት ወይም ሌላ ሸቀጥ  ነገ ‹‹የለም›› ይላል፡፡ የተበላሸ ዕቃ ሸጦ ‹‹መልስ ወይም ቀይር›› ቢሉት እሺ አይልም፡፡ ይህ ዓይነቱ ፀረ ሕዝብ ድርጊት፣ በለውጥ ማግስትም ተባባሰ እንጂ አልቀነሰም፡፡

         አንዳንዱ ሕገወጥም ዓይን በዓይን ክዶ ቀይር /አስተካክል የተባለውን ቁስ፣ ‹‹ከእኔ አልገዛህም›› ብሎ ሽምጥጥ አርጐ ይክዳል፣ አምባጓሮ ለማስነሳትም ይሞክራል፡፡ ለእያንዳንዱ ሸቀጥ ደግሞ፣ ወይም ሱቅ በተሄደ ቁጥር ምስክር ይዞ መሄድ አይቻልም፡፡ ከነጋዴው ጋር በቀና መንፈስ መግባባትም አይቻልም፡፡ በፖለቲካው መንፈስ የሚሰክረው ደግሞ ገበያ መር የንግድ ሥርዓትን ዘንግቶ ከሰው ሰው እየለየ፣ ከብሔር ብሔር እየለየ፣ ከሃይማኖት ሃይማኖት እየለየ ይሸጣል፡፡ ዋጋውንም እንዲሁ ከፍና ዝቅ እያደረገ ለአንዱ በአምስት ብር የሸጠውን ለሌላው በስድስትና በሰባት ብር ይሸጣል፡፡ እርስ በርስ የመጠቃቀም ሁኔታ አለ፡፡ የአገሪቱ የደረጃዎች ሥርዓት ጥራቱን ያረጋገጠለት ምርት እያለ፣ ጥራት የሌለውን ዕቃ በተመሳሳይ ዋጋ ያቀርባል፡፡ ስለሚሸጠው ዕቃ አጠቃቀም ቢጠይቁት መልስ መስጠት አይችልም፡፡

      ነጋዴው ስለንግድ አሠራር ምንነት አያውቅም፡፡ መንገድ ዳር ያለች ጠባብ ቤት ይከራይና አሮጌ መደርደሪያና ሚዛን አስቀምጦ በዝቅተኛ ካፒታል የተመዘገበ ፈቃድ ለጥፎ ሥራውን ይሠራል፡፡ የነጋዴነት መብቱ የት ድረስ እንደሆነ አይገነዘብም፡፡ የሸማቹን ጥቅም አይረዳም፡፡ ሸማቹ በነጋዴው አማካይነት በየጊዜው በሚደርስበት እንግልትና ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በአገሩና በመንግሥት ላይ ሲያማርር ይኖራል፡፡ ይህ ዓይነቱ ክፉኛ የተጣባንን ልማድ ቢያንስ ከለውጥ በኋላ ለመቀየር የሚተጋ የዘርፉ መዋቅርና የበታች አመራርና ባለሙያ አለመፈጠሩ ደግሞ አሳዛኙ እውነታ ሆኗል፡፡

    በእርግጥ ከጊዜ ወደጊዜ እየታየ እንዳለው ነጋዴው በተለይ የበታች ቸርቻሪው ከሸማቹ ጋር ብቻ ሳይሆን እርስ በርሱም አይስማማም፡፡ የአንዱን ነጋዴ ዋጋ ሌላው ነጋዴ እየሰበረ፣ ‹‹የእገሌ ሱቅ /መደብር ይሻላል›› እያስባለ እሱ እየበላ፣ ሌላውን ጦም እያሳደረ አግባብ ባልሆነና የነፃ ገበያ የውድድር አሠራርን ባልተከተለ አሻጥር ከገበያ እንዲወጣ ያደርገዋል፡፡ ነጋዴው ዋጋ የሚጨምረው በአድማ የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ በአድማው መሠረት ዋጋ ያልጨመረ ነጋዴ ከተገኘ ብዙ አፍራሽ ወሬዎች ይነዙበታል፡፡

       ለምሳሌ ያህል ሥጋ ነጋዴ ከሆነ ከፍተኛ በሚባል የአሉባልታ ዘመቻ ‹‹የሞተ ከብት እያስገባ ነው›› ይሉታል፡፡ በጥራቱ ይወነጅሉታል፡፡ ሳይወድ በግድ የአድማው ተካፋይ ያደርጉታል፡፡ ማንኛውም ነጋዴ በተለይ የምግብ፣ የሉካንዳ፣ የመጠጥ . . . ነጋዴ ቤቱን ቀለም ቀብቶ ሲጨርስ ሸቀጦቹ ላይ ዋጋ መጨመሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ በቀጥታ ሸማችና የፍጆታ ተጠቃሚ የሆነውን ዝቅተኛ  ማኅበረሰብ ለምሬት የሚያጋልጥና ለችግር የሚዳርገው ነው፡፡ ይህን መታገል ያለበት ደግሞ የዘርፉ አመራርና ባለሙያ በመቀናጀት ብሎም ሕዝብን በማሳተፍ ነው፡፡

     በድምር ሲታይ ባለፉት ዓመታት የተንሰራፋውም ሆነ ዛሬም ድረስ የሚታየው አገራዊ የግብይት ሥርዓቱና የንግዱ ኅብረተሰብ አሠራር በነፃ ገበያና በተወዳዳሪነት መርሆዎች ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ የሸማቾችን ጤንነትና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የንግድ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን መስፋፋት ለመግታት የሚያስችል መሠረት ያለው የንግድ አሠራርም አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ለሰው ልጅ ጤና ሳይቀር ጠንቅ የሆኑ ባዕድ ነገሮችን በገበያ ውስጥ እስከመክተት የሚደርሰው ሕገወጥነትና ኢሞራላዊነትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

      ለዚህም ነው በእነዚህና በሌሎችም በርካታ ምክንያቶች የንግዱ አሠራር ሥርዓትና ፈር መያዝ አለበት የሚሉ ተቆርቆሪዎች እየተበራከቱ የሚገኙት፡፡ የወጡትን ሕግጋት መተግበር ብቻ ሳይሆን ዘመኑን የሚዋጁ ሕጎችም ሊወጣለት የሚገባ ዘርፍና ወሳኝ የኢኮኖሚው ዘውግ በመሆኑም በመንግሥትም ሆነ በሕዝቡ በተለይም በራሱ በንግዱ ማኅበረሰብ ሊታሰብበት የሚገባ ነው መባሉ፡፡

     በየትኛውም ጊዜና ቦታ ወይም ሁኔታ ቢሆን የሸማቹ መብትና ጥቅም ከብልሹ የነጋዴዎች ባህርይ መጠበቅ አለበት፡፡ በመሠረቱ በየትኛውም መስክ እንደተሰማራው የሰው ልጅ ሁሉ የንግዱ ማኅበረሰብም የተጠላበትና የሕግና የሞራል ግዴታ መዘንጋት የለበትም፡፡ ለዚህ ደግሞ ሸማቹም በንግዱ አሠራር ተፈጥሮአዊ ባህርይና በአዋጅ የተሰጡትን የሸማችነት መብቶቹን ለማስከበር የራሱን ሚና መጫወት አለበት፡፡ አይደለም በጋራ ማኅበራቱ፣ ገበያ ውስጥም ቢሆን ትናንት የገባ ሸቀጥ ስኳር፣ ዘይት. . . ወዘተ ዛሬ የለም ሲባል ‹‹የት ሄደ?›› ብሎ የመጠየቅ መብት አለውና በዚህ መብቱ መጠቀም አለበት፡፡

      ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ሲደረግበትም ሆነ  በዘር፣ በሃይማኖት ወይም በሌላ በማንኛውም ሁኔታ አድልዎ ሲፈጸምበት ‹‹ለምን?›› ብሎ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ለፀጥታ አካላት መጠቆምም አለበት፡፡ ለሚመለከተው አካል ወይም አጠገቡ ላለው ፖሊስ ማሳወቅና ሒደቱን መከታተልም ግድ ይለዋል፡፡

    በንግድና የሸማቾች አዋጅ እንደተመለከተው፣ ሸማቹ ለፋብሪካ ወይም መልሶ ለመሸጥ ሳይሆን፣ ዋጋውን ራሱ ወይም ሌላ ሰው ከፍሎለት ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ፍጆታ የሚሆን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚገዛ የተፈጥሮ ሰው በመሆኑ፣ ለራሱ በሚገዛው የፍጆታ ሸቀጥ አማካይነት ከነጋዴው በኩል የሚደርስበትን እንግልትና ጭማሪ፣ የሚዛን ጉድለትም ሆነ የመረጃ አለማግኘት ችግር የራሱን ጥቅም በራሱ የማስከበር ግዴታ አለበት፡፡ ይህን ዕውን ለማድረግ ደግሞ ለውጥ መጀመሩ ያግዘው እንደሁ እንጂ የሚጋርድበት ሊሆን አይችልም፣ አይገባምም፡፡

     ነጋዴው ደግሞ የሙያ ሥራው አድርጐ፣ ጥቅም ለማግኘት ሲል በንግድ ሕጉ የተዘረዘሩትን ሥራዎች የሚሠራ ወይም አገልግሎት የሚሰጥ ወይም የንግድ ሥራ ነው ተብሎ በሕግ የሚወሰነውን ሥራ የሚሠራ ሰው በመሆኑ፣ በሕጉ መሠረት የመንቀሳቀስ ግዴታ አለበት፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ነጋዴ በግሉ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በአንድ የገበያ ክልል ውስጥ ዋጋን ወይም ሌሎች የንግድ ውድድር ሁኔታዎችን የመቆጣጠር ወይም ውድድርን የማጥፋት ወይም በግልጽ የመገደብ፣ በግልጽም ሆነ በሥውር አላግባብ በመጠቀም የንግድ ሥራ ማካሄድ አይችልም፡፡ በዚህ በኩል አስፈጻሚውም ከመዘናጋት ሊወጣ ግድ ይለዋል፡፡

የገበያ የበላይነትን አለአግባብ የመጠቀም ድርጊቶች የሚባሉት፡-

– ምርትን መገደብ፣ የንግድ ዕቃዎችን ማከማቸት ወይም መደበቅ ወይም በመደበኛው የንግድ መሥመር እንዳይሸጡ ማድረግ ወይም መያዝ፡፡

– የንግድ ውድድርን ለመገደብ ወይም ለማጥፋት በማሰብ ከማምረቻ ዋጋ በታች የመሸጥ ወይም የተወዳዳሪን ወጪ የማሳደግ፣ ወይም ግብአቶችን ወይም የሥርጭት መስመሮችን ቀድሞ በመያዝ ተወዳዳሪ ላይ ያነጣጠረ ጐጂ ድርጊት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ መፈጸም፡፡

– በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ፍትሐዊ ያልሆነ የመሸጫ ዋጋ ወይም የመግዣ ዋጋ መጠየቅ፡፡

– ግልጽና ወቅታዊ የሆነ የገበያ አሠራርን በሚቃረን መልኩ ገበያን በበላይነት የያዘው ነጋዴ በልማድ የሚያደርገውን ወይም ሊያደርገው የሚችለውን እንደማይችለው ሆኖ ለመደራደር ፈቃደኛ አለመሆን፡፡

– አሳማኝ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር ገበያን በበላይነት በያዘ ነጋዴ ቁጥጥር ሥር ያለን ተፈላጊ ግብአት ተወዳዳሪ ለሆነው ወይም ሊሆን ለሚችል ነጋዴ መከልከል፡፡

– የንግድ ውድድርን ለማጥፋት ወይም ለመገደብ በማሰብ በዕቃዎችና አገልግሎቶች አቅርቦትና ግዥ ላይ በደንበኞች መካከል በዋጋና በሌሎች ሁኔታዎች ልዩነት መፍጠር . . . ወዘተ ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ቅጣታቸው ከባድ የሆኑና ፍፁም የተከለከሉ ድርጊቶች አሉ፡፡ እነሱም፣ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ዋጋን መወሰን፣ ተመሳጥሮ መጫረት፣ ደምበኞችን ወይም የገበያ ክልልን ወይም ምርትና ሽያጭን በኮታ መመደብ፣ በነጋዴዎች መካከል አላማው ወይም ውጤቱ ዝቅተኛ የችርቻሮ ዋጋ መወሰን . . . ወዘተ በኅብረት አቋም መያዝ ወይም በማኅበር ውሳኔ ማሳለፍ ፍፁም የተከለከሉ ድርጊቶች ናቸው፡፡

– ማንኛውም ነጋዴ የሌላውን ነጋዴ ወይም የነጋዴውን ተግባራት በተለይም ነጋዴው ከሚያቀርበው የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ጋር በተገናኘ ሁኔታ ታማኝነትን ያሳጣ ወይም ሊያሳጣ የሚችል ማናቸውም ሐሰት የሆነ ወይም ማረጋገጫ የሌለው አገላለጽ ተገቢ ያልሆነ የውድድር ተግባር ክልከላ መሆኑ በአዋጅ ተረጋግጧል፡፡

– ማንኛውም ነጋዴ የንግድ ዕቃዎቹንና የአገልግሎቶቹን የዋጋ ዝርዝር በንግድ ቤቱ በግልጽ በሚታይ ቦታ ማመልከት ወይም በንግድ ዕቃዎቹ ላይ መለጠፍ እንዳለበትና የተጠቀሰው ዋጋ ቀረጥ፣ ታክስ ወይም ሌላ ሕጋዊ ክፍያ ያካተተ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡

– ማንኛውም ነጋዴ በሸማቾች መካከል ተገቢ ያልሆነ አድልዎ መፈጸም አይችልም፡፡ አንድን ዕቃ ወይም አገልግሎት ለመሸጥ ሸማቹ ያልፈለገውን ሌላ ዕቃ አብሮ እንዲገዛ ማስገደድም ነጋዴው አይችልም፡፡ መብት የለውም፡፡

– ሕጋዊ ከሆነው ውጪ በሚዛን ወይም በመሥፈሪያ ወይም በሌላ መለኪያ መሣሪያ ማጭበርበርም በአዋጁ ተከልክሏል፡፡ በንግድ ቤቱ ከተለጠፈው ዋጋ አስበልጦ መሸጥም ክልክል ነው፡፡ ደረሰኝ መስጠት የነጋዴው ግዴታ ነው፡፡

     አዋጁ (ቁጥር 685/2002) የሸማቾችን መብትና ጥበቃ የሚመለከቱ ድንጋጌዎችንም ይዟል፡፡ በዋናነት የሚከተሉትን እንመልከት፡- ማንኛውም ሸማች፣

– ስለሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ጥራትና ዓይነት በቂና ትክክለኛ መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት መብት አለው፡፡

– ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን አማርጦ የመግዛት መብት አለው፡፡

– የዕቃዎችን ጥራት ወይም አማራጮችን በማየቱ ወይም የዋጋ ድርድር በማድረጉ ምክንያት እንዲገዛ አይገደድም፡፡

– ሸማቹ በማንኛውም ነጋዴ በትህትናና በአክብሮት የመስተናገድና በነጋዴው ከሚደርስበት የስድብ፣ የዛቻ፣ የማስፈራራትና የስም ማጥፋት ተግባር የመጠበቅ መብት አለው፡፡

– በንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ግብይት ምክንያት ለሚደርስበት ጉዳት የመካስ (ካሳ የማግኘት) መብት አለው፡፡

– ሸማቹ የገዛው ዕቃ /አገልግሎት/ ጉድለት ያለበት /የተበላሸ/ ሆኖ ሲገኝ አገልግሎቱን ከገዛበት ቀን ጀምሮ በ15 ቀን ውስጥ በሸማቹ ምርጫ ነጋዴው አገልግሎቱን ለሸማቹ በድጋሚ ያለክፍያ ይሰጠዋል፡፡ ወይም ነጋዴው የተቀበለውን ዋጋ ለገዥው ይመልሳል፡፡ (የተበላሸ ዕቃ ሸጦ ‹‹እኔም የገዛሁት እንዲሁ ስለሆነ አልቀይርም›› ወይም ‹‹ገንዘቡን አልመልስም›› ማለት ነጋዴው አይችልም፡፡) ይህ ድንጋጌ ሁሉ ታዲያ እንደምን ሊዘነጋ ይችላል!!!

       ነጋዴው ሊያከብራቸው የሚገቡ ሌሎች ድንጋጌዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ማንኛውም ነጋዴ የንግድ ስሙን፣ በግልጽ በሚታይ ቦታ መለጠፍ አለበት፡፡ ነጋዴው ከሚሸጠው የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ጋር በተያያዘ ሸማቹ በሚያቀርብለት ጥያቄ መሠረት በአጥጋቢ ሁኔታ ራሱን መግለጽና ሸማቹ የሚፈልገውን መረጃ እንዲወስድ መፍቀድ አለበት፡፡ ማንኛውም ነጋዴ በሚሸጣቸው ዕቃዎች ላይ መግለጫ መለጠፍ ወይም በተለየ ወረቀት ላይ ጽፎ ለሸማቹ መስጠት አለበት፡፡

     ስለንግድ ዕቃዎች የሚለጠፈው መግለጫ፣ የሚከተሉትን ቁምነገሮች የያዘ ወይም የሚያመለክት መሆን አለበት፡፡ የንግድ ዕቃው ስም፣ የተሠራበት ወይም የመጣበት አገር፣ የተጣራ ክብደት፣ መጠንና ብዛት፣ የዕቃውን ጥራት፣ ዕቃው ከምን እንደተመረተ፣ የአሠራር ወይም የአጠቃቀም ዘዴ፣ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች፣ ነጋዴው ለገዥው ስለሚሰጠው ዋስትና፣ የተመረተበት ቀን፣ ከአገልግሎት ውጭ የሚሆንበትን ቀን፣ በኢትዮጵያ ደረጃዎች የተመለከቱት መሥፈርቶች ያሟላ ስለመሆኑ . . .የሚገልጽ መሆን አለበት፡፡

   እንግዲህ አዋጁ አልተሻረም ወይም ተዘንግቶ እንጂ በትግበራ ላይ ነው ከተባለ  በንግድ ውድድር ላይ ጉልህ ተፅዕኖ የሚያስከትል ወይም ሊያስከትል የሚችል መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ለምሳሌ ያህል የንግድ ውድድርን የሚያጠፋ የውህደት ተግባር ግላዊ ተቋምነታቸውን ይዘው ይኖሩ በነበሩ ሁለት የንግድ ማኅበራት መካከል መፈጸምን  መከልከሉ እንደ አንድ አብነት ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህም በአዋጁ ምዕራፍ ሦስት የውህደትና (Merger) ተገቢ ያልሆኑ የንግድ ውድድር ተግባራት ቁጥጥር ሥርዓት በሚለው ሥር በዝርዝር ሰፍሮ ይገኛል፡፡

      የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በውድድር ላይ የተመሠረተና ከላይ የተጠቀሱትን ክልከላዎችና የመብት ጥበቃዎች ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት፡፡ ነፃ ገበያ ማለት ነጋዴ ያለአንዳች ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እየተቧደነ ወይም በማኅበር እየሆነ በየሸቀጡ ላይ የዋጋ ጭማሪ አድማ ማድረግ ማለት አይደለም፡፡ ይህን ግን በቅርቡ  ለውጡ ያልተመቻቸው ጭምር እንደ ፖለቲካ ፍላጎት ማራመጃ ሲተገብሩት መታዘብ ችለናል፡፡

     በየትኛውም አገር ሞኖፖሊዝም እንደሚነቀፈው ሁሉ በእኛም አገር፣ ንግድን በቡድን ሆኖ ገበያን በበላይነት መቆጣጠርና ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ማግኘትም ፈጽሞ አይፈቀድም፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ባይነካካም በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የተሟላ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አዋጅ  685/02 ችግር ፈቺ አዋጅ ነው፡፡ የሕግ ሰነዱ ጉድለት አለበት ቢባል እንኳን በጣም ጥቃቅን ካልሆኑ በቀር ጉልህና ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ጉድለቶች የሉበትም፡፡ በፊትም ሆነ አሁን ከለውጥ ማግሥት ያለው ፈተና ግን ለተግባራዊነቱ በአስፈጻሚው ባለሥልጣንና በሚመለከታቸው አካላት በኩል ያለው ደታኝነትና የቅንጅት ማነስ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለውጡ የንግዱን ዘርፍም ይታደገው ማለታችን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles