Friday, June 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያ የበይ ተመልካች የሆነችበት የአፍሪካ ኅብረት!

ኢትዮጵያ የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ የአሁኑን የአፍሪካ ኅብረት ዕውን ለማድረግ የከፈለችውን መስዋዕትነት ለመዘርዘር መሞከር፣ ለቀባሪው ማርዳት ስለሆነ ዝርዝሩ ውስጥ አንገባም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ታላቅ ተምሳሌት እንደነበሩ፣ በታላቁ ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓድዋ ጦርነትና ከዚያም ከወራሪው የፋሽስት ኃይል ጋር ያደረጉዋቸው ተጋድሎዎች አይረሱም፡፡ ለፓን አፍሪካኒዝም ጥንስስ መሠረት የሆኑት ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች አፍሪካውያን ወገኖቻቸው ከቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅ ያደረጉትን ትግል ከማገዝ ጀምሮ፣ የጋራ መሰባሰቢያ የሆነ ድርጅት የመመሥረት ሐሳብ በማፍለቅና ከግብ በማድረስ ታላቅ ተጋድሎ ማድረጋቸውም አይዘነጋም፡፡ ባለ ራዕዮቹ ኢትዮጵያዊያን ይህንን የመሰለ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ግዳጅ ተወጥተው የአፍሪካውያን መሰባሰቢያ ቢፈጥሩም፣ ይህ ተቋም ግን ለኢትዮጵያ ያለው ፋይዳ ምንድነው? ኢትዮጵያዊያንስ ከዚህ ተቋም ተጠቃሚ ለመሆን ያደረጉት ጥረት ምንድነው? ተቋሙስ ይበልጥ ተጠናክሮ ለሁሉም አፍሪካውያን የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሠራ ምን አድርገዋል? እያደረጉስ ነው? የአፍሪካ ኅብረት በትክክል የአኅጉሪቱ መሠረታዊ ፍላጎቶችና ችግሮች ላይ እየሠራ ነው? ወይስ እዚህ ግባ በማይባሉ ፋይዳ ቢስ ጉዳዮች ነው የሚወጠረው? ወዘተ የመሳሰሉ ወቅቱን የሚዋጁ ጥያቄዎች ማንሳት የግድ ይላል፡፡ ከአፍሪካ ኅብረት አፍሪካውያን በጋራ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በተናጠል ያገኘችው ጥቅም ምንድነው? የአፍሪካ ኅብረት የሰጠው ጥቅም አለ ከተባለስ ምን ይሆን? ያጎደለውስ ምንድነው መባል ይኖርበታል፡፡ ኅብረቱ የፈጸመው ስህተት ካለም በግልጽ ታውቆ መስተካከልና መለወጥ አለበት፡፡

የአፍሪካ ኅብረት 33ኛ የመሪዎች ጉባዔ ሰሞኑን ሲጠናቀቅ አዲሱ ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ፣ የሊቢያና የደቡብ ሱዳን ግጭቶች ዋነኛ ትኩረታቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ሌሎች አካባቢዎች ያሉ ችግሮችና ቀውሶች ለማን ሊተው ነው? የ55 አባል አገሮችን ንብረት የሆነው የአፍሪካ ኅብረት በ57 ዓመታት ታሪኩ፣ በርካታ የአፍሪካ አገሮች በውስጣዊም ሆነ በውጫዊ ችግሮች ለበርካታ አፍሪካውያን ሕልፈት ምክንያት የሆኑ ግጭቶች ተከስተውባቸዋል፡፡ የውክልና ጦርነት ውስጥ በመግባት ጭምር አፍሪካውያን እንዲፋጁ ተደርጓል፡፡ ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ፀጋ በመጠቀም ወደ ልማት መግባት የተሳናቸው በርካታ አገሮች በጦርነት ምስቅልቅላቸው ወጥቷል፡፡ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶቻቸውን፣ የውኃ ሀብታቸውን፣ የከበሩ ማዕድናትና የነዳጅ ዘይት ፀጋዎቻቸውን መጠቀም ቀርቶ ሰላም የራቃቸው አገሮች በርካቶች ናቸው፡፡ ከረሃብና ከጦርነት በመሸሽ በየበረሃውና በየውቅያኖሱ ለሞት እጃቸውን የሰጡ የአፍሪካ ወጣቶች ቁጥር ሥፍር የላቸውም፡፡ ይኼም አልበቃ ብሎ ሥልጣን ላይ ከወጡ መውረድ በማይፈልጉ የሲቪልና የወታደር አምባገነኖች ምክንያት ለእስራት፣ ለሚዘገንን ሥቃይና ሞት፣ እንዲሁም ለስደት የተዳረጉ በጣም ብዙ አፍሪካውያን ናቸው፡፡ አሁንም ቁጥራቸው ትንሽ በማይባሉ አገሮች እነዚህ አምባነኖች እንደተንሰራፉ አሉ፡፡ አፍሪካ የድህነት፣ የኋላቀርነትና የአምባገነንነት መጫወቻ ሆና ኅብረቱ የፈየደው ምን ይሆን? ራሱን በራሱ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር መለወጥ ካልቻለ የመኖሩ ትርጉም ግልጽ አይደለም፡፡ ለመላ አፍሪካ አሳሳቢ ችግሮች በአንድነት የማይቆም ተቋም ፋይዳ ቢስ ነው፡፡

ከአጠቃላዩ የአፍሪካ ችግር ወደ ኢትዮጵያ ጉዳይ ስንመለስ ሁለት መሠረታዊ ችግሮችን እናነሳለን፡፡ የመጀመርያው የአፍሪካ ኅብረት ለኢትዮጵያ ያለው ፋይዳ ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊያን በአፍሪካ ኅብረት ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያንን የጋራ ቤት ለመገንባት በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ያለፈችበትን ውጣ ውረድ ታሪክ በሚገባ ከትቦታል፡፡ ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ለማሳካት ታላቅ ተጋድሎ ያደረጉ ኢትዮጵያዊያን በሚገባ ይታወቃሉ፡፡ አፍሪካውያን የጋራ የሆነው ተቋማቸው በተለያዩ ጊዜያት ባጋጠሙት ችግሮች የመፍረስ አደጋ ሲያጋጥመው፣ ባለ ራዕዮቹ ኢትዮጵያዊያን እንዴት እንደታደጉትም ይታወቃል፡፡ ታሪክም ምስክር ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ሲገጥማት፣ ይህ ተቋም ከንፈር ከመምጠጥ የዘለለ ያደረገላት ምንም ነገር የለም፡፡ በሶማሊያና በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተደጋጋሚ ድንበሯ ተጥሶ ስትወረር፣ ቻርተሬ ተጥሷል ብሎ ጥብቅና ሲቆም አይታወቅም፡፡ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ግዛት ወቅት ባለው ድንበር መፅናት አለባቸው የሚለው ቻርተር በብዙ አገሮች ተጥሶ፣ የበርካታ ንፁኃን ሕይወት እንዲያልፍ መደረጉም አይዘነጋም፡፡ በጎረቤት አገሮች የውክልና ጦርነት በተደጋጋሚ የተከፈተባት ኢትዮጵያን ለመታደግ ቀርቶ የማፅናኛ ቃሉ አይታወቅም፡፡ ሌላው ቀርቶ የኅብረቱ ዋና መሥሪያ ቤት ባለበት አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያዊያን በአብዛኛው ማለት ይቻላል ከጥበቃና ከጉልበት ሠራተኝነት የተሻለ ሥራ ማግኘት እንኳ አይችሉም፡፡ በዚህ ላይ በበላይ አለቆቻቸው የሚፈጸምባቸው ግፍ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ዘመናዊ ሕንፃ በመዲናዋ ቢገተርም፣ ልጆቿ ግን ከሩቅ የማየት የዘለለ ተሳትፎ የላቸውም፡፡ ለምን መባል አለበት፡፡

ኢትዮጵያ 500 ሚሊዮን ሕዝብ ያህል ይኖርበታል በሚባለው የዓባይ ተፋሰስ ውስጥ፣ ለዓባይ ወንዝ 86 በመቶ የውኃ ሀብት የምታበረክት አገር ናት፡፡ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ በዓባይ ወንዝ ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ግድብ ለመገንባት ስትነሳ፣ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ እየገጠማት ያለው ፈተና ይታወቃል፡፡ ውኃውን በፍትሐዊነት የመጠቀም መርህ መሠረት በታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት ሳታደርስ፣ ከድህነት ለመውጣት በምታደርገው ፍትሐዊ እንቅስቃሴ ታላቁን የህዳሴ ግድብ እየገነባች ዘጠኝ ዓመታት እየተቆጠሩ ቢሆንም፣ በተለይ ከግብፅ ጋር የምታደርገው እልህ አስጨራሽ ድርድር እየፈተናት ነው፡፡ የሦስትዮሽ ድርድሩ ከአቅም በላይ ሆኖ አሜሪካና የዓለም ባንክ ቢገቡበትም፣ ድርድሩ እንዲህ በዋዛ የሚቋጭ አልመስል እያለ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት እንዴት ፍትሐዊ አደራዳሪ አጣች? ይህ ጥያቄ የአፍሪካ ኅብረትንና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ይመለከታል፡፡ ‹አፍሪካውያን ችግራቸውን በራሳቸው መፍታት አይችሉም› እየተባሉ መሳለቂያ ከሚሆንባቸው ምሳሌዎች አንዱ ይህ ነው ቢባል ስህተት ይሆናል? ኢትዮጵያውያን ‹በቅኝ ግዛት ዘመን ሕግ አንገደድም፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚቃረን ስምምነት መስማት አንፈልግም፣ የመልማት መብታችን ይከበር›፣ ወዘተ እያሉ የአፍሪካ ኅብረትስ ምን ይላል? የእኛ ባለሥልጣናትስ ኅብረቱን ምን እያሉት ነው? ድርድሩ መቋጫው አላምር ብሎ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ቢያመራ መመለሻው ምን ይሆን? አፍሪካውያን ተፈጥሮ በሰጠቻቸው ሀብት መስማማት አቅቷቸው ጦር እስኪማዘዙ ነው ወይ የሚጠበቀው? መልስ የሚፈልግ ጥያቄ ነው፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ በተካሄደ ቁጥር እንግዶችን በሰላም ተቀብሎ በማስተናገድ ወደ መጡበት መሸኘት፣ የኢትዮጵያውያን የተለመደና የተመሠገነ ባህል ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ መንገዶች ሲዘጋጉ የሚደርሰው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳት ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል እንግዶች ይዘው ከሚመጡት አበል የሚቆነጥሩት ገቢ እንዳለም አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን ኅብረቱ ለአፍሪካ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ደግሞ እንደ አስተናጋጅነቷ በተናጠል ያለው ፋይዳ ሲመዘን፣ አሁንም የሚያነጋግሩ በርካታ እንከኖች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ ወደ ተግባር ለመለወጥ አዳጋች የሆነ አጀንዳ ያለ ዕቅድና ሁለንተናዊ ተሳትፎ መለፈፍ ነው፡፡ በአፍሪካ የጠመንጃ አፈሙዝ ፀጥ የሚለው ፍትሕ፣ ነፃነትና እኩልነት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡ ከመፈክር የማያልፍ አጃንዳ ይዞ መምጣት ሳይሆን፣ የአፍሪካውያንን የልብ ትርታ በማዳመጥ ውጤታማ ተቋም ማድረግ ይቅደም፡፡ ከአፍሪካ ምድር የአምባገነንነት ሥሩ ይነቀል፡፡ ዘረፋና ሌብነት ውግዝ ከመአርዮስ ይባሉ፡፡ በምርጫ ብቻ ሥልጣን ላይ የሚወጡ መሪዎች ይኑሩ፡፡ ሕገ መንግሥት በተደጋጋሚ በማሻሻል ሥልጣን ላይ የሚወዘፉ የጃጁ መሪዎች አይኑሩ፡፡ ምርጫና ፓርላማ የማያውቁ አምባገነኖችና አገራቸውን ያለ ተጠያቂነት የሚመሩ በቃችሁ ይባሉ፡፡ ኅብረቱም ካረጀና ካፈጀ አሠራር ተላቆ ይዘምን፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት የተጀመረው ተቋማዊ ለውጥ በፍጥነት ይከናወን፡፡ አፍሪካውያን በተባበረ ድምፅ የእኛ ነው የሚሉት ተቋም ለመሆን ይሥራ፡፡ የውጭ ዕርዳታ እየተማፀነ የለጋሾች ጉዳይ አስፈጻሚ ከሚሆን፣ በአባል አገሮች ቁርጠኝነት ራሱን ነፃ ያውጣ፡፡ በሌላ በኩል የበይ ተመልካች የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ከአስተናጋጅነት ባሻገር ዋና ተዋናይ ትሁንበት፡፡ ‹በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት› እያሉ ማላዘን ይብቃ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...

አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የምንዛሪ ገበያ እንዳይኖር ሊመክሩ ነው

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...

የባንኮች ብድር አሰጣጥ ፍትሐዊና ብዙኃኑን ያማከለ እንዲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

ባንኮች የብድር አገልግሎታቸውን በተቻለ መጠን ፍትሐዊ፣ የብዙኃኑን ተጠቃሚነት ያማከለና...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...

የሕዝቡን ኑሮ ማቅለል እንጂ ማክበድ ተገቢ አይደለም!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ለበርካታ ወጪዎቹ ገንዘብ ስለሚያስፈልጉት አስተማማኝ የገቢ ምንጮች ሊኖሩት ይገባል፡፡ በጀት ሲይዝም ሆነ ወጪዎቹን ሲያቅድ ጠንቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወቅቱ ለመጪው ዓመት በጀት...