Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለኢኮኖሚው ችግሮች የግሉ ዘርፍ ተጠያቂ ያደረገበት መድረክ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሰሞኑን ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ አንድ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ባለሙያ እስካሁን ብዙም የሚደፍረው እንዳጣ በሚገመት ጉዳይ ላይ ትንተና አቅርበው ነበር፡፡

እኚህ ባለሙያ አቶ ሚሊዮን ክብረት ይባላሉ፡፡ ‹‹የግሉ ዘርፍ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታና የፖሊሲ አቅጣጫዎች፤›› በሚል ርዕስ ምልከታቸውን ባሳዩበት ጽሑፋቸው፣ ቀዳሚ ያደረጉት በኢትዮጵያ ለሚከሰቱ ችግሮች ሰበቦችና ወደ ሌሎች ችግሩን የማላከክ አባዜን የሚያሳይ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታ በሁሉም መስክ የሚታዩ ችግሮች እንዳሉ ያስታወሱት አቶ ሚሊዮን፣ አብዛኛዎቹ ችግሮች እንዲፈቱ የሚፈለገው ግን በሦስተኛ ወገን በኩል በመሆኑ ለችግሮቹ መባባስ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ‹‹ችግር እናወራለን ወደ መፍትሔ ስንመጣ ግን ሦስተኛ ወገንን በመጥቀስ ችግር በገጠመን ቁጥር መንግሥትን፣ ዕርዳታ ድርጅቶችን፣ አንዳንዴም ንግድ ምክር ቤቱ ችግራችንን አልፈታ አሉን ብለን እንጠቁማለን፤›› ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ ይህ በሌሎች ላይ የማላከክ አባዜ የዘመናት ልምድ ሆኖ መቀየቱን ያነሳሉ፡፡

በየምክንያቱና ሰበብ አስባቡ ችግር እያወሩ ከመኖር ይልቅ እንደ ውጭዎቹ አባባል ‹‹ጉርጥ መብላት ካለብን መብላት ነው›› በማለት ሞግተዋል፡፡ ችግር ሲኖር እንደ ችግሩ እንደሚመለከተው ባለድርሻ ሁሉንም አፍረጥርጦ በመነጋገር ችግሩ በማን ይፈታ? ወደሚል የመፍትሔ አቅጣጫ ማምራት ሲገባ፣ በአብዛኛው በሦስተኛ ወገን ወይም በመንግሥት ላይ የማላለክ አካሄድ እንደማያዋጣ ገልጸዋል፡፡  

‹‹አብዛኞቹ ነጋዴዎች ችግራችሁ ምንድነው ቢባሉ ቁጥር አንድ ብለው የሚጠቅሱት የውጭ ምንዛሪ ዕጦት እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ትክክልም ነው፤›› ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ ይሁንና ይህ የነጋዴዎች ችግር ሊሆን እንደማይገባ ይልቁንም መፍትሔውን ነጋዴው ማግኘት እንደነበረበት የሚጠይቅ ሞጋች ሐሳብ አንፀባርቀዋል፡፡ ለአባባላቸው ምሳሌ ይሆን ዘንድ የሚመሩትን ድርጅት ዋቢ አድርገዋል፡፡ ‹‹እኔ የምመራው ድርጅት 80 በመቶ ደንበኞች የውጭ ኢንቨስተሮች ናቸው፡፡ ለአገልግሎታችን የሚከፍሉን በዶላር ነው፡፡ የብር አካውንት አለን፤›› ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ ችግሩ የውጭ ምንዛሪው ሳይሆን በጊዜው ወደ ብር ሳይቀር እየቆየ በሚፈጠር መጓተት ችግር እንደሚያጋጥም አስታውሰዋል፡፡ ‹‹በዶላር አካውንት ያለንን ሒሳብ ወደ ብር ቀይሩልን ብለን ብዙ ጊዜ እንጠይቃለን፡፡ ዶላሩ እያለ የብር እጥረት ይኖራል፤›› በማለት ችግሩ የብር አቅርቦት እጥረትም እንደሆነ አንስተዋል፡፡ በመሆኑም እንዲህ ያሉ ቀላል ችግሮችን ወደ ሦስተኛ ወገን ከመውሰድ ይልቅ መፍትሔውን በመፈለግ በቀላሉ ችግሩን መፍታት የሚቻልበት መንገድ እንደሚኖር አብራርተዋል፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት አብዛኛው የኩባንያቸው ደንበኛ የአገር ውስጥ ተገልጋይ እንደነበር ያወሱት አቶ ሚሊዮን፣ የገንዘብ ልውውጡም በብር ላይ የተመሠረተ ነበር ይላሉ፡፡ በዶላር ክፍያ ለመፈጸም ባስለፈጋቸው ጊዜ ዶላሩ እንዳልነበራቸው አስታውሰው፣ በሦስት ዓመታት ልዩነት ግን የዶላር ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚያስችል ሥራ በመሥራት፣ የዶላር የገቢ ምንጭ በመሆን፣ በብር መመንዘር የቻሉበት ጊዜ ላይ እንደደረሱ አብራርተዋል፡፡  

ከአቅም በላይ የሚመስሉ ችግሮችን የንግዱ ማኅበረሰብ በራሱ አካሄድ  ሊፈታቸው እንደሚችል ያላቸውን እምነት ይናገራሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ምንጭን ከማስፋት አኳያ የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል ስለሚቻልባቸው መንገዶች በሰጡት ትንታኔ፣ የወጪ ንግድ ዋናው ምንጭ የግብርናው ዘርፍ ቢሆንም አሁን ግን ሁኔታዎች እየተቀየሩ መምጣታቸውን አውስተዋል፡፡

ለኢኮኖሚው (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አንፃር) ግብርና ያለው ድርሻ ወደ 32 በመቶ ወርዷል፡፡ ንግድን የመሳሰሉት የአገልግሎት መስኮች ድርሻቸው 39 በመቶ ነው፡፡ እንዲሁም የኢንዱትሪ ዘርፉ ድርሻ 27 በመቶ ነበር፡፡ በመሆኑም በግብርና ላይ ያተኮረው የወጪ ንግዱ መስክ ወደ ኢንዱስትሪና ወደ አገልግሎት እያዘመመ በመምጣቱ፣ በርካታ አማራጮች መኖራቸውን ያመላክታል በማለት በጥቂት መስኮች ላይ ጥገኛ ከመሆን መላቀቅ እንደሚገባ ከኩባንያቸው ተሞክሮ በመነሳት አብራርተዋል፡፡ አዲስ አበባ ሆነው ለአሜሪካ ኩባንያዎች አገልግሎት በመስጠት የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት እንደቻሉ ጠቅሰዋል፡፡

ለውጭ ኩባንያዎች የሚያቀርቡት አገልግሎት በአይሲቲና በሒሳብ ሥራ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አብራርተው፣ የአሜሪካን የታክስ ሥርዓት ያጠኑ ባለሙያዎችን በመቅጠር ለአሜሪካ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ የሒሳብ ሥራ በመሥራት የውጭ ምንዛሪ እስያገኙ ነው፡፡

‹‹በአሜሪካ አንድ አካውንታንት ከሦስት እስከ አራት ሺሕ ዶላር ያገኛል፡፡ ከኢትዮጵያ አንፃር ጥሩ አካውንታንት አሠልጥኖ በአንድ ሺሕ ዶላር መቅጠር ስለሚቻል፣ በዚሁ ሥሌት መሠረት የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ለአሜሪካ ኩባንያዎች እየሠሩ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም፣ ‹‹በኢንተርኔት ስካን እየተደረገ ደረሰኛቸው  ለኩባንያችን ይመጣል፡፡ የሒሳብ አያያዝና ሥሌቱን እንሠራለን፡፡ ውጤቱም በኢንተርኔት ይልካል፡፡ ለዚህ አገልግሎታችን በወር 5,000 ዶላር ይከፍሉናል፡፡ ኩባንያው በአሜሪካ ሲከፍል የነበረው ግን 30 ሺሕ ዶላር ነው፡፡ እኛ በጣም ተደስተን ከሦስት ሺሕ ዶላር በላይ እናገኛለን፤›› በማለት በሙከራ ደረጃ ሲተገብሩት በነበረው የአገልግሎት ንግድ አማካይነት ስላገኙት ውጤት ገልጸዋል፡፡

የሙከራ ፕሮግራሙ አትራፊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የዶላር ገቢ ምንጭም ሆኗል የሚሉት አቶ ሚሊዮን፣ ይህን አገልግሎት ይበልጥ ማስፋፋት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡ ይህ የተጣራ የአገልግሎት የወጪ ንግድ እንደሆነ ያብራሩ ሲሆን፣ የተጣራ የአገልግሎት ወጪ ንግድ መበራከቱና የውጭ ምንዛሪውም በግሉ ዘርፍ የሚመነጭ በመሆኑ፣ ዘርፉ ምርታማ ከሆነና ሥራዎችን በአግባቡ መሥራት ከቻለ ውጤታማ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡

የአገልግሎት የወጪ ንግድ ዘርፉን ለማስፋፋት ባለሙያዎችን በሰፊው ማበራከት እንደሚገባና በዚህ መስክ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ወጪ የሌለበት ከመሆኑ አኳያ፣ በሚገባ ከተሠራበት አሁን ያለውን የውጭ ምንዛሪ ችግር በአምስት ዓመታት ውስጥ ታሪክ ማድረግ የሚቻልበት ዕድል እንደሚኖር እምነት አላቸው፡፡

በጽሑፍ ያቀረቡት ሌላው ነጥብ የንግድ ሚዛን ጉድለትን የሚቃኝ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የንግድ ሚዛን ከፍተኛ ጉድለት ይታይታል፡፡ በ2011 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከላከቻቸው ምርቶች የ2.6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አስመዝግባለች፡፡ ይሁንና ከውጭ ላስገባቻቸው ምርቶች ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጋለች፡፡ ይህ  ጤናማ አይደለም ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ የሁለት ሺሕ ብር ወርኃዊ ገቢ ያለው ዜጋ የ15 ሺሕ ብር ወጪ ይጠየቃል እንደማለት ነው፤›› የንግድ ሚዛን ጉድለቱ ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ በምሳሌ አሳይተዋል፡፡

የንግድ ሚዛኑን ጉድለት ለማስተካከል አማራጩ የወጪ ንግድን በማስፋፋት ገቢ ንግድን መቀነስ ቢሆንም፣ ‹‹ገቢ ንግድን መቀነስ የማይቻል ከሆነ፣ አማራጩ ያለንን አቅም ተጠቅመን መሥራትና የውጭ ምንዛሪ ምንጫችንን ማስፋት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚታየውን የንግድ ሚዛን ጉድለት ለመሙላት የተወሰደው የምንዛሪ ተመን ለውጥ ዕርምጃ፣ እንዲሁም የዋጋ ግሽበትን የሚያባብሰበው ምርትና ምርታማነት እንደ ልብ አለመኖሩ ሲሆን፣ የምርት አቅርቦት ሳይጨምር በቀየረ ቁጥር ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ዋጋ በየጊዜው እያደገ እንደሚሄድም አሳይተዋል፡፡ የአቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ መፍትሔው ያለው በነጋዴው እጅ እንደሆነና ምርቱም ያለው በዚሁ አካል እጅ ስለሆነ፣ ምርታማነት በጨመር ዋጋን አረጋግቶ አገር መጥቀም እንደሚቻል ሞግተዋል፡፡ ‹‹መተማመን ያለብን እንዲህ ያለውን ነገር መንግሥት ሊፈታው የማይችል መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም የግሉ ዘርፍ እንጂ መንግሥት ዶላር ማመንጨት ስለማይችል ነው፤›› በማለት የመንግሥት ሚና ከንግድ መለስ እንደሆነ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

የወጪ ንግድ አፈጻጸም መዳከም ያስገርማል ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ መንግሥት ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች አቅርቦ፣ የታክስ ዕፎይታን ፈቅዶና ከቀረጥ ነፃ ዕድል ሰጥቶ፣ በመጨረሻው ከውጭ ምንዛሪ የሚያገኘው ገቢ ሦስት ቢሊዮን ዶላር መሆኑን በማውሳት ነው፡፡ በአንፃሩ ከውጭ ሐዋላ የሚገኘው ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሲደርስ መታየቱ ማበረታቻና ድጋፍ እያገኘም የወጪ ንግዱ ውጤት ካላመጣ፣ መሠረታዊ ችግር እንዳለበት ይጠቁማል ማለት ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከውጭ በሕጋዊ መንገድ ከሚገባው ሐዋላ ይልቅ በኢመደበኛ መንገዶች የሚመጣው የውጭ ምንዛሪ አነጋጋሪ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ሚሊዮን፣ ‹‹እውነት እንነጋገር ከተባለ እኔ ብዙ ጓደኞችና ወዳጆች አሉኝ፡፡ የግል ዘርፉ ላይ የሚሠሩ በጣም የተከበሩ ሰዎች ግን የለፉበትን ነገር ለዘመዶቻቸው መላክ ሲፈልጉ በመደበኛውም መላኪያ መንገድ አይልኩም፤›› በማለት ስለችግሩ በሰፊው አብራርተዋል፡፡  

ሰዎች በሕጋዊ መንገድ ዶላር ከማልይኩባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ በመደበኛውና መደበኛ ባልሆነው የምንዛሪ ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት ነው፡፡ ማንኛውም ሕገወጥ መሆን ባይፈልግ እንኳ፣ ሳይወድ በግድ ወደ ጥቁር ገበያ የሚወስደው ሰፊ የጥቅም ጉዳይ በመሆኑና ማንኛውም ትክክለኛ አስተሳሰብ ያለው ሁሉ ሊያደርገው የሚችለው ጉዳይ እንደሆነ በመጥቀስ፣ ኢመደበኛ በሆኑ መንገዶች የሚላከው ገንዘብ ሆን ብሎ ወንጀል ለመሥራት ከመፈለግ ላይሆን እንደሚችል አብራርተዋል፡፡ ስለዚህ በመደኛው ገንዘብ የመላኪያ መንገድ ደፍሮ የሚልክ ሰው በሕጋዊና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው ልዩነት መቀራረብ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል፡፡

በኢመደበኛ መንገዶች እየገባ በጥቁር ገበያ የሚመነዘረውን ዶላር ወደ ሕጋዊ መስመር ለማምጣት መፍትሔው በፖሊሲ እንጂ፣ በፖሊስ የማስገደድ አካሄድ አግባብ እንዳልሆነ ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የንግድ ሚዛን ጉድለት ሊስተካከል የሚችለው የውጭ ምንዛሪ ማውጣት የሚጠበቅበትን ዋጋ ማውጣት ሲችል ነው ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ መመራት እንደሚገባውም ይሞግታሉ፡፡  

ገበያው በራሱ መንገድ መወጣት የሚችለውን ጉዳይ በአዋጅ መገደብ እንደማይቻል የሚከራከሩት አቶ ሚሊዮን፣ በኢትዮጵያ ሐዋላ እንቅስቃሴ መስክ የሚታየው ትልቅ ችግር የውጭ ምንዛሪን በሕጋዊ መንገድ እንዲያስተናግድ አለመደረጉ ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግሥት ፖሊሲ አስተዋጽኦ አበርክቷል ይላሉ፡፡ ‹‹አብዛኛው ገንዘባችን ያለው ከመደበኛው መንገድ ውጪ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ አንድ ኢትዮጵያዊ ዶላር ካመነጨ በኋላ በአዋጅ የዶላር ሒሳብ መክፈት እንዳይችል በመከልከሉ ነው፡፡ ይህም ማለት በአገር ውስጥ በዶላር ማስቀመጥ ስለማይችል መደበኛ ወዳልሆነው መንገድ ተቀማጭ ዶላር ይኖረዋል፡፡

የኢትዮጵያን ውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ማሟላት የሚችል የገንዘብ መጠን ማግኘት የሚቻልበት አጋጣሚ እያለ ዜጎች በሕግ ክልከላ በውጭ ምንዛሪ ገንዘብ ማስቀመጥ እንዳይችሉ መደረጋቸው፣ ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኛ የፈራነውን ሁሉ ልጆቻችን እንዲጋፈጡት እያስገደድናቸው ነው፡፡ ዕዳና ፍርኃት ማውረስ አይገባንም፡፡ የምንፈራውን ነገር ተጋፍጠን እውነታውን ማውረስ ይጠበቅብናል፡፡ እንዲህ ያለውን አካሄድ በኮሙዩኒዝም ወቅትም ዓይተነዋል፡፡ ምንም አላተረፍንበትም፤›› በማለት ከውጭ ምንዛሪ አንፃር ኢትዮጵያ የምትከተለውን የፋይናንስ ፖሊሲ ኮንነዋል፡፡

በጽሑፋቸው ማጠቃለያም ስለወቅታዊ ሁኔታዎች አብራርተዋል፡፡ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚያበረታቱ ፖሊሲዎችን እያወጣ ነው ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ የኢንቨስትመንትና ተያያዥ ሕጎች መሻሻላቸው በበጎ እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡ የኢንተርኔት ሥርዓትን በመጠቀም የስቶክ ገበያን ለማስጀመር የሚደረገው እንቅስቃሴ ጥሩ ጅምር እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡  

በሌላ በኩል በርካታ የውጭ ኢንቨስተሮች መግባታቸው መልካም እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሚሊዮን፣ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ብቸኛ መዳረሻ ባለመሆኗና  አማራጭ አገሮችም በዙሪያዋ ስላሉ፣ በየጊዜው አሠራሮችን እያስተካከሉና እያሻሻሉ መሄድ  ለኢኮኖሚ ጠቃሚ መንገድ እንደሆነ በመግለጽ አጠቃለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች