Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለትምህርት ጥራት ዝቅተኛ ትኩረት በመሰጠቱ አፍሪካን ዋጋ እያስከፈላት እንደሚገኝ አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአፍሪካ ልማት ባንክ በየዓመቱ የሚያወጣውና ‹‹አፍሪካን ኢኮኖሚክ አውትሉክ›› የተሰኘው ሪፖርት፣ ዘንድሮ ትኩረት የሰጠው ለወጣቶች ጥራቱ የተጠበቀ የትምህርትና የሥራ ዕድል መፍጠር የወደፊቷን አፍሪካ ህልውና ያረጋግጣል የሚል መፈክር በመያዝ ነው፡፡

በአፍሪካ በአማካይ ለትምህርት መስፋፋት፣ ከአኅጉሪቱ አማካይ ዓመታዊ የኢኮኖሚ አቅም (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) እስከ አምስት በመቶ ወጪ ይደረጋል፡፡ ይሁን እንጂ ለትምርህት መስፋፋት ወጪ ከሚደረገው እያንዳንዱ ዶላር በምላሹ የሚገኘው ውጤት ከ32 የአሜሪካ ሳንቲም ያነሰ ሆኖ እንደተገኘ የባንኩ ባለሙያዎች ይፋ አድርገዋል፡፡

ዓርብ፣ ጥር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ከ33ኛው መደበኛ የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን በአፍሪካ ኅብረት ይፋ የተደረገው የባንኩ ሪፖርት፣ ‹‹ቢውልዲንግ አፍሪካስ ወርክፎርስ ፎር ዘ ፊውቸር›› በሚል መነሻ ሲሆን፣ በባንኩ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የትንበያና የምርምር ክፍል ዳይሬክተር ሐናን ሞርሲ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፣ በአፍሪካ ለትምህርት ኢንቨስት የሚደረገው ገንዘብ ቀላል ባይሆንም በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ ስለማይውል የሚፈለገውን ውጤት አያስገኝም፡፡

ለትምህርት ዘርፍ የሚውለው የመንግሥት ኢንቨስትመንት ለሚፈለገው ዓላማ በተገቢው የጥራትና የሥርጭት ሒደት ባለመዋሉ ሳቢያ፣ በመላ አኅጉሪቱ ያለምንም ተጨማሪ ወጪ ለሁሉም ተደራሽ መሆን የሚችለው የትምህርት አገልገሎት ሊዳረስ እንዳልቻለ አመላክተዋል፡፡ ነገር ግን የአፍሪካን አምስት በመቶ ዓመታዊ በጀት የሚያገኘው የትምህርት መስክ፣ በተገቢው ተቋማዊ አቅምና ብቃት አገልግሎት ሊሰጡ ባለመቻላቸው በርካታ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሳይደርሱ ለማቋረጥ እንደሚገደዱ፣ አቅሙ ባላቸውና በሌላቸው መካከል የሚታው የትምህርት ተደራሽነት ልዩነት እየሰፋ ከመምጣት አልፎ በአሁኑ ወቅት የሚታየው የትምህርት ጥራትም ወጣቶች በሥራ ገበታቸው ላይ ውጤታማ እንዳይሆኑ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ባለሙያዋ አስታውቀዋል፡፡ የመምህራን የጥራትና የብቃት ችግሮች በርካታ ወጣቶችን ትምህርት ለማቋረጥ እንደሚያስገድዳቸው ተጠቅሷል፡፡

የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤፍሬም ታከለ (ዶ/ር) እንደገለጹትም፣ በኢትዮጵያ ብቻ ከ60 በመቶ በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ሲከታተሉ ከሚቆዩ ተማሪዎች ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከመግባታቸው በፊት ለማቋረጥ እንደሚገደዱ ይታመናል፡፡ ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያ ከ70 በመቶው በላይ በገጠር የሚኖር የሕዝብ ቁጥር እንደሚያስተዳድር የሚታመንበት የግብርናው ዘርፍ ለጠቅላላ ኢኮኖሚው የሚያበረክተው አስተዋጽኦ 30 በመቶ ገደማ መሆኑም፣ አብዛኛው የግብርና የሰው ኃይል ምርታማ አለመሆኑን ከማመላከቱም በተጨማሪ፣ አብዛኛው የገጠር ወጣት ያለ ክፍያ የሚሠራ ቤተሰቦቹን ለማገዝ የሚሠራ በመሆኑ በይፋ የማይገለጽ ወይም ድብቅ ሥራ አጥነት ከፍተኛ ሆኖ እንደሚገኝ ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡

በከተሞች አካባቢም ቢሆን ደመወዝ የሚከፈልባቸው የሥራ መስኮች ውስን በመሆናቸው የሥራ አጥነት ለመስፋፋቱ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት በየዓመቱ የሚመረቁ በርካታ ወጣቶች የዚህ ችግር ሰለባ በመሆናቸው፣ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ የግልና የመንግሥት ተቋማት መበራከት አንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ሪፖርቱ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) በቃኘበት ክፍሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሩዋንዳ፣ ጋና፣ ኮት ዲቯርና ታንዛንያ ፈጣንና ከፍተኛውን ዕድገት በማስመዝገብ ግንባር ቀዳሚነቱን እንደያዙ አስፍሯል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ከፍተኛ ዕድገት በማስዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚው አካባቢ ሲሆን፣ ደቡባዊ የአፍሪካ ክፍል የአኅጉሪቱን ዝቅተኛና የተቀዛቀዘ ኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበ ቀጣና ተብሏል፡፡

በመሆኑም በመላው አፍሪካ አማካይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በተያዘው ዓመት 3.9 በመቶ እንደሚሆን ሲጠበቅ፣ በመጪው ዓመት መጠነኛ ጭማሪ በማሳየት ወደ 4.1 በመቶ ከፍ እንደሚል የባንኩ ትንበያ አስፍሯል፡፡ ይሁን እንጂ የፀጥታ ሥጋቶች፣ የበሽታ መስፋፋትና የጤና ጥበቃ ችግሮች ከቻይና መነሻውን እንዳደረገው ኖቭል ኮሮና ቫይረስ ያሉ ወረርሽኞች በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ሥጋት መደገናቸውን የባንኩ ባለሙያዎች ይፋ አድርገዋል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች