Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​​​​​​​በዓመቱ 300 ሺሕ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያቀደው ባለሥልጣኑ በመንፈቁ ከውጥኑ በላይ እንዳሳካ ገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የኢትዮጵያ ቡና ብሔራዊ ንግድ መለያ ይፋ አድርጓል

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በአምስት ወራት ውስጥ ከ120 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ትልቅ ውጤት ማስመዝገቡን አስታወቀ፡፡ በዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት እንዲቻል ከ300 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የዓለም የቡና ዋጋ እየወረደ በመምጣቱ ሳቢያ በገቢ ደረጃ ተፅዕኖ ቢያሳድርም፣ በምርት ረገድ በየጊዜው እየታየ በመጣው ጭማሪ ኪሳራው በተወሰነ ደረጃ ሲካካስ ቆይቷል፡፡ ‹‹የዛሬ አሥር ዓመት ከነበረው ዋጋ አኳያ ብናነጻጽረው፣ አሁን ላይ የቡና ዓለም አቀፍ ዋጋ በ32 በመቶ ወርዶ እናገኘዋለን፡፡ እንደዚህም ሆኖ ግን በዋጋ ደረጃ እስከ 90 በመቶ በሚጠጋ አፈጻጸም ዕቅዳችንን ማሳካት ችለናል፡፡ የስድስት ወራት እንቅስቃሴያችንን የሚያስቃኝ ሪፖርት ገና አላጠናቀርንም፡፡ ነገር ግን በአምስት ወራት ውስጥ የተከናወነውን ስናይ፣ ዘንድሮ በታሪካችን 120 ሺሕ ቶን ቡና ወደ ውጭ ልከናል፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህ ‹‹ለእኛ በጣም ታሪካዊ ውጤት ነው፤›› በማለት የዘንድሮውን የቡና የወጪ ንግድ መጠን ገልጸውታል፡፡

እንደ አዱኛ (ዶ/ር) ከአምስት ዓመታት በፊት፣ ማለትም በ2007 ዓ.ም. አምስት ወራት ውስጥ ወደ ውጭ የተላከው የቡና መጠን 64 ሺሕ ቶን ነበር፡፡ ዘንድሮ የተላከው ምርት ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው አኳያ ሲታይ፣ በእጥፍ ጭማሪ የታየበት ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡

በአንፃሩ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ከታየው እንቅስቃሴ በመነሳት የቡና ምርት ከ180 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ዕድገት ማስመዝገቡን የቡናና ሻይ መረጃ ያሳያል፡፡ ባለፈው ዓመት የመተመዘገበው የምርት መጠን ከ495 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ እንደነበር ባለሥልጣኑ ይጠቅሳል፡፡ ይህም በ1996 ዓ.ም. ከነበረው የ313 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ምርት አኳያ ሲታይ፣ አሁን ላይ የታየው ዕድገት ከ180 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ሆኖ ይገኛል፡፡

የቡና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ከዚህም በላይ ሆኖ ከሚገኝባቸው መገለጫዎቹ መካከል የቡና አምራቾች ቁጥር ይጠቀሳል፡፡ ከአምስት ሚሊዮን በታች የቡና አምራቾች እስከ 95 በመቶ የሚገመተውን የቡና ምርት እንደሚያስገኙ ሲታመን፣ እስከ 25 ሚሊዮን የሚደርሱ ቤተሰቦች ኑሮ በቡና ላይ እንደተመሠረተ፣ ከ1.2 ሚሊዮን ሔክታር ያላነሰ መሬት ለቡና እርሻ እንደዋለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በሌላ በኩል የቡና ምርትና የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋፋት እየተወሰዱ ከሚገኙ ዕርምጃዎች መካከል፣ በብሔራዊ ደረጃ የአገሪቱ መገለጫ የሆነ አዲስ የቡና የንግድ መለያ ወይም ብራንድ ይፋ መደረጉ አንደኛው ጅምር ነው፡፡

የኢትዮጵያን የቡና ታሪክ ከጥንታዊ መነሻን በሎጎ ወይም በምስል ያስቀመጠው አዲሱ የቡና መለያ፣ የእረኛውን የካልዲ ምስል ቡናውን የቀመሰችው ፍየልና የቡና ፍሬ ያለበትን ዛፍ በአረንጓዴ ተቀልሞ፣ ዙሪያውን በኢትዮጵያ ካርታ ተከቦ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ቡና›› የሚል ጽሑፍ በእንግሊዝኛም ጭምር ከሥሩ አስከትሎ ሥራ ላይ የዋለው ብሔራዊ ሎጎ ኢትዮጵያ በዓለም የምትታወቅበት መደበኛ መለያዋ ተደርጓል፡፡

ይህንኑ ብራንድ ጨምሮ በአዲስ በሦስት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ50 ሚሊዮን ዶላር የሚገነባ የቡና ፓርክ ፕሮጀክትም ይፋ ተደርጓል፡፡ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴንን ጨምሮ ታዋቂ ቡና ላኪዎች፣ አምራቾችና አቅራቢዎች የውጭ ገዥዎች የተገኙበት ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የቡና ዓውደ ርዕይና ኮንፈረንስ በሚሊኒየም አዳራሽ ከጥር 28 ቀን እስከ ጥር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ተከናውኗል፡፡ ከ200 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፈውበታል፡፡ 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች