Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና​​​​​​​ሥጋት ያጠላበት የህዳሴ ግድብ ድርድር ወደ መቋጫው እየደረሰ ነው

​​​​​​​ሥጋት ያጠላበት የህዳሴ ግድብ ድርድር ወደ መቋጫው እየደረሰ ነው

ቀን:

ሥጋት ያጠላበት የህዳሴ ግድብ ድርድር ወደ መቋጫው እየደረሰ ነው

‹‹የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ አንድም ቃል ከተካተተ ስምምነቱ አይፈረምም››  

ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፣ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል ተብሎ የበርካቶች ሥጋት የሆነው በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን የታላቁን የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ለስምንት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ድርድር፣ በውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ለማድረግ ወደ መቋጫው እየተቃረበ ነው፡፡

በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት በአሜሪካ ሲካሄድ በቆዩ ሁለት የድርድር ዙሮች የሦስቱ አገሮች የውኃና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ደረጃን በተመለከተ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን፣ የአሜሪካ ትሬዠሪ ዲፓርትመንት ይፋ ያደረገው የጋራ መግለጫ ያመለክታል፡፡

የድርድሩ የቴክኒክና የሕግ ኮሚቴ አባላት በመጪው ሳምንት በአሜሪካ ተገናኝተው ድርድራቸውን እንደሚቀጥሉ፣ እንዲሁም የመጨረሻውን የስምምነት ሰነድ ያዘጋጃሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ይህ ዜና ይፋ ከተደረገ በኋላ በመደበኛውም ሆነ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሐሳባቸውን የገለጹ ኢትዮጵያውያን በርካቶች ሲሆኑ፣ አብዛኞቹም የሚያስተጋቡት ስምምነቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ በመሆኑ መፈረም የለበትም የሚል ነው፡፡

ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ግብፅም ሆነች ሱዳን ጉልህ ጉዳት ሳይደርስባቸው ግድቡን መገንባት ሲገባት፣ እጇ ተጠምዝዞ የገባችበት ድርድር የግብፅን ተጠቃሚነት የሚያጎሉ ምልክቶች እየታዩበት ነው ሲሉም ኢትዮጵያዊያኑ ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ የውኃ አሞላሉና አለቃቀቁ በጣም በተራዘመ ጊዜ እንዲካሄድ በማሰብ በግብፅ አማካይነት የስምምነት አንቀጾች እንዲገቡ እየተደረገ፣ እንዲሁም ድርቅን በተመለከተ የገቡ አንቀጾች የግብፅን ጥቅም የሚያስከብሩና የኢትዮጵያን ጥቅም ችላ ያሉ ናቸው ሲሉም ወቀሳቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለዘመናት የሚታወቅ የውኃ ዕዳ እንዲኖርባት ሊያደርግ ይችላል ሲሉም ያክላሉ፡፡

ግብፅ በዚህ ስምምነት ተጠቃሚ የመሆን ዕድሉን ካገኘች፣ በተዘዋዋሪ ግድቡን ለመቆጣጠር የሚያስችላት ኃይል እንደምታገኝም እየገለጹ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ ወደፊት በዓባይ ወንዝ ላይ በምታከናውናቸው ማናቸውም ፕሮጀክቶች ላይ ግብፅ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደር እንደምትችል መዘንጋት አይገባም ሲሉ ሥጋታቸውን ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ባለፉት ስምንት ዓመታት በህዳሴ ግድቡ ላይ ድርድር እያደረጉ ቢቆዩም፣ አሁን ላይ ግብፅ፣ አሜሪካንና የዓለም ባንክን በመጠቀም ኢትዮጵያ ያልተፈለገ ግዴታ ውስጥ እንድትገባ ግፊት እየተደረገባት መሆኑ አግባብ አለመሆኑ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን በፍጥነት እንድትፈርም እየተደረገባት ያለው ጫና ተገቢ አለመሆኑን የሚገልጹት ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ውሉን ጊዜ ወስደው እንዳይገመግሙ መደረጉ ሥጋት አጭሮባቸዋል፡፡ በተለይም አሜሪካና የዓለም ባንክ የድርድር ስምምነቱን ሱዳንና ግብፅን በሚጠቅም መንገድ እያደረጉ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የድርድሩ ሰነድ እንየተረቀቀበት ያለው መንገድም አግባብ እንዳልሆነና የኢትዮጵያ ቡድን የሚያቀርበው ሐሳብ ውድቅ እየተደረገበት መሆኑ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ጋር በተገናኘ ኢትዮጵያን በድርድሩ ላይ የወከለው ቡድን የድርድሩን ሚዛን አለመጠበቁን ለሕዝብ ከማጋለጥ ይልቅ፣ የድርድር ሒደቱን ትክክለኛነት መግለጻቸው ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ድርድሩ እንዲህ በተፋጠነና በተፅዕኖ ሥር ወድቆ መካሄዱ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ከአራት እስከ ሰባት ዓመታት ድረስ ለመሙላት ብታቅድም፣ የድርድሩ ረቂቅ ውል ግን ግድቡ የሚሞላበትን ጊዜ ክፍት ማድረጉ ተገቢ አለመሆኑን ባለሙያዎች እየገለጹ ነው፡፡

ግብፅና ሱዳን ድርቅ በሚያጋጥማቸው ወቅት ኢትዮጵያ ወደ ህዳሴ ግድቡ የሚገባውን ውኃ ሙሉ ለሙሉ መልቀቅ እንዳለባት የሚገልጸው የስምምነት ሰነድ፣ ድርቅ በሌለበት ወቅት ግን ኢትዮጵያ የምትለቀው ውኃ መጠን አለመገለጹ ሆን ተብሎ ኢትዮጵያን ለመጉዳት የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ድርድሩ ኢትዮጵያ ወደፊት በዓባይ ወንዝ ላይ በምታቅዳቸው ፕሮጀክቶች አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲሚኖረው የሚገልጹት ባለሙያዎች፣ ኢትዮጵያ ይህን የድርድር ሰነድ እንዳትፈርም ጠይቀዋል፡፡ በአሜሪካና በዓለም ባንክ መሪነት የሚደረገው ድርድርም ግብፅና ሱዳን የሚጠቅም በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከድርድሩ እንድትወጣ ባለሙያዎቹ ጠይቀዋል፡፡ 

ነገር ግን ሐሙስ ጥር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. የስትራቴጂካዊ ጥናት ተቋም ባዘጋጀው የግድቡን ሁኔታ የተመለከተ ሴሚናር ላይ ተገኝተው ገለጻ ያደረጉት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያን የብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ምንም ዓይነት ስምምነት አይፈረምም በማለት ሥጋቱን አጣጥለውታል፡፡

በውይይቱ ወቅት ከእሳቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ኤክስፐርቶች ቡድን አባላት ማለትም አቶ ጌዲዮን አስፋው (ኢንጂነር)፣ አቶ ክፍሌ ሆሮ (ኢንጂነር)፣ እንዲሁም አቶ ተፈራ በየነ በውይይቱ ላይ በመገኘት ግድቡ ስለሚሰጠው ጥቅምና አጠቃላይ የስምምነቱን ሒደት፣ እንዲሁም ግድቡ በአሁን ወቅት ስለሚገኝበት ሁኔታ ለተሳታፊዎች ማብራሪያና ገለጻ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ሚኒስትሩ ድርድሩ የሚካሄደው ሁሉንም ወገን አሸናፊ በሚያደርግ መርህ ላይ ተመርኩዞ መሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ስምምነት ፈፅሞ አንፈርምም፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ግድቡ እንዴት ይሞላል? ድርቅ በሚኖርበት ጊዜ እንዴት ይሆናል? የሚሉት ነጥቦችን በተመለከተ አሰልቺና አድካሚ ድርድር ማካሄዳቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በሚኖረው የአየር ሁኔታ ላይ ተመሥርቶ በደረጃ ሙሌቱ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡

የአየር ሁኔታ ማለት ደግሞ በደረቃማ ዓመታት፣ በተራዘመ የድርቅ ወቅት፣ እንዲሁም በድርቅ ወቅት የሚለው ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ከዚህ ጋር በተያያዘ በቃላቱ ላይ መግባባት አለመቻሉን በማስረዳት፣ ሙሌቱም ሆነ አለቃቀቁ የሚከናወነው በሚኖረው የዝናብ መጠን በመሆኑ ግድቡን ለመሙላት ከአራት እስከ ሰባት ዓመታት የሚወስድ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በስትራቴጂካዊ ጥናት ተቋም ከተካሄደው ሴሚናር አስቀድሞ ረቡዕ ጥር 27 ቀን 2012 ዓ.ም. በድርድሩ ላይ መግለጫ ሰጥተው የነበሩት ሚኒስትሩ፣ ‹‹የኢትዮጵያን የውኃ መጠቀም የሚጎዳ ‹አንዲት ቃል› እንኳን ብትኖር ኢትዮጵያ ስምምነቱን አትፈርምም፤›› ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡  

የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል የሆኑት አቶ ጌዲዮን አስፋው (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ ድርድሩ ስለህዳሴ ግድብ ብቻ መሆኑንና የኢትዮጵያን የወደፊት የውኃ አጠቃቀምን የማይመለከት መሆኑን ማስረገጥ የሚለው ዋነኛ ነጥብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ የሚያደርገው ድርድር ውጤት የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም እንደሚያስጠብቅ ማረጋገጫ የሰጡት የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ (/) ይህንን ኃላፊነት የተረከቡት አገራቸውን ለማገልገል እንጂ የፖለቲካ አባልና ሹመኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ኢትዮጵያ በግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ ከግብፅና ሱዳን ጋር እያደረገች ያለው ድርድር የደረሰበት ደረጃና ውጤቶችን በተመለከተ፣ ባለፈው ሐሙስ ተዘጋጅቶ በነበረ ሴሚናር ላይ ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቲንክ ታንክ ተቋም የሆነው የስትራቴጂክ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ባዘጋጀው በዚህ ሴሚናር ላይ የድርድሩን ይዘትና የእስካሁን ውጤቶችን የተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያን ተደራዳሪ ቡድን በበላይነት የሚመሩት ስለሺ (/)፣ በኢትዮጵያናግብፅ መካከል ትብብርን መሠረት ያደረገ ስምምነት መድረስ ከተቻለ የህዳሴ ግድቡ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሁለቱም የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች የተሻለ ጥቅም እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎችም የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም የሚጎዳ አንዲት ስምምነት እንደማይቀበሉና እንደማይፈርሙም ተናግረዋል። የሴሚናሩ ተሳታፊዎች ድርድሩ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም የሚጎዳ የቃላት አተረጓጎም እስካሁን በተደረሰው ስምምነት ስላለመካተቱና የውጭ ኃያላን ጣልቃ ገብነት የአገርን ጥቅም እንዳይጎዳ ያላቸውን ሥጋት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ለዚህ ያለውን አቋምና ዝግጁነት የተመለከቱ ጥያቄዎች አቅርበዋል።

ከተሳታፊዎች ለቀረቡላቸው፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሚዲያዎች የሚያነሱትን ተመሳሳይ ሥጋትና ጥርጣሬ አገናኝተው ሚኒስትሩ ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል። ‹‹እኔ የፖለቲካ ሹመኛ አይደለሁም፤›› በማለት የጀመሩት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ይኼንን ኃላፊነት የተቀበልኩት አገሬን ለማገልገል ነው፤›› ብለዋል። ብቃትና የረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ወደዚህ ኃላፊነት እንዲመጡ የመደረጋቸው ምክንያትም፣ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበርና የድርድር ሒደቱም እንዲፋጠን ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ቴክኒካዊ ስለሆነው የድርድሩ ይዘት የጠራ ግንዛቤ ሳይኖራቸው፣ የአገራቸውን ጥቅም እያስከበሩ በሚገኙ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ላይ የስም ማጥፋት ዘገባዎች ላይ መባዘናቸው እንደሚያሳዝናቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች በኩል ለሕዝብ የሚነገሩ መረጃዎችን ሚዲያዎቹ በጥርጣሬ እንደሚመለከቷቸው የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች የሚገለጸውን መረጃ ማመን ካልተቻለ ከግብፅ ሚዲያዎች ዘገባ ማመሳከር እንደሚቻል፣ ነገር ግን ከዚያ ይልቅ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎችን ማጥቃት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል

ኢትዮጵያ በከባድ ድርቅ ወቅት ከግድቡ ለግብፅ ውኃ ለመልቀቅ በድርድሩ እንደተገደደች የተዛባ ግንዛቤ መኖሩን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በከባድ ድርቅ ወቅት የሚለቀቅ ውኃ ኃይል ሳያመነጭ እንደማያልፍና ከባድ ድርቅ የሚባለው የመከሰት ዕድሉ እጅግ ጠባብና በበርካታ አሥርት ዓመታት ውስጥ አንዴ እንደሚያጋጥም ገልጸዋል።

ከባድ ድርቅ ለሚለው የተሰጠው ትርጓሜ ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን 31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እንደሆነና እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚ የተከሰተው ... 1973 እና 1984 እንደነበር ጠቁመዋል። ግድቡ ከሚገኝበት የባህር ወለል እስከ 595 ሜትር የሚደርሰውን የግድቡን ከፍታ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 18.4 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ለመሙላት ስምምነት መደረሱን፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ቀሪው የውኃ ሙሌት ቢበዛ በአምስት ዓመት ውስጥ እንደሚሞላም ገልጸዋል።

ከዚህ ሴሚናር አንድ ቀን ቀደም ብሎ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ከግብፅናሱዳን ጋር የሚደረገው ድርድር የኢትዮጵያን በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብት በዘላቂነት በሚያስጠብቅ ሁኔታ እንደሚፈጸም፣ ከዚህ ውጪ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ አንድም ቃል ከተካተተ እንደማይፈረም አስታውቀዋል፡፡

ግድቡን በተመለከተ አሜሪካና የዓለም ባንክ በታዛቢነት በተገኙበት በአራት የተለያዩ ሰነዶች ላይ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር ድርድር ተካሂዶ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ያብራሩት ሚኒስትሩ፣ በተለይም ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት የሦስቱን አገሮች ጥቅም የሚያስጠብቅ ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል። የግድቡ ውኃ አሞላልን በተመለከቱ ቴክኒካዊ፣ ሕጋዊ፣ የግጭት አፈታትና የትብብር ጉዳዮች ላይ ስምምነት ቢደረስም፣ ስምምነቶቹ ወደ ሕግ ማዕቀፍ ካልተቀየሩ በስተቀር ኢትዮጵያ ስምምነቱን ላለመፈረም አቋም በመያዟ አለመፈረሙን አስታውቀዋል፡፡  

ስምምነቱን ወደ ሕግ ማዕቀፍ የመቀየር ሥራ በሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች እየተከናወነ እንደሚገኝ፣ በዚህ ሒደት ሌላ ችግር ካልተፈጠረ በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ስምምነቱ ሊፈረም እንደሚችል ጠቁመዋል።

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...