Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ቻይናን ማግለል ለኮሮና ቫይረስ መፍትሔ አይሆንም››

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመቆጣጠር ቻይናን ማግለል መፍትሔ  እንደማይሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት ቻይናን ማግለል መፍትሔ አይሆንም፡፡ ‹‹የዓለም ጤና ድርጅት ወደ ቻይና የሚደረጉ በረራዎችን ማቋረጥ ለችግሩ መፍትሔ አይሆንም፣ እንዲውም ያባብሰዋል ሲል ግልጽ መግለጫ አውጥቷል፡፡ እኛም ይህን እንደግፋለን፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ ቢያቋርጥ በሽታው ወደ ኢትዮጵያ እንደማይገባ ማረጋገጥ እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

በርከት ያሉ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጓቸውን በረራዎች ያቋረጡ ቢሆንም፣ ብዙ አየር መንገዶች አሁንም ወደ ቻይና ይበራሉ፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጓቸውን በረራ በማቆም ላይ ሲገኙ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጓቸውን በረራዎች ቀንሰዋል፡፡

ግዙፉ የኤምሬትስ አየር መንገድ ወደ ሻንጋይና ጓንዡ የሚያደርገውን በረራ በማቋረጥ፣ ወደ ቤጂንግ የሚያደርገውን በረራ ቀጥሏል፡፡

አቶ ተወልደ እንደሚሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ ቢያቋርጥ፣ ሌሎች አየር መንገዶች የቻይና መንገደኞችን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣታቸው አይቀርም፡፡ ‹‹ወደ ቻይና ባንበር እንኳ ወደ ሲንጋፖር፣ ታይላንድ፣ ማሌዥያ፣ ኮሪያና ጃፓን እንበራለን፡፡ በስታር አልያንስ አባልነታችን፣ በኮድ ሼር ኢንተርላይን ስምምነቶች የቻይና አየር መንገዶች የቻይና መንገደኞች አምጥተው ይሰጡናል፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ባንኮክ በየቀኑ የሚበር በመሆኑ የቻይና መንገደኛ ከባንኮክ ተቀብሎ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ‹‹መታወቅ ያለበት የትራንዚት ግንኙነት እስካለ ድረስ መንገደኞች አይመጡም ማለት አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

በምሳሌነት የጠቀሱት የብሪቲሽ ኤርዌይስ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ ያቋረጠ ቢሆንም፣ የቻይና አየር መንገዶች ግን ወደ ለንደን በመብረር ላይ ናቸው፡፡ ‹‹ለንደን የገባውን የቻይና መንገደኛ እኛ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ልናመጣው እንችላለን ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በእስያ የታይላንድ፣ የኮሪያ፣ የጃፓን የሲንጋፖርና የአውስትራሊያ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ ቀጥለዋል፡፡ ‹‹ዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ ቢያቋርጥ እንኳ የቻይና መንገደኞችን ከታይላንድ፣ ከፊሊፒንስ፣ ከኢንዶኔዥያ፣ ከማሌዥያ፣ ከጃፓን፣ ከኮሪያ፣ ከሲንጋፖር ሊያመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሊደረግ የሚገባው በመነሻ፣ በትራንዚትና በመዳረሻ ኤርፖርቶች ላይ የሚደረገውን ጥንቃቄ ማጠናከር እንጂ ወደ ቻይና የሚደረጉ በረራዎችን ማቋረጥ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በቅርበት በመሥራት ላይ እንደሆነ ጠቁመው፣ የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው የአሠራር መመርያ መሠረት በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የሚደረገው ጥንቃቄ መጠናከር እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡

‹‹ለሥራ ባልደረቦቻችን፣ ለመንገደኞቻችንና ለሕዝባችን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አምስት የቻይና ከተሞች የሚበር ቢሆንም፣ ሁዋን የተባለችው የኮሮና ቫይረስ መነሻ የሆነችው ከተማ ግን እንደማይበር ታውቋል፡፡ በሳምንት 35 በረራዎች ወደ ቻይና የሚያከናውነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየቀኑ በአማካይ 4,000 ቻይናውያን፣ በቻይናና በአፍሪካ መካከል ሲያጓጉዝ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቻይና ወደ አዲስ አበባ ከሚያመጣቸው ቻይናውያን መንገደኞች መካከል 30 በመቶ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሲሆኑ፣ 70 በመቶ ወደ ሌሎች አፍሪካ አገሮች ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፡፡

የጤና ክትትሉ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ 1,500 ቻይናውያን ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ፣ በየዕለቱ 2,000 ያህል ቻይናውያን በአዲስ አበባ ኤርፖርት በትራንዚት ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች በመጓጓዝ ላይ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1972 ወደ ቻይና ፔኪንግ መብረር የጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ አሁን ቻይናና አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት በማገናኘት ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ‹‹የአፍሪካ አገሮች ከቻይና ጋር ጠንካራ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ አቋረጠ ማለት ይህ ግንኙነት ይቋረጣል ማለት ነው፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፓን አፍሪካን አየር መንገድ በመሆኑ ወደ አፍሪካ አገሮች የሚበረው በመልካም ጊዜ ብቻ ሳይሆን በመከራም ጊዜ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የአፍሪካ አገሮች በኢቦላ በተጠቁ ጊዜ በረናል፡፡ ያኔ አቁመን ቢሆን ኖሮ እነዚያ አገሮች ዛሬ ምን ይሰማቸው ነበር? የዛሬ 30 ዓመት አንጎላ በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመስበት ወቅት ሉዋንዳ ኤርፖርት በተኩስ መካከል እንበር ነበር፡፡ አፍሪካውያን እህቶቻችንና ወንድሞቻችን በመሆናቸው በችግር ጊዜ አብረናቸው ልንቆም ይገባል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ አየር መንገድ ነው፤›› ያሉት አቶ ተወልደ የተጠናከረ ጥንቃቄ በአውሮፕላን ውስጥ፣ በመነሻና በመድረሻ ኤርፖርቶች ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትና በ27 የድንበር ኬላዎች የሚካሄደው የማጣራት ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል፡፡ እስከ ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለ47,162 ተጓዦች የሙቀት መለያ ምርመራ መደረጉን፣ ከእነዚህም ውስጥ 1,605 ተጓዦች የመጡት ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገባቸው አገሮች እንደሆነ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሌሎች አገሮች አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ ሲያቋርጡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለምን አላቋረጠም?›› ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹አየር መንገዱ በሚበርባቸው አምስት የቻይና ከተሞች የሚታየው የበሽታው ሥርጭት ምጣኔ በጣም አነስተኛ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሌሎች አገሮች ያደረጉትን የበረራ ማዕቀብ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውንና ሁሉም አገሮች የተቀበሉትን ‹ኢንተርናሽናል ሔልዝ ሬጉሌሽን› (አይኤችአር) 2005 የጣሰ ነው በሚል ኮንኖታል፡፡ በረራውን ማቆም በሽታውን ለመቀነስ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያደናቅፍና እንደሚያውክ፣ የዓለም የጤና ድርጅት መግለጹን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ስለዚህ አገሮች በረራውን ከማቆማቸው በፊት ቆም ብለው ማሰብና በኤችአይአር 2005 የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ታሳቢ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ማሳሰቡን፣ ከዋናው ዳይሬክተር ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ (ታደሰ ገብረ ማርያም ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል)

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች