Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የአፍሪካ ዝግጁነት እስከምን?

ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የአፍሪካ ዝግጁነት እስከምን?

ቀን:

አፍሪካውያን ለተለያዩ በሽታዎች የመጋለጣቸው ምክንያት ድህነት ነው፡፡ በድህነት ጥላ ሥር የሚካተቱት የትምህርት ተደራሽ አለመሆን፣ የአካባቢና ግል ንፅህና ጉድለት፣ የሕክምና አለመዳረስ፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ አለመረጋጋት አፍሪካውያን በጤናና በሰላም እንዳይኖሩ ማነቆ ሆኗል፡፡

በጤናው ዘርፍ በኤችአይቪ ኤድስ ሳቢያ በሚሊዮን የረገፉትና ከቫይረሱ ጋር በብዛት የሚኖሩት አፍሪካውያን ናቸው፡፡ ኮሌራ፣ ወባና ሌሎችም በግልና አካባቢ ንፅህና ሊወገዱ የሚችሉ በሽታዎች ለአፍሪካውያን የዳገት ያህል የከበዱ ናቸው፡፡ የእናቶችና ሕፃናት ሞት ላይ አሁን መሻሻል ቢኖርም፣ ችግሩ ግን አልተወገደም፡፡

ተላላፊ የሆኑትም ሆነ ያልሆኑት በሽታዎች ለአፍሪካ ሁሌም ፈተና ናቸው፡፡ አፍሪካ ታክመው በሚድኑት ወይም ቀድመው መከላከል በሚችሉት በሽታዎች ብቻ ሳይሆን ከዚህ በከፉትም ትጠቃለች፡፡ ኢቦላ ምዕራብ አፍሪካን የፈተነ ገዳይ ቫይረስ ነው፡፡ የአፍሪካ የጤና ሥርዓት በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ሆኖም ለሠለጠነው ዓለም ቀላል የሆኑና እምብዛም የማይከሰቱ በሽታዎችን ለመመከት እንኳን የሚበቃ አይደለም፡፡

አብዛኞቹ ከሰሀራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮችም ለሌሎች ተራ የሚባሉ ግን ገዳይ በሽታዎችን በማከም የተጣበቡ ናቸው፡፡

 መነሻውን ቻይና ያደረገው ኮሮና ቫይረስ ደግሞ እስካሁን አፍሪካ ገብቷል ተብሎ ባይነገርም፣ የአኅጉሪቱ ቀጣይ የጤና ቀውስ ሊሆን እንደሚችል ሥጋት አለ፡፡

በቻይና ከ28 ሺሕ በላይ ሰዎችን አጥቅቶ ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎችን የገደለው የኖቭል ኮሮና ቫይረስ አፍሪካ ቢገባ ‹‹በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ከባድ ፈተና ይሆናል፡፡

ይህ ቫይረስ ወደ አፍሪካ እንዳይገባ፣ ቢገባም ባለበት ለማቆም አገሮች በየመግቢያ ኬላዎቻቸው ቅድመ ምርመራ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረጉም ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ቫይረሱ አገር ቤት እንዳይገባ፣ ከገባም ለማከም የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡ ከሦስት የሕክምና ቦታዎች በተጨማሪ ላቦራቶሪ ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በቫይረሱ የተጠረጠሩ ሰዎች ደም ደቡብ አፍሪካ ተልኮ ይመረመር የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ እዚሁ ኢትዮጵያ መመርመር የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል፡፡

አፍሪካ ኮሮና ቫይረስ ካልገባባቸው ሁለት አኅጉሮች አንዷ ናት፡፡ የኮሮና ቫይረስ ለአፍሪካ ሥጋት መሆኑንና የአፍሪካ ዝግጁነትን አስመልክቶ ቢቢሲ እንዳሰፈረው፣ የጤና ኤክስፐርቶች የኮሮና ቫይረስ በቅርቡ አፍሪካ ሊገባ ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አፍሪካና ቻይና ያላቸው ቅርብ ግንኙነት ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የዓለም ጤና ሥጋት ነው ብሎ ካወጀ ካለፈው ሳምንት ወዲህ በተለይ ደሃ አገሮች ችግሩን መቋቋም አይችሉም የሚል ሥጋት ተፈጥሯል፡፡

ኮሮና ቫይረስ የዓለም ጤና ሥጋት ሆኗል ብሎ መታወጁም ቫይረሱ በቻይና ስለተከሰተ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች አገሮች ቢስፋፋ ችግሩን መቋቋም ያቅታል ከሚል መሆኑንና ዝቅተኛ የጤና ሥርዓት ባላቸው ደሃ አገሮች ቫይረሱ የመሰራጨት አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ ችግሩን ከወዲሁ ለመቅረፍ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

በአፍሪካ በበርካቶቹ አገሮች የሚገኘው የጤና ሥርዓት ከአቅሙ በላይ የሆኑ ሕሙማንን ለማከም በሚፍጨረጨርበት በአሁኑ ሰዓት በጣም ከባድ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ኢንፌክሽን ለማከም ይችላሉ ወይ? የሚል ሥጋትም ተፈጥሯል፡፡

በድርጅቱ የአፍሪካ የአስቸኳይ ጊዜ ሕክምና ምላሽ ኃላፊ ማይክል ያኦ እንደሚሉትም፣ በአፍሪካ የሚገኙ አንዳንድ አገሮች ራሳቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል ያላቸው አቅም ውሱን ነው፡፡

‹‹በአፍሪካ ያለው የጤና ሥርዓት የተንኮታኮተ ነው፡፡ ይኼውም በአኅጉሪቱ በየጊዜው በሚከሰቱ ወረርሽኞች የሚጠቁ ሰዎችን በማከም የተጨናነቀ ነው፡፡ ስለሆነም ኮሮና ቫይረስ በየአገራቱ ከመሠራጨቱ አስቀድመን ልንገታው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

አፍሪካ በሽታውን ለመከላከል ምን ያህል ዝግጁ ናት?

ኮሮና ቫይረስ ተከሰተ ከተባለበት ጊዜ አንስቶ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ቫይረሱን ለመለየት የሚያስችል ላቦራቶሪ የነበራቸው ደቡብ አፍሪካና ሴኔጋል ብቻ ነበሩ፡፡ ሁለቱ አገሮች ከአኅጉሪቱ የሚላኩላቸውን በመመርመር እንደ ሪፈራል ላቦራቶሪ እያገለገሉ ነው፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ምርመራውን ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ ማድረግ የሚያስችል ላቦራቶሪም ተቋቁሟል፡፡

ጋና፣ ማዳካስካር፣ ናይጄሪያና ሴራሊዮንም ምርመራውን ማድረግ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅትም እስካለፈው ሳምንት ድረስ ለ29 ላቦራቶሪዎች የመመርመሪያ ኪት ልኳል፡፡ በቀጣዩ ወር 36 የአፍሪካ አገሮች ኮሮና ቫይረስን ሊመረምሩ የሚችሉበት አቅም የሚገነባም ይሆናል፡፡

የአፍሪካ አገሮች በበኩላቸው የቅድመ መከላከል ሥራውን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ናይጄሪያ አንድ ሚሊዮን በጎ ፈቃደኞች በንቃት እንዲጠብቁ ስታደርግ፣ የታንዛኒያ ጤና ሚኒስትር ኡሜ ሙዋሊሙ በአገሪቱ በደቡብ፣ በምሥራቅና በምዕራብ አካባቢዎች ለይቶ የማከሚያ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከሁለት ሺሕ በላይ የጤና ባለሙያዎችም ሠልጥነዋል፡፡

ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ አይቮሪኮስት፣ ጋና፣ ቦትስዋና ደግሞ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ ሰዎችን በማቆያ ቦታ እያስቀመጡ ምርመራ እንዲመረመሩ አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፣ ለሕክምና ባለሙያዎችም እየተሰጠ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ዘገባውን እስካጠናቀርንበት የካቲት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ አልተከሰተም፡፡

አፍሪካ ከኢቦላ ቫይረስ ምን ትማራለች?

እ.ኤ.አ. ከ2014 እስከ 2016 በምዕራብ አፍሪካ በቅርቡ ደግሞ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የተከሰተው ኢቦላ፣ የአፍሪካ አገሮች በሽታን የመቋቋም አቅማቸው ደካማ እንደሆነ ያሳየ ነው፡፡

አገሮች በሽታ ከመሠራጨቱ በፊት ቀድመው እንዲለዩ በዓለም ጤና ድርጅት በኩል ውትወታ ቢደረግም፣ አፍሪካ ይህንን ማሳካት አልቻለችም፡፡ በተለይ ለመቋቋም ፈታኝ የሆኑና የሚዛመቱ በሽታዎችን ለመቋቋም ቀድሞ የመከላከል ሥራው ደካማ ነው፡፡

በመሆኑም ኢቦላ ቫይረስን ለመከላከል የነበረው ከፍተኛ ለኮሮና ቫይረስ በሚደረገው ቅድመ ዝግጅት ላይ መታየት እንደሌለበት፣ ኮሮና ቫይረስ አፍሪካ ጉዳቱ የከፋ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

በአፍሪካና በቻይና መካከል የሚደረግ ጉዞ

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የአፍሪካና ቻይና የንግድ ልውውጥ የኮሮና ቫይረስ ወደ አፍሪካ እንዲገባ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ምልከታም አለ፡፡ ቻይና የአፍሪካ ቀዳሚ የንግድ አጋር ስትሆን፣ በአኅጉሪቱም አሥር ሺሕ ያህል የቻይና ኩባንያዎች ይሠራሉ፡፡

የቻይና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንዳሰፈረውም፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቻይናውያን በአፍሪካ  ይኖራሉ፡፡

ከ50 ሺሕ በላይ አፍሪካውያንም በቻይና ይማራሉ፡፡ ከአፍሪካ ወደ ቻይና የሚደረገው የአየር ትራንስፖርትም ከፍተኛ ነው፡፡ በርካታ አገሮች ወደ ቻይና የሚደረግ የአየር ጉዞን አግደዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል ሲባል ከአፍሪካ ግብፅ፣ ኬንያ፣ ሞሮኮና ሩዋንዳ ወደ ቻይና በረራ ያቆሙ ሲሆን፣ በአፍሪካ ትልቁ የሆነው የኢትዮጵያ ግን አላቋረጠም፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት አገሮች ወደ ቻይና የሚደረግ ጉዞ ላይ ገደብ መጣላቸው ትክክል አይደለም ቢልም፣ ከቻይና ጋር ከፍተኛ ግንኙነት ያላቸው ቀዳሚ  በቫይረሱ ሊጠቁ የሚችሉ 13 አገሮችን ገልጿል፡፡ እነርሱም አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ አይቮሪኮስት፣ ኬንያ፣ ሞሪሻየሻ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና ዛምቢያ ሲሆኑ፣ ድርጅቱ ለእነዚህ አገሮች ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞች ለማድረግ ማቀዱን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...