Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሙዚቃ አቀናባሪ ሻለቃ መላኩ ተገኝ (1937-2012)

የሙዚቃ አቀናባሪ ሻለቃ መላኩ ተገኝ (1937-2012)

ቀን:

ዜና ዕረፍት፣ ሙዚቃ፣ ሻለቃ መላኩ ተገኝ

‹‹ጥላሁን ገሠሠ

ዘፈኑ ነገሠ

ብዙነሽ በቀለ

ድምፅ እንዳንቺ የለ

ተፈራ ካሳ

ድምፀ ለስላሳ

መሐሙድ አህመድ

ድምፀ ነጎድጓድ

እሳቱ ተሰማ

ድምፅ የተስማማ፡፡››

እየተባለ ይነገርበት በዜማ ይተዋወቅበት የነበረው የ1950ዎቹና 1960ዎቹ ወርቃማ የሙዚቃ ዘመን ከነበሩትና በ1970ዎቹም ከተሻገሩት ከእነዚህ ታላላቅ ድምፃውያን ጀርባ ላቅ ያለ ተግባር ያከናወኑ የዜማና ግጥም ደራሲዎች የሙዚቃ አቀናባሪዎች እነ ሳህሌ ደጋጎ፣ አየለ ማሞ፣ መላኩ ተገኝና ሌሎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከገናናዎቹ  የሙዚቃ ክፍሎች አንዱ የነበረው የነጥላሁን ገሠሠ ቤት የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ካፈራቻቸው የሙዚቃ አቀናባሪዎች ሻለቃ መላኩ ተገኝ አንዱ ናቸው፡፡

በ12 ዓመት ዕድሜያቸው ሙዚቃን የጀመሩት ሻለቃ መላኩ ከክብር ዘበኛ (በኋላ ማዕከላዊ ዕዝ) በምድር ጦር፣ በሐረር ሦስተኛ ክፍለ ጦር የሙዚቃ ክፍል በኪቦርድ ተጫዋችነትና አቀናባሪነት ማገልገላቸው ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

የበኩር ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ የ13 ወር ጸጋ፣ ፈልጌ አስፈልጌ፣ ምን ታደርጊዋለሽ፣ የካሴት ሥራ ዋናውን የቅንብርና የዜማ ስኬት ውስጥ የላቀ ድርሻ እንደነበራቸው ይወሳል። በክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ውስጥ በድንቅ ቅንብር በሻለቃ አቀናባሪነት (ኦርጋን) ለታሪክ ከተሠሩት የብዙነሽ በቀለ ጭንቅ ጥብብየማህሙድ አህመድ ችሎታ፣ እንዳንቺ አላየሁም፣ መላኩን ዝነኛ ያደረጋቸው ልጨኛ ሥራቸው (ማስተርፒስ) ነው፡፡ የታምራት ሞላን፣ የዓባይ በለጠን፣ የጥላዬ ጨዋቃን የሲሳይ ገሠሠን ‹‹ቀበጥባጣ ወጣት››፣ ‹‹ማራቶን ልዕልቷ››፣ አለሙሽ አሰቡሽ፣ ምነው ተለየሽኝ ጨምሮ የሌሎችንም በርካታ ድምፃውያንን የሙዚቃ አልበሞችን ሙዚቃ ቅንብር ሠርተዋል።

ከአቀናባሪነታቸው በተጨማሪ በድምፃዊነት ካቀነቀኗቸውመዓዛ መዓዛ ‹‹መርሳት አይገባም›› ይጠቀሳሉ፡፡ ከ1983ቱ የመንግሥት ለውጥ በኋላም በጋዜቦ፣ ጣይቱ ሆቴል፣ ኢምፔሪያልና በለንደን ካፌ በሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነት ሲሠሩ ቆይተዋል።

በትግራይ በሙዚቃ አስተማሪነት ያገለገሉት ሻለቃ መላኩ፣ በተለይ ከሦስቱ ሴት ቫዮሊን ተጫዋቾች ፀሐይ ተስፋዬ፣ ሠናይት ደጀኔና ፍቅርተ ተሰማ እንዲሁም ከሳክስፎን ተጫዋቾቹ ጴጥሮስ ጋር 16 ዓመታት በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበረ ሙዚቃ መጫወታቸው ይወሳል፡፡ በግላቸውም አምስት በመሣሪያ የተቀነባበሩ አልበሞችን አሳትመዋል፡፡

ሻለቃ መላኩ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው 75 ዓመታቸው ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. አርፈው፣ በማግስቱ ሥርዓተ ቀብራቸው በአዲስ አበባ ለቡ በሚገኘው በምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል። ሻለቃ መላኩ ተገኝ የአራት ልጆች አባት ነበሩ፡፡

ባለማንዶሊኑ የዜማ ደራሲ አየለ ማሞ፣መላኩ ተገኝ አሻራው እስከዛሬ የዘለቀ፣ ዜማን በጥሩ ሁኔታ የሚረዳና ብቁ የሙዚቃ ሰው ነበር” ሲል ገልጸዋቸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...