በተመስገን ተጋፋው
ከሰማንያ አራት ዓመታት በፊት ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሰኔ 23 ቀን 1928 ዓ.ም. የፋሺስት ጣሊያን ወረራ በመቃወም በጄኔቭ የመንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ባደረጉት ንግግር፡ ‹‹…ከእግዚአብሔር መንግሥት በቀር የፍጡር መንግሥት ሁሉ አንዱ ከአንዱ የማይበልጥ ሥራ የለውም፡፡ ነገር ግን በምድር ላይ ኃይለኛ የሆነው መንግሥት ምንም በደል የሌለበትን የሌላውን መንግሥት ሕዝብ ለማጥፋት የሚገባው መስሎት በተነሳበት ጊዜ ተጠያቂው ወገን ለመንግሥት ማኅበር የተበደረውን የሚያቀርብበት ሰዓት ነው፡፡ እግዚአብሔርና ታሪክ ለምትሰጡት ፍርድ ለመንግሥት ማኅበርም ምስክር ሆነው ይመለከታሉ፤›› ብለው ነበር፡፡ ይህ የጃንሆይ ንግግር ኢትዮጵያን እንደ ነፃነት ተምሳሌት የሚወስዱ ጥቁር ሕዝቦችን እሮሮ ያስተጋባ ነበር፡፡ የዓድዋ ድል ጥቁሮች ነጮችን ድል መንሳት እንደሚችሉና ነፃነታቸውን ለመቀዳጀት እንዲታገሉ ያነሳሳ ነበር፡፡
የነፃነት ትግሉ ከተጧጧፈባቸው መንገዶች አንዱ በጃማይካ ምድር የተወለደው ሬጌ ሙዚቃ ነበር፡፡ ከነጮች የጭቆና ቀንበር ለመገላገል የታገሉ ጥቁሮች ኢትዮጵያ የነፃነት ምልክታቸው ናትና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንግግር በሬጌ ሙዚቃ ማስተጋባቱ አልቆመም፡፡
የሬጌ ሙዚቃን በመጫወትና ለሕዝቡ እንዲደርስ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው የሬጌ ሙዚቃ ፈር ቀዳጅና በዓለም ደረጃ ታዋቂ እንዲሆን ካደረጉት መካከል በቀደምትነት የሚጠቀሰው ቦብ ማርሌ ነው፡፡
ከሰባ አምስት ዓመት በፊት የተወለደው ቦብ የሙዚቃ ሕይወቱን የጀመረው በ1960ዎቹ ቺተር ቶሽና ቦኒ ዌይለር ከተባሉ ጓደኞቹ ጋር ዘዌይለርስ የተባለ ቡድን በመመሥረት ነበር፡፡ ከደጋፊ ዘፋኞቹ አንዷ የነበረችውን ራታ ማርሊን በማግባት አምስት ልጆች አፍርቷል፡፡ ከልጆቹ መካከልም ዚጊ ማርሊ የተዋጣለት የሬጌ ዘፈን ተጫዋች መሆን ችሏል፡፡ ከቦብ ሥራዎቹ ውስጥም “ኖውማን ኖ ክራይ” (አንድም ሴት አታልቅስ) የሚል ነበር፡፡
የቦብ ማርሌን 75ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግም ሻዴም ሚዲያ ኮሙዩኒኬሽን በዕለተ ልደቱ ጥር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በቪላ ቨርዴ ሆቴል ሥራዎቹን የሚዘክሩ መሰናዶዎች ቀርበዋል፡፡
በዝግጅቱም ሲዲኒ ሰለሞን፣ ኢምፔሪያል ማጂስቲክ ባንድ፣ አለንና ሌሎችም በመድረኩ ላይ በመገኘት ቦብ ማርሌን የሚያስታውሱ ሥራዎችን ሲያቀርቡ ታዳሚዎችም አብረው በመዝፈንና በመጨፈር አድናቆታቸውን ሲገልጹ አምሽተዋል፡፡
ቦብ ማርሌ ስለአንድነት፣ ስለሰዎች እኩልነት፣ ስለዓለም ሰላም በማቀንቀን መልካም አስተሳሰብን የሚዘክሩ ጠንካራ ሐሳቦችን በሬጌ የሙዚቃ ሥልት አዋዝቶ ለሕዝቡ በማቅረብ ትልቅ ሥራዎችን ሠርቶ ካለፉ ዘፋኞች መካከል አንዱ መሆኑን የሻዴም ሚዲያ ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ሔኖክ ይርጋ ገልጸዋል፡፡
ዘጋርዲያን እንደዘገበው፣ የቦብ የልደት በዓል በትውልድ አገሩ ጃማይካ ቤተሰቡና አድናቂዎቹ በኪንግስተን ከተማ በሚገኘው ቦብ ማርሌ ሙዚየም በሙዚቃ ኮንሰርት አክብረውታል፡፡ የሬጌ ወንድማማቾች ተብለው የሚታወቁት ኬይ ማኒ፣ ዴሚያን እና ጁሊያን ማርሌ በጋራ አዚመዋል፡፡
ቦብ በአንድ ወቅት ስለሚያቀነቅነው የሙዚቃ ሥልት ተጠይቆ ነበር፡፡ ጥያቄውም የሬጌ ሙዚቃ ሥልት እንዴት ተፈጠረ የሚል ነበር፡፡ ቦብም ጥያቄውን እንዲህ ሲል መልሷል፡፡ ‹‹ሬጌ እኮ በጃማይካውያን ሳይንቲስቶች አማካይነት ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ የከበሮ ምት ዜማ በመጠቀም ተቀናብሮና ጣፍጦ የተፈለሰፈ የንጉሡ ሙዚቃ ነው፡፡››
ቦብ በ1970ዎቹ እና 80ዎቹ ከፍተኛ ዕውቅናን ያገኘ እስካሁን ድረስም ተወዳጅነቱ ዘልቋል፡፡ ዘፈኖቹም ስለጃማይካ ኑሮ የሚተርኩና ስለራስ ተፈሪያን የሚያትቱ፣ ስለፍቅር ከመተረክ ይልቅ ወደ ፖለቲካና ሃይማኖት ያጋደሉ ናቸው፡፡
ቦብ ከመሞቱ በፊት ለልጁ ለዚጊ የተናገረው የመጨረሻ ቃል ‹‹ገንዘብ ሕይወትን አይገዛም›› የሚል ነበር፡፡
እ.ኤ.አ. በ1981 በቆዳ ካንሰር ምክንያት በ36 ዓመቱ በሞት የተለየው ቦብ ማርሌ በጃማይካ ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓትና በራስ ተፈሪያን ትውፊት የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ተፈጽሟል፡፡ ቦብን ለማስታወስ ከተዘፈኑ ዘፈኖች መሀል
‹‹የእምዬን አፈር አቅምሱኝ ካለ
ቃሉ ቢፈጸም እስኪ ምናለ
የሙት ኑዛዜው እንዳይረሳ
አምጪው ሪታ የቦብን ሬሳ
በባንዲራው ፊት ለኢትዮጵያ አገሬ
ቃል ግቢ መጥተሽ ሪታ ማርሌ›› የሚለው የቴዎድሮስ ካሳሁን ዘፈን ተጠቃሽ ነው፡፡
በተለያዩ አገሮች በቦብ አድናቂዎች እየተከበረ የሚገኘው 75ኛ ዓመት የልደት በዓልን ዓመቱን ሙሉ በሙዚቃ፣ በፋሽን፣ በሥነ ጥበብ፣ በፎቶግራፍ፣ በስፖርትና ፊልም ለማክበር የማርሌ ቤተሰብ ማቀዱ ተገልጿል፡፡