Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሕግ በግለሰቦች የሚለዋወጥ አይደለም!

ሕግ በግለሰቦች የሚለዋወጥ አይደለም!

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ                

በየትኛውም አገር ሁኔታዎች ይለያያሉ እንጂ፣ ሕግ አለ፡፡ ሕግ በእንስሳት ቤተሰብ ውስጥ እንኳ አለ። ለምሳሌ ዝንጀሮዎች ሕግ አላቸው፡፡ ገመሬ ዝንጀሮ ሁሉንም በበላይነት ያስተዳድራል፣ ልጆችንም ሳይቀር አርጩሜ ቀፍጦ ይቀጣል። አንበሶችም  በአውራቸው ይመራሉ። ሰው ደግሞ ከእነዚህ አራዊት በመሻሉ በረቀቀ መንገድ ሕግን መሥርቶ በሕግ ይተዳደራል።

ቀደም ሲል አገራችን እንደ ዛሬው በቴክኖሎጂ ሌሎችን ባትቀድምም፣ በሕግና ሥነ ሥርዓት ስትተዳደር በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን አሳልፋለች። በዓለም የረቀቀና ቀለል ያለ ራሱን የቻለ ፊደል ያላት ታላቅ አገር መሆኗን የጀርመን፣ የሆላንድ (ደች) የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲዎች መስክረዋል። ያንን ማገላበጥና ማየት በቂ ይሆናል።

ሕግ ከወጣ በሕግ ካልተሻረ እንደጠና (ፀና) ይቆያል ማለት ነው። በቁጭት የሚሠራ ሁሉ ጊዜያዊ እንጂ ዘለቄታ የለውምና ተረጋግቶ፣ በሰከነ ልቦና ተወያይቶ መልካሙን መያዝ እንጂ፣ በቁጭትና አለሁ አለሁ ባይነት የአንድን  አገር ታሪክ መደምሰስ ለባዕድ ታሪክን ሸጦ ከማለፍ የዘለለ ጊዜያዊ ‘ቀርሺ’ ይሰጥ ወይም ያመጣ እንደሆን እንጂ፣ ከመናቅና አገርን ሸጦ የታሪክ አተላ ከመሆን አይዘልም።

ኢትዮጵያዊነት እንደ ሸቀጥ ዕቃ ሲፈለግ የሚገዛ፣ ሲፈለግ የሚሸጥ አይደለም። ሦስስት ሺሕ ዘመናትን እንተውና ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ብቻ እንኳ አንስተን ታሪካችንን ብንመለከት፣ ነፃነታችንን ጠብቀውና አስጠብቀው ያለፉትን ወገኖቻችንን ማስታወስ ተገቢ በሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን ምን ያደርጋል ሁሉ ቃልቻ ማን ይሸከም ስልቻ ሆነና ሁሉም መሪ ለመሆን ቃጣው። አዎን የሰው ልጅ ሁሉ እኩል ነውና የመምራት ችሎታ ካለው ይምራ፣ ለማንም የተወሰነ የአመራር ክልል የለምና ግን ዜጋ መሆን በየትም አገር ያለ ግዴታ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

በሌላ በኩል ደግሞ ዋሽቶና ወሻክቶ የሌላ አገር ዜጋ ከሆኑ በኋላ ለሹመት ሲባል በሩጫ ዜግነቴን ኢትዮጵያዊ አድርጌያለሁና አሁን አገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ተዋናይ ለመሆን እችላለሁ ማለት፣ ከቶውንም ሕጋዊና ተቀባይነት ሊኖረው የማይችል ጉዳይ ነው። አዎን በሕጉ ሁሉንም አሟልቶ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ባሉበት አገር ግፍ ደርሶባቸው ተውግዘው፣ ፍትሕ አጥተው፣ በመጨቆን ግፍ ደርሶባቸው በሕይወታቸው ላይ አሥጊ ሁኔታ ተፈጥሮባቸው ብሔራዊ መብት ተነፍገው ከሆነ፣ ያ በማስረጃ ተረጋግጦ ከቀረበ ባኋላ ወደሚመለከተው ፍርድ ቤትም ሆነ ሌላ አካል ዘንድ ቀርቦ ውሳኔ ሲሰጥበት ጊዜውን ጠብቆ የዜግነት ሳይሆን የመኖሪያ ፈቃድ ይሰጣል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ቆይቶ ጠባያቸውን አገናዝቦ የዜግነት መብት ይሰጣል እንጂ፣ እንዲያው ያመቻል ተብሎ ተሰርቆም ሆነ የአገርን ሚዛን ለማቃወስ ከየአገሩ በተጠራቀመና በምን ዓይነት መነገድ እንኳ መግባቱ ባልታወቀ በኩንታል በተጋዘ ሕገወጥ ዶላር የኢትዮጵያ ዜግነት መጣል የለበትም።

ለግማሹ የውጭ ዜጋ ከሆንክ የባንክና የኢንሹራንስ አክሲዮንና የመሳሰሉትን መግዛት፣ በማንኛውም የፖለቲካ መስክ መሠለፍም ሆነ መሳተፍ አትችልም ይባላል። በሌላ በኩል በይፋ በሬዲይና በጋዜጣ ወንጀል አሠርተሃል ሲባል በሕግ መጠየቅ ሲገባው፣  መንግሥት አጃቢና የፀጥታ ኃይል በማሠለፍ ሲንከባከብ መመልከቱ እጅግ ይገርማል:: ጃዋር መሐመድን ልዩ የሚያደርገው ጉዳይ ምንድነው? ለአገራቸው ጠዋትና ማታ ወገን ሳይለዩ፣ አካባቢ ሳይመርጡ ታች ላይ የሚሉ ኢትዮጵያዊያን ተረስተው፣ ይህንን የዱብ ዕዳ ዓይነት ሰው ምነው ዓላማና ግቡን የሚገነዘብ ወገን ጠፋ?

ወገኖቼ በኢትዮጵያ ላይ በ1982 ዓ.ም የደረሰውን የምፅዋን አወዳደቅ፣ የተዘረፈውን የባህር ላይ ንብረት፣ የፈሰሰውን የኢትዮጵያዊያንን ደም ስናስታውስ ማን ነበር ተጠቃሚው? እርስ በርሳችን እየተራኮትን የጠላቶቻችንን ጎተራ መሙላት ምነው ቢበቃን? ወገኖቼ በመለፍለፍ ብቻ አገር አይቀናም፡፡ ግርግሩን ለመጠቀም በሚሊዮኖች ዶላር የሚነዙት ገንዘብ አገር ለማፍረስ መሆኑንም አንዘንጋ። የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያወጣው ሕግ ለሁሉም 100 ሚሊዮን ሕዝብ አንድ ዓይነት መሆን አለበት። የትኛውም ክልል ዜግነትን ሊሰጥም ሆነ ሊከለክል ሕግ አይፈቅድለትም፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ የዜግነት ጥያቄ ውስጥ ክልሎች ሊገቡ አችሉምና ይህ ቢታወቅ መልካም ነው። የዚህ መብት ያለው የፌዴራሉ የሚመለከተው ክፍል መሆን ይገበዋል። ይህ ነው ብዬ ላመለክት ስለማልችል የሚመለከተው ይወስናል ብዬ አምናለሁ።

በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ በፈረንሣይና በመሳሰሉት አገሮች መጀመሪያ የኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ወደ ኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ያቀርብና ፍርድ ቤቱ በሕጉ መሠረት ይወስናል። እዚህ ግን የፖለቲካ ጓዶች ሲንጫጩ ሳይ እየተገረምኩ ነው። አንዱ የእንጀራ ልጅ፣ ሌላው የበኩር ልጅ  እየሆነ እያየሁ ነው። ይህ በሚገባ መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነውና ከመሠረቱ ይታይ እላለሁ። ይህንን አስመልክቼ ለራሴ መጠቀሚያ መንገድ መፈለጌ እንዳልሆነ ሁሉም እንዲገነዘብልኝ እሻለሁ። እግዜብሔር ይመስገን ያለሁበት አገር ከተወለድኩበትና እትብቴ ከተቀበረበት በተሻለ መንገድ ቢይዘኝም፣ የአገር ፍቅር ስለያዘኝ ብቻ ነው በጉዳዩ ገብቼ ሐሳቤን ላካፍል የተነሳሳሁት። ጥቅም ፈላጊም አገር ሻጭም እንዳልሆንኩ እወቁልኝ። ሁሌም ዓባይ ሞኝ ነው፣ ከራሱ ይልቅ ለባዕድ በማድላቱ፡፡ ይህ ሁሉ ብር በዓባይ ተሽቆልቁሎ ይሆን ይሚገባው ብዬ ራሴን ከጠየቅሁኝ በኋላ፣ ታዲያ ከየት የመጣ ይይመስልሃል ብዬ ለራሴው መለስኩ።                                                                                                 

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በቅርቡ ለአንባብያን የቀረበው ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› የተባለው መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡             

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ