Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በዛን ወይስ በዛብን?

እነሆ መንገድ ከስታዲየም ወደ ሳሪስ ልንጓዝ ነው። ሁሉም ነገር ከጥር ድንገቴ ደመና ሥር በግርዶሽ ተንሰራፍቷል። የሒደትን ፍጥነት ሕዝበ አዳም እየታዘበ ሽምጥ በሚጋልብ ዕድሜው የተከዘ ይመስላል። ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ እያተማታበት ወዳለፈ ታሪኩ ዳና ዞር ይላል። ጎዳናው በስስት በሚለኩ ዕርምጃዎች፣ በአጭር በተቀጩ ህልሞች፣ ባልተኖሩ ልጅነቶች የተቀለመ ግራጫ ነፀብራቅ ይተፋል። በጊዜ ጉልበት እንደ ቀልድ የምታልፍ ዕድሜ በቅፅበት ምዕራፍ ተጠርዛ ታሪክ ተብላ ትወራለች፣ ትዘከራለች። ከዓመት እስከ ዓመት ሽምጥ ሲጋልብ፣ ትውልድ በትውልድ ድምፁን አጥፍቶ በለሆሳስ ሲተካ መንገድ ብዙ ያሳየናል። ከጥግ እስከ ጥግ ተዝረክርኮ ፈር በሳተው የእኛ የሰው ልጆች ኑሮ ሸፍጥና ሀቅ፣ ሐዘንና ደስታ ፍሬያቸውና ገለባቸው እኩል ክምር ይወጣዋል። ይህን ለመገንዘብ መማር አይጠይቅም፣ መፈላሰፍም ሆነ ሐይቅ ዳርቻ መመነን አያሻም። እንዲሁ መኖር በቂ ነው። ለዚህ ደግሞ የሥጋውን ለከት አጣሽ ምኞትና አምሮት ማስታገስ ያቃተው ሥጋ ለባሽ መሀል መዘዋወር ብቻ በቂ ነው። ለአንዳንዱ ደግሞ ከበቂ በላይ ነው!

ከዚህ ሰው ከመሆን ቋንቋ የተረፈውን ሚስጥር ጎዳናው ይገልጸዋል። ዛሬም ያን ሚስጥር ልንሰማ፣ የሕይወትን ትግል እንቆቅልሽ ልንፈለቅቅ በጉዳዮቻችን አሳበን ታክሲ ተሳፍረናል። የወያላው ጩኸት ጆሮ ይበሳል። ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመች እመጫት የታቀፈቻት ሕፃን በእሪታዋ ያዙኝ ልቀቁኝ ትላለች። አጠገቧ የተቀመጠ ጎልማሳ፣ “ኧረ እባክሽ አንድ በያት . . .” እያለ የጋጋሪ ቆስቋሽ ሊሆን ሲሞክር እሱ ብሶ ቁጭ ይላል። ከእነሱ ቀጥሎ ያለው መቀመጫ ላይ ሁለት ፍቅረኛሞች እየተሻሹ በሹክሹክታ ያወራሉ። “ስማ ወያላ! የፔንሲዮን አገልግሎት መስጠት ጀመራችሁ እንዴ?” ይላል ለአፉ ሳይቀፈው አንደኛው ፈጣጣ። ከእነሱ ጀርባ ጥንድ አዛውንቶች በዝምታና በእርጋታ ተቀምጠው ታድመዋል። ቀሪዎቻችን መጨረሻ ወንበር ላይ ተረፍርፈናል። ዳሩ እንኳን በነጠላነት እንዲህ በኅብረት ውስጥም ሰሚ ያገኘን አንመስልም!

ወያላው የበቃው አይመስልም። “እንሂድ እንጂ ሾፌር?” እመጫቷ እንደ ቸኮለች ያስታውቃል። የልጇ ለቅሶ የኑሮዋ እሪታ አካል መሆኑን ስለምታምን፣ ቤቷ ገብታ እንደሚሆን የምታደርገው ጉዳይ ሳይኖራት አልቀረም። “እንሂድ እባክህ!” መልስ ብታጣ ወደ ወያላው እየዞረች በመለማመጥ ጠየቀች። “ቆይ! ገና ምኑን አይተሽ? 18 ሰው ካልሆነ ንቅንቅ የለም። ይኼን ሁሉ ወጪ ያወጣነው፣ ይኼን በትራንስፖርትና በህልም ላይ በተንጠለጠለ የኑሮ ዕቅድ መከራውን የሚያይ ሕዝብ ለማገልገል መሰለኝ?” ብሎ ተጠርቦ ለመቀመጫነት እንዲያመች የተለሰለሰ ጣውላ ጠቆማት። አብዛኛዎቹ ተሳፋሪዎች በዚህ መስመር አዘውትረው ተመላላሽ ስለሆኑ ወያላውን ሰቅዘው አልያዙትም። ነገራችን ሁሉ አጥብቆ ጠያቂነት ጠፍቶበት እኮ ነው የምንራኮተው!

መጨረሻ ወንበር ጥጉን ይዞ ይኼን ጉድ የሚያይ የሚሰማ አንድ ዳያስፖራ ብቻ፣ “እግዚኦ አሁን ይኼ አገር መንግሥት አለው ይባላል? ጉድ እኮ ነው! እናንተስ እንዴት ዝም ትላላችሁ? ወይ ወኔ ማጣት?” ሲል ጠየቀ። ተሳፋሪዎች ንግግሩን ያቆማል ሲሉ ብዙ ጠበቁት። ዝምታችን ጭራሽ አባሰበት። ዝምታችን ያላባባሰው ችግር ለመሆኑ ተቆጥሮ ያልቃል? ወዲያው ጋቢና ከተሰየሙ ወጣቶች አንዱ ዞሮ፣ “እኔ እኮ እናንተ ሰዎች እኛ ችለነው የምኖረው እያለን እናንተ ባልተቃጠለ ‘ቪዛ’፣ ‘በአሳይለም’ በተለወጠ ዜግነት፣ ለወር ‘ቫኬሽን’ መጥታችሁ ስትንጫጩት አታፍሩም? ወኔ ይላል ደግሞ! ወኔ ያለውማ የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ ሊያርስ ጠቅሎ የተወለደበት እትብቱ የተቀበረበት አገር የሚኖር ነው እንጂ፣ ስለአያት ቅድም አያቶቹ ታሪክ የአብራኩን ክፋይ በባዕድ ቋንቋ የሚሸመድድ ስደተኛ ዘንድ አይደለም። ወኔ ተባለ?” ብሎ ደነፋ። አጠገቡ ያለው ተቀበለውና ደግሞ፣ “አይ መሬት ላይ ያለ ሰው ብለህ እለፈው ወንድሜ። ‘ብለነው ብለነው የተውነውን ነገር ዛሬ አዲስ አድርጎት ያቅራራብን ጀመር’ ብለህ ከነገርከው በቂ ነው፤” አለው። ዳያስፖራው መልስ ለመስጠት አልደፈረም። ታክሲያችን ውስጥ ዝምታ ነገሠ። በየሄድንበት ነገር ሲበዛ ‘ዝምታ ነው መልሴ’ ተለመደ አይደል!

 ወያላው በበኩሉ የተፈጠረው ነገር ደስ ስላላለው ርዕስ ሊያስቀይርና ዝምታውን ሊያስተነፍስ ጨዋታ ይቀይራል። “እንዲህ በየመንገዱ ይተሻሹ ይተሻሹና ምኑንም ሳይዙ ሦስተኛ ወገን አምጥተው ቁጭ ይላሉ። እንዲህ ያሉት ናቸው እኮ የኑሮን ዙር እያከረሩ ያስቸገሩን፤” ይላል በንዴት በሩን እየዘጋ። “ተው አንተ ልጅ ተረጋጋ! ያቺ ልጅ ሰሞኑን እንዳትደርስብኝ አለችህና ጥንዶችን ስታይ በቃ የምትይዝ የምትጨብጠውን ታጣለህ። ምን ይሻልሀል እንዲያው?” ሾፌሩ በውስጥ አዋቂ ስልት ኩም ያደርገዋል። መጨረሻ ከተቀመጥነበው ከአራታችን መሀል አንዱ ወደ ጓደኛው ዞሮ፣ “በቃ ከሠራን አይቀር መሥራት ያለብን፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጁ ተብለንም ቢሆን አልጋ የማከራየት ሥራ ነው። ያዋጣል ስልህ? ሰው ለምን ይመስልሃል በየካፌው፣ አውቶብስ ውስጥ፣ መኪና ውስጥ ከንፈር መነቃቀስ የጀመረው? አይ የቤት ችግር!” ያወራል በወኔ፡፡ ለወሬ ደግሞ መቼ ወኔ ጠፍቶ!

መሀል መቀመጫ ላይ ተሰይመው በስሜት ዓለምን ረስተው ከወግ ሠልፍ ተነጥለው፣ በራሳቸው ዓለም የተመሙት ወጣቶች የሚባሉትን ከመጤፍ የሚቆጥሩት አይመስሉም። “አልጋ ለማከራየት ደግሞ ምን መደራጀት ያስፈልጋል?” ይላል ጓደኛው፡፡ “ወንድሜ እኛ ሥራ ከሠራን ስለሱ ምን አገባን?” ይመልሳል አዲስ የሥራ ሐሳብ ፈልቆልኛል ባዩ። “አይ ዘመን አሁን እንዲህ ሰው በስሜት በሚነዳበት ጊዜ እንዴት ተደርጎ ነው፣ እንኳን የካፒታል ምጣኔ የቤተሰብ ምጣኔ ተግባራዊ የሚሆነው?” ብሎ የሚጠይቀን ደግሞ ጎልማሳው ነው። ይኼን ሁሉ አቧራ ያስነሱት ወጣቶች አሁንም ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ከንፈር ለከንፈር እንደገጠሙ ናቸው። አይ ይኼ የፈረደበት ዘመን!

ጉዟችን ቀጥሏል። ሦስተኛው መቀመጫ ላይ በዝምታ ተሸብበው ተቀምጠው የቆዩት ባልና ሚስት አዛውንቶች፣ የገዛ ዘመናቸውን እያንቆለጳጰሱ የልጆቻቸውን ጊዜ ማጣጣሉን ተያይዘውታል። “ታያለሽ የሚሠራውን? እኛ መቼ ነገር ሁሉ ፈሩን ስቶ እዚህ የሚደርስ መሰለን?” ሲሉ ባልየው ሚስትየው ደግሞ ከንፈር እየመጠጡ፣ “ይተውኝ እስኪ!” ይላሉ። “እዚህ ለመድረስ ነበር? መጀመሪያ ነገሩን ሲጀምሩ አብዮት ብለው እኚያን የመሰሉ ንጉሥ እንደ ዕቃ አሽቀንጥረው ጣሉ። ይታይሽ እንግዲህ ያዩትን ቢያዩ ነው የቆጠሩት ፊደል ታላቅ ህልም ለአገራቸው አስረግዞ እንቅልፍ ቢነሳቸው ነው ብለን ታገስን። ያ ሁሉ ፍጅት ያ ሁሉ ደም ፈሰሰ። እርስ በእርሳችን በአሮጌ ጠመንጃ ስንጠዛጠዝ ያሳለፍነውን ክፉ ታሪክ በዘመናዊ የጦር መሣሪያ ተገዳድለን አደስነው። ይታይሽ! ይኼው አሁን ደግሞ በሥልጣኔ ስም፣ በቴክኖሎጂ ስም፣ በአወኩኝ ነቃሁ ባይ ሰበብ ልቅነት በየአቅጣጫው ተስፋፍቶ ሥርዓተ አልበኝነት አሳራችንን ያበላናል። በዚህ ስንመጣ (ወያላውን እየጠቆሙ) ሕግ አልዳኛቸው ባሉ ጋጠወጦች እንገለመጣለን። በየቀኑ ሥጋቸውን ሽጠው ለማደር የሚወስኑት፣ ከአገር ተሰደው የአርባ ቀን ዕድላቸውን ለመሞከር የሚቆርጡት ሴት ልጆቻችን ቁጥር ሰማይ ደርሷል። ለማኙ ጨዋ ስለሆንኩ እንጂ የምለምነው ከባሰብኝ አሳይሃለሁ እያለ አስፈራርቶ አምጡ ይለናል። ውጥንቅጣችን እኮ ነው የወጣው! ይኼው እንዲህ ደግሞ (እነዚያን የፈረደባቸውን የተቆላለፉ ወጣቶች ይጠቁማሉ) የሌቱ ጉድ ሲገርመን በጠራራ ፀሐይ መንገድ የማያስኬዱ የፈላባቸው ሕፃናት መፈጠራችንን ያስጠሉናል፤” ብለው አፍታ ትንፋሽ ሰብስበው፣ “ቆይ ግን ምኑን ነው አገር እየተገነባ ያለው?” ሲሉ ጥያቄያቸውን ለመላው የታክሲዋ ታዳሚ አቀበሉ። የሰማውን ውጦ ዝም ከማለት በቀር አስተያየት እንኳ የሚጨምር ጠፋ። ዘንድሮ በሽበሽ ሆኖ የተገኘ ብቸኛ ነገር ዝምታ ሳይሆን አይቀርም ያሰኛል የታክሲው ፀጥታ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። የዛሬው አጭሩ መስመራችን ጉዞ በጥያቄ እየተሟሸ በዝምታ የሚቋጭ ሆኖ እዚህ ደረስን። ወያላችን ከማውረድና ከመጫን ድካሙ ጊዜ ሲያገኝ ሒሳብ እየሰበሰበ ከጨረሰ ቆይቷል። ጎተራ ስንደርስ ደግሞ ሊገላገለን ከመቸኮሉ የተነሳ ገና ታክሲያችን ቦታ ከመያዙ “መጨረሻ” ብሎ በሩን ከፈተው። ተሳፋሪዎች በወያላው ያልተገራ ፀባይ እየተበሳጩ ከታክሲው ወርደው ቶሎ ለመሸሽ ሲጣደፉ አንድ ፈጣን ታዳጊ ብቅ ብሎ፣ ‹‹መጣንባቸው ሳይታጠቁ እንደ ዝንጀሮ ፀሐይ ሲሞቁ!›› ብሎ ዜማ የሌለው ጩኸት ለቀቀብን። አብዛኞዎቹ ተሳፋሪዎች ታዳጊው ከእናቱ እቅፍ በቅርቡ የተላቀቀ መሆኑን ገምተው ሳቃቸው አመለጣቸው። “ያንተ ተሻለን!” አለ ጎልማሳው ታዳጊውን እያየ። ወዲያው ታዳጊው፣ “ሰውና ዝንጀሮ ይመሳሰላሉ የሚባለው እውነት ነው?” ብሎ ሲጠይቅ ተሳፋሪዎች እየተጠቃቀሱ ከሆታ ሳቃቸው ጋብ ሊሉ አልቻሉም።

“እሱ ምን ያድርግ ብላችሁ ነው? ያየውን አይቶ የያዘውን ይዞ ነው። በዚህ ዘመን ታናሽ ከታላቆቹ ቀድቶ የሚያድገው አቋራጭ መንገድ ነው። በእኛ ጊዜ መጠየቅ የሚያስቀጣ ነውረኛ ተግባር ነበር። ከታላላቆቻችን ዓይተን የተማርነው እንዲያ ነው። እንዳሁኑ በተገኘው አጋጣሚ ጥያቄ የማቅረብ ልማድ አልነበረንም፤” አሉ አዛውንቱ መሀላችን ገብተው። ታዳጊው አቋርጧቸው፣ ‹‹መጠየቅና መመራመር ነውር ሆኖ እኮ ነው በድፍረት እየተኖረ በድፍረት ድፍት የሚባለው . . .›› ብሎ የመጣበትን ዋነኛና በኩር ዓላማ አፈረጠው። ሁሉም ሐሳብ ገብቶት ነገር እያወጣ እያወረደ ጉዞውን ቀጠለ። መጨረሻ የተቀመጥነው ተሳፋሪዎች አዛውንቶቹን ጥንዶች አስቀድመን ስንወርድ፣ “ጥያቄ የቃሉ ትርጉም ማሰስ፣ መፈለግ፣ ለማወቅ መጣጣር፣ መመራመር . . . ማለት ነበር። አሁን ደግሞ የተያዘው ፋሽን በጥያቄ ስም የበራውን ማጨለም የነጋውን ማስመሸት ሆኗል። ክፉ ክፉውን ስንቀባበል አንደኞች ነን። ደግ ደጉንና የሚያንፀውን ግን ማጣመም የሚደርስብን የለም፤” ሲባባሉ እንሰማ ነበር። ዞሮ ዞሮ ነገሩን በተለያየ አቅጣጫ ስናየው መውጣትና መውረድ፣ ላይና ታች፣ ሽቅብና ቁልቁል እያልን ልናስበው እንችላለን፡፡ ለነገሩ አኗኗራችንስ ሽቅብና ቁልቁል አይደል? አንደኛው አዛውንት ግን፣ ‹‹አጥብቆ መጠየቅ፣ ያወቁትን ደግሞ ለዕውቀት ማስፋፊያ ማዋል፣ ታናናሾችን ማስተማሪያ ማድረግ የተባረከ ተግባር ነው፡፡ ጥያቄን ለጥፋት ዓላማ ማዘጋጀትና እርስ በርስ መጠፋፋት ግን የረከሰ ተግባር ነው . . .›› እያሉ ሲያዘግሙ ከሰው በታች መኖር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የተገለጸልን ብዙ ሳንሆን አንቀርም መሰለኝ፡፡ አሁንስ በዛን ወይስ በዛብን? መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት