Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክ​​​​​​​ሕገ መንግሥቱና የፖለቲካ ፓርቲዎች

​​​​​​​ሕገ መንግሥቱና የፖለቲካ ፓርቲዎች

ቀን:

በወልዱ መርኔ

በአገራችን የተጻፈ ሕገ መንግሥት ከወጣ ከ1923 ዓ.ም. ጀምሮ አንድ ክፍለ ዘመን የሚጠጋ የሕገ መንግሥት ዕድገት ታሪክ ቢኖረንም፣ የፓርቲ ፖለቲካን በተመለከተ ግን ያለን ታሪክ አጭር ዕድሜ ያለው ነው:: በንጉሡ የአገዛዝ ዘመን የነበረው ሥርዓተ መንግሥት ፍፁማዊ የዘውድ አገዛዝ ስለነበር በመጀመርያውም ሆነ በተሻሻለው ሕገ መንግሥት ዜጎች ለፖለቲካ ዓላማ የመደራጀት መብት እንዲኖራቸው የሚፈቅዱ ድንጋጌዎች ስላልነበሩ የፓርቲ ፖለቲካ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ሆኖም ከተማሪዎች እንቅስቃሴ መጠናከር ጋር ተያይዞ በ1950ዎቹ መጨረሻና በ1966ቱ አብዮት ዋዜማ የተማሪው እንቅስቃሴ የወለዳቸው የተለያዩ አገራዊና በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች መመሥረታቸው ይታወቃል::

የ1966ቱን አብዮት ተከትሎ የመንግሥትን ሥልጣን የተቆናጠጠው ወታደራዊ ደርግ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰበሰብና የመደራጀት መብቶችን በመገደቡ የተወሰኑ የፖለቲካ ድርጅቶች የትጥቅ ትግልን የመረጡ ሲሆን፣ ኢሕአፓን የመሰሉት በህቡዕ ለመንቀሳቀስ ሲወስኑ መኢሶንና ሌሎች ፓርቲዎች የደርግ ዕርምጃ ሰለባ እስኪሆኑ ድረስ አብረው ለመሥራት የወሰኑ ነበሩ፡፡ ከዚህ በኋላ በደርግ መንግሥት በ1980ዓ.ም. ሥራ ላይ እንዲውል የተደረገው የኢሕዴሪ ሕገ መንግሥት በሶሺያሊስት መርህ የተቃኘና በቀጥታ ከሶቪየት ሕገ መንግሥት የተቀዳ ስለነበር፣ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ቦታ የማይሰጥ ከመሆኑም በላይ በብቸኛነት አገርን የመምራት መብት የተሰጠው ፓርቲ ኢሰፓ ብቻ የነበረ በመሆኑ የፓርቲዎች ሚናና ፉክክር ጨርሶ የሚታሰብ አልነበረም::

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በ1983ዓ.ም. የመንግሥትና የሥርዓት ለውጥ በመደረጉ የወቅቱ የሽግግር ቻርተር የመደራጀት መብትን ማክበሩን ተከትሎ፣ የተለያዩ ነባርና አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ መድረኩ ወጥተው መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ ከዚያም በ1987ዓ.ም የፀደቀው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ለዜጎች የመደራጀት መብት ዕውቅና በመስጠቱና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን በማስቀመጡ፣ የተለያዩ ፓርቲዎች ወደ ፖለቲካው መድረክ ለመምጣት ችለዋል፡፡ ሆኖም በርካታ ፓርቲዎች እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ሕገ መንግሥታዊና ሕጋዊ ማዕቀፍ የመኖሩን ያክል ገዥው ፓርቲ መድረኩን አጥብቦ ሥልጣንን በብቸኛነት ለረጅም ጊዜ ተቆጣጥሮ ለመቆየት ከነበረው ከጤናማ ውድድር የወጣ ፍላጎት የተነሳ፣ በሽግግሩ ወቅትና ከ1997ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ታይቶ የነበረው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትና የፓርላሜንታዊ ዴሞክራሲ በጎ ጅምር ቀስ በቀስ እየተዳከመ ሊሄድ ችሏል::

ይሁን እንጂ በአገሪቱ ሕዝቦች በተፈጠረው የለውጥ ፍላጎትና ግፊት እንዲሁም በኢሕአዴግ ውስጥ በተነሳው የለውጥ እንቅስቃሴ መነሻነት ወደ ሥልጣን የመጣው አዲስ አመራር ከወሰዳቸው የፖለቲካ ማሻሻያ ዕርምጃዎች አንዱ፣ በአገር ውስጥ ያሉና ከውጭ የገቡ ፓርቲዎች በአንፃራዊ መልኩ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ማድረጉ ነው:: ይህን ተከትሎም በርካታ አገር አቀፍና ክልላዊ ፓርቲዎች በፖለቲካ መድረኩ ላይ እየታዩ ነው::

ይህ የፖለቲካ ምኅዳሩን የማስፋት ጅማሮ ለእኔ ሁለት ተቃራኒ ሁኔታዎችን ማለትም ተስፋና ሥጋት በአዕምሮዬ አጭሮብኛል፡፡ በአንድ በኩል የዴሞክራሲ ሥርዓት እንገነባለን ካልን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ማስፈን የግድ በመሆኑ፣ አሁን እየታየ ያለው አንፃራዊ የፓርቲዎች ነፃ እንቅስቃሴ ተስፋን የሚያጭር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእኛ አገር ፓርቲዎች ከተለመደው የርዕዮተ ዓለምና የፖሊሲ ልዩነት ያለፈ በአገረ መንግሥትና አገራዊ ግንባታ ታሪክ ያላቸው ዕይታ የተራራቀ መሆንና የጋራ አገራዊ ራዕይ ማጣት የጽንፈኛ ብሔረተኛነት አስተሳሰብ መጠናከር መድረሻው የት ነው? በአገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ምን ተፅዕኖ ይኖረዋል? የሚለውን ሳስብ ሥጋት ይጫርብኛል፡፡

ከዚህ ተነስቼ የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች አጠቃላይ አቋም ምን ይመስላል? ከሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ግንባታ አኳያ፣ ሚናቸው ምን ይሆናል? የሚሉ ሐሳቦችን አንድ የአገሩ ፖለቲካና ሕልውና እንደሚያሳስበው ዜጋ ለማንሳት ወደድሁ፡፡ በእርግጥ የፓርቲዎቹን መርህና የሚመሩበትን ርዕዮተ ዓለም በዝርዝር ማየት ዓላማዬም ፍላጎቴም አይደለም፡፡ ይህን ዓይቶ በሚዛን ማስቀመጥና መምረጥ የሕዝቡ ይሆናል፡፡

1 ሕገ መንግሥቱና ፓርቲዎች

የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሥፍራና ሚና ከሕገ መንግሥቱ ጋር በማያያዝ የማነሳው የፓርቲዎች አመሠራረት እንቅስቃሴ የፖለቲካ ሥልጣን በውድድር የመያዝ ዓላማና በመንግሥት አስተዳደር በገዥነትም ሆነ በተቃዋሚነት የመሳተፍ ሒደት ከሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውጪ የማይታሰብ ስለሆነ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደራጁት ፖለቲካዊ ዓላማን ለማሳካት በመሆኑ፣ በመንግሥት አስተዳደርና በአገረ መንግሥት ግንባታ የአገራችንን ሉዓላዊነትና አንድነት አስጠብቆ በማቆየት የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት በማፋጠን ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ መነሻ እንዳለ ሆኖ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ዜጎች ለፈለጉት ዓላማ የመደራጀት መብታቸውን የሚያከብሩ ድንጋጌዎችን የያዘ በመሆኑ፣ በተለይ በአንቀጽ 31 ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት እንዳለው ደንግጓል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግም ዜጎች ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ለማሳካት የፖለቲካ ማኅበራትን ማለትም ድርጅቶችን ለማቋቋም፣ የሚያስችል ሁኔታ ስለተፈጠረላቸው በአገራችን በርካታ አገር ዓቀፍና ክልላዊ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

እንደሚታወቀው በዘመናዊ የዴሞክራሲ፣ የመንግሥት አስተዳደር ሥልጣን የሚገኘው በዘር ሐረግ ትውልድ ወይም በኃይል ሳይሆን፣ በምርጫ በመሆኑና ሕገ መንግሥቱም ያስቀመጠው በምርጫ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሥልጣን አያያዝና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አመራር መርህ ስለሆነ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲና ፕሮግራማቸውን ለሕዝብ በማስተዋወቅ አሸናፊ ሆነው ከወጡ መንግሥታዊ ሥልጣን በመያዝ አገርን የማስተዳደር ኃላፊነት ስላለባቸው በአገረ መንግሥትና ጠንካራ አገር ግንባታ የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ ፓርቲዎች የፖለቲካ ሥልጣንን በመያዝ ለአገርና ለሕዝብ ሁለንተናዊ ልማት ለሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት ጉልህ ሚና እንዳላቸው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ያሳያሉ::

ከፖለቲካ ሥልጣን አያያዝ ጋር በተገናኘ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 56 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል እንደሚያደራጅ ወይም እንደሚያደራጁ የተደነገገ ሲሆን፣ በአንቀጽ 73/2/ም ተመሳሳይ ድንጋጌ ተቀምጦ እናገኛለን:: ከዚህ አንፃር ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅም የሚተገበር ፖሊሲና ስትራቴጂ ያለው ፓርቲ ወደ ሥልጣን ቢመጣ፣ የሕዝብን ሁለንተናዊ ዕድገት እንደሚያፋጥን የተረጋጋ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲቀጥል እንደሚያደርግ የታወቀ ነው::

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በአገራችን የሚታየውን ጤናማ ያልሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ፓርቲዎች በአብዛኛው እያንፀባረቁ ያሉትን የብሔርተኝነትና የክልላዊነት አስተሳሰብ በየቦታው ሥፍራ እያገኘ የመጣ የሚመስለውን ጽንፈኛነትና ብሔርተኛነት ስንመለከት፣ በእውነት እነዚህ ፖርቲዎች የመንግሥት ሥልጣን ቢይዙ በዴሞክራሲ መርህ በሕግ የበላይነት በጋራ አገራዊ ራዕይና መግባባት ተመርተው የተረጋጋ መንግሥታዊ ሥርዓት በማስቀጠል ልማት በማምጣት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ግንባታ መምራት ይችላሉ ወይ? ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን፡፡ የፓርቲዎችን በተራራቀ ጽንፍ የቆመ የአገር ግንባታ ዕይታና የጋራ አገራዊ ራዕይ ያለመኖር በገለልተኛነት ለሚከታተል ማንኛውም ዜጋ፣ ፓርቲዎቹ  ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተረጋጋ መንግሥታዊ አስተዳደር መገንባት የሚያስችል ቁመናና አማራጭ አላቸው ወይ? የጋራ አገራዊ ራዕይ ይዘው የአገርን ሕልውናና የሕዝብን አንድነት አስጠብቀው ማስቀጠል ይችላሉ ወይ? የሚል ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም::

በእኔ የግል ዕይታ በአሁኑ ወቅት በአገራችን በሚያራምዱት አስተሳሰብና የድርጅት አቋም ሲታዩ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጎራ እንዳለ አስባለሁ፡፡ በመጀመርያው ረድፍ ያሉት ራሳቸውን በብሔር ያደራጁና የሚያራምዱትም የብሔር ፖለቲካ ሆኖ ትኩረታቸውም በአብዛኛው እንወክለዋለን በሚሉት ብሔር ላይ የሆኑ ናቸው፡፡ በሁለተኛው ረድፍ የማያቸው በአገር ዓቀፍ ደረጃ የተደራጁና አሁን ባለው ኅብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ላይ ጥያቄ ያላቸውና እንደ ሥጋት የሚያዩት ራሳቸውን የአንድነት ኃይሎች አድርገው የሚቆጥሩ ሲሆኑ፣ በሦስተኛ ረድፍ የማየው አገራዊ አንድነትን ከብዝኃነት ጋር አጣጥሞ ኅብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ እንዲጠናከር የሚያደርግ ፕሮግራም አለኝ የሚለውን የብልፅግና ፓርቲ ነው፡፡

በአራተኛ ረድፍ የማያቸው በቁጥር ምናልባት የበዙት ክልላዊም ሆነ አገር ዓቀፍ ፓርቲዎች ሆነው የጎላ ሚና የሌላቸው በአንድ ወቅት በራሺያ በብዛት ተፈጥረው እንደነበሩትና የሩሲያ ሕዝብ የሶፋ ፓርቲዎች ብሎ እንደጠራቸው ዓይነት የሆኑት ናቸው፡፡ (የሶፋ ፓርቲ ማለት አባላቱ በአንድ ሶፋ ላይ ከሚቀመጡ ሰዎች የማይበልጡ ማለት ነው)፡፡

እነዚህ ፓርቲዎች በተለይ ተፅዕኖ ያላቸው በተራራቀ ጽንፍ ላይ የቆሙ በመሆናቸው፣ ያላቸው ልዩነት በሌላው ዓለም እንደሚታየው ከፖሊሲና ፕሮግራም ያለፈና እስካሁን በዘለቀ አገራዊና አገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ አተያይ ላይ መሆኑ፣ የአገራችንን ፖለቲካ አስቸጋሪና ውስብስብ አድርጎታል:: ይህ የፓርቲዎች የተራራቀ የታሪክና አገራዊ ግንባታ ዕይታ ዛሬ የተከሰተ ሳይሆን፣ የቆየ መነሻ እንዳለው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩና ፖለቲከኛው መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) “Contradictory Interpretations of Ethiopian History፡ The need for a new Consensus” በተሰኘው ጽሑፋቸው የኢትዮጵያን አገረ መንግሥት አመሠራረትና ዕድገት የአገሪቱን ታሪክ የተለያዩ የብሔር ልሂቃን ካላቸው ፖለቲካዊ ግብና ፍላጎት በመነሳት በራሳቸው ዕይታ የመተርጎም አካሄድ እንደተከተሉ ይገልጻሉ፡፡ ይህ የልሂቃን ዕይታ አሁን ላሉት የአገሪቱ ችግሮችም ከሚሰጡት መፍትሔና ምላሽ ጋርም የሚገናኝ እንደሆነ ሲገልጹ፣ በእሳቸው አረዳድ ሦስት ዓይነት የብሔር ልሂቃን ዕይታዎች አሉ::

የመጀመርያው ዕይታ የአገር ግንባታ (Nation-Building Perspective) ሲሆን፣ የዚህ ዕይታ አራማጆች የአገራዊ ግንባታ ሒደቱን በመሩት ገዥዎች ተግባራት የተፈጸሙ ኢፍትሐዊ ያልሆኑ አካሄዶች እንዳልነበሩና ቢኖሩም እንኳ የጎሉ እንዳልሆኑ ድርጊታቸውም አገርን እንደገና የማዋሀድ እንጂ፣ ሌላ ዓላማ እንዳልነበረው የሚገልጹ ናቸው፡፡ የሚመሩበትም አስተሳሰብና መርህ አንዲት ኢትዮጵያ የሚል ሆኖ ራሳቸውንም የማትከፋፈል የአንዲት ኢትዮጵያ እውነተኛ ተወካዮች አድርገው የሚያቀርቡ ናቸው::

የሁለተኛው ዕይታ ከኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ መቀንቀን የጀመረው የብሔር ጭቆና ዕይታ (National Oppression Perspective) የሚባለው ነው፡፡ በዚህ ዕይታ ኢትዮጵያ የብሔሮች እስር ቤት ተደርጋ ትታይ የነበረ ሲሆን፣ በቀዳሚነት መፈታት ያለበት የብሔር ጥያቄ እንደሆነ አድርጎ የሚያቀርብ ነው፡፡ ለጥያቄው የሚሰጠው መፍትሔም የብሔሮች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት መከበርና በማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴሬሽን ማዋቀር ነው፡፡ የአሁኑ ሕገ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓት የዚህ ዕይታ ማሳያና ውጤት ነው፡፡ ይህ ዕይታ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት በእነዋለልኝ መኮንን ይቀነቀን እንደነበረው ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በጨቋኝና ተጨቋኝ ብሔር ትርክት መቀጠሉ ይታወቃል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የነበረው ዕይታ የቅኝ ግዛት ወይም የመስፋፋት ዕይታ (The Colonial Perspective) ሲሆን፣ መነሻው የዘመናዊ ኢትዮጵያ መንግሥት ምሥረታ የተካሄደው የወታደራዊ ፊውዳል ቅኝ አገዛዝ መስፋፋትን ተከትሎ ነው የሚል አሰተሳሰብ ነው፡፡ ይህን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ኃይሎች በአሁኑ ወቅት አቋማቸውን ስለመለወጣቸው ግልጽ የሆነ ነገር የለም፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ተቃራኒ ዕይታዎች (Contradictory Perspectives) በየራሳቸው ጎራ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ተቀባይነት ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡

እነዚህ በተቃራኒ ጽንፍ የቆሙ አሰተሳሰቦች ለአሁኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪካዊ መነሻ ይሁኑ እንጂ፣ አሁንም ያለው የፓርቲዎች የታሪክና የሥርዓት ግንባታ ዕይታና ተቃርኖ የፖለቲካ ምስቅልቅል እየፈጠረ ያለ ሲሆን፣ ይህም የወደፊቱ የአገሪቱ ሁኔታ እንዲህ ይሆናል ብሎ ለመናገር እስከማያስችል ድረስ የደረሰ ነው፡፡ እንዲያውም በአሁኑ ወቅት የብሔር ጽንፈኛነት አስተሳሰብ በየክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ እየተቀነቀነ ያለና የዚህ አስተሳሰብ ባለቤት የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ልሂቃን ተደማጭነታቸውን ለማሳደግ በከፍተኛ ሁኔታ ሲንቀሳቀሱ ይታያል፡፡ በአንፃሩ የአንድነት አስተሳሰብና የጋራ አገራዊ ራዕይ እየተሸረሸረ እንዳለ የምንመለከተው ጉዳይ ነው፡፡

የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን እንወክላለን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራቸው ጥግ ቆመው የእኛ ብሔር ጥያቄ አልተመለሰም፣ ብሔራችን በተለያዩ ሁኔታዎች ተጎጂ ነው የሚሉ የብሶትና ስሜት ቀስቃሽ ትርክቶችን በማስተጋባት የሕዝባቸውን ድጋፍ ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ፡፡ እውነቱ ግን ሁሉም ተጎጂ ነኝ ሲል መታየቱ ጎጂው ማን እንደሆነ ግራ ከማጋባቱም በላይ በአገራችን የትኛውም ብሔር ከሌላው የተሻለ ተጠቃሚ የሆነበት ሁኔታ አልነበረም የለምም፡፡ በእርግጥ አንድ ፓርቲ ስለብሔሩ ጥቅም መብት መታገሉ ሕዝቡን ወክሎ ስለመብቱ ድምፁን ማሰማቱ የሚነቀፍ አይደለም፡፡ ሆኖም የአንድ ብሔር መብት የሚከበረው በተናጠል ሳይሆን፣ በተደጋጋፊነት በመሆኑ ከሌሎች ብሔሮችና አገራዊ ጥቅም ጋር አስተሳስሮ ማስኬድ ካልተቻለ ጩኸቱ ሊተገበር የማይችል ፕሮፓጋንዳ ሆኖ ይቀራል፡፡

እንግዲህ ይህን የፖለቲካ ፓርቲዎች በተራራቀ ጽንፍ የቆመና እስካሁን የዘለቀ  አገራዊና የታሪክ ዕይታ ተቃርኖ ስንመለከት፣ ፕሮፌሰር መራራ ያሉት አንድ ሐሳብ እውነት ሆኖ ይታያል፡፡ ይህም ፈጽሞ የማይስማማ የሚመስል አስተሳሰብ ያላቸው የፖለቲካ ልሂቃን በሚያራምዱት ሕዝብን የመቀስቀሻ ስትራቴጂ ተቃርኖ የተነሳ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ዜጎች ሊያሰባስብ የሚችል የጋራ የፖለቲካ ራዕይ እንዳይኖር ምክንያት ሆኗል::

2 የፓርቲዎች አቋምና የሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ዘላቂነት ፈተና

በአገራችን በፖለቲካው መድረክ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች በመርህ ደረጃ ይነስም ይብዛም ጤነኛ አካሄድ እስካላቸው ድረስ ዓላማቸው ፕሮግራምና ፖሊሲዎቻቸውን ለመራጩ ሕዝብ አቅርበው በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ካሸነፉ የመንግሥትን ሥልጣን በመረከብ አገርን ማስተዳደርና የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ ወደ ልማትና ሁለንተናዊ ዕድገት ማምራት ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት አገራችን ስድስተኛውን ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገች ያለችበት ወቅት እንደመሆኑ፣ የግማሽ ክፍለ ዘመን የፓርቲዎች የተራራቀ ሕልምና ዕይታ የጽንፈኛ ብሔርተኛነት ሥፍራ ማግኘት ሲታይ በእርግጥስ ፓርቲዎቹ ጤናማ ውድድር አድርገው ወደ ሥልጣን ቢመጡ የተራራቀ ልዩነታቸውን አቻችለው በጋራ ራዕይና ፕሮግራም ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲንና የአገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት ማስቀጠል ይችላሉ ወይ? የሚለውን ጥያቄ እያንዳንዱ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ዜጋ ሊያነሳው የሚገባ ነው፡፡

የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ወቅታዊ እንቅስቃሴና ከሁለት ጽንፎች የሚሰማው ድምፅ ከጤናማ የዴሞክራሲ ሽግግርና የተረጋጋ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ማሰቀጠል አንፃር ሥጋትን የሚያጭር ነው፡፡ መቼም በወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ላይ ሥጋትን ማንፀባረቅ ጨለምተኛ የሚያሰኝ አይመስለኝም፡፡

በአንድ በኩል ጫፍ የወጣና ሌሎችን የሚያገል የሚመስል የብሔረተኛነት አመለካከትን የሚያራምዱ ክልላዊ ፓርቲዎች በፖለቲካው መድረክ አሸንፎ ለመውጣትና ሕዝብን ከጀርባቸው ለማሠለፍ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አሳሳቢ ነው፡፡ ሁሉም ቆምን የሚሉት እንወክለዋለን በሚሉት ብሔር ዙሪያ ሲሆን፣ ሁኔታውን አደገኛ የሚያደርገው እነዚህ ፓርቲዎች አሁንም ከመግባባትና ከመቀራረብ ይልቅ ያለፉት ዘመናትን የታሪክ ቁስሎችንና የበዳይ ተበዳይ ትርክቶችን ሲያንፀባርቁና ሕዝብን የመቀስቀሻ ስትራቴጂ ሲያደርጉ መታየታቸው ነው፡፡ በእርግጥ ባለፈው የአገረ መንግሥት ግንባታ ታሪካችን የተሠሩ ስህተቶችና መጥፎ አካሄዶች መኖራቸውን መካድ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም እነዚህን ሁኔታዎች ለትምህርት ወስዶና አርሞ በአንድነትና በመከባበር ወደፊት መጓዝ እንጂ፣ ያለፉ ዘመናትን የታሪክ ጠባሳዎች እያጎሉ ተቀባይነት ለማግኘት መጠቀም ለዛሬዋ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ አብሮነት ልማት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አንዳችም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡

በሌላው ጥግም ያለውን አመለካከት ጎጂነት ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡ ይኸውም የአገራችንን የብሔር፣ የቋንቋና የባህል ብዝኃነት አለመቀበል ወይም ይህን ብዝኃነት ለአገራዊ አንድነት እንደ ሥጋት ማየት በራሱ አንድነትንና ብዝኃነትን አጣምሮ መገንባት ላለበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንቅፋት መሆኑ አይቀርም፡፡ ከላይ ካየነው የአገር ግንባታ (Nation Building Perspective) ዕይታ ጋር ተያይዞ አሁንም ወደ ኋላ ሄዶ ብዝኃነትን በመፍራት የሚንፀባረቀው ጭፍን የሆነ የአንዲት ኢትዮጵያ የአንድነት አመለካከት በእኔ ዕይታ በዚህ ዘመን ጠቃሚ ካለመሆኑም በላይ ለብሔራዊ መግባባትም አይበጅም፡፡

ስለብሔር ብሔረሰቦች ራስን የማስተዳደር፣ በቋንቋ የመጠቀምና ባህል የማሳደግ መብት ሲነገር መስማት የማይፈልጉ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም አገርን የሚበታትን አድርገው የሚያዩ ከእነ ብዙ ችግሩም ቢሆን፣ ብዝኃነትን ማስተናገድ መለማመድ በጀመረች በአሁኑዋ ኢትዮጵያ አስተሳሰቡ ብዙ ርቀት የሚያራምድ አይመስለኝም፡፡ በአጠቃላይ ሁለቱንም ጽንፎች በሚያራምዱ የፖለቲካ ኃይሎች ክልላዊ ስሜትን የያዘ ብሔርተኛነትም ሆነ በአንድነት ስም የሚቀነቀን ለአገር ግንባታ አይበጅም፡፡ ብዝኃነት ባለባት አገር አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ሆኖ አንዱ ሌላውን አግልሎ መኖር አይቻልም፡፡ አንድ ጸሐፊ  “Multi-ethnic societies can survive only if all respective groups within the polity feel themselves as winners” እንዳሉት ነው፡፡

በመሆኑም ፓርቲዎች አገርን እንደ አገር ለማስቀጠል ከሁለቱም ጫፎች በመውጣት ለብሔራዊ መግባባትና የጋራ ራዕይ መኖር ቁርጠኛነትን ካሳዩ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲን ማስፈን የሁሉንም መብቶች የምታከብርና በፕሮፌሰር መረራ አገላለጽ ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባት ይቻላል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምንም እንኳ የራሳቸውን ፕሮግራምና መርህ ማራመድ የተቋቋሙበት ዓላማና መብታቸው ቢሆንም፣ ለአገር አንድነትና አገረ መንግሥቱን ለማስቀጠል ሲባል ካለፈው የበዳይ ተበዳይ ትርክትም ሆነ የጭፍን አንድነት አስተሳሰብ በመውጣት የሚያሰማማ መካከለኛ መንገድ ላይ መገናኘት አለባቸው፡፡ አለበለዚያ እንደ ጥንት ባቢሎናውያን በቋንቋ ተለያይቶና ተደበላለቆ አገራዊ ሕልውናን ማጣት ይመጣልና፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...