Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዓባይ ባንክ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመንፈቅ ተቀማጭ ሒሳቡ ከ1.9 ቢሊዮን በላይ ነበር

ዓባይ ባንክ በግማሽ ሒሳብ ዓመቱ ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 1.9 ቢሊዮን ብር ሲደርስ፣ ጠቅላላ ተቀማጩን ከ13.5 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ እንደቻለ አስታወቀ፡፡

ባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ የማሰባሰብ እንቅስቃሴውን ለማሳደግ ከሚጠቀምባቸው ሥልቶች አንዱ በሆነውና በመላ አገሪቱ በጀመረው ቁጠባን የማስተዋወቅ ሥራ በማስመልከት የካቲት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በዚሁ ወቅት በባንኩ ኃላፊዎች እንደተገለጸው፣ በስድስት ወራት ውስጥ ከ1.9 ቢሊዮን ብር በላይ የተቀማጭ ገንዘብ ተሰብስቧል፡፡

 በ2011 ዓ.ም. ዓባይ ባንክ ያስመዘገበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 11.6 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዘንድሮው ግማሽ ዓመት መጨረሻ 13.5 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ እንደቻለ ይፋ አድርጓል፡፡ በግማሽ ዓመቱ የተሰበሰበው አዲስ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ካለፈው ዓመት ሙሉ ሒሳብ መጠን አኳያ እኩል ሊባል የሚችል ሆኖ ተገኝቷል፡፡ አምና ሙሉውን ዓመት ያሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ሁለት ቢሊዮን ብር እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

ከጥር 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በመላ አገሪቱ የጀመረው የቁጠባ ባህል ዘመቻና የባንኩን አገልግሎቶች በማስተዋወቅ በኩል በሚያደርገው እንቅስቃሴ፣ አዳዲስ የባንክ ደንበኞችን እያመጣለት በመሆኑ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ማሳደግ እንዳስቻለው የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በለጠ ዳኛው አብራርተዋል፡፡

ባንኩ ከጥር 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በ220 ቅርንጫፎቹ አማካይነት የባንክ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ከተሞች ብቻም ሳይሆን፣ ቅርንጫፎቹ በሌሉባቸው አካባቢዎችም ጭምር በድንኳን የታገዘ የቅስቀሳና የአዳዲስ ደንበኛ ምልመላ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ዓባይ ባንክ እንዲህ ያለውን አሠራር ሲተገብር የመጀመርያው እንደሆነና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ባከናወነው እንቅስቃሴ ምናልባትም አብዛኞቹ ባንኮች እንዳጋጠማቸው ከሚነገረው የገንዘብ እጥረት ጋር የሚያያዝ ስለመሆኑ ለቀረባቸው ጥያቄ አቶ በለጠ በሰጡት ምላሽ፣ እንቅስቃሴው ከገንዘብ እጥረት ጋር የሚያያዝ እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡ ይልቁንም የባንኩ እንቅስቃሴ ከዚህ ቀደም በዕቅድ ተይዞና በጀት ተመድቦለት  ሲተገበር የሰነበተ ሥራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠንን የማሳደግ ተልዕኮ ዋና ዓላማ የመቆጠብ ባህል ለማስረፅና ዜጎች እንደየሙያቸውና የሥራ ባህሪያቸው ከሚያገኙት ገንዘብ የተወሰነውን በባንክ አስቀምጠው ለነገ ፍላጎታቸው እንዲያውሉት፣ የገንዘብ አስተዳደር ልምዳቸውም በዘመናዊ የባንክ ቁጠባ ዘዴ እየታገዘ የነገ ሕይወታቸውን መምራት የሚችሉበትን ዕገዛ ለመፍጠር በማሰብ የሚካሄድ ተግባር እንደሆነ በምክትል ፕሬዚዳንቱ ተብራርቷል፡፡

ባንኩ በአሁኑ ወቅት ለደንበኞች ልዩ ልዩ ጥቅም የሚያስገኙ፣ የአስቀማጮችን አቅም ለማጠናከር የሚያስችሉ አገልግሎቶች እያዘጋጀ እንደሚገኝና እነዚህን አገልግቶችም በሰፊው ለማስተዋወቅ እየሠራ ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ከቁጠባ አማራጮቹ መካከል የተማሪዎች የቁጠባ አገልግሎት፣ ጥሪት የቁጠባ አገልግሎት፣ ሙዳይ የቁጠባ አገልግሎት፣ ለቤትና መኪና ግዥ የሚሰጥ የብድርና የቁጠባ አገልግሎት፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች እንዳቀረበ የገለጹት አቶ በለጠ፣ እነዚህ የተለመዱ አገልግሎቶች ቢሆኑም የዓባይ ባንክ ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎችም ጭምር የቁጠባ አማራጮቹን በማቅረብ መደበኛ የባንክ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች