Thursday, June 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዳያስፖራ ስልክ ደወለላቸው]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰላም ወዳጄ፡፡
 • ምን ሆነው ነው ስልክ የማያነሱት?
 • የእኛን ነገር እያወቅከው፡፡
 • ምኑን?
 • ቢዚ መሆናችንን ነዋ፡፡
 • አይ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምነው?
 • ሕዝቡ የሚፈልገው እኮ ቢዚ መሆናችሁን አይደለም፡፡
 • ታዲያ ሌላ ምን ይፈልጋል?
 • ጥቅሙን ማስከበራችሁን ነዋ፡፡
 • ለዚያ አይደል እንዴ ቢዚ የሆነው፡፡
 • አልመሰለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ሕዝቡ ምን እያለ እንደሆነ አልሰሙም?
 • ስለምኑ?
 • ስለግድቡ ነዋ፡፡
 • ምን አለ ደግሞ?
 • ክቡር ሚኒስትር ሁላችንም ሥጋት ውስጥ ነን፡፡
 • ለምን?
 • የለፋንበት ግድብ መና እንዳይቀር ሠግተን ነዋ፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • ድርድሩ ግብፅን እንጂ ኢትዮጵያን የሚጠቅም አይደለም፡፡
 • ማን ነው ያለው?
 • ሚዲያው ሁሉ እሱን አይደል እንዴ የሚያወራው?
 • ወሬኞች በላቸው፡፡
 • እነሱ ምን አደረጉ?
 • ይኸው እነሱ አሉባልታቸውን እየረጩ ሥራ መሥራት አቃተን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እነሱም እኮ ሥራቸውን እየሠሩ ነው፡፡
 • አሉባልታ ማሠራጨት ነው ሥራቸው?
 • እናንተ ወጥታችሁ በግልጽ ካላወራችሁ አሉባልታ መወራቱማ አይቀርም፡፡
 • እኛ እኮ አገራችንን እንወዳለን፡፡
 • ታዲያ በሥራ አሳዩና?
 • ምን እያልክ ነው?
 • ይኸው እናንተ አገሪቱን እየመራችኋት አይደል እንዴ ቀውስ በቀውስ የሆነችው?
 • እኛ ምን አደረግን?
 • ክቡር ሚኒስትር ጣት መጠቋቆሙ አያዋጣችሁም፡፡
 • ማን ጠቆመ?
 • ይኸው እኛ ምን አደረግን ምናምን እያሉ አይደል እንዴ?
 • እ…
 • ብቻ ለማንኛውም ሁላችንም እየተከታተልናችሁ ነው፡፡
 • በምኑ?
 • በህዳሴ ግድቡ ጉዳይ ነዋ፡፡
 • እንግዲህ የቻልነውን እናደርጋለን፡፡
 • ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአገሩ ቀልድ እንደማያውቅ ያውቃሉ፡፡
 • እሱማ ግልጽ ነው፡፡
 • እንግዲያው አንድ ነገር ልንገርዎት?
 • ምን?
 • በግድቡ የሚነሳ ቁጣ…
 • እ…
 • አይገደብም!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ምንም አላማረኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ?
 • አካሄዳችን ነዋ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ሕዝቡ ደስተኛ አይደለም፡፡
 • በምኑ?
 • በብዙ ነገሮች፡፡
 • ምን እናድርግ ታዲያ?
 • መነጋገር አለብን፡፡
 • አንድ ላይ አይደል እንዴ አገር እየመራን ያለነው?
 • ነበር ባይሰበር፡፡
 • አልገባኝም ምን እያልክ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ሁሉም እንዳሻው ነው እየተጓዘ ያለው፡፡
 • ማለት?
 • በአገራችን ጉዳይ ሌሎች ገብተው እየፈተፈቱ አይደል እንዴ?
 • ምን አልከኝ?
 • ክቡር ሚኒስትር አገራችን በሯ ተበረጋግዷል፡፡
 • እ…
 • ይህ ደግሞ ለብዙ ችግሮች ሊዳርገን ይችላል፡፡
 • የምታወራው ምንም አልገባኝም?
 • እንዲገባዎት ካልፈለጉማ እንዴት ይገባዎታል?
 • አስረዳኝ እያልኩህ እኮ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ሁሉም በየፊናው የፈለገውን እያደረገ ነው እኮ፡፡
 • ለምን በግልጽ አትነግረኝም?
 • አገሪቱ በጎረቤት አገሮች ሰላዮች ተሞልታለች፡፡
 • እ…
 • የቀድሞ ጓዶቻችንን ለማናደድ ብለን እየሄድንበት ያለው ርቀት አደገኛ ነው፡፡
 • እ…
 • በዚያ ላይ በተለያዩ ቦታዎች ለሚፈጠሩ ግጭቶች አንዳንድ ባለሥልጣናት እጃቸው እንዳለበት መረጃዎችም አሉን፡፡
 • ይኼማ ሊሆን አይገባም፡፡
 • በሚያሳዝን ሁኔታ ግን እየሆነ ነው፡፡
 • እ…
 • በተለይ ከሌሎች አገሮች ጋር ያለን ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባዋል፡፡
 • ትክክለኛ ነጥብ ነው ያነሳኸው፡፡
 • እየተደረገ ያለው ግን ሌላ ነው፡፡
 • እ…
 • ለማንኛውም ሕዝቡም እየታዘበን ነው፡፡
 • እኛን?
 • ምን ጥያቄ አለው፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • ከዚያም አልፎ መልዕክት እያስተላለፈ ነው፡፡
 • ምን ብሎ?
 • አታሽቃብጡ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጋር ተገናኙ]

 • ታሳፍራላችሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • ለሥልጣን ብላችሁ አገር ትሸጣላችሁ?
 • ማን ነው የሸጠው?
 • እናንተው ናችኋ?
 • አንተን መሰልንህ እንዴ?
 • ማለት?
 • አንተ እኮ ነህ ከጥቅምህ ውጪ ሌላ ነገር ማየት የማትችለው፡፡
 • እ…
 • አንተ አይደለህ እንዴ ያልሆነ ትርክት እየፈጠርክ ሕዝብ ከሕዝብ የምታባላው?
 • ቢያንስ ከእናንተ እሻላለሁ፡፡
 • በምን?
 • እናንተ እኮ አገር እየሸጣችሁ ነው፡፡
 • ከአንተ ብሶ እንዲህ ስታወራ አታፍርም?
 • ምን ያሳፍረኛል?
 • ለማንኛውም እናንተ መቃወም እንጂ መምራት የት ታውቁበታላችሁ?
 • እልህ አያሲዙኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማለት?
 • እኔ የምሬን ከሠራሁ በዜሮ ነው የማስወጣችሁ፡፡
 • ማን ከለከለህ?
 • እናንተው ናችኋ፡፡
 • ምን ብለን?
 • አንተ መቃወም እንጂ መምራት አትችልም ብላችሁ ነዋ፡፡
 • ታዲያ ዋሸን?
 • እሱማ ትክክል ናችሁ፡፡
 • ስለዚህ አርፈህ ተቃወም፡፡
 • እኔ እኮ በመቃወም የሚገኘው ጥቅም በልጦብኝ እንጂ ጉድ ነበር የምሠራችሁ፡፡
 • እ…
 • ያው እናንተም ሥራ ስለምትሰጡኝ ብዬ እንጂ ድምጥማጣችሁን ነበር የማጠፋችሁ፡፡
 • ከእኛ ጋር እንደምትሠራ ማውራት የለብህም ብዬሃለሁ፡፡
 • እኔማ ለእርስዎ እንጂ ለሌላ ሰው አልናገርም፡፡
 • ለማንኛውም አንተም አቅምህን ማወቅ አለብህ፡፡
 • የምን አቅም?
 • ከእኛ ጋር መወዳደር እንደማትችል ነዋ፡፡
 • እሱን እንኳን ይተውት፡፡
 • እንዴት?
 • ምርጫውን ብወዳደር ድሮ እናንተ እንደምታሸንፉት ነበር የማሸንፈው፡፡
 • በምንድነው የምታሸንፈው?
 • በዝረራ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]

 • አላቆምም አላችሁ አይደል ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑን?
 • ብሽሽቁን ነዋ፡፡
 • የምን ብሽሽቅ ነው?
 • በየሄዳችሁበት ስለእኛ ብቻ ነው እንዴ የምታወሩት?
 • ኧረ እኛ ብዙ ሥራ አለብን፣ ለወሬ ጊዜ የለንም፡፡
 • የት እንደሚያደርሳችሁ ግን እናያለን፡፡
 • መቼም አሁን የሚፈራችሁ እንደሌለ ታውቃለህ?
 • እሱማ ጥርሳችን እንዳልተነቀለ ጠንቅቃችሁ ታውቃላችሁ፡፡
 • ግን ያው ኬጅ ውስጥ ስላስቀመጥናችሁ ምንም አታመጡም፡፡
 • ለማንኛውም እኛን ለማናደድ ብላችሁ የምታደርጉት ነገር መስመር እያለፈ ነው፡፡
 • መስመር እያለፋችሁማ ያላችሁት እናንተ ናችሁ እኮ፡፡
 • ምን አደረግን?
 • የቱን ከየቱ ልዘርዝርልህ?
 • እናንተስ ምን እያደረጋችሁ ነው?
 • ምን አደረግን?
 • ይኸው አርፈን እንዳንቀመጥ እያደረጋችሁን ነዋ፡፡
 • እናንተ መቼ አርፋችሁ ተቀምጣችሁ ታውቃላችሁ?
 • እ…
 • እያንዳንዱን ሴራችሁን እናውቀዋለን፡፡
 • ለማንኛውም ይኼ ብሽሽቅ እናንተን የትም አያደርሳችሁም፡፡
 • እኛማ እናንተን እያበሸቅን አይደለም፡፡
 • ታዲያ ምን እያደረጋችሁ ነው?
 • እያወራረድን ነዋ፡፡
 • ምን?
 • ሒሳብ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ አመሻሹን መኖሪያ ቤታቸው ሲደርሱ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈው የማዕከላዊ ኮሚቴ ገለጻ እየተከታተሉ አገኟቸውና አጠገባቸው ተቀምጠው የደረሱበትን አብረው መከታተል እንደጀመሩ፣ ባለቤታቸው ቴሌቪዥኑን ትተው መጠየቅ...

እኔ ምለው? እሺ... አንቺ የምትይው? የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ አባላት እንዲያወሩ ወይም እንዲጠይቁ አይፈቀድም እንዴ? እንዴት ይከለከላል? ታዲያ ለምንድነው ፕሬዚዳንቱ ብቻ የሚያወሩት? እያወሩ አይደለም፣ ገለጻ እያደረጉ ነው። ቢሆንም አንድም አባል...

[ክቡር ሚኒስትሩ አምሽተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው ‹‹ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን›› የሚለውን የቴሌቪዥን ዜና ተመልክተው ለብቻቸው ሲስቁ አገኟቸው]

ስልክ እያወራሽ ነበር እንዴ? ኧረ በጭራሽ... ምነው? ታዲያ ምንድነው ብቻሽን የሚያስቅሽ? አይ... በቴሌቪዥኑ የሚቀርበው ነገር ነዋ። ምንድነው? ድሮ ድሮ ዜና ለመስማት ነበር ቴሌቪዥን የምንከፍተው፡፡ አሁንስ? አሁንማ ቀልዱን ተያይዘውታል... አንተ ግን በደህናህ...

[ክቡር ሚኒስትሩ የቢሮ ስልካቸው ጠራ። ደዋዩ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊ እንደሆኑ ሲነገራቸው የስልኩን መነጋገሪያ ተቀበሉ]

ሃሎ፡፡ እንዴት አሉ ክቡር ሚኒስትር። ደህና ነኝ። አንተስ? አስተዳደሩስ? ሕጋዊ ሰውነታችን ተነጥቆ እንዴት ማስተዳደር እንችላለን ክቡር ሚኒስትር? ለዚህ ጉዳይ እንደደወልክ ገምቻለሁ። ደብዳቤም እኮ ልከናል ክቡር ሚኒስትር፡፡ አዎ። ሁለት ደብዳቤዎች ደርሰውኛል።...