Monday, May 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ተናቦ አለመሥራት አገር ለመምራት ያስቸግራል!

የመንግሥት አካላት ተናበው መሥራት ሲያቅታቸው አሠራራቸው ግልጽነት ማጣት ብቻ ሳይሆን፣ ተጠያቂነት እየጠፋ ሁሉም እንዳሻቸው በመሆን በሕዝብ ላይ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት በየደረጃው ያሉ መዋቅሮቹ እርስ በርስ መግባባት አለባቸው፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት አለበት ሲባል አመራሮቹ የሐሳብና የተግባር አንድነት ሊያሳዩ የግድ ነው፡፡ የፌዴራል፣ የክልልና የሁለቱ አስተዳደር ከተሞች (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) በየደረጃው የሚያዟቸው የፀጥታ አካላትም በዚህ ሁኔታ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርብ ከታዩ ክስተቶች ብንነሳ እንኳ የአስተዳደር መዋቅሮችና የፀጥታ አካላት አሠራር ግርታ እየፈጠረ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ወቅት የአንድ ታዋቂ ግለሰብ ጥበቃ ለማንሳት በሌሊት የተደረገው ሥምሪት፣ ለ86 ንፁኃን ወገኖች ዕልቂት ሰበብ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ሰሞኑን ለቤተ እምነት ግንባታ ተከልሏል የተባለ ሥፍራን ለማስለቀቅ እንዲሁ በሌሊት የተደረገ ዘመቻ፣ ለሦስት ወገኖች ሕልፈት ምክንያት ሆኗል፡፡ ሌሊቱን አካባቢውን በመቆጣጠር ከነጋ በኋላ ኃላፊነትን መወጣት ሲገባ፣ ለማመን በሚቸግር ሁኔታ ተደጋጋሚ ስህተቶች መሥራት እጅግ በጣም ያሳዝናል፡፡ ሕግ የሚከበረው በሕጋዊ መንገድ መሆኑ ችላ እየተባለ የንፁኃን ሕይወት በከንቱ ሲቀጠፍ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ምን ሊፈጠር እንደሚችል አለማሰብ ከማስገረም አልፎ ያበሳጫል፡፡ አሁንም መጥራት ያለባቸውና ለሕዝብ ግልጽ መደረግ ያለባቸው እውነታዎች እንዳሉ መታወቅ አለበት፡፡

እንደሚታወቀው ግልጽነት በሌለበት አገርን መምራት ፈፅሞ አይቻልም፡፡ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የመንግሥታቸው አሠራር ለሕዝብ ግልጽ እንደሚሆን መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን የመንግሥት አሠራር ግልጽነት የተጓደለበት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የመንግሥት አካላትም እርስ በርስ እየተናበቡ እየሠሩ አይደሉም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሰሞኑን የተፈጸመውን አሳዛኝ ድርጊት ‹‹ልብ ሰባሪ ነው›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለከተማው ፖሊስ አስተዳደራቸው ደመወዝ እንደሚከፍል እንጂ፣ ዕዙና ሥምሪቱ በእሳቸው ሥር እንዳልሆነ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ድሬዳዋ ከተማን ጨምሮ ክልሎች በሙሉ የሚያዙበት የፖሊስ ኃይል ሲኖራቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ባይተዋር መሆን ምን የሚሉት አሠራር ነው? የከተማ አስተዳደሩስ የማያዘውና የማያሰማራው የፖሊስ ኃይል፣ በስሙ እየተጠራና በጀት እየመደበለት እስከ መቼ ነው የሚቀጥለው? ከዚህ ባለፈ ግን የከተማ አስተዳደሩ ሕግ በማስከበር ስም የተፈጸመውን ልብ ሰባሪ ድርጊት ተዋንያን ሕግ ፊት አቅርቦ ለነዋሪዎች በግልጽ ማሳየት አለበት፡፡ የሟች ቤተሰቦችን ከማፅናናት በተጨማሪ ካሳ ወይም ድጋፍ የሚያገኙበትን፣ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካባቢዎች ነዋሪዎች ላይ ተመሳሳይ ድርጊቶች እንደማይፈጸሙ መተማመኛ መስጠት አለበት፡፡ የአገር ጉዳይ የሚያሳስባቸው ወገኖችም እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ድርጊቶች ሲያጋጥሙ፣ በሰከነ መንገድ መፍትሔ የሚያገኙበት ጉዳይ ላይ እንዲተኮር ማገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚያ በተረፈ በግራና በቀኝ በመሠለፍ ይህንን አሳዛኝ ድርጊት ለፖለቲካ ፍጆታ ለመጠቀም የሚቅበዘበዙትን ማስቆም ተገቢ ነው፡፡ ለማንም የማይጠቅም ርካሽ ነገር ነው፡፡ በሟቾችና በቤተሰቦቻቸው ላይ እንደመቀለድ ይቆጠራል፡፡

መንግሥት ሕግ ያስከብር ሲባል ኃላፊነቱን እንዴት መወጣት እንዳለበት በሕግ የተሰጠው ሥልጣን አለው፡፡ ሕገወጥ ግንባታን ለማፍረስ ከመሰማራቱ በፊት፣ ውስጡ ያሉ ሕገወጦችን ማስተካከል ወይም ማስወገድ አለበት፡፡ አንድ ቦታ በሕገወጥ መንገድ ተይዟል ተብሎ በአስተዳደሩም ሆነ በሌላ የመንግሥት አካል ውሳኔ ላይ ሲደረስ፣ በግልጽ በሚዲያ ማስታወቂያ ወይም መግለጫ ማስጠንቀቂያ መሰጠት አለበት፡፡ ቀነ ገደቡም እንዲሁ፡፡ አንድ ቦታ ሕገወጥ ነው ሲባል፣ በሌላ ሥፍራዎች በሕገወጦች የተያዙ ጭምር ተመሳሳይ ውሳኔ ሊተላለፍባቸው ይገባል፡፡ ግማሽ ጎፈሬ ግማሽ ልጩ ሆኖ አገር ማስተዳደር አይቻልም፡፡ መንግሥት የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ተመሳሳይ፣ ከአድልኦና ከመድልኦ የፀዱ፣ ለሐሜት የማያጋልጡና ተዓማኒነት ሲኖራቸው ሕዝብም አሠራሩን በግልጽ ይረዳል፡፡ የሚወሰደውንም ዕርምጃ ይደግፋል፡፡ ዕርምጃውም በሌሊት ሳይሆን በጠራራ ፀሐይ ሕዝብ እያየው ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ተጠያቂነትና ኃላፊነት ስላለበት ውጤቱ በጋራ ተቀባይነት ያገኛል፡፡ ይህንን ዓይነት ግልጽ አሠራር የሚፃረሩ ደንቦች ወይም መመርያዎች ካሉም፣ በሕጋዊ መንገድ በፍጥነት መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ሕገወጥነትን ለመከላከል የሚሠሩ በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎችም ሆኑ ሠራተኞች፣ በራስ መተማመናቸው ጨምሮ ሥራቸውን ለማከናወን ይጠቅማቸዋል፡፡ የተዝረከረኩ አሠራሮች የሚመሩባቸው ደንቦችና መመርያዎች ዓላማቸው ምን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለዘረፋ፣ የመንግሥትን አሠራሮች ለማበላሸትና ሕገወጥነትን ለማበረታታት ብቻ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ለንፁኃን ሕይወት መጥፋትም ትልቅ ሚና አላቸው፡፡

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ከግለሰብ ጀምሮ ትልልቅ የመንግሥት ኃላፊነቶችን የሚመሩ ሰዎች ድረስ፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ለሕግ ጥሰት ተባባሪ መሆን እንደሌለባቸው ነው፡፡ አንዱ ቦታ የተወገዘ ድርጊት ሌላ ቦታ ቅዱስ ሊሆን አይችልም፡፡ ቀበና ላይ ሕግ እየተከበረ መርካቶ ሕግ ሲጣስ ትክክል አይሆንም፡፡ መንግሥት ውስጡን ሲያፀዳና አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ የማድረግ ቁመና ላይ ሲገኝ፣ ሕገወጥነትን ለመከላከል የሕዝብን ድጋፍ በቀላሉ ለማግኘት አያዳግተውም፡፡ እየቸገረ ያለው ወይ እርስ በርሱ አይናበብ፣ ወይ አሠራሩ በግልጽ አይታወቅ፣ ከዚህ የባሰው ደግሞ በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አደጋ የሚጋብዝ ድርጊት ይፈጽማል፡፡ ሕግ ማስከበር በሥርዓት ሲመራና ተጠያቂነት ሲኖርበት የሕዝብ አመኔታ ይጨምራል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በዘፈቀደ አሠራር የዘፈቀደ ግድያ ይፈጸምና የሰሞኑ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ የመንግሥት የመረጃ ፍሰት አሁንም በሽተኛ ስለሆነ መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነ፣ ለምን እንደሚሠራ፣ ጥቅምና ጉዳቱ ምን እንደሚያስከትልና የቁጥጥር ሥርዓቱ ምን እንደሚመስል በግልጽ አይታወቅም፡፡ በዚህም ምክንያት በሐሰተኛ መረጃ ወረርሽኝ ከውይይት ይልቅ መፋጠጥ፣ የተበላሹ ነገሮችን በሥርዓት ከማስተካከል ይልቅ መጋጨትና ደም መቃባት ይከተላል፡፡ እየተለመደ ያለውም ይህ ዓይነቱ አደገኛ መንገድ ነው፡፡ በከንቱ የንፁኃን ሕይወት ካለፈ በኋላ መፀፀት፣ መወቃቀስና ከዚያም ባለፈ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ለመስማት በሚዘገንኑ ቃላት መሰዳደብ ልማድ ሆኗል፡፡ አሁንም እየታየ ያለው ይኸው ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን በዚህ ዘመን ጥብቅና መቆም ያለባቸው ለፍትሕ ነው፡፡ ፍትሕ የሚገኘው በርካሽ የፖለቲካ ትርፍ አይደለም፡፡ ፍትሕ እንዲሰፍን ሁሉም ሰው በሕግ ጥላ ሥር መሆን አለበት፡፡ ሕግ ማክበርም ሆነ ሕግ ማስከበር ከሕገወጥነት ጋር ዝምድና የለውም፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር መተዳደርም ሆነ ማስተዳደር ፍትሕ ለማስፈን ጠቃሚ ነው፡፡ ትናንት ለፍትሕ ታግያለሁ ያለ ዛሬ ፍትሕን የሚደረምስ ድርጊት ሲደግፍ ከተገኘ፣ የታገለው ለእውነት ሳይሆን ለሐሰት ነው የሚሆነው፡፡ በመንግሥት ሥልጠን ላይ ያሉም ሆኑ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የሚፎካከሩ ማወቅ ያለባቸው፣ ድምፅ የሚሰጣቸው ምስኪን ሕዝብ ፍትሕ መጠማቱን ነው፡፡ በአስመሳይነትና በርካሽ ተወዳጅነት ሕዝብን ማማለል አይቻልም፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው ለፍትሕ፣ ለነፃነትና ለእኩልነት በቁርጠኝነት የሚሠራውን ነው፡፡ ሕዝብም በሚገባ መመርመር ያለበት ይህንን ነው፡፡ ብሔርን፣ ቋንቋን፣ ባህልንና ሃይማኖትን እየተከለሉ በስሙ የሚቆምሩትንና የሚነግዱትን መለየት አለበት፡፡ ዛሬ መንግሥትን የሚመራው አካልም ሆነ ነገ መንግሥትን ለመምራት የተዘጋጀው ሳይቀር አበክረው መገንዘብ ያለባቸው፣ ማንም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆን የሚችልበት ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ አንዱን ልጅ ሌላውን የእንጀራ ልጅ በማድረግ በፍትሕ መሸቀጥ አይገባም፡፡ ቦሌ ተግባራዊ የሆነ ሕግ ጉለሌም ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል፡፡ በተለይ ደግሞ መንግሥትን የሚመራው አካል ከላይ እስከ ታች መዋቅሩን ይፈትሽ፡፡ ከዘፈቀደ አሠራር ይውጣ፡፡ በሰብዓዊ ፍጡራን ላይ አደጋ የሚፈጥሩ ድርጊቶችን ያስወግድ፡፡ መዋቅሮቹ እየተናበቡ ይሥሩ፡፡ ይህንን ማድረግ ካቃተው ግን እንኳን አገር መምራት ህልውናውም ተስፋ አይኖረውም!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከወለድ ነፃ ባንክ የተሰበሰበውን በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለምን ሥራ ላይ ማዋል አልተቻለም?

  ባንኮች ከወለድ ነፃ የሚሰበስቡት ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ዕድገት እያሳየ...

መንግሥት ባለፈው ዓመት ለማዳበሪያ የደጎመው 15 ቢሊዮን ብር ለአርሶ አደሮች አለመድረሱ ጥያቄ አስነሳ

መንግሥት ለ2014/15 በጀት ዓመት እርሻ በአፈር ማዳበሪያ ላይ ያለውን...

የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሁሴን አህመድ (1930-2015)

ኢትዮጵያ የሁለተኛውን የፋሺስት ጣሊያን ወረራ (1928-1933) በድል ከተወጣች በኋላ...

የመስጅድ ፈረሳን በመቃወም እንዲቆም ለመጠየቅ በተደረገ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ የሰው ሕይወት አለፈ

በ56 የፖሊስ አካላትና አጋዥ ኃይሎች ላይ ጉዳት ደርሷል ‹‹በሕዝበ ሙስሊም...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...

ለመጪው ዓመት የሚያስፈልገው 4.3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ 4.4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል

ለመጪው 2016 ዓ.ም. ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ለታቀደው 4.3...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ የቢሮ ስልካቸው ጠራ። ደዋዩ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊ እንደሆኑ ሲነገራቸው የስልኩን መነጋገሪያ ተቀበሉ]

ሃሎ፡፡ እንዴት አሉ ክቡር ሚኒስትር። ደህና ነኝ። አንተስ? አስተዳደሩስ? ሕጋዊ ሰውነታችን ተነጥቆ እንዴት ማስተዳደር እንችላለን ክቡር ሚኒስትር? ለዚህ ጉዳይ እንደደወልክ ገምቻለሁ። ደብዳቤም እኮ ልከናል ክቡር ሚኒስትር፡፡ አዎ። ሁለት ደብዳቤዎች ደርሰውኛል።...

[ክቡር ሚኒስትሩ አየር መንገዱ ወጪ ቆጣቢ የሥራ እንቅስቃሴ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን በሚያሳድግበት ሁኔታ ላይ ከተቋሙ ኃላፊ ጋር እየተወያዩ ነው]

ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ትልቁ ወጪያችን ለነዳጅ ግዥ የሚውለው ነው። ክቡርነትዎ እንደሚገነዘቡት የዩክሬን ጦርነት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በእጅጉ አሻቅቧል። ቢሆንም አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር ውስጥ...

[ክቡር ሚኒስትሩ የነዳጅ ግብይት በዲጂታል ክፍያ መንገድ ብቻ እንዲፈጸም የተላለፈውን ውሳኔ አተገባበር ላይ ስለተነሱ ቅሬታዎች ከባልደረባቸው ጋር እየተወያዩ ነው]

ክቡር ሚኒስትር አተገባበሩ ጥሩ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ወቀሳ እየደረሰብን ነው። ዲጂታል የግብይት ሥርዓቱን ለማስፋፋት በመጣራችን መመስገን ሲገባን እንዴት እንወቀሳለን? የሚገርመው በዲጂታል ክፍያ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ናቸው በዋነኛነት...