Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጎደሎዎቻችን በምን ይሞሉ?

ሰላም! ሰላም! ‹‹በሬ ስም በሚወጣለት አገርሥጋ ስም አነሰውብሎ ሐሜት መቼም አይኖርም፤›› ብሎ አንድ በቅርብ የማውቀው ወዳጄ ለሕፃናት መዋያ ያከራየውን ግቢውን፣ ወደ ሥጋ ቤትነት ማሸጋገሩን በሩ ላይ ባለሻኛ በሬ አስሮ ነገረኝ። የሠፈራችን ሰውም መዋዕለ ሕፃናቱ ሲዘጋ ዝም ብሎ፣ ዘመናዊ ሥጋ ቤት ሲከፈት ወሬውን አዳረሰው። የእውቀት ማዕድ ተዘግቶ የመብል ማዕድ ሲዘረጋ ነገን የረሳ ሁሉ እጁን መታጠብ ሲጀምር ፈራሁ። ዘንድሮ በስንቱ ፈርተን እንዘልቀው እንደሆን የላይኛው ጌታ ብቻ ነው የሚያውቀው። ሕፃን አዋቂውቆራጭበሆነበት ጊዜ አንተስ ምንቆርጦህ የሰው ልጅ ታማለህ አትሉኝም? እኔም ዘንግቼው እንጂ ከደላላነት የሚብስብኝ ቆራጭነቴ መስሎኝ። ይኼም ሥጋ፣ ያም ሥጋ። ልዩነቱ የእኔ የሥጋት፣ የዚያኛው የአምሮት መሆኑ መሰለኝ። ካላመናችሁ ላመሳክርላችሁ። እኔ ሠፈር የተዘጋው መዋዕለ ሕፃናት ነው። የተከፈተው ደግሞ ሥጋ ቤት ነው። እንግዲህ የእናንተን ሠፈር አላውቅም። ግን ልገምት። ትናንትና መለስተኛ ክሊኒክ የነበረው ምናልባት ስጠረጥር ዛሬ ጫት ቤት ሆኗል። ወይም ደግሞ መለስተኛ መጻሕፍት አከፋፋይ የነበረ ከሆነም፣ ዛሬ ወይ መጠጥ ቤት ነው ወይም ማሳጅ ቤት ሆኗል። ባይሆን እንኳ በዚህ አያያዛችን ከቀጠልን እመኑኝ ይሆናል።ሳያዩ የሚያምኑ መልካሞች ናቸውእንዳልላችሁ እኔም እንደ እናንተው በሚመጣ በሚሄደው ስም ያጠረው ነገር ተገዥ ነኝ። ታዲያ ሌላ ምን እላለሁ? ብቻ እንዲያው ሲገርመኝ ሰነበተ። ‹‹ኤድያ ያንተ ግርምት ነው እኔን ያስቸገረኝ፤›› ይሉኛል ባሻዬ። እሳቸው ደግሞ ማሳለፍ አልፈጠረባቸውም!

‹‹እንዴት?›› ስላቸው፣ ‹‹ምን አገባኝ ብለህ ነው እንዲህ የምትብሰከሰከው? ሥልጣን የለህ፣ ድምፅ የለህ፣ ወይ ጉልበት የለህ። ምን በልተህ ብትጠግብ ነው በዚህ የኑሮ ውድነት ላይ የትም ለፍተህ የምትቆርሰውን እንጀራ አንጀትህ ሳይደርስ የምታበነው?›› ይሉኛል። ቆይ ግን ልክ አይደለም ወይም ኧረ ይኼ ነገር ሲል አድማጭ ቢጠፋ ቢያንስ የመገረም መብቱን ይገፈፋል? ሌላው ሁሉ ቢቀር የሚገረሙ ታዛቢ ለመሆን ሲባል ብቻ በሥጋ ተሟሽቶ፣ በቅጠል ተብላልቶ፣ በገብስ ውኃ ወይም በደረቅ አልኮል የሚታጠብ የዕለት ተዕለት የኑሮ ዘይቤ ከተማችንንና ሙሉ አገራችንንማኖሲያስነካ ኧረፋውልነው የሚል ይጥፋ? ለስሙ ግን ኳስ ስንተነትን አንደኛ ነን። ድንቄም ተመልካች ይባል ነበር ድሮ። ዘንድሮማ ከተመልካችነት ወደ ተወዳዳሪነት መግባት ነው የሚያዋጣው እንጂ ዝም ብሎ መፍዘዝማ አይገባም!

 

እሺ ይሁን ግድ የለም። የዓይኑን ተውትና ወደ ጆሮ ልውሰዳችሁ። መቼም በስሚ ስሚ የነገር ሐረጋችንን አንጠራጠርም። ዓይቶ ማመንማ ዘበት ሆኗል። ይኼ አባባሌ ፌስቡክን እንደማይመለከት አስምሩልኝ። ማስመሩን ስትጨርሱ ወደ ስልክ ጥሪ ልውሰዳችሁ። ድሮ አንድ መልካም ጎረቤት ነበረችኝ። በመላ ጎረቤቶቻችን የተመሠገነች ባለሙያም ነበረች። ምን ያደርጋል ባሏ ያለ አመሉ መጠጥ ለምዶ የመጠጥ ቤት ደንበኛ ሲሆን፣ አንዷን ለመደና እንደ ወጣ ቀረ። ደግሞ ይኼን ስላችሁ በመጠጥ ብቻ ነው ወይ ሰው ቤቱን ጥሎ የሚጠፋው አለ እንዳትሉኝ፣ እኔም አልወጣኝም አደራ። ሚስትየው ገና ሁለት ዓመት ያልሞላት ልጅ አላት። እናም ቸጋግሯት የተወሰነ ገንዘብ ልኬላታለሁ። ስልኬ ሲጠራ ሳየው የእሷ ቁጥር ነው። ውሎ አድሮ ምሥጋና የለም። ‹‹ምን ልትለኝ ነው?›› ስል ማንጠግቦሽ ሰምታኝ፣ ‹‹አንተ ደግሞ…›› ብላ ስልኩን አነሳችው።

ከላውድ ስፒከሩ የምሰማው ድምፅ ጩኸት ነው። ‹‹ገደልኳት . . . ገደልኳት . . .›› እያለች እሪ። ኋላ አንድ የተረጋጋ ሰው ስልኳን ነጥቆ ሲነግረን፣ በቴሌቪዥን ፊልም እያየች ዓይኗን ሳትነቅል ለሕፃኗ በጡጦ ወተት ስታቀብላት ሕፃኗ ፀጥ። ምን ሆኖ መሰላችሁ? ወተቱን ከእነ ጡጦው ለብ አድርጋ ልትሰጥ የፈላ ውኃ ውስጥ ነክራው እሷ ቀልቧ ፊልሟ ላይ ነው። ሙቀቱን ሳትገምት እንደ ወረደ ስታወርድላት ፍግም። ይኼውላችሁ እንግዲህ። ቴሌቪዥን ፍርድ ቤት የምንገትርበት ጊዜ ሊመጣብን ነው። ነው ወይስ ዓይን ሊከሰስ ነው? ያዩትበእኛ ይብቃሲሉ ሰሚዎች እንዳልሰሙ ኖረው ሌሎች በሚቀሰፉባት ዓለም ያተረፍነው ተረትና ንግርት ብቻ ሆነ። ጆሮ ለባለቤቱ እንዲሉ። የሆነስ ሆነና የልጆቻችን ዕገታ ጉዳይ ግራ ግብት ባደረገን በዚህ ጊዜ ምን ይሻለን ይሆን!

ሁሉ በደጃችን አልሆን እያለ ቢያስቸግረን የምናወራው ነገር መቼም አናጣ። እናላችሁ ብለን ብለን የምበላው አታሳጣኝፈንታ የማወራው አታሳጣኝየምንልበት ጊዜ ላይ ሳንደርስ አልቀረንም። ታዲያ ይኼ ምኑም አይገርምም! ምኑ ይገርማልና? በቃ መኖር ካቃተን መኖር ስለቻሉት ማውራቱ፣ ሌላው ቢቀር አኗኗሪነታችንን ሲያረጋግጥልን በዓይናችን በብረቱ ዓይተናል። አባባል ስለሆነ እንጂ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ብረት ይሁን አይሁን፣ ደረቅ ይሁን እርጥብ የተረጋገጠ አይመስለኝም። ወሬው መላ ቅጥ አጥቶ መተናፈሻ ሲያሳጣን፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ብቻ የሚነዛው አሉባልታ ግራ ሲያጋባን፣ የሚመለከታቸው በዝምታ ታፍነው እኛንም አፍነው ሲያስጨንቁን ብዙ ታዝበናል። ‹‹እሱ የለመኑትን የማይነሳ የምንጎርሰው ሳይኖረን የምናወራው ነገር ይለቅብናል። መፍጠር አይታክተው እሱ!›› የሚለኝ አንድ የሠፈሬ ጫት ነጋዴ ወዳጄ ነው። ለጫት ካለው የተለየ ፍቅር የተነሳ በማይቅሙ ሰዎች ይናደዳል። ‹‹ሰው እንዴት ኑሮን በምርቃና መፎረፍ ሲችል አበሳ ያያል?›› ይለኛል ባገኘኝ ቁጥር። እሱ ምን አለበት በምርቃና ውስጥ ሆኖ ወጀቡን እያሳለፈ በነገር ወላፈን የምንለበለበውን ይባሳጭብናል። ብስጭት ወይ ጤና ይነሳል ወይ ዕድሜ ያሳጥራል እንዳልለው መቼ ቀልብ ኖሮት!

ስለዚህ የሚጎረስ ሲጠፋ በወሬ ጥግብ ማለትን ከልጅ እስከ አዋቂ ሁሉም ተግባራዊ ሲያደርገው ስታዩ ያስገርማችኋል። ላስረዳችሁ። እንደምናውቀው በከተማችን ሦስት የወሬ ዘርፎች አሉ። እነሱም ገንዘብ፣ ኳስ፣ ፖለቲካ ይባላሉ። ሦስቱም ግን በቀጭን የነገር ትብታብ ከኑሯችን ዋና ጥያቄ ጋር የተያያዙ ናቸው። ግልጽ ሳደርገው ለምሳሌ ስለሴት ሲወራ እንዲህ ሲባል ትሰሙ ይሆናል። ‹‹ውይ! እሱማ ምን የመሰለ ባለሥልጣን ተጠግቶ ከቀረጥ ነፃ ተፈቅዶለት ቢሊዮኖችን እያረሰ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ አምስት ሕንፃ አጠናቆ ሌሎች ማስገንባት ሊጀምር ነው . . .›› ይባልልኛል። ቀጥሉ ደግሞ ስለኳስ፣ ‹‹‘ሊዮኔል ሜሲና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ፓሪስ ተገናኝተው ምርጥ ፒዛቸውን ግጥም አድርገው በሉተባለ . . .›› ሲባል ትሰማላችሁ። ስለፖለቲካ ደግሞ፣ ‹‹እከሌ የሚባለው ፖለቲከኛ ፓርቲውን እከሌ ለተባለው ሀብታም ሸጦለት መሳቂያ ሆነ። ድሮም ለገንዘብ ብሎ እንጂ ለሕዝብ እንደማይታገል ይታወቅ ነበር . . .›› የሚሉትን ትሰማላችሁ። እንግዲህ በእነዚህ ሦስት ዋና ዋና የጨዋታ አርዕስቶች ውስጥ ስንታዘብ፣ ለራሳችን ያጣናውን በሌሎች ሕይወት ስንቆጥረው መዋልን ሙያ ማድረጋችን ነው። የኗሪነት ስሜት ላልተሰማው አኗኗሪ ከመሆን ዘሎ ምን ምርጫ አለ? በነገራችን ላይ ምርጫ ሲባል ዘንድሮ የሚለይልን አይመስላችሁም!

ሰሞኑን እጅግ ቸግሮኝ የነበረ ነገር ቢኖር ያገኘኝ አላፊ አግዳሚ ሁላአንበርብር ምነው ከሳህ?’ ሲለኝ የሰነበትኩበት ጉዳይ ነው። ‹‹አራት እንቁላል ሃያ ብር እየተሸጠ እንዴት ብለን ልንወፍርላቸው አስበው እንደሆነ እግዜር ይወቀው? ባልበላ አንጀታችን ሠልፍ በየነገሩና በየቦታው በሆነበት አገር ቆመን ስናዛጋ እየዋልን ከሳህ ብሎ ሀተታ ምን ማለት ነው? በዘረፋ በተገኘ ሀብት የምተዳደር መሰልኳቸው እንዴ ይህን ያህል?›› እያልኩ ስነጫነጭ ማንጠግቦሽ ታዳምጠኝ ነበር። ውዷ ባለቤቴ እውነቴን ደግፋ እንዲህ ተናገረች። ‹‹ዝም አትላቸውም? ለነገሩ እንኳን ተራው ሰው መንግሥትስ በዚህ ዕድል መቼ ተጠቀመበት?›› ብላ ወደ እኔ እየተመለከች ጠየቀችኝ። ‹‹እንዴ? ደግሞ መንግሥትን እዚህ ምን ዶለው?›› አልኳት ትስስሮሹን እስክትገላልጠው እየተቁነጠነጥኩ። አንዳንዴ እኮ ምኑ ከምኑ ተሳስሮ እንደሚመጣባችሁ አታውቁትም!

‹‹መቼም በዚህ ጊዜ ሰው በደህና ቀን የሞላው ጎተራ ከሌለው በቀር፣ አልያም ደህና የሰው ድጋፍ ካልኖረው ይዞ መገኘትና በምቾት መታየት አይታሰብም። መንግሥት ቢያውቅበት ኖሮካልጠቆማችሁኝ የት አገኛቸዋለሁ?’ እያለ እኛ ላይ ማፍጠጡን ትቶ በርካታ ሰነዶችንና የሰው ምስክሮችን እየተከተለ፣ በአንድ ምሽት በሚሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ ውድ የአልኮል መጠጦች የሚንቆረቆሩባቸውን መሸታ ቤቶች እያሰሰ፣ የታዳጊ ሴት ወጣቶችን ሕይወት እየሰለለ ቢተጋ ስንቱን ዘራፊ፣ ስንቱን ሞራል አልባ ዜጋ በራዥ በመነጠረልን ነበር?›› አለችኝ። እንግዲህ በማንጠግቦሽ አገላለጽሌብነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የሞራል ዝቅጠት ጉዳዬ የሚላቸው አካል ባጡበት ጊዜ ከሳህ ብሎ ነገር ምን ይባላል? እንኳን ዜጋ አገር ከስታ ሳለ። አገር ሲባል እኮ አንዱ ሲያዝን አብሮ የሚያዝን፣ አንዱ ሲከፋው ሌላው አለሁልህ ወይም አለሁልሽ የሚባልበት እንጂ፣ ብዙኃን እየተቸገሩ ጥቂቶች የሚያናፉበት በረት አይደለም። አገርን እንደ በረት ኮርማ የሚበጠብጡና የትውልዱን ሞራል የሚያላሽቁ ወረበሎች የሚያገሱበትም አይደለም። ተሳሳትኩ እንዴ!

ሳትኩ እንዴ! በሉ እንሰነባበት። ተፍ ተፍ ብዬ ያጋለኝን ትዝብትና የፀሐይ ንዳድ በንፋስ ሽውታ፣ ደግሞም የገበያ ምኅዳሩ ባንቦረቀቀው የቢራ ገበያ የመረጥኩትን ጠርሙስ ይዤ ላበርድ ሠፈር ስደርስ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አገኘኝ። ‹‹ከማን ጋር ልሂድ ስል አገኘሁህ . . .›› ብሎ አጄን አፈፍ አደረገው። ወዴት ሊወስደኝ መሰላችሁ? ወደሚመረቀው የሠፈራችን ዘመናዊ ሥጋ ቤት። ለብቻ አንድ በሬ ታርዷል። የታረደው ደግሞ ለሠፈሩ ሰፋፊ አፎች ማስያዣ ነው። ይሁና ብዬ ተጎትቼ ስገባ ማንጠግቦሽ ቀድማኝ ታድማ ከባሻዬ አጠገብ ተቀምጣለች። በሩ ላይ በሬ የሚያህል ሞንታርቦ ስፒከር የዘመኑን አሰልቺ ሙዚቃዎች እየደጋገመ ማስደለቁ ሳያንስ፣ ሠፈሩን በድምፅ ብክለት ተቆጣጥሮታል። ከፊት ለፊቱ እኮ የንግድ ፈቃድ አውጥቶ መሸታ ቤት የከፈተ ደንበኛዬ ድምፅ በክለሃል ተብሎ ቤቱ ታሽጓል። እንኳን ነዋሪውን በቤቱ ጩኸት እንቅልፍ ሊነሳ ይቅርና የሞባይል ስልክ ከያዘ ጀምሮ ያለ ቫይብሬሽን የመጥሪያ ድምፅ መርጦ አያውቅም። ብቻ ተውኝ። ዘንድሮ እኮ ገንዘብ ያለው ተቀናቃኙን ብቻ አይደለም ሕዝቡን ጭምር መንገድ ሊያዘጋበት ይችላል። ለአንዱ ገልቱ ሹም ደህና ገንዘብ ሸጎጥ ከተደረገለት ደግሞ መንገድ አይደለም የምንተነፍሰውን አየር ላቁመው ብሎ ትግል መጀመሩ አይጠረጠርም። ይኸው ነው የዘመናችን ነገር!

ድምፅ ባልሆነባት አገሬ ይኼን ማውራት አይጠቅምም። ገና ለገና ከፊታችን ምርጫ አለ ብለን ተስፋ ብንሰንቅም፣ ተስፋ የሚያስቆርጡ ብዙ ችግሮች አሉብን። እናላችሁ ገና ሳንቀመጥከረሜላተቆርጦ መጣ። እያቅማማን እሱን በዳጣ መጎራረስ ስንጀምር ከሽንጡና ከዳቢቱ የተቀላቀለበት ሥጋ ቀረበ። ሥጋ በሥጋ ላይ ሲደራረብ እኔ ሥጋቴ ባሰ። ሐሜተኛ ሁሉ የቀረበለትን እየጎረሰ ነገ እንደማያሽሟጥጥ ሆኖአጀብ! አጀብ!› ሲል እየገረመኝ፣ የተነቃብኝ ሲመስለኝ ሰላምታ ለማስመሰል አንገቴን ደፋ ቀና አደርጋለሁ። ተበልቶ ሲያልቅ ደግሞ ተራውን ውስኪ በውስኪ ላይ ተነባበረ። እነበልተን እንሙት መብልና መጠጥ ዓይተው እንደማያውቁ ሲያስመስሉ ያቅረኝ ጀመር። የሙዚቃው ጩኸት የጆሮ ታንቡሬን ሊበጥሰው ሲሆን አላስችል ብሎኝ በራስ ምታት አሳብቤ አመስግኜ ልወጣ ስል፣ ነገ እንዳትቀር ሌላ በሬ ይታረዳል ተባልኩ። ምን ፈራህ በሉኝማ? በሌለ አቅማችን በሉ፣ ጠጡ፣ ሞቱም ተብሎ እንዳይጻፍ ነዋ ታሪካችን። ቆይ እስቲ? አንዱን አምሮት ሌላውን አንቆት እንዴት ይሆናል? የሆነስ ሆነና ለመሆኑ ከልብ ነው ከአንጀት የምንተሳሰበው? መተሳሰብን ለዘመናት በሰበክንባት አገር ውስጥ ሆነን በዚህ ዘመን ምን አጨካከነን? ከጭካኔ በስተጀርባ ያሉ ጉድለቶቻችንን እንመልከታቸው። አንዳንዴም ቢሆን ወደ ውስጥ እንመልከት። ጎደሎዎቻችን በምን ይሞሉ እንባባል። መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት