በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በገናሌ ዳዋ ሦስት የኃይል ማመንጫ ግድብ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የገናሌ ዳዋ ስድስት የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታን ለማስጀመር አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሰኞ ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በተከናወነው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ፣ ‹‹አሁን የተገነባውን መመረቅ ብቻ ሳይሆን፣ በገናሌ ዳዋ ስድስት የኃይል ማመንጫ ግድብ እንዴት ጀምረን መጨረስ እንዳለብን የሚለው ትኩረታችን መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡
የገናሌ ዳዋ ስድስት የኃይል ማመንጫን ለመገንባት በርካታ የውጭ ኩባንያዎች ፍላጎት እንዳላቸው፣ ይሁንና መንግሥታቸው ኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶች እንዲሳተፉ እንደሚፈልግ አመልክተዋል፡፡
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የገናሌ ዳዋ ስድስት የኃይል ማመንጫ 246 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይልና እስከ 25,000 ሔክታር መሬት የሚለማ የመስኖ ልማት እንደሚያስገኝ አስታውቀዋል፡፡
ማክሰኞ ዕለት የተመረቀው የገናሌ ዳዋ ሦስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 254 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ሲኖረው፣ ግድቡ 2.57 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የመያዝ አቅም እንዳለው ታውቋል፡፡ ግንባታውም 451 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሲደረግበት፣ ከቻይና ኤግዚም ባንክ ከተገኘ ብድር 60 በመቶ ከመንግሥት ደግሞ 40 በመቶ ተሸፍኗል፡፡ የግንባታው ፕሮጀክት በአራት ዓመታት መጠናቀቅ ቢኖርበትም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ለዘጠኝ ዓመታት ዘግይቷል፡፡ የግንባታ ስምምነት የተፈረመው በ2003 ዓ.ም. ነበር፡፡