Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዘነጋቸው ባለድርሻዎችና ቶኪዮ ኦሊምፒክ የዝግጅት ምዕራፍ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዘነጋቸው ባለድርሻዎችና ቶኪዮ ኦሊምፒክ የዝግጅት ምዕራፍ

ቀን:

በቶኪዮ 2020 አሊምፒክ ላይ ለሚደረገው ዝግጅትና ተሳትፎ በሚመለከት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለፈው ሰኞ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱ ተሰምቷል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከምክክር መድረኩ በመነሳትም የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡

በዝግ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የተሳትፎ ጥያቄዎች ቢነሱበትም፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ይፋ ባደረገው በአቋም መግለጫው የቀረቡት ሐሳቦች መሠረታዊ ሆነው መውጣታቸውን ሪፖርቱ የደረሳቸውና በምክክር መድረኩ የተሳተፉ አባላት ይገልጻሉ፡፡ ሪፖርተርን ጨምሮ የስፖርቱ መገናኛ ብዙኃን የምክክር መድረኩን እንዲዘግቡ ባይፈቀድም መድረኩ ሲጠናቀቅ የወጣው የአቋም መግለጫ ከተቋሙ ድረ ገጽ ተገኝቷል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ‹‹ባለድርሻ አካላት›› ናቸው ከሚላቸው አካላት ጋር በመሆን የቶኪዮ 2020 ዝግጅትን በሚመለከት ስለሚያከናውናቸው ተግባራት በዝርዝር አስታውቋል፡፡ ይሁንና የኦሊምፒክ ዝግጅት በሚመለከት ዋነኛው ባለድርሻ የሚባለው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በመድረኩ አለመሳተፉም ታውቋል፡፡ ዝግጅቱ ለቶኪዮ 2020 የሚያግዙ ግብዓቶችን በመሰብሰብ ካለፉት ኦሊምፒኮች በተሻለ ተዘጋጅቶ ለመቅረብ እስከሆነ ድረስ መድረኩ ለሚዲያ ዝግ የሆነበት ምክንያትም ማነጋገሩ አልቀረም፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ባለድርሻ አካላት ካላቸው ማለትም የስፖርት ኮሚሽን፣ ኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የክልልና ከተማ አስተዳደሮች አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች፣ አንጋፋ አትሌቶችና የሙያ ማኅበራት፣ ከለቦች፣ ማሠልጠኛ ማዕከላት፣ አትሌቶች፣ አሠልጣኞች፣ ማናጀሮችና የማናጀር ወኪሎች እንዲሁም ከልዩ ልዩ ሙያተኞች ጋር በመሆን ውይይት መደረጉን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የመድረኩ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት ባያከራክርም ባልተለመደ መልኩ በዝግጅቱ ላይ መሳተፍ የነበረበት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ኃላፊዎች አለመገኘታቸው ታውቋል፡፡ የተቋሙ ኃላፊዎች ይህንኑ ሲያረጋግጡ ‹‹በመድረኩ እንድንሳተፍ መልዕክት አልደረሰንም›› የሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ስለጉዳዩ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹በደብዳቤ አሳውቀናል›› በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አትሌቲክስ ፈዴሬሽኑን ጨምሮ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች በጋራ የሚወከሉበት ብሔራዊ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ብሔራዊ ተቋም በሕግ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ኢትዮጵያን ጨምሮ አባል አገሮች የሚሳተፉበት የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን ሲያዘጋጅ ግንኙነት የሚፈጥረው ከየአገራቱ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ጋር መሆኑም ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለምን አልተሳተፈም? መድረኩ ስለኦሊምፒክ ከሆነ ጉዳዩ በዋናነት የሚመለከተው ማንን ነው? መድረኩ ለጋራ ጉዳይ እስከሆነ ሁለቱ ተቋማት ተነጋግረው በጋራ ቢያዘጋጁት የሚሉ ከተሳታፊዎች የተደመጡት አስተያየቶች መነሻ ይህ እንደነበርም የሪፖርተር ምንጮች ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው ይህ የውይይት መድረክ ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ፣ በውድድሩ የሚሳተፉ የአትሌቶችና የአሠልጣኞች ምልመላና ምርጫ አቅምንና ችሎታ መሠረት ያደረገ መሆን እንዳለበት ያለመ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡

ኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንዲሁም ሌሎች አገራዊ ውድድሮች ሲኖሩ ከአትሌቶች ምልመላና አሠልጣኞች ምርጫ ጋር ተያይዞ ችግሮች ሲፈጠሩ መመልከት የተለመደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በተለይ በምልመላ፣ በሥልጠናና በአሠራር እንዲሁም አትሌቶች በተፈጥሮ ኃይልና አቅም ብቻ ንፁህ ሆኖ ስለመወዳደር፣ ከግል ፍላጎት ይልቅ የኢትዮጵያን ጥቅም በማስቀደም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተግባብቶና ተቀናጅቶ መሥራት የሚሉ ሐሳቦች በውይይት መድረኩ በስፋት መንፀባረቃቸው ተነግሯል፡፡

መድረኩ ውይይቱን ሲያጠቃልልም ባወጣው የአቋም መግለጫ፣ የአትሌቶችና የአሠልጣኞች ምርጫና ምልመላ በተሻሻለው የፌዴሬሽኑ የውስጥ አሠራር መመሪያ መሠረት ግልጽና ተጠያቂነት ያለው መሆን እንዳለበት፣ ለአትሌቶች ዘመናዊና ሳይንሳዊ ሥልጠና እንዲያገኙ በተለይ አሠልጣኞች ወቅቱ የሚጠይቀው የሥልጠና ዓይነትና ይዘት በዕቅድ ማዘጋጀትና ከቶኪዮ አየር ፀባይ ጋር ሊጣጣም በሚችል መልኩ መሆን እንዳለበት አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በመተባበር የገንዘብና የግብዓት አቅርቦት ወቅቱን ጠብቆ እንዲያቀርብና ለሥራው እንዲውል ማድረግ፣ የፌዴሬሽኑና የባለድርሻ አካላት የሥራ ግንኙነት፣ ስለአበረታች ቅመሞችና ንጥረ ነገሮች በቂ ግንዛቤ ያለው ንፁህ አትሌት እንዲሁም በዓለም አቀፍ፣ አኅጉር አቀፍና አገር አቀፍ የፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲዎች የሕክምና መመሪያ መሠረትም የምርመራ ሒደቱን በአግባቡ የሚያልፍ አትሌት በውድድር ላይ ይዞ መቅረብ ለዚህም ጥብቅ የሆነ የክትትልና የድጋፍ ሰዓት መዘርጋት ሌሎቹ የተነሱት ነጥቦች ናቸው፡፡

የቶኪዮ ኦሊምፒክ ከሐምሌ 17 እስከ ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚከናወን ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...