Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመረጃ ነፃነት ኮሚሽን የሚያቋቁም ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

የመረጃ ነፃነት ኮሚሽን የሚያቋቁም ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

ቀን:

የመረጃ ነፃነት አዋጅ ተፈጻሚነትን ለመከታተል፣ በአዋጁ ላይ የሕዝቡን ዕውቀት ለማዳበር፣ መረጃ በነፃነት ተደራሽ መሆኑን ለማጠናከር የሚሠራና ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነ የመረጃ ነፃነት ኮሚሽን የሚያቋቁም ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ፡፡

የሕግና የፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ምክር ቤት የሚዲያ ጥናት ቡድን ጥር 23 ቀን 2012 ዓ.ም. አዘጋጅቶት በነበረው የግማሽ ቀን ውይይት፣ የመረጃ ነፃነትና የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ አዋጆችን አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡

በመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ከተካተቱ በርካታ ድንጋጌዎች ውስጥ አንዱ፣ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነ የመረጃ ነፃነት ኮሚሽን ማቋቋም መሆኑን ረቂቁ ያስረዳል፡፡ ኮሚሽኑ የሕግ ሰውነት ኖሮት፣ ከማንኛውም የመንግሥት ወይም ሌላ አካል ተፅዕኖ ነፃ የሆነና ራሱን የቻለ መሆን እንዳለበትም ተገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው የሙሉ ጊዜ ሠራተኞች ሲኖሩት፣ የሕዝብ እንደራሴም ሆነ የማንኛውም የመንግሥት አካል አባል መሆን እንደሌለባቸው በረቂቁ ተገልጿል፡፡ የኮሚሽኑ አባላት የሥራ ዘመን አምስት ዓመታት እንደሚሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቋቋመው ገለልተኛ ኮሚቴ ተመልምለው በሕዝብ ድምፅ ከተሰጠባቸው በኋላ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሾሙም በረቂቁ ተመልክቷል፡፡

የመረጃ ነፃነትና መገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 590/2000 ተጠሪነቱ ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መሆኑን ያስታወሱት የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ተወካይ፣  ‹‹ከተጠሪነት አንፃር ‹ኮሚሽንም› ተባለ ‹ተቋም› ልዩነት የለውም፤›› በማለት፣ እንደ አዲስ እንዲቋቋም በረቂቅ አዋጁ ላይ የቀረበው የመረጃ ነፃነት ኮሚሽን ምሥረታ አልተቀበሉትም፡፡

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ከተቋቋመ የ‹‹ስምንት ዓመታት ብቻ›› ዕድሜ ያስቆጠረ ተቋም መሆኑንና ጊዜው አጭር እንደሆነ ጠቁመው፣ ችግሩ የአዋጅ ቁጥር 590/2000 መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹አዋጁ ሥልጣን አልሰጠውም፤›› በማለት፣ ረቂቁን ያዘጋጀው የጥናት ቡድን የጥናት ውስንነት እንዳለው ገልጸው ለተቋማቸው ተከራክረዋል፡፡ ተቋሙ ተጠሪነቱ ለፓርላማ መሆኑን ጠቁመው፣ በተመሠረተበት አጭር ዕድሜ ውስጥ ሪፖርት ሳያቀርብ የቀረበበት ጊዜ እንደሌለና የሚበጀው ማጠናከር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃንና መረጃ ነፃነት አዋጅ ለተቋሙ ተጠሪ ተደርጎ የተሰጠው ግን ለሕዝብ ግንኙነት ክፍል እንደሆነ አስታውሰው፣ አሁን ተጠሪነቱን ለምክትል ዕንባ ጠባቂ በማድረግ ሥልጣን መስጠት በቂ መሆኑን በመግለጽ ኮሚሽን ይቋቋም መባሉን ተቃውመዋል፡፡

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ተወካዩ ላቀረቡት አስተያየት ምላሽ የሰጡት የጥናት ቡድኑ አባል አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ፣ ‹‹የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ስምንት ዓመታት ምን ሲሠራ ነበር? ጋዜጠኞች አቤቱታ ሲያቀርቡ (መረጃ አልሰጥ ያላቸውን የመንግሥት ተቋማት ሲከሱ) ለምን ምላሽ አልሰጣችሁም?›› የሚሉ ጥያቄዎችን ካነሱ በኋላ፣ ተወካዩ ተቋሙን ለመደገፍ ካልሆነ በስተቀር ሁሉንም ነገር የሚያውቁት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅና የኮምፒዩተር ወንጀል ረቂቅ አዋጅ ላይ ጠቅለል ያሉ አስተያየቶች ከታዳሚዎች ተሰጥተዋል፡፡ አንዳንድ አንቀጾች ከጥላቻ ንግግር አዋጅ ጋር ተመሳሳይነት ስላላቸው፣ ከወጡት አዋጆች ጋር ማስተያየት አስፈላጊ መሆኑን፣ ኢንተርኔት ያለ ምንም ማስታወቂያ ሲቋረጥ ተጎጂ ለሚሆን አካል እንዴት ካሳ መጠየቅ እንደሚቻል የሚደነግግ አንቀጽ ቢካተት ጥሩ መሆኑን፣ የሚቋረጥበት (የሚዘጋበት) ምክንያት ከሕግ አንፃር እንዲካተትና ከትርጉም አሰጣጥ አንፃርም ግልጽ ሆነው መተርጎም ያለባቸው ጥቅል ቃላት እንዲተረጎሙ ‹‹ፕሪዘምፕሽን›› የሚለውን ቃል በምሳሌነት በመጥቀስ የተለያዩ አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡ ውይይቱን የሚዲያ ጥናት ቡድኑ አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ጎሹ፣ የቡድኑ አባላት መሰንበት አሰፋ (ዶ/ር) እና አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ መርተውታል፡፡        

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...