Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም በ173 ሚሊዮን ብር የሠራውን የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ አስመረቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አድቫንስድ “4G LTE” ሥራ ላይ ውሏል

ኔትወርኩ ለ5G  ዝግጁ ነው

በለውጥ ሒደት ላይ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም በ173 ሚሊዮን ብር ወጪ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ያከናወነውን የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አስመረቀ፡፡

ሰኞ ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል የኢትዮ ቴሌኮም ማኔጅመንትና የኩባንያው ኮርፖሬት ደንበኞች በተገኙበት በተካሄደው የማስተዋወቂያ ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ ኩባንያው በነደፈው የሦስት ዓመት የንግድ መርሐ ግብር አዳዲስ አገልግሎቶችና ምርቶች ለደንበኞቹ ማቅረብ ተቀዳሚ ተግባሩ እንደሆነ ገልጸው፣ የአዲስ አበባ የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ የዚሁ አካል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በቻይናው ሁዋዌ ኩባንያ በአሥር ቀናት ውስጥ የተከናወነው የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ በአዲስ አበባ በአንዳንድ አካባቢዎች ይሰጥ የነበረውን “4G LTE” (Long Term Evolution) አገልግሎት፣ በመላው አዲስ አበባ እንዲኖር ያስቻለ እንደሆነ ወ/ት ፍሬሕይወት አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ፈጣን የሆነ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጠውን የአድቫንስድ “4G LTE” አገልግሎት በአዲስ አበባ በተመረጡ ከፍተኛ የዳታ አገልግሎት ፍላጎት ባለባቸው 50 ቦታዎች ተግባራዊ እንደተደረገ ተገልጿል፡፡

የኤልቲኢ አድቫንስድ አገልግሎት የተጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሞባይል ኢንተርኔት አጠቃቀም በሚበዛባቸው በአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት፣ ቦሌ ፍሬንድሺፕ፣ ቦሌ መድኃኔዓለም፣ ቦሌ አትላስ፣ መስቀል አደባባይ፣ ስታዲየም፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና መሥሪያ ቤት፣ ካዛንቺስ፣ አራት ኪሎ (አንድነት ፓርክ)፣ ስድስት ኪሎ፣ ልደታ (ኢሲኤክስ)፣ አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ፣ አፍሪካ ኅብረት፣ የዓለም የምግብ ድርጅት መሥሪያ ቤት የሚገኝባቸው አካባቢዎች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

የኤልቲኢ አድቫንስድ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልጉ ደንበኞች ቀፎዎቻቸውንና ሲም ካርዶቸቸውን አገልግሎቱን ለመጠቀም የሚያስችሉ መሆኑን ለማረጋገጥ፣ በአቅራቢያቸው የሚገኙ የሽያጭ ማዕከላትን መጎብኘት ወይም ዝርዝር መረጃዎችን ከድርጅቱ ድረ ገጽ ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

የ“4G LTE” አገልግሎት በመላው አዲስ አበባ ተደራሽ እንዲሆን መደረጉን የገለጹት ወ/ት ፍሬሕይወት፣ በቀጣይ በክልል ከተሞች ያለው የሞባይል ኢንተርኔት (ዳታ) ፍላጎት እየታየ አገልግሎቱ እንደሚቀርብ አስረድተዋል፡፡

የደንበኞች የሞባይል ኢንተርኔት ፍላጎት በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የደንበኞች የሞባይል ኢንተርኔት ፍላጎት በ82 በመቶ፣ ኢትዮ ቴሌኮም የዋጋ ማሻሻያ ካደረገ በኋላ በ169 በመቶ እንዳደገ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ከአንድ ዓመት በፊት ከ25 እስከ 50 በመቶ የዋጋ ማሻሻያ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

‹‹በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣው የደንበኞች ፍላጎት እንቅልፍ እየነሳን ነው፤›› ያሉት ወ/ት ፍሬሕይወት፣ በአዲስ አበባ ያለው የዳታ ፍሰት እየታየ የአድቫንስድ “4G LTE” በተጨማሪ ቦታዎች እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኢንቨስትመንቱ ውድ በመሆኑ በአንድ ጊዜ ሁሉም ቦታ ማድረጉ አዋጪ አይሆንም፤›› ያሉት ወ/ት ፍሬሕይወት፣ የአድቫንስድ “4G LTE” አገልግሎት እጅግ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ የአየር ሰዓት አጠቃቀሙም ከፍተኛ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ሞባይል ኔትወርክ 5G አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡ ‹‹የተወሰነ መሣሪያ ጨምረን አገልግሎቱን ማስጀመር እንችላለን፡፡ ነገር ግን 5G አገልግሎት የሚችል ፍላጎት፣ የኢኮኖሚ አቅም መኖር አለበት፡፡ ያለበለዚያ የተሳሳተ ኢንቨስትመንት ነው፤›› የሚሆነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ 54.4 ሚሊዮን የሞባይል ስልኮች እንደሚገኙ፣ ከእነዚህ ውስጥ 5.5 ሚሊዮኑ ስማርት ስልኮች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ከ54.4 ሚሊዮን ውስጥ አምስት ሚሊዮን ያህሉ “4G LTE” አገልግሎት፣ 1.4 ሚሊዮን ያህሉ የአድቫንስድ “4G LTE” መቀበል የሚችሉ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በብሮድባንድ ኢንተርኔት ላይ የማስፋፊያ ሥራ በማከናወን ላይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ማርኬቲንግ ኦፊሰር አቶ ኤፍሬም አረፈዓይኔ በአዲስ አበባ ሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ለተጠቃሚዎች፣ በተለይም ለድርጅቶችና ለንግድ ተቋማት ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ኢትዮጵያ እየገነባቸው ላለችው የዲጂታል ኢኮኖሚ የበኩሉን ዕገዛ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ ሥራቸው በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ለተመሠረተ ድርጅቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ የሞባይል ስልክ አፕሊኬሽን የሚሠሩ የአይቲ ኩባንያዎች፣ የገንዘብ ተቋማት በቀረበው ፈጣን የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸው፣ አገራዊ ይዘት ያላቸው ጠቃሚ መረጃዎች በማቅረብ ለመረጃ ቅርብ የሆነ ማኅበረሰብ በመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል፡፡

‹‹ኢንተርፕራይዞች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለመጨመር ያስችላቸዋል፡፡ የንግድ ተቋማት በመረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ እንዲያሳልፉ ያስችላቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሞባይል ኔትወርክ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ያጠናቀቀውን ሁዋዌ ኩባንያን ወ/ት ፍሬሕይወት አመሥግነዋል፡፡ የሥራ ውሉ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 4 ቀን 2020 መፈረሙን ጠቁመው፣ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አስፈላጊዎቹን መሣሪያዎች አቅርቦ ሥራውን በተሳካ ሁኔታ እንዳጠናቀቀ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ ከፍተኛ የመደራደር አቅም እየተፈጠረ እንደመጣ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ መሣሪያዎችንና አገልግሎቶችን እስከ 80 በመቶ ቀንሶ መግዛት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

የሁዋዌ የሰሜን አፍሪካ ቀጣና ፕሬዚዳንት ዴቪድ ዛንግ እ.ኤ.አ. በ1987 የተመሠረተው ሁዋዌ ኩባንያ በ170 አገሮች ውስጥ በመሥራት ላይ እንደሆነ፣ ዓመታዊ ገቢው 121 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው በ2005 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መግባቱን የገለጹት ሚስተር ዴቪድ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በጋራ ተባብሮ ሲሠራ መቆየቱንና አስቸጋሪ ወቅቶችን ማለፉን ጠቁመው፣ እ.ኤ.አ. በ2018 በወ/ት ፍሬሕይወት የሚመራ አዲስ ማኔጅመንት ወደ ኃላፊነት ከመጣ በኋላ በድርጅቱ ውስጥ ሥር ነቀል የለውጥ ፕሮግራም በመካሄድ ላይ እንደሆነ፣ በቴክኖሎጂና አገልግሎት ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን አስረድተዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የነደፈውን የሦስት ዓመት የንግድ መርሐ ግብር ሁዋዌ መመልከቱን ገልጸው፣ በቀጣይ ኩባንያው በጋራ ጥቅም ላይ የተመረኮዘ ግንኙነቱን አጠናቅሮ መቀጠል እንደሚፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ሁዋዌ የሞባይል ኔትወርክ ጨረታውን ያሸነፈው ከዜድቲኢ ኤሪክሰንና ኖኪያ ኩባንያዎች ጋር ተወዳድሮ እንደሆነ ወ/ት ፍሬሕይወት ገልጸው፣ ለፕሮጀክቱ ወጪ የተደረገው የውጭ ምንዛሪ በብድር የተገኘ ሳይሆን ራሱ ኢትዮ ቴሌኮም ካመነጨው የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ የተከፈለ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች