Friday, September 30, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የሴራና የሽብር ፖለቲካ የሚቆመው ሕግ በማስከበር ነው!

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኞ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ፣ ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች መሆኗን ገልጸው፣ የሴራና የሽብር ፖለቲካን በማስቆም ኢትዮጵያን ወደፊት እናስቀጥላታለን ብለዋል፡፡ መንግሥት በወሰደው ዕርምጃም አገር ላይ የተደቀነውን አደጋ መቀነስ እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡ እሳቸውንና አስተዳደራቸውን ወደ ሥልጣን ካመጣው ለውጥ በፊት፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር በሁሉም መስኮች የማትቀጥልበት ደረጃ ላይ ደርሳ እንደነበር በማውሳት፣ አገረ መንግሥቱ በግለሰቦች እጅ ወድቆ ነበር ሲሉም አክለዋል፡፡ መደበኛ ያልሆነና በጥቅም፣ በዝምድናና በትውውቅ የተሳሰረ የመንግሥት ጥልፍልፎሽ ነበረ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህም ምክንያት በለውጡ ማግሥት የነበረው የመንግሥት ሥራ አደጋ ውስጥ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለነበሩ አብዛኞቹ ችግሮች ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ምክንያት ነበረ ሲሉም አስረድተዋል፡፡ በሕግ የማይመራ የፖለቲካ ፓርቲና መንግሥት ችግር ከመሆን አልፎ አገር እንደሚያፈራርስ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ጦርነትን መምራትና አገርን መምራት የተሳከረበት ኢሕአዴግ፣ እንኳንስ በአገረ መንግሥት ግንባታ ዋና ተዋናይ ሊሆን ቀርቶ አገርን መቀመቅ የሚከት ተግባር ውስጥ ተጠምዶ መቆየቱ አይካድም፡፡ ሕግ ማክበርና ማስከበር ተግባሩም ስላልነበረ ሕዝብ በፍትሕ ዕጦት ተሰቃይቷል፡፡ ለመግለጽ የሚያስቸግር አፈና በመስፈኑም ከባድ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ለለውጡ መጀመር ምክንያት ሆኗል፡፡ ለውጡ የገጠመው ፈተናም ካለፈው የቀጠለ በሽታ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይህ በሽታ ደግሞ ከሕግ የበላይነት ጋር መጣላት ነው፡፡

  የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር የገጠመው ፈተና ፈርጀ ብዙ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም፣ ከቀድሞው አስተዳደር የተወረሱ በርካታ ስንክሳሮች ቢገጥሙትምና በለውጡ ምክንያት ሥልጣናቸውን ያጡ፣ እንዲሁም በተገኘው አጋጣሚ በአቋራጭ ሥልጣን ለመቆጣጠር ያሰፈሰፉ ኃይሎች ቢኖሩም፣ ሕግና ሥርዓት ካልተከበረ ሴራና ሽብር ይቆማሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ በየቦታው የሚለኮሱ ግጭቶች ከብሔርና ከተጠቃሚነት ፍላጎቶች በማለፍ ሃይማኖቶች ውስጥ ጭምር እየዘለቁ ያሉት፣ ሕግ ለማስከበር የሚታየው ዳተኝነት በመብዛቱ እንደሆነ መተማመን ይገባል፡፡ እርግጥ ነው ሕግ በማስከበር ስም አፈና እንዳይፈጸም፣ የሐሳብና የንግግር ነፃነት እንዳይታፈን፣ የሰዎች የመሥራትና የመዘዋወር መብት አደጋ እንዳያጋጥመውና በአጠቃላይ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መሰናክል እንዳይፈጠርባቸው መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ለዚህ ዓይነቱ ጥንቅቄ ደንታ የሌላቸው፣ ከአገር ህልውና በላይ ቡድናዊ ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ፣ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት እየተፈታተኑ ቀውስ የሚፈጥሩ ኃይሎችን በሕግ ማለት ይገባል፡፡ ሕግ ማስከበር ደግሞ የመንግሥት አንደኛው ኃላፊነት ሲሆን፣ የሚመለከታቸው አካላትም ተሳትፎ ሊታከልበት የግድ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ኃላፊነትን መወጣት እየተቻለ ሕግ ማስከበር ችላ ማለት ወይም ደንታ ቢስ መሆን፣ አገርን ከማዳከም አልፎ መፈረካከስ ሊያስከትል ይችላል፡፡

  ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር ሆና ፀንታ መቆም የምትችለው ማንኛውም ሰው ከሕግ በታች ሲሆን ነው፡፡ ይህንን ማድረግ አለመቻል ግን አደገኛ የሆነ ቀውስ ውስጥ ይከታል፡፡ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ እየታዩ ያሉ ግጭቶች፣ የቤተ እምነቶች ቃጠሎ፣ የንፁኃን መገደልና መፈናቀል፣ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚታየው ሁከትና ግድያ፣ እንዲሁም አፈናና ዕገታ፣ ከ35 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ግጭት በመሸሽ ትምህርት ማቆማቸው፣ በየቦታው መንገድ በመዝጋት የሰዎችንና የምርቶችን እንቅስቃሴ ማወክ፣ በአጠቃላይ አገርን ቀውስ ውስጥ የሚከቱ ቅስቀሳዎች መበራከትና የመሳሰሉት በሕግ ማስከበር ማቆም ካልተቻለ ፈተናው እየተጠናከረ ነው የሚሄደው፡፡ ጠንካራ ተቋማትና አስፈጻሚዎች ማግኝት ብርቅ በሆነበት አገር ውስጥ አጉራ ዘለሎች እንዳሻቸው የሚፈነጩበት ዕድል ከተስፋፋ፣ እንኳንስ ምርጫ ማከናወንና በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት መመሥረት ቀርቶ የአገር ህልውናም ያጠራጥራል፡፡ የአገሪቱን ህልውና እየተገዳደሩ ካሉ ኃይሎች በተጨማሪ ከውጭ ሆነው አደጋ የደቀኑም አሉ፡፡ አልሸባብን የመሰለ ለምንም ነገር የማይመለስ ሽብርተኛ ኃይል በቅርብ ርቀት እያለ፣ በዓባይ ውኃ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብትን የሚጋፋ ጠላትነት ተጋርጦና የውስጥ ክፍፍሉ ሰፊና ጥልቅ እየሆነ ቸልታ ማብዛት አደጋው የከፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሥርዓት መኖር የምትችለው፣ መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት ሲችል ብቻ ነው፡፡

  ሌላው ችግር በአንድ አገር ውስጥ ትጥቅ መያዝ የሚችለው ማን ነው የሚለው ጥያቄ መልስ አለማግኘቱ ነው፡፡ በአንድ አገር ሁለት ኃይል መታጠቅ እንደማይችል ግልጽ ቢሆንም፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አገር ውስጥ የገባ ኃይል መሣሪያ ይዞ እየተዋጋ ነው ሲባል ከማስገረም አልፎ ያሳፍራል፡፡ ችግርን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ትዕግሥትና ሆደ ሰፊነት ቢጠይቅም፣ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ትጥቅ ይዞ የሚዋጋ ኃይል መኖር አልነበረበትም፡፡ በአንድ አገር ሁለት መንግሥት ስለማይኖር ሕጋዊው መንግሥት ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰዳል ተብሏል፡፡ ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል በወለጋ ዞኖች ውስጥ ሕዝብ ፍዳውን እያየ ስለሆነ፣ ሕጋዊው መንግሥት ሕገወጡን በፍጥነት በሕግ አደብ ማስገዛት አለበት፡፡ ከተቻለ ሰላማዊ መንገድ ተመርጦ ሕዝቡንና የአገር ሽማግሌዎችን በማሳተፍ መፍትሔ መፈለግ፣ ካልተቻለ ደግሞ የተሻለ ኃይል ያለው መንግሥት የሕዝቡን ሰላም ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ትጥቅ አንግቦ ጫካ የገባው ኃይል ፍላጎቱ ምን እንደሆነ ሲታወቅ ነው ‹ወንድም ወንድሙን መግደል የለበትም› የሚባለው፡፡ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ተቃውሶ አገር መምራት ስለማይቻል፣ የጠቅላይ ማኒስትሩ መንግሥት ኃላፊነቱን በብቃት ይወጣ፡፡ የአገሪቱ ሰላም ተቃውሶ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አይታሰብም፣ የሕዝብ ጎስቋላ ኑሮ አይለወጥም፡፡ ስለዚህ ሕግ ይከበር፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ከ25 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አሁንም ከድህነት ወለል በታች ነው፡፡ ከ17 ሚሊዮን የማያንሱ ወጣቶች ሥራ አጥ ናቸው፡፡ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ብዙ ቢወራለትም ብዙኃኑ ሕዝብ በድህነት ውስጥ እየማቀቀ ነው፡፡ አገሪቱን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ የነበረው ኃይል ከአገር ይልቅ ቡድናዊና ግላዊ ጥቅም ለማስከበር፣ ለረዥም ዓመታት ሥልጣን ላይ ሙጭጭ ብሎ ለመቆየት ሲተጋ ነበር፡፡ ለዚህ እኩይ ዓላማው ሲልም የሥልጣን ተቀናቃኞችን ተራ በተራ ማስወገድ፣ ማሰር፣ ማፈን፣ ማሳደድና ማሰቃየት የተለመደ ተግባሩ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አገሪቱ ከባድ ነውጥ ውስጥ የገባችውም በሥልጣን ጥመኝነትና ራዕይ አልባነት ሳቢያ እንደነበር መካድ አይቻልም፡፡ ለመካድ የሚሞክሩ ካሉ ካረጀና ካፈጀ አስተሳሰብ መላቀቅ የማይችሉ ብቻ ናቸው፡፡ ዴሞክራሲን ለስማቸው መጠሪያ ቢጠቀሙበትም፣ መርህና መመርያ ማድረግ ባለመቻላቸው ብቻ ኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ዘረፋ፣ ተጠያቂነት የሌለበት ብልሹ አሠራር፣ አፋኝነትና አገር አጥፊነት ተጠናውቷት ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ብቃት የሌላቸው ተሿሚዎች በመብዛታቸው፣ የመንግሥትና የፓርቲ ሥራ በመደበላለቁ አሉ ይባሉ የነበሩ ጥቂት ተቋማት ሳይቀሩ ፍርክስክሳቸው ወጥቷል፡፡ የትምህርት ጥራት በማሽቆልቆሉ ተምረዋል የሚባሉ ማይሞች በዝተዋል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሞራልና የሥነ ምግባር ልሸቀት አጋጥሟል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ኃላፊነት የጎደለው ሥርዓት እንዲመለስ የሚፈልጉ መኖራቸው ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሥርዓት ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱ ብቻ ሳይሆኑ፣ በጉልበት ጭምር የሚዋደቁ እየታዩ ነው፡፡ እነሱም ያንን የመከራና የጨለማ ጊዜ ለመመለስና ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ዕልቂት ለማምጣት አስፈሪ ቅስቀሳ ጀምረዋል፡፡ የሕዝብን ተስፋ የሚያጨልም መንገድ የመረጡ ኃይሎች በሕግ አደብ ይግዙ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥትም ለዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ይስጥ፡፡ የሴራና የሽብር ፖለቲካ አደብ የሚገዛው ሕግ በማስከበር ብቻ ነው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በቤንዚንና ነጭ ናፍጣ ላይ ጭማሪ ተደረገ

  ከዛሬ መስከረም 18 ቀን 2015 ዓም እኩለ ሌሊት ጀምሮ...

  የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት ለመፍታት በሚያስችል የአሠራር ማዕቀፍ ላይ መወያየታቸውን የኬንያው ፕሬዚዳንት ተናገሩ

  በቅርቡ የኬንያ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዊሊያም ሩቶ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ...

  ኦፌኮ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ስምንት አመራሮች እንደታሰሩበት አስታወቀ

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለክልሉ ደብዳቤ ጽፏል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ...

  የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ሕገወጥ ገንዘብ አስተላላፊዎችን አስጠነቀቀ

  የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በሕገወጥ የገንዘብ ማስተላለፍ ድርጊት ተሰማርተዋል ያላቸው...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች