በቫትና በገቢ ግብር ላይም አዲስ ማሻሻያ ለማድረግ አቅዷል
መንግሥት በውርስና በስጦታ በሚገኝ ሀብት ላይ ግብር በመጣል የግብር መሠረቱንና ገቢውን ለማሳደግ ማቀዱን፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ግምገማን አስመልክቶ ያወጣው ሪፖርት አመለከተ፡፡
የገንዘብ ተቋሙ ‹‹አርቲክል ፎር›› ተብሎ በሚታወቀው ዓመታዊ የኢኮኖሚ ግምገማ መሠረት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያደረገውን ግመገማ ሪፖርት ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በዚህ ሪፖርትም የኢትዮጰያ መንግሥት የአገር ውስጥ የታክስ ገቢን ለማሳደግ በውጥን የያዛቸው ፕሮግራሞች ተካተው ቀርበዋል፡፡
በዚህም መሠረት መንግሥት የታክስ ገቢውን ለማሳደግ ካቀዳቸው ፕሮግራሞች መካካል፣ የገቢ ግብርና ታክስ አዋጆቹን እስከ 2013 ዓም ድረስ በማሻሻል ተጨማሪ ገቢ ማግኘትና የታክስ ማነቆዎችንም በዚሁ አጋጣሚ ለመቅረፍ ዕቅድ አለው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የታክስ መሠረቱን ለማስፋት አዳዲስ የታክስ ዓይነቶችን ለመጣል ማቀዱን፣ የአይኤምኤፍ ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራሞች መረዳታቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
መንግሥት በዕቅድ ይዟቸዋል ተብለው በሪፖርቱ ከተጠቀሱት የታክስ ዓይነቶች አንዱ፣ ከውርስ በሚገኝ ሀብት ላይ ታክስ መጣል ይገኝበታል የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሪፖርቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር መረጃ አላቀረበም፡፡ ከውርስ በሚገኝ ሀብት ላይ ታክስ የጣሉ በርካታ የዓለም አገሮች መኖራቸውን መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካካል አሜሪካ በበርካታ ግዛቶቿ ይህንን የታክስ ዓይነት በመጣልና ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ልምድ በማካበት ትታወቃለች፡፡
በውርስ ሀብት ላይ የሚጣል ታክስ ተገቢ አይደለም የሚል ክርክር የሚያነሱ ባለሙያዎች ሲኖሩ፣ ይህንን ታክስ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ በኋላም ያስቀሩ አገሮች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ካናዳና አውስትራሊያ ይጠቀሳሉ፡፡
በውርስ በሚገኝ ሀብት ላይ ለመጣል ከታሰበው ታክስ በተጨማሪ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጁን በማሻሻል በቀጣዩ ዓመት ተግባራዊ ለማድረግ መንግሥት ማቀዱን የአይኤምኤፍ ሪፖርት ጠቁሞ፣ በዚህ ማሻሻያ ከቫት ነፃ እንዲሆኑ የተደረጉ ምርቶች ላይ ቫት እንዲጣል መታቀዱን አመልክቷል፡፡
በቫት ላይ በሚደረገው ማሻሻያም መንግሥት እስከ 30 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ማቀዱን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ በገቢ ግብር ላይም ተመሳሳይ ማሻሻያ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን፣ በዚህ ማሻሻያም በዋናነት ታክሱ የሚጣልበት ዝቀተኛ መነሻ ገቢን ከፍ ለማድረግ መታቀዱ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡