Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንብ ባንክ በሆሳዕና ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ ያወጣበትን ሕንፃ ሥራ አስጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የሀብትና የቋሚ ንብረት አቅሙን ለማሳደግ በያዘው ዕቅድ መነሻነት በአዲስ አበባ ከተማና በክልሎች ሕንፃዎችን እያስገነባ ይገኛል፡፡ የሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ ከሚጠይቁት ሕንፃዎች መካከል በሆሳዕና ያስገነባውን ሕንፃም ከሰሞኑ አስመርቋል፡፡ በግማሽ ዓመቱ እንቅስቃሴው ከ61 በመቶ በላይ ብልጫ የተመዘገበበት ትርፍ ማግኘቱንም አስታውቋል፡፡

ቅዳሜ ጥር 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው የሕንፃ ምረቃ ፕሮግራሙ ላይ እንዳስታወቀው፣ በሆሳዕና የተገነባው ሕንፃ አምስት ወለሎች ያሉትና ከ55.8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የጠየቀ ነው፡፡  ሕንፃው በ432 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ነው፡፡ የሕንፃው ክፍሎች ከቅርንጫፍ ባንክ አገልግሎት በተጨማሪ ለተለያዩ ሱቆች፣ ለካፍቴሪያና ለእንግዳ ማረፊያ አገልግሎት እንዲውሉ ታስበው የተዘጋጁ ናቸው፡፡ የስብሰባ አዳራሽም አካቷል፡፡ በሆሳዕና አካባቢ የሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፎች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የሆነው የሆሳዕና ዲስትሪክት ቢሮም በአዲስ በተገነባው የባንኩ ሕንፃ ሥራ ጀምሯል፡፡

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ገነነ ሩጋ በሕንፃው ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፣ ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት ጎን ለጎን በቋሚ ንብረቶች ላይ ተጓዳኝ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ግንባታቸው እየተከናወኑ ከሚገኙ የባንኩ የሕንፃ ፕሮጀክቶች ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ከስድስቱ ፕሮጀክቶች እስካሁን የዱከም፣ የወልቂጤና የሆሳዕና ሕንፃዎች ሥራ የጀመሩ ሲሆን፣ ሌሎች ሦስት ሕንፃዎችን የማስገንባት ሥራ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ግንባታቸው እየተካሄዱ ያሉት ሦስቱ ግንባታዎች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ሲሆን፣ በተለይ በአዲስ አበባ ባንኩ ሁለት ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክቶች አሉት፡፡ ‹‹ሰንጋ ተራ›› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ከ1.7 ቢሊዮን ብር ወጪ ይጠይቃል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፣ የማጠቃለያ ሥራ ላይ ይገኛል፡፡ በ3,682 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ይህ ሕንፃ በአጠቃላይ 37 ወለል ያለው ነው፡፡ ግንባታውን የቻይናው ጃንግሱ ኢንተርናሽናል ኢኮኖሚና ቴክኒካል ኮርፖሬሽን ግሩፕ እያካሄደው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ገነነ ለሪፖተር እንደገለጹት፣ ይህ ሕንፃ በቀጣይ ዓመት መጀመርያ ላይ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሌላው ከባንኩ የሕንፃ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ የሚጠቀሰውና በአራት ኪሎ በጨረታ የተገዛው ጅምር ሕንፃ የማጠናቀቂያ ሥራ ነው፡፡ ይህን ባለ ስምንት ወለል ሕንፃ በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ይህም ሕንፃው በጨረታ የተገዛበትን ዋጋ ጨምሮ በጥቅሉ ከ870 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚጠይቅ ታውቋል፡፡ ግንባታው ከአንድ ወር በኋላ እንደሚያልቅ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ ሕንፃ ውስጥ ባንኩ ልዩ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥበት ቅርንጫፍ ይከፍታል ተብሏል፡፡   

አሁኑ ወቅት ባንኩ በሐዋሳ ከተማ ፒያሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለከተማዋ ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታና ድምቀት ይሰጣል ተብሎ የታመነበት ባለ አሥርና ባለ 12 ወለል መንትያ ሕንፃዎችን ከ305 ሚሊዮን ብር በላይ እየገነባ ሲሆን፣ ባለ ሁለት ቤዝመንቱ ሕንፃ በ1,980 ካሬ ሜትር  ቦታ ላይ ያረፈ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከዚህም ሌላ ባንኩ እሴት ማሳደግን ተቀዳሚ ግቡ በማድረግ በአዲስ አባባ ከተማና በክልል ከተሞች ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ቤቶችን በግዥ የባንኩ ንብረት ማድረግ ስለመቻሉ ተጠቅሷል፡፡ ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ፣ ላፍቶ፣ ሃያ ሁለት፣ ልደታና የካ አባዶ አካባቢዎች የሚገኙት በከፊል የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ውጭ በጅግጅጋና በመተማ ዮሐንስ በተመሳሳይ የራሱ ሕንፃ ባለቤት የሆነበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡

የባንኩን ወቅታዊ አቋም የሚያመለክቱ አኃዛዊ መረጃዎችን በተመለከተ እንደተጠቀሰው፣ ጠቅላላ የባንኩ ሀብት መጠን 40 ቢሊዮን ብር፣ ተቀማጭ ገንዘብ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ፣ የብድር መጠኑም ከ23.3 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን አቶ ገነነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት በተሻለ ሁኔታ ውጤት እያመጣ ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡ በግማሽ የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙ ግብርና ሌሎች ተቀናሾች ታሳቢ ሳይደረጉ 750.2 ሚሊዮን ብር ማትረፉ መቻሉንም ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ ይህም በ2011 ዓ.ም. ከነበረው የግማሽ ዓመት የትርፍ መጠን ጋር ሲነፃፀር የ61 በመቶ ዕድገት እንዳለው ያሳያል ተብሏል፡፡

ባንኩ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ጥቅም ላይ በማዋል ደንበኛ ተኮር አሠራርን እየተከተለ መሆኑን የሚገልጸው የባንኩ መረጃ፣ እስከ 2012 የሒሳብ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ የባንኩ ኤቲኤም ማሽኖች 170 መድረሱንና ከ350 በላይ የፖስ ማሽኖች፣ የቪዛና ማስተር ካርድና የቻይና ዩኒየን ካርድ ለያዙ ተጠቃሚዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡

በዚህም የኤቲኤም ካርድ ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛት እስከ 2012 የሒሳብ ዓመት አጋማሽ ድረስ 263,845 ደርሷል፡፡ እስከ ሒሳብ ዓመቱ አጋማሽ ድረስም የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚ ደንበኞቻችን ቁጥር 75,255፣ የኢንተርኔት ደንበኞቻችን ብዛት ደግሞ 1,182 ማድረስ መቻሉንም አስታውቋል፡፡

ባንኩ የአስቀማጭ ደንበኞችን ቁጥር 1.1 ሚሊዮን አድርሷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተወሰኑ ቅርንጫፎች ብቻ አገልግሎት ሲሰጥበት የነበረው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በሁሉም ቅርንጫፎች የሸሪዓ ሕግን በሚከተል አሠራር ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ ተደግፎ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉን ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር ያሳደገ ሲሆን፣ ከ4,600 በላይ ባለአክሲዮኖች፣ ከ5,375 በላይ ቋሚ ሠራተኞችና ከ280 በላይ ቅርንጫፎች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች