Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሴቶች የመሬት ባለቤትነት መብት በሕግ የተቀመጠውና የሚተገበረው አልተገናኙም 

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማኅበራዊ ጥናት መድረክ በመሬት ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ተከታታይ መርሐ ግብሮች እያካሄደባቸው ከሚገኙት የመወያያ ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ የሴቶች የመሬት ባለቤትነት መብት ሲሆን፣ ሴቶች ከወንዶች እኩል የመሬት ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጥላቸው የሕግ ሥርዓት እየተተገበረ ቢሆንም በአፈጻጸሙ ብቻም ሳይሆን በባህልና በልማድ ተፅዕኖ ሳቢያ በርካታ ክፍተቶች እንደሚታዩበት ተመልክቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ጥናታዊ የውይይት መድረክ ላይ ‹‹የሴቶች የመሬት ይዞታ መብትና አጠቃቀም ሁኔታ›› በሚል ርዕስ ወ/ት መሳይ ያሬድ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ የልማት ፕሮጀክቶች ትግበራ ባለሙያዋ፣ በሴቶች ሥነ ፆታና አካባቢ ጉዳዮች ላይም ተመራማሪዋ ባቀረቡት ጽሑፍ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የመሬት ይዞታና የባለቤትነት መብት ማረጋገጫ ሥርዓት እየተተገበረ እንደሚገኝ አውስተዋል፡፡

በዚህም አምስት ሚሊዮን የገጠር ቤተሰቦች በባለይዞታነት ተመዝግበዋል፡፡ ይሁን እንጂ በመሬት ይዞታ ማረጋገጥና በሰነድ አሰጣጥ ላይ የሴቶች ሚና ተገድቦ መቆየቱን የገለጹት ወ/ት መሳይ፣ አንዳንዶቹ ክልሎች ሴቶችና ወንዶችን በተናጠል በመመዝገብ የማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሲሰጡ፣ ሌሎች ክልሎች በወል የማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ምዝገባ ሲሰጡ እንደቆዩ ገልጸዋል፡፡

በ1997 ዓ.ም. የወጣው የመሬት ፖሊሲ ሴቶችም የገጠር መሬትን በይዞታ ባለቤትነት የመጠቀም መብት እንዳላቸው መደንገጉን አስረግጠው የሞገቱት ወ/ት መሳይ፣ በተለይም የግብርና ሥራዎችን ከማካሄድ ጀምሮ ያሉ የገጠር ልማት እንቅስቃሴዎችን የማከናወን መብት እንደሚሰጣቸውም ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጥናት አቅራቢዋ ባስቀመጡት የፖሊሲው ይዘት ላይ በፆታ ለይቶ የወንድና የሴት መብቶችን እንዳላስቀመጠ ከተሳታፊ ማስተካከያ ቀርቦባቸው ተቀብለዋል፡፡ ይህም ሆኖ የመሬት ፖሊሲው ሴቶችን በውሳኔ ሰጪነት ከማሳተፍ እንዳጎደላቸው፣ በኮሚቴ በሚሠሩ ሥራዎችና ውሳኔዎች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ወደ ጎን መደረጉን አቅራቢዋ አውስተዋል፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ባለው መረጃ መሠረት 11 ሚሊዮን ወይም 77 በመቶ የመሬት ይዞታዎች የሴቶችን የመሬት የይዞታ ባለቤትነትና ተጠቃሚነት መብት በወል እንዲሁም በተናጠል ማረጋገጣቸው ትልቅ ዕርምጃና ለውጥ እንደሆነ ጽሑፍ አቅራቢዋና ሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎች አብራርተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት በስፋት እንደተመደጠው የሕግ ተርጓሚዎችና አስከባሪዎች፣ ብሎም በልማድ ሴቶች በወንዶች ጥገኛ ተደርገው የመታየታቸው ተፅዕኖና ሴቶችም መብታቸውን ለማስከበርና የሚደርስባቸውን ጫና ለመጋፈጥ የሚያድርባቸው የመገለል ሥጋትና ፍራቻ እንደሚያድርባቸው ተብራርቷል፡፡ በመሬትና በንብረት ጉዳይ ላይ አሁንም ለወንዶች የበላይነት ያደላ አስተሳሰብ በሰፊው እንደሚንጸባረቅ፣ በገጠሩ ክፍል ይህ በሰፊው እንደሚታይ ወ/ት መሳይ አመላክተዋል፡፡ 

ማኅበራዊ ጥናት መድረክ (ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ) ካለፈው ታኅሳስ አጋማሽ ጀምሮ በመሬት ጉዳዮች ላይ በአገር አቀፍና በክልሎች ደረጃ የመሬትና የምግብ ዋስትና ላይ ያተኮሩ ርዕሶችን በማዘጋጀት እስከ መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የሚዘልቁ የውይይት መድረኮችን ዘርግቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች