ከ1,000 በላይ የብቃት ማረጋገጫ መደቦች ታጥፈዋል
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የማሻሻያ ዕርምጃዎችን ማካሄድ ላይ ሲሆን፣ በተለይ በንግድ ፈቃድና ምዝገባ ሒደት ላይ ካደረገው መሠረታዊ ማሻሻያ በተጨማሪ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት የሚጠየቁ የብቃት ማረጋገጫ መደቦች ላይ ሰፊ ለውጥ መተግበር ጀምሯል፡፡
ከታኅሳስ ወር መጨረሻ ጀምሮ እንዲተገበር የተወሰነውና ብቃት የሚጠየቅባቸውን የንግድ ሥራ ፈቃድ መስጫ መደቦች ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜ ያህል አሻሽሎ የነበረውን አሁን ወደ 52 ዝቅ አድርጓቸዋል፡፡ ዓምና በተደረገው ማሻሻያ መሠረት 303 የንግድ ሥራ መደቦች ላይ ይጠየቅ የነበረውን የብቃት ማረጋገጫ ሥነ ሥርዓት አዲሱ መመርያ አስቀርቶቷል፡፡
የንግድ ምግዘባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሪፎርም ለማካሄድ የሚደረገውን እንቅስቃሴ መነሻ ያደረገውና እንዲተገበር ለንግድና ኢንዱስትሪ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በሰርኩላር የተላለፈው ውሳኔ፣ ከታኅሳስ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ እንዲተገበር አስታውቋል፡፡
በመሆኑም በ20 የብቃት አረጋጋጭ ተቋማት አማካይነት በ52 የንግድ ሥራ ፈቃድ መደቦች ላይ ብቻ የብቃት ማረጋገጫ ሠርቲፊኬት የሚጠየቅባቸው መደቦች ዋና ዋና ተብለው የተመዘገቡ ሲሆኑ፣ ከቡናና ሻይ ልማት ጀምሮ፣ በሚዲያ መዝናኛ መስክ፣ በተንቀሳቃሽ ፊልም ሲኒማና ቪዲዮ ሥራ ቀረፃና ሥርጭት እንዲሁም በስፖርት፣ በስፖርት መዝናኛ፣ በሰርከስ ማሠልጠኛና በመሳሰሉት ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች የብቃት ማረጋገጫ የማቅረብ ግዴታ ይጣልባቸዋል፡፡
በተጨማሪም በማማከር ሥራ፣ በላኪነትና አስመጪነት መስክ መሠረታዊ በሚባሉ፣ በፋብሪካ፣ በምርት ጅምላ ንግድና አገልግሎት መስክ የሚሰማሩ አካላትም የብቃት ደረጃቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ በተለይም የቴክኒክና ሳይንሳዊ ክህሎትን በሚጠይቁ መስኮች ላይ ያነጣጠሩ መደቦች ላይ ብቃትን ማረጋገጥ እንደሚጠይቅ ተቀምጧል፡፡ በአንፃሩ በችርቻሮ ንግድ ሥራ መስክና አነስተኛና መካከለኛ ሥራዎች ላይ የሚሰማሩ ከዚህ ቀደም ከነበሩት መደቦች ውጭ ተደርገዋል፡፡
የብቃት ማረጋገጫው በከፍተኛ ደረጃ ወደ 52 መደቦች ብቻ ዝቅ መደረጉ ብቻም ሳይሆን፣ ወደፊት የሚተገበረው በኦንላይን የንግድ ምዝገባ የፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት ትግበራ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት የሚፈጀውን ጊዜ በእጅጉ እንደሚያሳጥረው ይጠበቃል፡፡
ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቀላጠፈና ተደራሽ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ አገልግሎት ለማቅረብ ስለተነሳበት ጉዳይ ባብራራበት ሰርኩላር፣ ኢትዮጵያ በዓለም ባንክ የንግድ ምቹነት መመዘኛ መሠረት፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ደረጃ ከ190 አገሮች የንግድ ሥራ ለመጀመር በሚጠይቀው ሒደት በ167ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን በማውሳት፣ ይህንን የማሻሻል አንዱ ዕርምጃ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት የሚጠየቁ የብቃት መስጫ መደቦችን ማስተካከል አስፈልጓል፡፡ በንግድ ሥራ ምቹነት የዓለም ባንክ ከዓመት በፊት ያወጣው የአገሮች ዝርዝር ውስጥ የኢትዮጵያ ደረጃ 159ኛ ሲሆን፣ በቅርቡ ወደ 161ኛ ደረጃ የተንሻራተተችበት ሪፖርት መውጣቱም የሚታወስ ነው፡፡
በዚህ ያልተገበደው ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ንግድ ሥራ ለማስጀመር በአማካይ ይወስድ የነበረውን የ32 ቀናት የቆይታና የምልልስ ጊዜን ወደ አራት ቀናት ለማውረድ ብሎም ወጪና እንግልትን በከፍተኛ ደረጃ ለመነቀስ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኩል በሚመራው የንግድ ሥራ ከባቢና ቅልጥፍናን የማሻሻል (ኤዝ ኦፍ ዱዊንግ ቢዝነስ) ፕሮግራም፣ ኢትዮጵያን ከመጀመሪያዎቹ 100 አገሮች ተርታ የማሠለፍ ዕቅድ ይፋ ካደረገ ሰነባብቷል፡፡ በእ.ኤ.አ. በ2021 ይህንኑ ዕቅድ የማሳካት ትልም አስቀምጧል፡፡
የዓለም ባንክ አገሮችን የሚመዝንበት የንግድ ከባቢ ሁኔታ ምቹነት መመዘኛ ሪፖርት አሥር ዋና ዋና ጠቋሚ መሥፈርቶች አሉት፡፡ ከአሥሩ መካከል የመጀመሪያው መሥፈርት ንግድ ለመጀመር የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ምቹነት ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ መስክ ንግድ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም በአስገዳጅነት ያስቀመጣቸውን የኩባንያ ስምን በጋዜጣ የማሳወጅ፣ የሊዝ ወይም የኪራይ ውል ስምምነትን በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ በኩል አረጋግጦ የማቅረብ ግዴታን አስቀርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን የሶፍትዌር ቅያሬን የሚፈቅድ የሕግ ማዕቀፍም ተዘጋጅቶ ጥያቄው በቀረበ ጊዜ የሚስናገድበት ሥርዓት ተበጅቷል፡፡
በብድር አቅርቦትና ተደራሽነት መስክም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአሁኑ ወቅት አነስተኛ የገንዘብ አቅራቢ ድርጅቶችና የሊዝ ፋይናንስ ሰጪዎችን በብድር ምዝገባ ሥርዓቱ እንዲካተቱ የሚፈቅድ መመርያ ከማውጣቱም ባሻገር፣ ስለ ብድር አቅርቦት መረጃው ያላቸው በዕድሜ አዋቂ ተርታ የሚመደቡትን ዜጎች ቁጥር አሁን ካለው የ0.4 በመቶ መጠን ወደ አምስት በመቶ ወይም ወደ 5.5 ሚሊዮን ማድረስ በማሻሻያ ፕሮግራሙ የተቀመጠው ግብ ነው፡፡
እንዲህ ያሉትን ጨምሮ በድንበር ዘለል ንግድና በታክስ ክፍያ ሥርዓት የኤሌክትሮኒክ ታክስ መክፈያ ዘዴዎችን የማስተግበር ጅምሮች እንደሚስፋፉ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም 2800 ከፍተኛ ግብር ከፋዮች እንዲሁም በመካከለኛ ግብር ከፋይነት ከተመደቡት ውስጥ 25 በመቶው በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የሚስተናገዱበት ሥርዓት እየተዘረጋ ይገኛል፡፡
በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ሒደትም በኦንላይን እንዲሆን የሙከራ ሥራ መጀመሩ ተጠቅሷል፡፡ የውኃ መስመር ለማገናኘት የሦስት ቀናት ሒደት ሲቀመጥ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ዝርጋታዎችን በ12 ቀናት ውስጥ መጠናቀቅ የሚችሉበት ሥርዓት እንዲመሠረት የተመቀጠው የአጭር ጊዜ የሪፎርም አጀንዳ ነው፡፡ የግንባታ ፕላን ገምግሞ ለማፀደቅ ከዚህ ቀደም ይጠይቅ የነበረውን የ21 ቀናት ቆይታ አሁን ወደ 13 ቀናት ዝቅ የማድረግ፣ የመሬት ካርታ ባለቤትነትን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለማዛወር የሚሠሩ ሥራዎች እየተገባደዱ ይገኛሉ፡፡ ከታክስ ዕዳ ነፃ የማረጋገጨ ሠርቲፈኬት ለማግኘት የሚፈልግ ባለንብረት በአንድ ቀን ውስጥ ጥያቄው እንዲስተናገድ የሚያደረግበት ዕቅድም ተቀምጧል፡፡
እነዚህን ጨምሮ የውል ስምምነትን የማስከበርና ሕጋዊነትን የማስፈን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና መሰል አገልግሎቶችን በአጭር፣ በመካከለኛ በረዥም ጊዜ ውስጥ በማሻሻል አብዛኞቹ የትግበራ ውጤቶችም ከዚህ ዓመት ጀምሮ መታየት እንደሚጀምሩ፣ በመጪው ዓመትም ሙሉ በሙሉ ትግበራቸው ተጀምሮ የአገሪቱን የዓለም ባንክ ደረጃ ወደ 100 አገሮች ተርታ ለማስቀመጥ እየተሠራ እንደሚገኝ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡