በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ከ1940ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ለአራት አሠርታት በመድረክና በቴሌቪዥን ትወና ሲተውኑ ኖረዋል፡፡ ጀምበሬ በላይ የአዛውንቶች ክበብ፣ ኦቴሎ፣ ሐምሌት፣ ዋናው ተቆጣጣሪ፣ የድል አጥቢያ አርበኛ፣ የከተማው ባላገር፣ ሥነ ስቅለት፣ የፌዝ ዶክተር፣ ሻጥር በየፈርጁ ከተወኑባቸው ቴአትሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀረቡ ድራማዎች ያልተከፈለው ዕዳ፣ ግራ የገባው ግራ፣ አመል አለብኝ፣ የዘመቻው ጥሪ ላይ መተወናቸው ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
በቀድሞ የኢትዮጵያ ሀገር ፍቅር ማኅበር በአሁኑ የሀገር ፍቅር ቴአትር ከ1949 እስከ 1953 ዓ.ም. ያገለገሉት አቶ ጀምበሬ፣ በመቀጠል ከ1953 ዓ.ም. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት (አሁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር) በመቀላቀል እስከ 1988 ዓ.ም. በመድረክ ትወና ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
በቀድሞ አጠራር በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በ1933 ዓ.ም. የተወለዱት አቶ ጀምበሬ በላይ፣ የካቲት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. አርፈዋል፡፡ ከያኒ ጀምበሬ የሁለት ሴቶችና የአራት ወንዶች አባት ነበሩ፡፡