ኢትዮጵያ በቅርቡ የህዋውን ዓለም መቀላቀሏን ያሳየችው ኢቲ አር ኤስ ኤስ-1 (ETRSS-1) የተሰኘ የመሬት ምልከታ ሳተላይቷን ከቻይና በማምጠቅ ነበር፡፡
ይቺ ለኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነችው ሳተላይት ሥራዋን እያከናወነች ሲሆን መሰንበቻውን አዲሱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብርሃ በላይ (ዶ/ር-ኢንጂነር) ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሳተላይት የምስል መረጃዎች በፍጥነት ጥቅም ላይ ለማዋል ከተጠቃሚ አካላት ጋር ግንኙነት በመጀመር ተደራሽ ለማድረግ እንዲሠራም ዶ/ር አብርሃ አቅጣጫ መስጠታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
ከተወነጨፈችው ሳተላይት ባለፈም የኮሙዩኒኬሽን ሳተላይት ለማምጠቅ የተጀመሩት ሥራዎችን ለማፋጠን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በስፔስ ምህንድስና የጀመረችው ተሳትፎ እንዲጎለብት የተጀመሩ ሥራዎችና ከሪሞት ሴንሲንግ ሳተላይት በተጨማሪ በኮሙዩኒኬሽን ሳተላይት ባለቤትነት ዙሪያ የተጀመሩት ሥራዎች እንዲፋጠኑም አሳስበዋል፡፡
ባለፈው ታኅሣሥ ወር የተወነጨፈችው ሳተላይት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር፣ ከግብርና ጋር የተያያዙ ጥናትና ምርምሮች ለማካሄድና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚያስችል፣ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ የኮሙዩኒኬሽንና የብሮድካስት ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በወቅቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክና ኤርያል ከተባለ ተቋም ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የሳተላይት መገጣጠሚያና መሞከሪያ ጣቢያ ለመገንባት በትብብር እየሠሩ ሲሆን የመገንባቱ ሒደት እንዲጠናከር አዲሱ ሚኒስትር ማሳሰቢያ መስጠታቸው ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢትዮጵያ ሳተላይት በማምጠቅ ከአፍሪካ ስምንተኛዋ አገር መሆኗ ይታወቃል፡፡