Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለክፉም ለደጉም እንመርመር!

ሰላም! ሰላም! አንዱ ባለፈው እንዲህ እንዳሁኑ ሁለት ጊዜ ሰላም ስለው፣ ‹‹በተማፅኖ ሥር ላለ ሰላም አንዱ አይበቃህም?›› አለኝ። እንዲያው የእኛ ሰው እኮ ሰላም ስትሉትም ነገር መመተር ሆኖ ሥራው ግራ ግብት ያደርጋል። አሁን ለዚህ ሰው ምን ተብሎ ይመለስለታል? አንዳንዴ እኮ አንዳንድ የከተማችን ነዋሪዎች እየተባለ ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ ስለሰላም ሲደሰኩር ከሚውለው ውስጥ የዚህ ቢጤው የሚበዛ እየመሰለኝ ነው፡፡ ለምን ብትሉኝ ለሰላም የሚሰብኩ እየበዙ ለምን ፍዳችን በዛ ነው መልሴ፡፡ ‹‹ሌላው ቢቀር ሕዝብ ሰላም ርቦትና ጠምቶት እየጮኸ ለምን ድምፁ አያከብርም?›› ስለው ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሆዱ እስኪነፍር ስቆ ከተፈጠርኩ እንዲህ ቀልጄ እንደማላውቅ ነገረኝ። አሁን ማን ይሙት እንደ ሕፃን ልጅ በአንቀልባ የታዘልን ይመስል ሰላም እንደ ቀልድ ከእጃችን እያመለጠ ከቀን ወደ ቀን ወደ ቀውስ ስናዘግም ምን ይባላል? ወይስ እኔ ነኝ እየቀለድኩ ያለሁት? የምር ግራ ገብቶኛል። ለበለጠ ማብራሪያ ከፈለጋችሁ ይህንን ከባድ ጊዜ ማለፍ ስንችል የሆዴን አጫውታችኋለሁ። ለጊዜው ግን ተከድኖ ይብሰል። ደግሞ በኋላ አፌ ቢስትስ? የዘንድሮ ሰው እንደሆነ አፉና ዓይኑ ሲፈጥረው ነው መሰል ዝም ብሎ ይስታል። ‘አይሽ አይሽና ይፈሳል ዕንባዬ. . .’ ብሎ ዘፈን ድሮ ቀረ እየተባለ ነው!

ምክንያቱም የዘንድሮ ዓይን ስህተቱ ከመብዛቱ የተነሳ የድርቀት እንጂ የእርጥበት ችግር የለበትም። እንኳን በደጉ ቀን መርዶ ሰምቶም የሚንከባለል ዕንባ እየጠፋ ነው። ማስረጃ ካላችሁ ብዙ አለኝ። ከመቅበዝበዛችንና ቀልብ ከማጣታችን ብዛት የኑሮ ውድነት ጣሪያውን በርቅሶ መሄድ አላንጫጫንም። ለምን? እንደ ወትሮው ቢሆን ‘እሪ በይ አገሬ. . . ተከልከይ ባዋጅ. . .’ ብለን የምናስነሳው አቧራ አውሮፓ ይደርስ ነበር። ምናልባት አንድ ቀን እኛም እንደ አውሮፓውያን ምግብ ተትረፍርፎን ሌሎች ለምንተርፍበት ያበቃንና ይኼ ሁሉም ይረሳ ይሆናል። እስኪረሳ ድረስ መረሳት ያልነበረባቸው ብዙ ጉዳዮች ነበሩ። ሌላው ቀርቶ እንዲያው እዚህ ድረስ ኪሳችን ሲዘረፍ ምንም የማይመስለን ለምን ነው አትሉም? ከመቅበዝበዝና ቀልብ ከማጣታችን ጋር ተዳምሮ ብዙ ስህተቶችን እንደ ቀልድ ስለለመድን ነው። ስህተትም ሲለመድ መግደልና መሞት እንዴት ቀልድ እንደሚመስል እያያችሁ ነው አይደል? እያዩ መካድ ብርቅ ነው እንዴ ብላችሁ ራሳችሁን እንዳታታልሉ!

‘ውኃ ወርዶ ወርዶ አቀበት ይዋኛል፣ አትበሳጭ ልቤ የባሰ ይገኛል’ አለ የወንዙን ልጅ ትቶ የሰው አገር በማሳደድ የመነመነው። ምን በምግብ ዋስትና ራስን ቢችሉ መመንመን አይተወንማ። እና ውዷ ማንጠግቦሽ ራሷን አልችል ብላው ደረቴ ላይ ጣል አድርጋው ሳለ ቅዠት ነው መሰል ብንን አልኩ። በቀን ሳንባንን በሌሊት ይቀናናል። እንዲያው እኮ! ስባንን ቀሰቀስኳት። እየተገላበጠች፣ ‹‹ስንት ሰዓት ነው?›› ብላ ጠየቀችኝ። አይገርምም? እስኪ አሁን የጨለማ ሰዓት ምን ይፈይዳል? ‘ከሌሊቱ ስንት ሰዓት ነው?’ ይሉናል ደርሰው። እንጃ የእናንተን። ብቻ እኔ ሳልደርስባቸው የሚደርሱብኝ እያደር ጨምረዋል። ምናልባት እኔ ሳባርራቸው ወደ እናንተ ከመጡ መልሱ ‘አልነጋም ገና ነው!’ ነው። አደራ ከእኔ አልቀዳችሁትም እሺ። ደግሞ ያስኮርጃል ተብዬ ኋላ ጣጣ እንዳታመጡብኝ። የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ማንም አይነካህም አይዞህ። መጀመርያ በኩረጃ እያለፉ ያስመረቁዋቸውን ይከልሱ፤›› ሲለኝ ነበር። ማን ተመራቂ ማን አስመራቂ እንደሆነ እሱ ሲያወራ ግራ ገባኝ። የምንቀልድበት ብናጣ ብለን ብለን በትምህርት ላይ እየቀለድን ነው መከራችን የበዛው፡፡ ‹‹ከዲፕሎማ እስከ ማስተርስ ዲግሪ ድረስ በስጦታ መጠቅለያ እየተሰጠ የምን ትምህርት ነው የምትለው እባክህ?›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ እኔ ደላላው የጨነቀኝ እሱን ካላስጨነቀው ምን አገባኝ ብዬ ልሸብለል እንዴ? ወይ ጉዳችን!

ግን እንዲያው አደራችሁ እንቅልፍ አልባ ከሆነ ሰዓት መቁጠር ምን ይጠቅማል? ጊዜው ሰቅዞ ይዞኝ እኮ ነው የምደጋግምባችሁ። የቀኑን ብርሃን ሳይቀር ይህ የዘመን ጨለማ ከል እያለበሰው በመንገድ ላይ 24 ሰዓት ይብራልን ሳንል አንቀርም ትላላችሁ ትንሽ ቆይተን? ‹‹አይ አንበርብር! ‘ዩ አር ቱ ፋር ፍሮም ዘ ሪያሊቲ’›› ይለኛል ምሁሩ ወዳጄ። ‹‹አብራራ!›› ስለው፣ ‹‹አንተም ቤት ለቤት በቅጡ ያልተዳረሰና የሚቆራረጥ ኃይል እንዴት ሆኖ መንገድ ለመንገድ 24 ሰዓት ሊበራ እንደምታስብ አብራራ!›› ብሎ ይስቅብኛል። ኧረ እኔስ አልስቅም። ቀኑ በጨለማ ኃይል የተያዘበት ምስኪን ይኼን ሁሉ ዕልቂት፣ ይህን ሁሉ ፍጅት፣ ይኼን ሁሉ የፖለቲካ የበላይነትን ለማስጠበቅ የሚደረግ የአውሬዎች በሴራ የተጀቦነ ድራማ እያየ እንዴት ይስቃል? ማን ነበር ‘የሳቅ መቆራረጥ ያስቸገረን ያለ ምርጫ ሥልጣን በሚይዙ መንግሥታት የአስተዳደር ብልሹነት ነው’ ብሎ ሲደመድም የሰማሁት? የሰማሁት ልበል እንጂ አየሁ ብዬ ለመናገር ዕውቀቱም ድፍረቱም አይፈቅድልኝም፡፡ አይ የደላላ ነገር!

ታዲያላችሁ ሰሞኑን አንድ ባለ ሁለት ደርብ ቪላ አሻሽጬ ነበር። ገዥዎቹ ቤቱን ገብተውበት ሰንብተው ምሳ ጠሩኝ። ለእኔ ቢጤው የቲማቲም ቁርጥ እንደ በግ አሮስቶ የሚናፈቅበት ዘመን ላይ ስለደረስን፣ የነነዌ ፆም ፍስክ ተብሎ በየቦታው የሚታየውን የአስረሽ ምችው የተንዛዛና የብልግና ድግስ ለታዘበ ለእኛ ከፈጣሪ አዲሱ ዮናስ ቢላክ እንዳይገርማችሁ። እናላችሁ ሰዓቴን አክብሬ ስደርስ የደንበኞቼ የመጨረሻ ልጅ ቴሌቪዥኑ ላይ ተሰክቶ ኳስ ያያል። ‹‹ማንና ማን ናቸው?›› ስለው ‹‹ሊቨርፑልና ማንቸስተር ሲቲ፤›› አለኝ። ‹‹ማን እየመራ ነው?›› ስለው ‹‹እኔ!›› አለኝ። ግራ ገባኝ። ትኩር ብዬ ሳያቸው ለካ ተጫዋቾቹ አሻንጉሊቶች ናቸው። ነገሩ ‘ጌም’ እንደሆነ ገባኝ። ‹‹ኧረ አንተ ልጅ በቃህ ዜና እንስማበት?›› ስትለው እናቱ፣ ‹‹አንዴ ጠብቁኝ ይኼን ጨዋታ ካላሸነፍኩ እባረራለሁ›› አላት። ‹‹ማን ነው የሚያባርርህ?›› ስለው፣ ‹‹የእንግሊዝ ኤፍ ነዋ፣ አሠልጣኛቸው እኔ ሆኛለሁ፤›› ሲለኝ አልቻልኩም ሳቄ አመለጠኝ። ነገሩም ዘመኑም ገረመኝ። ወይ ቴክኖሎጂ እያልኩ ሳስብ ምናለበት ሕይወትም እንደዚህ የ’ሲሙሌሽን ጌም’ የዝውውር መስኮት ቢኖራት ብዬ ተመኘሁ። አስባችሁታል? በዕውን አልገፋ ያላችሁን በሲሙሌሽን ስታዘዋውሩት? ድግስ ልበላ ሄጄ ሌላ ለምርምር የሚጋብዝ ጉዳይ ጭንቅላቴን ወጥሮት ነበር፡፡ ለምን አንወጠር!

እኔ ለምሳሌ ‹ጌም› የማዘዋውረውን ላስቆጥራችሁ። አንደኛ ከእኛ በላይ አዋቂ ላሳር እያሉ የአየር ሰዓቱን የሚያጣብቡ ጥራዝ ነጠቆችን ወደ ቦታቸው አዘዋውራለሁ። ያውም በነፃ ዝውውር። ሁለተኛ አድማጭ መሆን ሲገባቸው እኛን አዳምጡን የሚሉትን ‘ኦቨር ቤንች’ አደርጋቸውና በሦስተኛ ደረጃ ሰማይ ዝናብ ራቀው፣ ሁዳዴ ሊገባ ነው፣ ፋሲካ እየተቃረበ ነው፣ ወዘተ. እያሉ በመሠረታዊ የምግብ ፍላጎቶች ላይ ያለ ከልካይ፣ ያለ መካሪ ዘካሪ እንዳሻቸው ዋጋ የሚያንሩትን ጫማ አሰቅላቸው ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል ህልም ነው። ታዲያ ሕፃን አዋቂው ወዶ መሰላችሁ ዓለም ስንት ሥራ በሚሠራበት የቴክኖሎጂ ውጤት ‘ጌም’ ሲቀጠቅጥ ውሎ የሚያድረው? ኑሮ ‘ክራሽ’ ሲያደርግባችሁ መቆጣጠር ካልቻላችሁ ‘ካንዲ ክራሽ’ አስጭናችሁ ተጫወቱ እሺ፡፡ ተጫወቱ የምለው እኔ ምስኪን ሆኜ ነው እንጂ፣ የዘመኑ ሰው እኮ ከበስተጀርባችሁ ምን እየሸረበ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ አንዳንዴማ አለማወቅ ሳይሻል አይቀርም!

ጨዋታን ጨዋታ እያስታጠቀውም አይደል? ታዲያ የሚያስታጥቀው ሽጉጥ ስላልሆነ አይዟችሁ አትደንግጡ። ለነገሩ ብትደነግጡም አልፈርድባችሁም። ‘እንዴት?’ አትሉኝም? የከተማ ታጣቂው በዝቷላ! እንደ ነገርኳችሁ ቅጥቅጥ አይሱዙ ለማሻሻጥ ወዲያ ወዲህ ስል ምሁሩን የባሻዬን ልጅ እግር ጥሎት አገኘሁት። ‹‹ሥራ እንዴት ነው?›› እየተባባልን ሳለን ከበስተጀርባችን አምባጓሮ ተፈጥሮ ገላጋዩና ታዛቢው ይግተለተላል። የመገላገላቸውን ቁርጥ ያወቁት ፀበኞች ማዶ ለማዶ ቆመው ‘እገልሃለሁ፣ እገልሃለሁ’ ይባባላሉ። እኛም እንደ ቀልድ እየሰማናቸው ለአፍ ልማድ ለፀብ ሞገስ እንዲያ የሚባባሉ ስለመሰለን ነገሩን አላካበድነውም፡፡ አቦ አታካብዱ በሚባልበት ዘመን ሁሉ እየከበደን ተቸገርን እንጂ፡፡ አታካብዱ እያሉ ያሞኙን ቢበዙ አይደንቅም፡፡ ኋላማ አንዱ እንደ ጀምስ ቦንድ በብርሃን ፍጥነት ሽጉጡን አወጣና ‘ዶንት ሙቭ’ ቢል ሰማይ ምድሩ ድብልቅልቅ፣ አዳሜ ሁሉን ትቶ ሩጫ በሩጫ። ‹‹ወይ ዘመን! አንድ ዘራፍ የሚል ይጥፋ?›› ስል የሰማኝ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ከራሱ ዘራፍ ከሚለው ቃል ውጪ ዘራፍ ባይ ደመ መራራ በእነ አባቴ ጊዜ ቀርቷል፤›› ብሎ መለሰልኝ። ጉድ ነው አትሉም!

አንዱ ለስንቱ ብለን እንችለዋለን ሲል፣ ሌላው ብናውቀው ምን አስደበቀን አለ አሉ፡፡ በኋላ ፖሊሶች መጥተው እንደ ምንም ሲያረጋጉ የባሻዬ ልጅ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹እኔምለው አንበርብር ባለፈው የሄድንበት ኤግዚቢሽን ላይ ሽጉጥ ዕደላ ነበረ እንዴ? ታጣቂው በዛብኝ፤›› ሲለኝ፣ እኔም ነገርን በነገር አውቅበት የለ? ‹‹ወንድሜ! ዘመኑ ነው እንጂ እኛ ስላልሆንን መረጃ የታጠቅነው መልስ የሌለው ጥያቄ መጠየቅ አቁም፤›› አልኩታ። ለማንኛውም እግረ መንገዴን አንድ ሁለት ነገር ጣል ላድርግላችሁና ቅጥቅጡን ልሽጠው። አንደኛ ከአልፎ ሒያጅ መንገደኛ ጋር አፍ ዕላፊ ማብዛት ቀንሱ። ሁለተኛ አንደኛ ብዬ የተናገርኩትን ደጋግማችሁን አንብቡ። ‘እስኪ ፈገግ’ ይል ነበር ፎቶ አንሺ ቢኖር፡፡ ፍቶ አንሺ ስትሉ አንዱ ፎቶ ሊነሳ አንሺውን እንዴት እንደሚያነሳው ይነግረዋል፡፡ ‹‹ይኸውልህ ቁመቴን ረዘም፣ ጉንጬን ሞላ ሞላ፣ ደረቴን ፈርጠም፣ ዓይኔን ጎላ ጎላ፣ ከጀርባዬ በግራና በቀኝ ሪሃናንና ሻኪራን አስገብተህ በቀኝ እጄ ቶምሰን፣ በግራ እጄ ማካሮቭ ታስይዘኝና ሙሉ ለሙሉ ጥይቶች የጎረሰ ዝናር አስታጥቀህ እንድታነሳኝ፤›› ይለዋል፡፡ ፎቶ አንሺው ግባ ብሎት ከአንገት በላይ አንስቶት ነገ ና ብሎ አንድ ሺሕ ብር ተቀብሎት ያሰናብተዋል፡፡ በነጋታው ሲደርስ በተለያዩ አክሽኖች የተነሱ አሥር ፎቶዎች ደርድሮ ይጠብቀዋል፡፡ ሰውየው በደስታ ጮቤ እየረገጠ፣ ‹‹እንዴ ዝነኛ የፈረንጅ አክተር መሰልኩ አይደል?›› ሲለው ፎቶ አንሺው እየሳቀ፣ ‹‹ብሩን ጨመርመር እያደረግህ ከመጣህ ብትፈልግ ትራምፕን፣ ብትፈልግ ሜሲን፣ ካሻህ ደግሞ ሮናልዶን አደርግሃለሁ. . .›› እያለ ሲነግረው ሰውየው በደስታ ዕንባው በጉንጮቹ ላይ ኩልል እያለ ይፈስ ጀመረ፡፡ ዘንድሮ እኮ ደህና አድርጎ የሚመረምረን ብናገኝ ብዙዎቻችን በፅኑ የአዕምሮ ሕመም ምክንያት አልጋ እንይዝ ነበር፡፡ ማን ነበር ለይቶልናል ያለው!

በሉ እንሰነባበት። በቀደምለት ባሻዬን ወደ ቤተስኪያን ልሸኛቸው ከቤት ወጣሁ። ሰዓታቱ ሳይጀመር ለመድረስ እየተጣደፉ ይራመዳሉ። አካላቸው ቢዝልም አዕምሯቸው ንቁ ነውና አንዳንዴ አደናቅፏቸው ወይ ወለም ብሏቸው እንዳይወድቁ ስለምሠጋ፣ ‹‹ቀስ ይበሉ እንጂ ባሻዬ ይደርሳሉ. . .›› አልኳቸው። ኋላ ፈገግ ብለው፣ ‹‹ሂድና ለእነዚያ ችኩሎች ንገራቸው። እኔ ብቸኩልም በሁለት እግሬ ነው። ምነው ባለ አራት እግሮቹ አይታዩህ?›› ብለው ማዶ ሲጠቁሙኝ አንድ ቪትዝ መኪና እንደ ካርቶን ተጨመዳዳ፣ አንድ አይሱዙ ደግሞ የፊት መስታወቱ ረግፎ አየሁ። ‹‹አሁን እኮ ሰላም ነበር ከመቼው?›› ብዬ ክው አልኩ። ‹‹ለመዋደድ ስንዝር ለፀብም መዳፍ በቂ ነው ያለውን ባለቅኔ አታውቀውም እንዴ? ሰው ከንቱ! ሁሉ ነገር ቀሪ መሆኑ በምን ቋንቋ ቢነገረው እንዴት ባለ ልምድ ቢያየው እንደሚገባው እንጃ። ረግፎ ለመቅረት ይኼ ሁሉ አበሳ፣ ይኼ ሁሉ ሩጫ፣ ይኼ ሁሉ ስደት፡፡ አይገርምህም ግን አንበርብር? መጽሐፉ እኮ ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ የሚለው ያለ ምክንያት እንዳይመስልህ። ከሟች በላይ የቋሚ አበሳ ነው ከባዱ። ግን እኛ ነገር ካላለፈ አልገባን ብሏል፤›› ብለው የዕርምጃችንን ዙር አቀዘቀዙት። ‹‹ምነው ባሻዬ አመመዎ እንዴ?›› ስላቸው፣ ‹‹እንዴት አያመኝ አንበርብር? በየቀኑ ጥፋት መቁጠር እንዴት አያመኝ? በየቀኑ አስከሬን መሸኘት እንዴት አያመኝ? በየቀኑ ውሸትና ሀቅን መውገር እንዴት አያመኝ?›› ብለው ሲያፈጡብኝ ማረጋጊያ ዘዴና የምገባበት ጉድጓድ ጠፋኝ። ውሎ አድሮ የባሻዬ ሕመም ተጋባብኝ መሰለኝ የደመነፍስ ሩጫ፣ የስሜት ውዥንብር የሚነዳው ሆታና ዕልልታ፣ እየደገሰ የሚያስገብረን አካልና አዕምሮን መቁጠር እኔንም ታከተኝ። ጥቂት ማንቀላፋት ደግሞ መንቃት፣ እንደገና ማንቀላፋት ደግሞ መባነን፡፡ መልሶ ማንቀላፋት፡፡ የቆምን እየመሰለን የወደቅን በዝተናል መሰለኝ፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የሚመረምረን ብናገኝ የደዌያችን ብዛቱም ታሰበኝ፡፡ አሁንስ ለክፉም ለደጉም ራስን መመርመርም ሆነ ማስመርመር ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት