Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየድህነት መገለጫዎቹ የሐሩር በሽታዎች

የድህነት መገለጫዎቹ የሐሩር በሽታዎች

ቀን:

በሽታዎቹ መነሻቸው ሐሩራማ ከሆኑ አካባቢዎች ቢሆንም፣ ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረገው ፍልሰት በየትኞቹም ከተሞች ላይ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከአብዛኞቹ ነዋሪዎቿ ላይ ድህነትን ማራገፍ ባለመቻሏ፣ ከዚህ ቀደም ከአዲስ አበባ የጠፉና ታይተው የማይታወቁ ሐሩር ወለድ በሽታዎችን ጭምር ማየትም ተለምዷል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ቆንጥር በሌላ አካባቢዎች ደግሞ ሻሂ የሚባለው አፍንጫን የሚያቆስለው ካልአዛር፣ የግልና አካባቢ ንፅህናን በመጠበቅ ብቻ ቀድሞ ሊወገድ፣ ሕመሙ ከተከሰተም ሊድን የሚችለው ሆኖም ብዙዎችን ለዓይነ ሥውርነት እየዳረገ የሚገኘው ትራኮማ፣ በመጫማት ብቻ መከላከል የሚቻለውንና ይህ ባለመሆኑ እግርን የሚያሳብጠው ዝሆኔ፣ ገጠር ላይ ባብዛኛው የሚከሰተውና አዲስ አበባ ላይ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ የሚያውቀው ፎከት (እከክ) እና የዓለም ጤና ድርጅት ከድህነት ጋር ይያያዛሉ ብሎ ያስቀመጣቸው ቀዳሚ ሃያ የሐሩር በሽታዎች (Tropical Diseases) የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ጫና ናቸው፡፡

ጊኒዎርምና ‹ለኢትዮጵያውያን ቤተሰብ ሆኗል› የሚባለው የአንጀት ጥገኛ ትላትልን ጨምሮ ሃያዎቹ የሐሩር በሽታዎች፣ ለጤናው ዘርፍ ጫና ከመሆናቸውም በላይ ለሕሙማኑ መሸማቀቂያም ናቸው፡፡

በዝሆኔ አሊያም በካልአዛር ብሎም በሥጋ ደዌና በጊኒዎርም የታመሙ ሰዎች በተለይ በገጠራማ አካባቢዎች ከቤት መውጣት አይፈልጉም፡፡ አዲስ አበባ ላይ የዝሆኔና ሥጋ ደዌ በሽታን ለልመና የሚጠቀሙበት ቢኖሩም፣ ከከተማ ሲወጣ ግን ታማሚዎች የሚያፍሩበት ተሸማቀው እቤት የሚቀመጡበት የጤና እክል ነው፡፡

ጊኒዎርም መታከምና መዳን የሚችል ቢሆንም፣ ሕሙማን በግልጽ ወጥተው ወደ ሕክምና መሄድን አይመርጡም፡፡ በመሆኑም የማኅበረሰቡን በሽታን የመደበቅ ልማድ ለመስበር ጤና ሚኒስቴር ‹‹በበሽታው የተያዘ ሰውን ለጠቆመኝ እሸልማለሁ›› ብሎ ማስታወቂያ እስከማስነገር ደርሷል፡፡ ሕመሙን በተለይም ሰውነትን የሚያቆስሉ በሽታዎችን አውጥቶ ለማሳየት የሚሸማቀቅ ማኅበረሰብ ውስጥ፣ የአገሪቱ የጤና ሥርዓት ተደራሽ አለመሆን ተደምሮ፣ ሐሩራማ በሽታዎችን አክሞ ማዳኑም ፈታኝ ነው፡፡

በድህነት ምክንያት የሚመጡትና የግልና የአካባቢ ንፅህናን በመጠበቅ ብቻ መከላከል የሚቻሉት ትራኮማ፣ ጊኒዎርም፣ ቢሊሃርዚያ፣ የአንጀት ትላትል፣ ፎከት፣  ጫማ በመጫማት ብቻ መከላከል በሚቻለው ዝሆኔና ሌሎችም የሐሩር በሽታዎች፤ ንፁህ የውኃ አቅርቦት ባለመሟላቱና የማኅበረሰቡም ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ የብዙዎችን ሕይወት አመሰቃቅለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቅድሚያ ሰጥታ እየሠራች ያለችውም የዓለም ጤና ድርጅት ቀዳሚ ብሎ ካስቀመጣቸው ከሃያ የሐሩር በሽታዎች ለዘጠኙ ነው፡፡ የሥጋ ደዌና ሬቢስ (የእብድ ውሻ በሽታ) ቀድሞ እየተሠራበት በመሆኑ፣ ከዘጠኙ አለመካተቱን በጤና ሚኒስቴር በበሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬት ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ፍቅረ ሰይፈ ይናገራሉ፡፡

እነዚህን የሐሩር በሽታዎች መቶ በመቶ ማለት በሚያስችል ሁኔታ መከላከል የሚቻል ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ለዚህ አልታደለችም፡፡ ማኅበረሰቡ ሥልጣን ለሚያስገኘው ፖለቲካ የሚራኮተውን ያህልም፣ ጤናውን በመጠበቅና ድህነትን ማስወገድ በሚቻሉባቸው አሠራሮች ላይ ያለው ግንዛቤ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡  ያሉት የጤና ተቋማትና ባለሙያዎችም ሁሉንም ሕዝብ በወቅቱ የሚደርሱ አይደሉም፡፡

ኢትዮጵያም ትኩረት ከሚሹት ከሃያዎቹ ሐሩራማ በሽታዎች ነፃ ናት የሚል የምስክር ወረቀት የላትም፡፡ ከበሽታው ነፃ ናት የሚል የምስክር ወረቀት ለማግኘት እየሠራች ያለችውም በጊኒዎርም ላይ ብቻ ነው፡፡

እንደ አቶ ፍቅረ፣ ሙሉ ለሙሉ ደኅንነቱ የተጠበቀ የውኃ አቅርቦት በሌለበት ሁኔታ ከኢትዮጵያ እነዚህን በሽታዎች ለማጥፋት ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡

ድህነት በተንሰራፋበትና ዝቃጭ ውኃ (በቆሻሻ የተበከለ) ውኃ የሚጠጣ ማኅበረሰብ ባለበት ሁኔታ ሐሩራማ በሽታዎችን በአጭር ጊዜ ከኢትዮጵያ ማስወገድ ከባድ ቢሆንም፣ የጤና ሚኒስቴር ለዘጠኙ በሽታዎች ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

የበሽታዎቹ ሥርጭት ከአዲስ አበባ ይልቅ በገጠር አካባቢ የሚበዛ ቢሆንም፣ ሁሉንም የተዘነጉ የሐሩር በሽታዎች ንፁህ ውኃ በማቅረብ ብቻ መከላከል እንደሚቻል አክለዋል፡፡

ያደጉት አገሮች የተዘነጉ በሽታዎችን ንፅህናን በመጠበቅ ብቻ አጥፍተው ታሪክ አድርገውታል፡፡ በድህነት ውስጥ በሚገኙ አገሮች ደግሞ ችግሩ የከፋ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሙቀት መጠን መጨመር የበሽታዎቹን ሥርጭት ማዛመቱ ከድህነት ጋር ተደምሮ እያደረሰ ያለውን የጤና ቀውስ ለመከላከል አሜሪካና ሌሎች ረጂ ድርጅቶች ትኩረት ሰጥተው መሥራት ከጀመሩ አሠርታት ቢቆጠሩም፣ ኢትዮጵያ ለችግሩ ትኩረት ሰጥታ መሥራት የጀመረችው እ.ኤ.አ. ከ2013 በኋላ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እስከ 2006/7 ድረስ ለትራኮማ እንኳን የተጠናከረ መረጃ አልነበራትም፡፡ የበሽታው ጉዳት፣ መጠንና የደረሰው ዓይነ ሥውርነትም አይታወቅም ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ በተሠራው ሥራ ትራኮማ በኢትዮጵያ 70 ሚሊዮን ሰዎችን ያጠቃል ተብሎ እንደሚታሰብ ታውቋል፡፡ በሽታው ከወንዶች ይልቅ ሴቶችን በሦስት እጥፍ እያጠቃ ሲሆን፣ የአገሪቱ የጤና ጫናም ሆኗል፡፡

ፎከት ብቻ ሲታይ 25 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለበሽታው ተጋላጫ ናቸው፡፡ የአንጀት ጥገኛ ትላትል ተማሪዎች እንዳይማሩ የሚያደርግና ካለው የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ጋር ተዳምሮ ልጆች የበሏትንም የሚሻማ ነው፡፡ የልጆቹን የአዕምሮ ዕድገት የሚያቀጭጨው የአንጀት ጥገኛ ትላትል መጥፋት የሚችል በሽታ ቢሆንም፣ ይህም ለኢትዮጵያ አልተቻለም፡፡

የተዘነጉ ነገር ግን ትኩረት የሚሹ የሐሩር በሽታዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥር 21 ቀን 2012 ዓ.ም. መከበሩን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ለማስታወስ፣ ላይት ፎር ዘ ወርልድ የኢትዮጵያ ቢሮ ባዘጋጀው መድረክ የተገኙት የዓለም ትራኮማ ኢንሽየቲቭ የአፍሪካ ዳይሬክተር ተሾመ ገብሬ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በዓለም ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎች በተዘነጉ የሐሩር በሽታዎች ይታመማሉ፡፡

አንድ ሰውም አንድና ከአንድ በላይ የሐሩር በሽታ ሊያጠቃው ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሁለት ቢሊዮን ሕዝብ ለበሽታው የመጋለጥ ሥጋት ውስጥ ይገኛል፡፡

በየዓመቱ 185,000 ሰዎች በእነዚህ በሽታዎች ሳቢያ ይሞታሉ፡፡ በበሽታው ተይዘው በሕይወት የቆዩት ደግሞ ለዓይነ ሥውርነት፣ ለአካል መጉደል፣ ለሥነ ልቦና ቀውስና ለተያያዥ ችግሮች ይጋለጣሉ፡፡  ሕመሞቹ የአዕምሮ ዕድገትን በማቀጨጭ ተማሪዎች በትምህርታቸው ብቁ እንዳይሆኑ ያደርጋሉ፡፡ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያጓትቱት እነዚህ በሽታዎች በተለይ ሴቶችና ሕፃናትን ያጠቃሉ፡፡

በአፍሪካ፣ በእስያና በላቲን አሜሪካ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የሚኖሩ ሕዝቦችን እያጠቁና ለሞት እየዳረጉ የሚገኙት የተዘነጉ የሐሩር በሽታዎች በቀላሉ መከላከል፣ ችግሩ ከተከሰተም ማከም የሚቻሉ ናቸው፡፡ ሆኖም ደሃ አገሮች ሁለቱንም የማድረግ ጫና አለባቸው፡፡

ዶ/ር ተሾመ እንደሚሉትም፣ በሽታዎቹን ለመከላከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚሠሩ ሥራዎች በተጨማሪ አገሮች የንፁህ ውኃ አቅርቦትን በማረጋገጥና የግልና የአካበቢ ንፅህናን በማስጠበቅ በሽታዎቹን ማጥፋት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በሽታዎቹን ለመከላከል ኅብረተሰብ አቀፍ ሕክምና (የጅምላ) መድኃኒት ሥርጭት በማድረግ፣ ትራኮማን፣ ፎከትን፣ የአንጀት ትላትልንና የዝሆኔ በሽታን ማጥፋትና መቆጣጠር እንደሚቻል፣ በሽታው ሥር ሰዶ ግለሰብን የጎዳ ከሆነ ነፍስ ወከፍ ሕክምና ማድረግ፣ በሽታ አስተላላፊ የሆኑ ነፍሳትን የኬሚካል ርጭት በማድረግ በማጥፋትና የግልና የአካባቢ ንፅህናን በመጠበቅ በሽታውን መቆጣጠር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ 

ጤና ሚኒስቴር የተዘነጉ የሐሩር በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዕቅድ ነድፎና የራሱ ዳይሬክቶሬት አቋቁሞ እየሠራ እንደሚገኝ፣ ሆኖም የንፁህ ውኃ አቅርቦት ካልተሻሻለ ሚኒስቴሩ ብቻውን ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...