Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየኢትዮጵያና የኦርቶዶክስ ታሪክ በመደበላለቁ እውነተኛው ታሪክ ተለይቶ እንዲነገር ተጠየቀ

የኢትዮጵያና የኦርቶዶክስ ታሪክ በመደበላለቁ እውነተኛው ታሪክ ተለይቶ እንዲነገር ተጠየቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ታሪክ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሆነ ስለሚገለጽ፣ እውነተኛው ታሪክ የትኛው እንደሆነ የታሪክ ተመራማሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ ተጠየቀ፡፡

ጥያቄው የቀረበው የቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምርያ ‹‹በጎውን ማን ያሳየን?›› በሚል መሪ ቃል ሐሙስ የካቲት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ባዘጋጀው የአንድ ቀን ውይይት ላይ ነው፡፡

ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሑፍ ካቀረቡት ውስጥ አንዱ የነበሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪው ሽፈራው በቀለ (ፕሮፌሰር) ሲሆኑ፣ ‹‹የታሪክ እውነታ ተፋልሶ በኢትዮጵያ ታሪክ›› የሚል የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ በጽሑፋቸው እንዳብራሩት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ጥቁር ሕዝቦች በርካታ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡ አርኪዮሎጂስቶች በቅርቡ ከአክሱም ወደ የሃ በሚወስደው መንገድ ላይ ባደረጉት ቁፋሮ አንድ የቤተ ክርስቲያን ቅሪት አግኝተዋል ብለዋል፡፡

- Advertisement -

ይኼ ቅሪተ አካል ‹ካርቦን ዴቲንግ› በሚባለው ሳይንሳዊ መንገድ ሲመረምር ከ400 ክፍለ ዘመን በላይ እንደኖረ በመረጋገጡና ከዚያ በፊት በአፍሪካ አንድም አገር ቤተ ክርስቲያን ወይም የክርስትና እምነት ያለው ስለሌለ፣ ቀደምት አገር መሆኗን ተናግረዋል፡፡ በአፍሪካ የክርስትና እምነት የተስፋፋው ቅኝ ግዛት ከመጣ በኋላ በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመን መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ ከዚህ አንፃር የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊና ቀዳማዊት መሆኗን እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በየመን፣ በሱዳንና በግብፅም የጎላ ታሪክ ያላት መሆኗንም አክለዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በቅርስ፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በዜማና በሥነ ሥዕል አፍሪካ ቀደምት አገርና የጥቁር ሕዝቦች ኩራት መሆኗንም አስረድተዋል፡፡

አፍሪካውያን በሥዕል ሙያ ሳይሆን በእንጨትና ድንጋይ ላይ ቅርፃ ቅርፅ እንደሚታወቁ ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ ግን በአቡነ ገሪማ ገዳም በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ወንጌል ውስጥ የተገኙ ሥዕሎች አውሮፓውያን ዛሬ ከሚከራከሩበት የሥዕል ታሪክ የሚበልጥ እንጂ የማያንስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዛሬ ድረስ በዩኔስኮ እየተመዘገበ የሚገኘው እንደ ጥምቀት ያሉ ሥርዓተ አምልኮዎች የቤተ ክርስቲያኗ ውጤቶች መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ በታሪክ ውስጥ የጎላ ሥፍራ ቢኖራትም ያደረገችው ጉዞ አልጋ በአልጋ እንዳልነበር የተናገሩት ፕሮፌሰሩ ቤተ ክህነት ጨቋኝ፣ በዳይና መንግሥትን ተክታ በመሥራት ብዙ በደል እንደፈጸመች የሚነገረው የሐሰት ትርክት ዓይነት እንዳልሠራች ተናግረዋል፡፡ ተበዳይና ተጨቋኝ እንደነበረች ግን በሰነድ የተደገፈ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በ16ኛው ክፍለ ዘመን በዮዲት ጉዲት የደረሰው የቤተ ክርስቲያናትና አገልጋይ ምዕመናን ውድመትና ግድያ፣ የካቶሊካውያን ደም አፋሳሽ ውድመትና ጥፋትን ለማሳየት በደብረ ሊባኖስ ገዳም የደረሰውን ብቻ በምሳሌነት ማንሳት በቂ መሆኑን ሽፈራው (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡ በግራኝ መሐመድ የተፈጸሙባት ውድመት ብቻ ሳይሆን፣ በጣሊያን ወረራም እስከ ኤርትራ ድረስ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የደረሰው ጉዳት እጀግ በርካታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በሁሉም ነገሥታት በተለይ እስከ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ እጅግ ዘግናኝና አሳዛኝ ውድመት እንደደረሰባትም በምሳሌ እየጠቀሱ አስረድተዋል፡፡

በተለይ ከቦምብ፣ ከመርዝ ጋዝና ከጠመንጃው በተጨማሪ በርዕዮተ ዓለም የደረሰው አደጋ እጅግ በጣም ዘግናኝ መሆኑን ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የሚነገሩትና የተደረጉት ሁሉ በታሪክ ስላልተሰናዱና ቤተ ክርስቲያኗም የምርምር ተቋም ስለሌላት ማስረጃዎችን እያጣሩ ማቅረብ ባለመቻሉ፣ የውሸት ትርክቶች እውነት እየመሰሉ መቀጠላቸውን ገልጸዋል፡፡  

ያለፈውን እውነት የሚመስል የሐሰት ትርክት እንደ እውነት በመናገር አሁን እያደገና የተለያዩ መልኮችን እየያዘ የመጣው ትርክት፣ ከፍተኛ አደጋ መሆኑን ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡

ታሪክን እያፋለሱና እውነታውን እየተው የተለያዩ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሁሉ ማለትም የፖለቲካ ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የሃይማኖት ተቋማት እንቅስቃሴያቸው ሁሉ አደጋ የሚያመጣ በመሆኑ፣ የሃይማኖች አባቶች ሊነቁ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ የመወያያ ጽሑፋቸውን ካቀረቡ በኋላ የውይይቱ ተሳታፊዎች ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡ በተለያዩ ምሁራን የተጻፉ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት እንዳሉ ጠቁመው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ነው፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው›› ይባላል፡፡ ትክክለኛው ታሪክ የትኛው እንደሆነ እንዲያስረዱ ለፕሮፌሰሩ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡

የታሪክ መደበላለቅ እንደሌለ በመግለጽ ምላሽ መስጠት የጀመሩት ሽፈራው (ፕሮፌሰር)፣ እውተኛ ታሪክ የሚባለው በማስረጃ ተመርምሮ እውነተኛ መሆኑ የተረጋገጠ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ ቋንቋዎች ከተጻፉ የታሪክ መጽሐፍት ውስጥ፣ ‹‹የኦሮሞ አመለካከት ‹ኢላልቻ ኦሮሞ› የሚለው በኦሮሚኛ የተጻፈው መጽሐፍ አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ታዳሚዎች፣ መጽሐፉ ታሪክ ብሎ የሚያነሳቸው ቤተ ክርስቲያኗ አስገድዳ እንዳጠመቀቻቸው፣ የዋቄፈታ ቦታዎችን በጉልበት ወስዳ ቤተ ክርስቲያን እንደሠራችባቸው፣ ዝቋላ ገዳምን በምሳሌነት በመጠቆም እውነቱ ምን እንደሆነም ጠይቀዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፣ ዝቋላ ገደም ከኦሮሞ እንቅስቃሴ በፊት ከ1,300 ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ ‹‹ግራኝ አህመድ አዋሽን ተሻግሮ በናዝሬትና በደብረ ዘይት አድርጎ ወደ መሀል ሲመጣ ዝቋላ ገዳምን አፈረሰው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንንም አቃጠለ፡፡ ስለዚህ ዝቋላን ቤተ ክህነት በጉልበት የወሰደችው ሳይሆን፣ የኦሮሞ ማኅበረሰብ በአካባቢው ሳይሰፍር የነበረ መሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ከውይይቱ ታዳሚዎች ተነስተው ፕሮፌሰሩ፣ ሊቀ ጳጳሳት፣ ሌሎች ጽሑፎችን ያቀረቡ የሕግ ባለሙያና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ወንደሰን ደምሴ (ዶ/ር)፣ መምህር ግርማ ባቱ፣ መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ውይይቱን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በፀሎት ከፍተውታል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...