Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በአዲስ አበባ ኤርፖርት የሚደረገው ጥንቃቄ ተጠናክሮ መጠቀሉ ተገለጸ

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በአዲስ አበባ ኤርፖርት የሚደረገው ጥንቃቄ ተጠናክሮ መጠቀሉ ተገለጸ

ቀን:

በቻይና ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ የተከሰተውና ወደ ሌሎች አገሮች በመዛመት ላይ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የሚካሄደው ጥንቃቄ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች፣ ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ኤርፖርት የሚደረገውን የመከላከል ጥንቃቄ አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል፡፡ አየር መንገዱ በመንገደኞች ላይ የሚካሄደውን የጤና ምርመራና በአውሮፕላኖች ውስጥ የሚደረገውን የመከላከያ ጥንቃቄ፣ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሐሙስ የካቲት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. አስጎብኝቷል፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ከጋንዲ ሆስፒታል ለኮሮና ቫይረስ ልየታ የመጡት የጤና ባለሙያ ምሥጋናው ብሩ፣ በመንገደኛ ማስተናገጃ ሕንፃ አንድና ሁለት በቂ የጤና ባለሙያዎችና ቴርሞስካን (የሰውነት ሙቀት መለኪያ) መሣሪያዎች መመደባቸውን ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

ከውጭ የሚገቡ ማናቸውም መንገደኞች በቴርሞስካን መሣሪያ በኩል እንዲያልፉ እንደሚደረግ፣ የሰውነት ሙቀቱ ከ38.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ የሆነ መንገደኛ ካለ መሣሪያው ለይቶ ምልክት እንደሚሰጥ አቶ ምሥጋናው አስረድተዋል፡፡

ከፍተኛ ሙቀት ያለው መንገደኛ ተለይቶ ተጨማሪ ምርመራ ወደሚካሄድበት ክፍል እንደሚወሰድና የጉዞ ታሪኩም እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ከኤርፖርቱ ውጪ ወደ ተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ ተወስዶ የሕክምና ክትትል እንደሚደረግለት ጠቁመዋል፡፡

ከቻይና የተነሱ መንገደኞች በሙሉ የጤና ምርመራ እንደሚደረግላቸው፣ በሚሞሉት ፎርም መሠረት ኢትዮጵያ የሚቆዩ ከሆነ በተመዘገበው አድራሻቸው በጤና ባለሙያዎች ለ15 ቀናት ያህል የጤና ክትትል እንደሚደረግላቸው ተገልጿል፡፡ በአማካይ በቀን በአዲስ አበባ ኤርፖርት 7,000 ያህል መንገደኞች ላይ የልየታ ሥራ እንደሚከናወን ተነግሯል፡፡

የኤርፖርት ከስተመር ኬርና ተርሚናል ኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ጉልላት፣ ከየትኛውም አገር የሚመጡ መንገደኞች ከአውሮፕላን ወርደው በድልድይም ሆነ በአውቶቡስ ወደ ተርሚናሉ ሲገቡ በኤርፖርቱ ሠራተኞች እየተመሩ በቴርሞስካን መሣሪያ በኩል እንዲያልፉ እንደሚደረግ፣ ሁሉም መንገደኞች ከአውሮፕላን ከወረዱ ጀምሮ ከኤርፖርቱ እስከሚወጡ በካሜራዎች የታገዘ ክትትል እንደሚደረግባቸው ገልጸዋል፡፡ የመንገደኞች የጉዞ ታሪክ እንደሚጠየቅ፣ ከቻይና በሚመጡ መንገደኞች ላይ ልዩ ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ የቴርሞስካን መሣሪያ የቪአይፒን ሳሎን ጨምሮ በሁለቱም ተርሚናሎች መተከሉን፣ የኤርፖርቱና የአየር መንገዱ ሠራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ መሰጠቱንና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛና የእጅ ጓንት ለሠራተኞች በመታደል ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እስክንድር ዓለሙ ከቻይና የሚመለስ አውሮፕላን ራቅ ባለ አውሮፕላን ማቆሚያ ሥፍራ እንደሚቆም፣ መንገደኞችና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ከወረዱ በኋላ የዓለም አቀፍ ጤና ድርጅት መመርያ በሚያዘው መሠረት ኬሚካል እንደሚረጭ አስረድተዋል፡፡ እንደ ብርድ ልብስ የመሳሰሉ አልባሳት ከአውሮፕላኑ ተወግደው እንደሚቃጠሉ ተገልጿል፡፡

የኬሚካል ርጭቱን የሚያከናውኑ ሠራተኞች ሥልጠና የተሰጠ መሆኑን፣ በባለሙያዎችም ክትትል እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ ‹‹የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውን የጥንቃቄ መመርያ ሙሉ በሙሉ በመተግበር ላይ እንገኛለን፤›› ያሉት አቶ እስክንድር፣ ሁሉም አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ ያቁሙ እስካልተባለ ድረስ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ ስላላቋረጠ መንገደኞች ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ አይመጡም ማለት እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የቻይና መንገደኞች በዱባይ፣ በፍራንክፈርት ወይም በሌላ ኤርፖርት በኩል አድርገው ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ይችላሉ፡፡ አሁን በዓለም ላይ ባለው የተሳሰረ የአየር ትራንስፖርት በተለያዩ ኤርፖርቶች ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና ባይበር እንኳ በሌሎች አየር መንገዶች ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ማድረግ የሚሻለው የመከላከል ጥንቃቄያችንን ማጠናከር ነው፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት ወደ ቻይና አትብረሩ የሚል መግለጫ እስካሁን አላወጣም፤›› ብለዋል፡፡

የቻይና መንግሥት የሁቤይ ግዛት ነዋሪዎች ከግዛቷ እንዳይወጡ እንዳደረገ እየተነገረ ሲሆን፣ ዜጎች ከአገር ውጭ ለመጓዝ የተለየ የይለፍ ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸው ደንግጓል፡፡ ለቻይና አዲስ ዓመት ወደ አገራቸው ከተለያዩ አገሮች ተጉዘው የነበሩ ቻይናውያን ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው ለመመለስ መቸገራቸው ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ያለ አንድ ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የፕሮጀክት ተቋራጩ ቻይናዊያን ሠራተኞቹ ከቻይና በወቅቱ ለመመለስ ከይለፍ ፈቃድ ጋር በተያያዘ ተቸግሯል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያሰማራቸው ግዙፍ ቦይንግ 777-300 አራት መቶ ያህል መንገደኞች የሚያሳፍሩ ሲሆን፣ በመንገደኞች ፍሰት ማነስ ምክንያት በቦይንግ 777 ምትክ 200 ያህል መንገደኞች የሚያሳፍሩትን ቢ787 መለስተኛ አውሮፕላኖችን አሰማርቷል፡፡ ወደ ቻይና የሚያደርገውን የበረራ ምልልስ መጠንም ከገበያው መቀዛቀዝ ጋር በተያያዘ መቀነሱ ታውቋል፡፡

‹‹አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት እየከሰረ ነው ወደ ቻይና የሚበረው፡፡ ለገንዘብ ሳይሆን ያለውን ቁርጠኝነትና አጋርነትን ለማሳየት ነው ሥራውን ያላቋረጠው፤›› ሲሉ የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...