Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናክልሎች ለስኳር ፋብሪካዎች የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ታወቀ

ክልሎች ለስኳር ፋብሪካዎች የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ታወቀ

ቀን:

የክልሎቹ አቋም ስኳር ፋብሪካዎቹን ለመሸጥ የተያዘውን ዕቅድ እንዳይስተጓጎል ሥጋት ፈጥሯል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መፍትሔ እንዲያሰጡ ተጠይቋል

በፌዴራል መንግሥት ለተቋቋሙ ነባርና በግንባታ ላይ ለሚገኙ አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንዲሰጡ ተደጋጋሚ ጥያቄ ለሚመለከታቸው ክልሎች ቢቀርብም፣ ክልሎች ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ አመለከተ፡፡

የተገኘው የሰነድ መረጃ እንደሚያመለክተው የፌዴራል መንግሥት ከበርካታ ዓመታት በፊት ላቋቋማቸው ነባር የስኳር ፋብሪካዎችም ሆነ፣ በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ ለሚገኙት የስኳር ፋብሪካዎች የይዞታ ማረጋገጫ ማግኘት ባለመቻሉ መንግሥት ፋብሪካዎቹን ወደ ግል ለማዘዋወር እያደረገ ያለውን ጥረት እንዳያስተጓጉል ሥጋት ፈጥሯል፡፡

መንግሥት በያዘው ዕቅድ መሠረት ከዘንድሮ ጀምሮ ሁሉንም የስኳር ፋብሪካዎች ወደ ግል ለማዘዋወር፣ የፋብሪካዎቹን ሀብት በተናጠል እንዲገመት ከማድረግ አንስቶ በርካታ የቅድመ ፕራይቬታይዜሽን ተግባራትን እያከናወነ ቢሆንም፣ ፕራይቬታይዜሽኑን ዕውን ለማድረግ መሠረታዊ የሆነውን የይዞታ ማረጋገጫ ማሟላት እንዳልተቻለ ሰነዱ ያመለክታል፡፡

በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ሥር የሚተዳደሩ ነባርና በግንባታ ሒደት ላይ የሚገኙ በጥቅሉ 13 ስኳር ፋብሪካዎች ቢኖሩም፣ ከእነዚህ መካከል የተሟላ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ያላቸው ሁለት ስኳር ፋብሪካዎች ብቻ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

‹‹ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶች ላይ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ለማግኘት ከጅምሩ አንስቶ በድርጅቶቹና በኮርፖሬሽን አማካይነት ያላሰለሰ ጥረት ቢደረግም፣ ከወንጂ ሸዋና ከፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች በስተቀር ነባሩን የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ጨምሮ ሌሎቹ ነባርና በግንባታ ላይ የሚገኙ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ማግኘት አልተቻለም፤” ሲል ሰነዱ ይገልጻል፡፡

ለስኳር ፋብሪካዎቹ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ለመስጠጥ ፈቃደኛ አልሆኑም ተብለው የተጠቀሱት አምስት ክልሎች ናቸው፡፡ እነዚህም ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ትግራይና አፋር መሆናቸውን መረጃው ያመለክታል፡፡

‹‹ይህ ሥራ በአሁኑ ወቅት ከስኳር ኮርፖሬሽን ቦርድና ማኔጅመንት አቅም በላይ ሆኖ በመገኘቱ፣ እንዲሁም ሰነዱን የማግኘቱ ሥራ ለፕራይቬታይዜሽን ሒደቱ ወሳኝም ስለሆነ፣ ጉዳዩ በቀጥታ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኩል ሊያዝ እንደሚገባ ግንዛቤ ተወስዷል፤” ሲል ሰነዱ ይገልጻል፡፡

ለተንዳሆና ለከሰም ስኳር ፋብሪካዎች የመሬት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለማግኘት ከክልሉ፣ ከዞንና ወረዳ አመራሮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጉን፣ እንዲሁም የከሰም ስኳር ፋብሪካን ወደ ሙሉ አቅም ለማስገባት ለአገዳ ልማት የሚውል ተጨማሪ 5,000 ሔክታር መሬት ጥያቄ ለክልሉ ቢቀርብም ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን ሰነዱ ይገልጻል፡፡ ‹‹ላቀረብነው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ጥያቄም ‹መሬቱ የጎሳዎች በመሆኑ መስጠት አንችልም› የሚል ምላሽ ነው ከክልሉ መንግሥት የተገኘው፤›› ሲል ሰነዱ ያመለክታል፡፡

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሥር ለሸንኮራ አገዳ ልማት የሚውል 21 ሺሕ ሔክታር ይዞታ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህ ይዞታ ላይ ለምቶ የነበረ የሸንኮራ አገዳ ተክል በአሁኑ ወቅት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በተያያዘ ችግር ሙሉ በሙሉ በቤት እንስሳት ተበልቷል፡፡ በከሰም ስኳር ፋብሪካ ሥር ለሸንኮራ አገዳ ልማት የሚውል 2,800 ሔክታር መሬት ይዞታ ቢኖርም፣ ይህ ይዞታ በጨው የተጠቃ በመሆኑ ተጨማሪ 5,000 ሔክታር መሬት እንደሚያስፈልግ መረጃው ያስረዳል፡፡

በኦሞ ኩራዝ የስኳር ፕሮጀክት ሥር ለስኳር ልማት ፕሮጀክቱ የሚውል ይዞታ የሚያሳይና በክልሉ በኩል ስምምነት የተደረሰበት ሰነድ (Development Map) በኮርፖሬሽኑ እጅ የሚገኝ ቢሆንም፣ ኮርፖሬሽኑ ባለማው መሬት ውስጥ በስብጥር ለአርብቶ አደሮች መሬት በመስጠቱ አርብቶ አደሮቹ በዚሁ መሬት ላይ የይዞታ ካርታ በተደራቢነት ማግኘታቸውን ይገልጻል፡፡

በተጨማሪም የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የኦሞ ፓርክን አስመልክቶ፣ ቀደም ሲል ለፕሮጀክቱ በተሰጠው ሰነድ (Development Map) የተካተተ መሬት ላይ የይገባኛል ጥያቄ ማንሳቱን መረጃው ያመለክታል፡፡

በኮርፖሬሽኑ ሥር ከሚገኙ ስኳር ፋብሪካዎች መካከል የወንጂ/ሸዋና የፊንጫ ፋብሪካዎች ብቻ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንዳላቸው የሚገልጸው ሰነዱ፣ በእነዚህ ፋብሪካዎችም ቢሆን ለማስፋፊያ ፕሮጀክቶች የተሰጡ ይዞታዎች ለአብነት በፊንጫና በነሼ አካባቢ የለሙ መሬቶች የይዞታ ማረጋገጫ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም አለመቻሉን ያስረዳል፡፡

የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ በሥሩ ላለውና ግብር ለሚከፈልበት 14,700 ሔክታር ነባር መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እስካሁን እንደሌለው፣ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነዱ እንዲሰጠው በተለያዩ ጊዜያት ለዞንና ለወረዳ አስተዳደሮች ጥያቄ ማቅረቡን ይገልጻል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከኦሮሚያ ክልል፣ ከዞንና ወረዳ አመራሮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ቢካሄዱም አመራሮቹ እስካሁን ድረስ ሰነዱን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆቸናውን መረጃው ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይም ለአርጆ ደዴሳ ስኳር ፋብሪካ የይዞታ ማረጋገጫ እንዲሰጥ ለኦሮሚያ ክልል ቢቀርብም፣ እስካሁን ክልሉ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑን መረጃው ይገልጻል፡፡

የአርጆ ደዴሳ ስኳር ፋብሪካ አል-ሀበሻ ፒኤልሲ በተባለ የግል ኩባንያ ሥር የነበረ ሲሆን፣ የግል ኩባንያው በገጠመው የራሱ ችግር ምክንያት ፋብሪካውን ጥሎ ከአገር በመውጣቱ መንግሥት እንዲያለማው የተወሰነ ነው፡፡

ይህ ኩባንያ ለሚያካሂደው የስኳር ልማት 28,000 ሔክታር መሬት ከክልሉ የወሰደ ሲሆን፣ ፋብሪካው ወደ ስኳር ኮርፖሬሽን ከተዘዋወረ በኋላ መሬቱ በኮርፖሬሽኑ ስም ተዘዋውሮ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሰነድ እንዲሰጥ ለክልሉ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ክልሉ ፈቃደኛ አለመሆኑን መረጃው ያመለክታል፡፡

በትግራይ ክልል እየተካሄደ ለሚገኘው የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ለክልሉ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንዲሰጥ በተደጋገሚ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ለክልሉ እስካሁን ሰነዱን ለመስጠት እንዳልቻለ ሰነዱ ይገልጻል፡፡

በወልቃይት በሁለት ምዕራፍ ለሚካሄዱት የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች የሚውል በአጠቃላይ 60,128 ሔክታር መሬት የሚያሳይና በክልሉ በኩል ስምምነት የተደረሰበት ሰነድ (Development Map) በኮርፖሬሽኑ እጅ እንደሚገኝ፣ በዚህ ይዞታ ውስጥ የተወሰነ ሔክታር መሬት ላይ ሰፍረው ለነበሩ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ክፍያ ተፈጽሞ እንዲነሱ መደረጉንም ይኸው ሰነድ ያመለክታል፡፡

በአማራና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች አስተዳደር ወሰን ውስጥ እየተካሄደ ለሚገኘው የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የይዞታ ማረጋገጫ ለማግኘት፣ ለሁለቱም ክልሎች የቀረበው ጥያቄም በተመሳሳይ ምላሽ እንዳላገኘ መረጃው ጠቁማል፡፡

ለመሬቱ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለማግኘት በሁለቱም ክልሎች ከሚገኙ የወረዳ፣ የዞንና የክልል አመራሮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጋቸውን፣ ነገር ግን ሁለቱም ክልሎች ለፕሮጀክቱ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ሊሰጡ እንዳልቻሉ መረጃው ያመለክታል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የስኳር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጋሸው አይችሉህም መረጃውን አጣርተው ምላሽ እንደሚሰጡ ገልጸው የነበረ ቢሆንም፣ ከዚያ በኋላ በተለያዩ ቀናት በተደጋጋሚ ቢደወልላቸውም ስልካቸውን አይመልሱም፡፡ የተጠቀሱት ክልሎች ምላሽ እንዲሰጡበት ሪፖርተር ያደረገው ሙከራም አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...