Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለህዳሴ ግድብ ድርድር አሜሪካ የስምምነት ሰነድ የማርቀቅ ሒደቱን ልታመቻች ነው

ለህዳሴ ግድብ ድርድር አሜሪካ የስምምነት ሰነድ የማርቀቅ ሒደቱን ልታመቻች ነው

ቀን:

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን እያደረጉ የሚገኘውን ድርድር በማመቻቸት በታዛቢነት ስትሳተፍ የቆየችው አሜሪካ ሦስቱ አገሮች ስምምነት የሚያደረጉበትን የሕግ ሰነድ የማርቀቅ ሒደት ልታመቻች ነው።

የሦስቱ አገሮች የሕግና የቴክኒክ ባለሙያዎች በግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ እስካሁን ድረስ በተደረገው ድርድር ስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ወደ ሕግ ማዕቀፍነት እንዲቀይሩ፣ ይህንንም እስከ የካቲት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ እንዲያጠናቅቁ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር።

የመጨረሻው ድርድር በተካሄደበት ዋሽንግተን ዲሲ ቆይተው ስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ወደ ሕግ ሰነድነት እንዲቀይሩ ኃላፊነት የወሰዱት የሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች ግን፣ በተባለው ጊዜ ውስጥ ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻላቸው ታውቋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፋት መረጃ፣ የሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ለማዘጋጀት ሲያደርጉት የነበረው ውይይት፣ በዚህም ዙር ሳይቋጭ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ይህንን ተከትሎ ሦስቱ አገሮች በአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ድረ ገጽ ላይ ባወጡት የጋራ መግለጫ አሜሪካ በገንዘብ ተቋሟ በኩልና በዓለም ባንክ የቴክኒክ ድጋፍ በመታገዝ፣ በወሩ መጨረሻ ላይ ለሦስቱ አገሮች ፊርማ የሚቀርብ የስምምነት ሰነድ የማርቀቅ ሒደቱን እንደምታመቻች ይፋ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በተመሳሳይ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ በአሜሪካ በተደረገው የሦስቱ አገሮች ድርድር የተወሰነ መሻሻል ቢኖርም እ.ኤ.አ. ፌብሯሪ ወር መጨረሻ ቀነ ገደብ ስምምነት ለመፈራረም ብዙ ሥራ እንደሚቀር ገልጸዋል።

 አክለውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና እሳቸው የሚመሩት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በቀጣዮቹ ቀናት ድርድሩን የተመለከተ ብሔራዊ ውይይት እንደሚጠራ፣ በዚህም ውይይት የሚመለከታቸው ተቋማት፣ ባለሙያዎች ያገባናል የሚሉ ዜጎች እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሴክሬታሪ ማይክ ፖምፒዮ በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ የታወቀ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ጉዟቸው ዋና ዓላማም ይኸው የህዳሴ ግድብ ድርድርን የተመለከተ እንደሆነ ተገልጿል።

ሦስቱ አገሮች የሚያደርጉትን ድርድር አሜሪካ በአመቻችነትና በታዛቢነት እንድትከታተለው የጠየቀችው ግብፅ ስትሆን፣ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማሟላት ከግብፅ የምትሻውን ድጋፍ ለማግኘት እሷም ግብፅ በዓባይ ውኃ ላይ ያላትን ጥቅምና ፍላጎት ለማስከበር፣ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እያሳደረች እንደምትገኝ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በበኩሏ የህዳሴ ግድቡንም ሆነ የዓባይን ውኃ የመጠቀም የትውልዶች መብት ለማንም አሳልፋ እንደማትሰጥ፣ ነገር ግን በታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት እንደማታደርስና በትብብር እንደምትሠራ ይፋ አድርጋለች። እስካሁን በተካሄደው ድርድር ስምምነት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል ለድርቅ ወቅትና ለከባድ የድርቅ ወቅት የተሰጡት ትርጓሜዎች ይገኙበታል።

ለእነዚህ ሁኔታዎች የተሰጠው ትርጓሜ ወደ ህዳሴ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን መሠረት ያደረገ ነው። በዚህም መሠረት ወደ ግድቡ የሚደርሰው የውኃ መጠን 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ከሆነ የድርቅ ወቅት አመላካች እንደሚሆን፣ ወደ ግድቡ የሚደርሰው የውኃ መጠን 31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብና ከዚያ በታች ከሆነ ደግሞ የከባድ ድርቅ ወቅት አመላካች እንደሆነ ስምምነት መደረሱን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ የሰጧቸው መግለጫዎች ያመለክታሉ።

ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አንድ ባለሙያ ረቂቅ የስምምነት ሰነዱን እንደተመለከቱት በመጥቀስ፣ ድርቅና ከባድ ድርቅን በተመለከተ ስምምነት የተደረሰው ኢትዮጵያ ወደ ግድቡ የሚመጣውን ውኃ በቀጥታ እንድታሳልፍና ክስተቱም ለተከታታይ ዓመታት ከቀጠለ በግድቡ ከያዘችው ውኃ ላይ እንድትለቅ የሚያስገድድ መሆኑን ገልጸዋል።

በስምምነቱ መሠረት የመጣውን 37 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ በቀጥታ እንድታሳልፍ፣ የድርቅ ሁኔታው ለተከታታይ ዓመታት ከቀጠለ ደግሞ በግድቡ ከተያዘው ውኃ ላይ በመልቀቅ ወደ ታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች በዓመት እስከ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ኢትዮጵያ እንድትለቅ ግዴታን እንደሚጥል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ካላደረገች ቅጣት የሚጣልባት፣ ቅጣቱም በግድቡ የያዘችውን ውኃ በአምስት ዓመት ውስጥ የመልቀቅ ግዴታን የሚጥል እንደሆነ አስረድተዋል።

በመሆኑም ግድቡ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ፍላጎት ለማሟላት ሳይሆን፣ በድርቅ ወቅት ለግብፅ አገልግሎት የሚሰጥ መጠባበቂያ ሲሉ ተችተዋል። በመፍትሔተነትም ይህ ድርድር የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጓዳ መሆኑን በማስረዳት አቋርጣ መውጣት እንዳለባት ያሳስባሉ።

አሁን ባለው ድርድር ስምምነት ካልተደረሰ ሦስቱ አገሮች ገለልተኛ አካል እንዲያሸማግላቸው ሊያደርጉ እንደሚችሉ የድርድሩ ገዥ በሆነው የመርህ መግለጫ ስምምነታቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከጥቂት ሳምንታት በፊት በደቡብ አፍሪካ ባደረጉት የሥራ ጉብኝትና ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የኅብረቱ ሊቀመንበር ሆነው የተሰየሙት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንትን እንዲያሸማግሉ ጥያቄ አቅርበውላቸው መስማማታቸው ታውቋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...