Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

እሑድ ጥር 17 ቀን 2012 ዓ.ም. በወጣው ዕትም አቶ መስፍን አበራ (ከሰሜን ማዘጋጃ) የሳምንቱ ገጠመኝ በተሰኘው ዓምድ የጻፈውን አነበብኩ፡፡ መስፍን (በተለይ ስለውርስ ጠያቂዎቹ ልጆች) የጻፈው ትርክት እውነት ነው ብዬ ለመቀበል ተቸግሬአለሁ፡፡ ዳንኤል ክብረት በአንድ ወቅት ያነበባችሁትን ወይም የሰማችሁትን ነገር ዝም ብላችሁ እንደ ጋማ ከብት አትዋጡ፣ አላምጡት ብሎ የመከረን ይታወሳል፡፡ እናም እኔ ነገሩን ካላመጥኩ በኋላ የሚከተለው አስተያየት፣ ጥያቄና ጥርጣሬ በአዕምሮዬ ስለዞረ በጋዜጣው እንዲወጣ ይፈቀድልኝ፡፡

ይኼ የድሮውን ዘመን እንደገነት የመቁጠር፣ የዛሬውን ዘመን እንደ ሲኦል የመቁጠር ሁናቴ በብዙ ሰዎች ዘንድ ሲንፀባረቅ ይታያል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ መስፍን አንዱ ነው፡፡ የድሮው ዘመን ጨዋነት የተሞላበት ፈሪኃ እግዚአብሔር የሰፈነበት፣ የዛሬው ዘመን ግን ደግነት የሌለበት ታማኝነት የጎደለበት አድርገው ያቀርቡታል፡፡ የወሬ ማድመቂያ ያረጉታል፡፡ ይህ ግን ትክክል አይመስለኝም፡፡ ለምን ቢባል የጅምላ ንግግር የጅምላ አጻጻፍ ስለሆነ፡፡ ድሮ ጨዋ ልጆች ነበሩ፣ ዛሬም ጨዋ ልጆች አሉ፡፡ ድሮ ባለጌ ልጆች ነበሩ፣ ዛሬም ባለጌ ልጆች አሉ፡፡ ድሮ ፈሪኃ እግዚአብሔር ያደረባቸው ሰዎች ነበሩ፣ ዛሬም አሉ፡፡ ይኼንን መስፍን መገንዘብ አለበት፡፡

መስፍን በጽሑፉ እናትና አባታቸውን በቁማቸው መውረስ የፈለጉት ልጆች ስድስት መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡ እነዚሁ ልጆች የተማሩ ከመሆናቸው በላይ አግብተው ጎጆ መውጫ ሁሉ የተሰጣቸው፣ ቦታ ቦታ የያዙ ናቸው፡፡ ስድስቱ ልጆች ትዳር ይዘዋልና ከሚስቶቻቸው ወይም ከባሎቻቸው ጋር 12 ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

- Advertisement -

እነዚህ ሁሉ ልጆች ነፍስ ያወቁ፣ ያገቡ፣ የተማሩ ክፉና ደጉን መለየት የሚችሉ ሰዎች ያልተማረ ማገናዘብ የማይችል መንደረኛ “አሲቡሲ” ይመስል ወላጆቻቸውን በቁማቸው ንብረት ካላወረሳችሁን ብለው ስቃይ አደረሱባቸው፣ ደበደቡዋቸው ብሎ መስፍን የጻፈውን ትርክት ለማመን ተቸግሬአለሁ፡፡

መስፍን በጽሑፉ ልጆቹ ወላጆቻቸውን ከቃል ማስፈራራት አልፈው መደባደብ ጀመሩ በማለት ይጠቅስና ወረድ ብሎ ግን አባቱን የደበደበው አንደኛው ልጅ ብቻ እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ እናትየዋ ለመገላገል ጣልቃ ሲገቡ “በልጃቸው ቡጢ” አራት ጥርሳቸው እንደረገፈና የመንጋጋ አጥንታቸውም እንደተሰበረ ጠቅሷል፡፡

ሁሉም ልጆች የውርስ ጥያቄ አቅርበዋል ከተባለ ከነሱ ውስጥ አንዱ ብቻ ተነጥሎ አባትና እናቱን መደብደብ ውስጥ እንዴት ሊገባ ቻለ? ደግሞስ እናት በገዛ ልጃቸው ቡጢ (ምናልባትም በአንድ ቡጢ) ደረሰባቸው የተባለው ውልቃትና ስብራት የሚታመን ነውን?

ልጆቹ ሁሉም (ልብ በሉ፣ ከእነ ባለቤቶቻቸው 12 ናቸው) አባታቸው ቀብር ላይ አልተገኙም ተብሏል፡፡ ከነዚያ ሁሉ የተማሩ የተዳሩና የተኳሉ ልጆች አንደኛውም እንኳን በአባቱ ቀብር ላይ አልተገኘም ተብሎ የተጻፈው የሚታመን አይደለም፡፡

 አባትና እናት ተስማምተው ባዘጋጁት ኑዛዜ መሠረት ንብረታቸው ለሕፃናት ማሳደጊያና ለአረጋውያን መጦሪያ እንዲውል አደረጉ ሲል መስፍን የጻፈውም ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ ከልጆቹ ውስጥ ቀይ መስመር አልፎ ወደ ድብደባ የተራመደው አንዱ ልጅ ብቻ ነው፡፡ ሌሎቹ ውርስ ከመጠየቅና ከማስፈራራት አላለፉም፡፡ እናም በአንዱ ልጅ ጥፋት ወላጆቻቸው እነዚያን ሁሉ ልጆች በኑዛዜ ከውርስ ነቀሏቸው ብሎ መስፍን የጻፈውን (ለዚያውም በውርስ የተነቀሉበት ምክንያት በኑዛዜው ሳይጠቀስ) ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡

የባላቸውን ሞት የሰሙት እናት ከባላቸው ጋር ተስማምተው ያዘጋጁትን ሕጋዊ ኑዛዜ ለዘመዶቻቸውና ለሽማግሌዎች አስረከቡ የተባለውም ሌላ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እንደሚታወቀው ሁለት ሰዎች በአንድ ሰነድ ተናዝዘው ከፈረሙ ኑዛዜው በፍትሕ ብሔር ሕግ ቁጥር 858 መሠረት ፈራሽ ነው፡፡ አይፀናም፡፡ እናም የእነዚያ ሁሉ የተማሩ ልጆች ወላጆች ባለፀጋዎች አንድ የመንደር ጠበቃ እንኳን ሳያማክሩ ያንን የመሰለ ኑዛዜ ሊፈርሙ አይችሉም፡፡

በአጠቃላይ አቶ መስፍን በጋዜጣው ላይ ያሰፈረው ትርክት የፈጠራ ሥራ (ፊክሽን) ይመስለኛል፡፡ ምንም ውሸት የሌለበት ነው ብሎ በአቋሙ የሚፀና ከሆነ ከዚህ በላይ ለዘረዘርኳቸው ጥያቄዎችና ጥርጣሬዎች በቂ ምላሽ እንዲሰጥ እንዲጠይቅልኝ እለምናለሁ፡፡

(በዛወርቅ ሺመላሽ፣ ከመሿለኪያ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ