በሊንዳ ዮሐንስ
‹‹መደመር›› የተሰኘውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን መጽሐፍ የገዛሁት በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በሥልጣን ላይ ባለ መሪ ለኢትዮጵያ ዕድገት መመርያ እንዲሆን የተጻፈውን መጽሐፍ ባላነብ፣ ራሴን ኢትዮጵያዊ ብዬ ለመጥራት አፍ እንደማይኖረኝ ከራሴ ጋር ካደረኩት ሙግት በኋላ ነበር፡፡ የተወሰኑ ገጾችን ካነበብኩ በኋላ ግን ‹‹ማንበብ አለብኝ›› የሚለው ይህ ስሜት ማንበብ ወደ መፈለግና መጓጓት ተለወጠ፡፡
የመደመር መሠረታዊ ሐሳብ፣ ማኅበራዊና ቁሳዊ ሀብታችንን በመደመር ወደ አዎንታዊ ለውጥ አቋራጭ ስለመውሰድ ነው፡፡ ተከፋፍለን ከምናስገኘው ውጤት ይልቅ በአንድነት ውስጥ እጥፍ ድርብ ውጤት እንዳለ ይሰብካል፡፡ እንደ ግለሰቦች፣ እንደ ንግድ ተቋማት፣ እንደ መንግሥታት፣ እንደ አገሮች፣ እንደ የዓለም ክልሎች እንዲሁም አንዳችን ከሌላው ጋር እንደመራለን፡፡ እንደ ጸሐፊው አባባል የድህነት መንስዔው የመደመር አለመኖር ነው፡፡
መደመር የደሃ ሕዝቦች አገር ለሆነችው ኢትዮጵያ ዓለም የደረሰበት ላይ ለመድረስ ዕድል እንዲኖራት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የሚያሰሙት የማንቂያ ደውል ነው፡፡ በምሳሌ ብናየው የኢትዮጵያ የቡና ላኪ ነጋዴዎች ለገበያ መወዳደራቸው እንዳለ ሆኖ፣ የጋራ የሆኑ ግቦችን ለማሳካት ገበሬዎችን በጋራ በመደገፍ ወይም የጋራ ጎተራን የመገንባት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ መተባበርን ይመስላል፡፡ ወይም ደግሞ በአንድ ቤት ውስጥ የሚተባበሩ ሆኖም የግል ችሎታቸውን ለማውጣት የሚወዳደሩ የቤተሰብ አባላትን፡፡
እንደ ብሔራዊ ዕሳቤ የአፍሪካውያን ሁሉ ባህሪ ነው ተብሎ ከሚታሰበው ‹‹ኡቡንቱ›› ከሚባለው የደቡብ አፍሪካው ማኅበረሰባዊና አብሮነት ዕሳቤ ይልቅ፣ ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የተመቸ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ‹‹ኡጃማ›› ከሚባለው በስዋሂሊ ተመሳሳይ ፍቺ ካለው የታንዛኒያው ጁሊየስ ኔሬሬ ለአገሪቱ ሶሻሊስት ዕቅዳቸውን የገለጹበት በውስጡ የአንድ ፓርቲ ሥርዓት፣ ኢንዱስትሪዎችን ብሔራዊ ማድረግና ግብርናን በተደራጀ የደቦ ሥርዓት ማካሄድን ከሚያካትተውም ዕሳቤ እንዲሁ፡፡
መደመር በሰው ልጆች ሁሉ ውስጥ ያለው የውድድርና የመተባበር ባህሪ በፍፁም ሚዛን ታርቀው የሚሄዱበት ዕሳቤ ነው፡፡ መወዳደርና መተባበር፣ ሰዎች የምሉዕነት ስሜት እንዲሰማቸው የየራሳቸውን ሚና የሚጫወቱና አንዱ በአንዱ የማይተካ የተፈጥሮ ሕግጋት ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ሰዎች ማኅበራዊ ግንኙነቶችን የሚያደርጉት፣ ለመተባበርና ለመወዳደር። አንድ ሰው ከሌሎች ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ከመጠን ያለፈ የመወዳደር ስሜት ካለው፣ አንዳቸው ከግንኙነቱ ራሳቸውን ማግለላቸው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ምሉዕነት ከማግኘት ይልቅ የባዶነት ስሜትን ስለሚያበዛ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ግንኙነቱ ከመጠን በላይ ትብብር የበዛበት ከሆነ፣ የፈጠራና ሥራን የማሳለጥ ብቃት እንዲዳከም ስለሚያደርግ፣ ሰዎች ውድድር ባለመኖሩ ምክንያት ተነሳሽነታቸው ስለሚጠፋ ከግንኙነቱ ይሸሻሉ፡፡ ሰዎች ከኅብረት ሲሸሹ ደግሞ ብቸኝነት ይፈጠራል፡፡
የመደመር ዕሳቤ ጥልቀት፣ ስፋትና ልዩነት ያለው በመሆኑ ለአገሪቱ ፖለቲካዊና ሥነ ምጣኔያዊ መመርያዎች መሠረት ሆኖ ከማገልገልም አልፎ፣ ከታሪካችን ሊወረሱ የሚገባቸውን ነገሮች የያዘና አሁን ላለውም ወደ ፊት ለሚመጣውም ትውልድ ሊያገለግል የሚችል ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ መደመር ንድፈ ሐሳብ ብቻ ነው። ተፈጻሚነቱንም ለመገምገም ይከብዳል፡፡ ሆኖም የመደመር ታላላቅ ተስፋዎች ፍሬ ያፈሩ ዘንድ በትዕግሥት፣ ሐሳበ ሰፊ በመሆን፣ ጠቃሚ የሆኑ አስተያየቶችንና ሒሶችን በመስጠትና ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ማዳበር ይኖርብናል፡፡
በመደመር ገጾች ውስጥ
አሁን ስለጠቅላይ ሚኒስትራችን በሕዝብ ዘንድ ያለው አስተያየት የተለያየ በመሆኑ፣ መጽሐፋቸውን ይዤ ስታይ ትንሽ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ ከፊት ለፊቴ ካስክ ውስጥ የነበሩ ሴቶችም ያሳዩኝ አስተያየት ይህንኑ የሚያመላክት መሰለኝ። ለማንኛውም መጽሐፉን ቶሎ መጨረሴ ጠቅሞኛል፡፡
መጽሐፉ ሦስት ዓበይት ክፍሎች አሉት፡፡ የመጀመርያው ክፍል ስለመደመር ዕሳቤ ይተርካል፡፡ በተለመደው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥተኛ፣ ቀልድ አዘልና ውስጥን በሚያነሳሳ የአነጋገር ዘይቤ ስለመደመር ባህሪያትና ለመደመር አስፈላጊ ስለሆኑ ቅድመ መጠይቆች፣ በዋነኝነት ስለቅንነት ያብራራል፡፡ ሥልጣን ላይ ያሉትን ለማስደሰት ማሸርገድን ጨምሮ አሁን ላይ የሚስተዋሉ የኢትዮጵያውያን አሉታዊ ባህሪያትንም ይገልጻል (‹‹በአገራችን ይህ የአድርባይነት አስተሳሰብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት የሕዝብን ድጋፍና ተቃውሞ መለየት እስኪሳነን ድረስ ደርሶ ነበር፡፡››ገጽ 67)፡፡ ሕዝቦች ሀቀኛና ጠንካራ ሠራተኛ እንደሆኑ ያለውን አዎንታዊ ተፅዕኖም አስረግጦ ያብራራል፡፡
ይህ ክፍል የኢትዮጵያን አብዮታዊ፣ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በጥልቀት ይወቅሳል፣ እንዲሁም ያወድሳል፡፡ ሆኖም ስላለፉት ባለሥልጣናት ‹‹ሰነድ የሚሸጥ›› ጽሑፍ በጭራሽ አይደለም፡፡ እንዲያውም ስላለፉት መንግሥታት ጥፋት ሲገልጽ ከአድራጊዎቹ ይልቅ ድርጊቶቹ ላይ በማተኮር፣ ቁጥብነት በሚታይበት መንገድ በደፈናው መነገር የሚገባውን በደፈናው፣ የተወሰነ አካልን መውቀስ በሚያስፈልግበት ጊዜ ደግሞ በግልጽ የሚናገር ጽሑፍ ነው። ጸሐፊው ያለፉ መሪዎችን ወይም ሁነቶችን በስም ብዙም አይጠቅሱም፡፡ ሆኖም በመጀመርያው ምዕራፍ ስለሜቴክ እንዲህ ተብሏል፡፡ ‹‹መንግሥት ቀስ በቀስ ከገበያው እየወጣ ይሄዳል የሚለው መርህ ተዘንግቶ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በፕራይቬታይዜሽን ወደ ግል ካዞርናቸው ተቋማት የሚበልጡ ተቋማትን እንደገና አቋቋምን። በብረታ ብረትና መሰል ግዙፍ ዘርፎች እንዲሰማሩ ያቋቋምናቸው ተቋማት ቴሌቪዥን መገጣጠም ጀመሩ ብለን ፈነደቅን።››
የመጽሐፉ የመጨረሻዎቹ ሁለት ክፍሎች ደግሞ ከፍልስፍና ይልቅ፣ ስለኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ተቋማዊ ነባራዊ ሁኔታ የሚተነትኑ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በመዋቅራዊና ግለሰባዊ ጭቆና ምክንያት የተከሰቱ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ፖለቲካችን የዘረኝነት ጉዳይ ጎልቶ እንዲታይበት ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ በድሮ ጊዜ የነበረው ጭቆና ነው፡፡ አንድ የኅብረተሰብ ክፍል የመጨቆን ታሪክ ካለው ሰዎች ስለ ዘር ማንነታቸው፣ (ከትውልድ፣ ከመደብ ከፆታ ማንነታቸው በላይ) ያላቸውን አመለካከት ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ዓብይ አህመድ እንደሚገልጹት ዘር ሕዝብን ለትግል ለማንቀሳቀስ የሚያገለግለው ግን፣ በዋነኝነት ልሂቃን ዘርን ለፖለቲካ እንቅስቃሴ መጠቀሚያ አድርገው በሚያውሉበት መጠን ነው፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ ተቋማት ቴክኒካዊ ብቃት በሌላቸው፣ ሕዝቡን ማገልገል በማይፈልጉ፣ የግል ጥቅማቸውን ከማኅበረሰቡ ደኅንነት በሚያስቀድሙ፣ ራሳቸውም አግባብ ባልሆነ መንገድ ቦታውን በያዙ ሰዎች የተሞላ እንደሆነ መደመር ይገልጻል፡፡ ተቋማት ሥር የሰደደ የግትርነት ችግር አለባቸው፡፡ ሆኖም ለውጥ ግን ቀላል አይሆንም፡፡ እንደ ቢፒአርና ካይዘን ባሉ በተደጋጋሚ የተነሱ አገር አቀፍ እንቅስቃሴዎችም የተነሳ በአገሪቱ ውስጥ ‹‹የለውጥ ዝለት›› አለ። ይልቁንም እንደ ጸሐፊው የሚያስፈልገን በጠንካራ አመራር የተደገፈ፣ በለውጥ ሐዋርያት የሚመራ እንደ ዘርፉ ልዩ ባህሪይ ለየዘርፉ የሚተለም ለውጥ ነው፡፡
ከምዕራፍ አምስት እስከ አሥር ያለው ክፍል በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ሐደት ውስጥ የተስተዋሉ መልካም ሁኔታዎችንና ህፀፆችን ያብራራል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የዘር ክፍፍል መሠረታዊ ምክንያቶች በመዘርዘር፣ ክፍፍሉን አቻችሎ አገራዊ መግባባትና ሰላም ለማምጣት የሚረዳ መመርያ ያቀርባል፡፡ በጣም አከራካሪ ለሆኑት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥያቄዎች ደግሞ የክርክሮቹ መሪዎች አመለካከታቸውን በመደመር አመለካከት መቃኘት እንዳለባቸው መጽሐፉ የሚያሳስብ ይመስላል፡፡ ይኸውም እነዚህ አካላት ሰላማዊ ውይይቶችን እንዲያደርጉ፣ ለተከታዮቻቸውም መልካም መሪ በመሆን ለማሳመን እንዲሞክሩ፣ ታማኝነትን ለመግዛት እንዳይሞክሩ፣ ያለፈውን እንዲያልፍ በመተውና የከፋ ኢፍትሐዊነት ያጋጠመበት ታሪክ ካለ ደግሞ፣ ጥልቅ ጥናት በማድረግ እውነቱን አጣርቶ ስህተትን ማረምና ሁልጊዜም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ዘር ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ ሌሎች የማንነት ቡድኖችን ለመመሥረት ማሰብ እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡
ምዕራፍ ስድስት ምናልባትም በጣም አስደሳች የሆነውን ርዕስ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ዴሞክራሲ ያስፈልጋታል?›› የሚለውን ይዳስሳል፡፡ ጸሐፊው ኢትዮጵያዊ የሆነ ዴሞክራሲ የመገንባት ሒደት እንዴት ማስጀመር እንዳለብን ያስረዳሉ፡፡ በመጀመርያ በልዩነት ላይ ባተኮሩ ፓርቲዎች መካከል ትብብርን የሚያበረታታ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሊኖረን ይገባል፡፡ ባለፈው የሕገ መንግሥት ግንባታ ወቅት ማኅበረሰባዊ ብሔርተኞች ላይ በማተኮር፣ ገሸሽ ተደርገው ከነበሩ ሲቪክ ብሔርተኞች ጋር ቀጣይነት ያለው ድርድርም ያስፈልጋል፡፡
ይህንን ደግሞ ያለ አድልኦና ቅሬታ ለማድረግ አገራዊ ሰላምና ዕርቅ ላይ ቀድሞ ሊደረስ ይገባል። ጥልቅ የሆነ ጥናትና ታሪካዊ ኢፍትሐዊነትን ለማጥራት እውነታን የመፈለግ ሥራም ሊያስፈልግ ይችላል። ከዚህ በፊት ተጨቁነው የነበሩ የኅብረተሰብ ድምፆች የሚናገሩበት አገራዊ መድረኮች ሊዘጋጅ ይገባል። ልሂቃንና የአገሪቱ ምሁራን ከውድድርና ከትብብር ዕጦት የተነሳ ብቻቸውን እየሞቱ ካሉበት ሊወጡና በንቃት ሊሳተፉ ይገባል፡፡ እንዲሁም ሕዝባዊ ማኅበራትና ሚዲያዎች ሊጠናከሩና ምክንያታዊ አስተሳሰብን ሊያስተምሩ ይገባል፡፡ ይህ ሒደት በሙላት መንቀሳቀስ ሲጀምር ልዩ የሆነ፣ ለእኛ ማንነት የሚስማማ ዴሞክራሲ መታሰብ ይጀምራል ይላሉ፡፡
ምዕራፍ ዘጠኝ ስለአመራር ዓይነቶች በማስረዳት ራሳቸው መሪውን የምንገመግምበትን ጠቃሚ መሥፈርት ይሰጣል፡፡ ከምዕራፍ አሥራ አንድ እስከ አሥራ ስድስት ያለው ክፍል ከሞላ ጎደል ሙያዊ (ቴክኒካዊ) ነው፡፡ ስለኢትዮጵያ ሥነ ምጣኔና ፖለቲካ ሊታሰቡ የሚችሉ ርዕሶችን ሁሉ በመዳሰስና ጉዳዮቹን በመደመር ዓይን እንዴት እንደሚታዩ አጭር አስተያየት ብቻ በመስጠት፣ የትምህርት መጽሐፍ በሚመስል ደረቅ አገላለጽ ያቀርባል። የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን፣ የኢኮኖሚ ሥርዓቱ መዛባቶችን፣ ሥራ አጥነትን፣ የገቢ ልዩነትን፣ የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ውድቀትን፣ የውጭ ዕርዳታን፣ በግሉ ዘርፍና በንግድ ውስጥ የመንግሥት ተሳትፎን በተመለከተ ምክንያታቸውንና ውጤታቸውን፣ እንዲሁም በመጨረሻ ስለመደመርና የውጭ ግንኙነትን በተመለከተ ይዳስሳል፡፡
ሐሳቡ ጥልቅ ነገሩ ጥብቅ
መጽሐፉ የንግድ ዓላማ የለውም፣ የሽያጭ ገቢውም ለገጠር ትምህርት ቤት ግንባታ እንደሚውል ተገልጿል፡፡ ባይሆንም ግን መደመር ራሱን ለመሸጥ የሚሞክር መጽሐፍ አይደለም። መጽሐፉ ብዙ ጊዜ በአገራችን እንደሚስተዋለው ሳይሆን ዲዛይኑ፣ አርትኦቱና የኅትመቱ ጥራት ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ነው ማለት ይቻላል። ሆኖም ልክ በቴሌቪዥን እንደምናየው የዓብይ አህመድ መጽሐፍ አጻጻፍ ‹ውሰዱት ወይም ተውት› ዓይነት ድምፀት አለው፡፡ መግቢያው አንባቢን አንቆ ለመያዝ አይሞክርም፡፡ አንባቢውንም እንዲያነበው የሚለምን ዓይነት አይደለም። ጸሐፊው የእኔ ያሉትን እውነት ረጋ እና ቀለል አድርገው ነው የገለጹት። ሐሳብ የመሰብሰብ ችሎታውና ራስን የመጠራጠር ፍንጭ እንኳን የሌለው መሆኑ ድንቅ ነው፡፡
ከመጽሐፉ የምረዳው አንድ ነገር ቢኖር ጸሐፊው ለሚዛናዊነት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ ነው። ሚዛናዊነት በወግ አጥባቂነትና በተራማጅነት መሀል፣ ሚዛናዊነት በብሔርተኝነትና በሲቪክ ብሔርተኝነት መሀል፣ ሚዛናዊነት ባህላዊ ዕውቀትን ይዞ በመቀጠልና የውጭውን ዕውቀት በማስገባት መሀል። ጸሐፊው አዲስ ዕውቀትን ለመፈልሰፍ ዓላማ እንደሌላቸው ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ዕውቀት ሁላችንም የምንጋራው፣ የሁላችንም ንብረት የሆነ ፀጋ እንደሆነ መርሳት የለብንም፤›› ይላሉ፡፡ የመደመር ሥነ ምጣኔያዊ አስተሳሰብም በዓለምና በኢትዮጵያ ከካፒታሊዝምና ከሶሻሊዝም ልምድ በመውሰድ የተወለደ አስተሳሰብ ይመስለል፡፡ መደመር ዕድሜ ልክ ከቆየ ጥልቅ ሐሳብና የሁለት ፅንፍ አመለካከቶችን ካሰላሰሉ በኋላ የመነጨ ንድፈ ሐሳብ ይመስላል፡፡ ሆኖም መደመር ከምሳጤ አስተሳሰብ የተወለደ ቢመስልም ኃይለኛና ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው፡፡ በአንድ ቦታና ጊዜ ከተገደበ ዕምነት ይልቅ፣ ጊዜ የማይገድበው የማሰቢያ መሣሪያ ነው፡፡
መደመር ከሞላ ጎደል የፍልስፍናም መጽሐፍ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለእውነት፣ ጊዜ፣ የሰው ልጆች እርካታ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ስላለው ዋጋና ስለዴሞክራሲ ለማንበብ ደስታን በሚሰጡ አጻጻፎች አቅርቧል። አስተሳሰባችንን ካለፈው ልምዳችንና ለወደፊቱ ካለን ተስፋ ማስተካከል እንዳለብን የገለጹት አንዱ የማልረሳው በውስጤ የቀረልኝ ምሳሌ ነው፡፡ ‹‹የዛሬውን ጉልበታችንን የሚያጠነክር፣ ከትናንት የወኔ ስንቅ የሚቀበል የተስፋ መነጽር ነው የሚያስፈልገን። ትናንትን ከዛሬ ጋር ፈትለን ከህልማችን ሰም ውስጥ ስንነክረው ነው ተስፋችን ጧፍ ሆኖ ጭለማውን የሚያሻግረን፤›› ይላሉ፡፡
የተስፋችን ጧፍ
መደመር ቀለል ባለ ቋንቋ ቢሆንም የተጻፈው ነገሮችን የሚያቃልል ግን አይደለም፡፡ አማርኛው በጣም መሳጭ ነው፡፡ እንዲያውም ለመጀመርያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋሉ ናቸው ብዬ ያሰብኳቸውን ቃላት አግኝቼበታለሁ (ውላጅ፣ ዳረጎት መንግሥታት፣ ራስ–በቅ፣ ክሱትነት፣ ቀቢፀ–ተስፋ አዲስ ቃላት ካልሆኑ ጥፋቱ የእኔ ይሆናል)፡፡ ይህን ለመሰለ ኦፊሴላዊ አጻጻፍ አማርኛው ባልተለመደ ሁኔታ ምቹ ነው፡፡ እንግሊዝኛ ጭራሽ አይጠቀምም ማለት ይቻላል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ መደመር ቀላል መጽሐፍ አይደለም፣ በተለይ ደግሞ ሁለተኛው ክፍል፡፡ የመጨረሻዎቹን ምዕራፎች ለመጨረስ ትንሽ ትዕግሥት የሚፈልግ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የመጽሐፉ አንባቢያን ሊሆኑ የሚችሉት የረዥም ንባብ ልምድ ያላቸው በደንብ የተማሩ ኢትዮጵውያን ናቸው ማለት ነው፡፡
ይህ ደግሞ ስለማንበብ ባህላችን እንዳስብ ያደርገኛል፡፡ ‹የተማሩ ኢትዮጵያውያን› ከሚባሉት ውስጥ ምን ያህሉ ይህንን መጽሐፍ አነበቡት? ምን ያህሉስ የፖለቲካ ልዩነትን አሳበው ሳያነቡት ቀሩ? የሌሎችን ሐሳብ ለመረዳትና ራሳችንን ለመግለጽ ምን ያህሎቻችን በእውነት እንችላለን የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ያ ደግሞ ለዴሞክራሲ ወሳኝ ነው፡፡ ምክንያቱም ዴሞክራሲ ‹‹የአላዋቂ ብዙኃን›› አገዛዝ እንዳይሆን ነው፡፡
በመጽሐፉ መገባደጃ ላይ ጸሐፊው በውስጤ እየጠየቅኩ የነበረውን ብዙኃኑን ለመድረስ በሌላ መንገድ ቢቀርብ የተሻለ ተቀባይነት ይኖረው ነበር ወይ የሚለውን ጥያቄ ዳሰዋል፡፡ መጽሐፉ በሌሎች ዓይነት ቅጂዎች እየመጣ ነው፡፡ በተጨማሪም በእንግሊዝኛም ቅጂ እየመጣ ነው፡፡
ሳጠቃልል ለመጽሐፉ ያለኝ ምሥጋና ቁጥብ መሆን እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ ብዙ ማድነቁ የጥልቀት ማጣት ተደርጎ ሊወሰድ ስለሚችል ወይም ምሥጋና ሲበዛ አመዛዝኖ አሳቢነትን ጥያቄ ውስጥ እንዳያስገባው ከመሥጋት ነው። እውነታው ግን በመጽሐፉም ሆነ መጽሐፉን ለመጻፍ ተነሳስተው ስለጀመሩት፣ ጀምረውም ስለጨረሱት በጣም ተደምሜያለሁ፡፡ መደመርን እንድታነቡት አበረታታለሁ፡፡ ችግር የሚያረዱ ሰበር ዜናዎችን በሰማችሁ ቁጥር ያጣችሁትን ተስፋ ለማደስ ስትሉ አንብቡት፡፡
ኢትዮጵያ ልዩ አገር እንደሆነች ያላችሁን እምነት የሚገዳደሩ ንግግሮችን ወደ ጎን ትታችሁ፣ በእምነታችሁ እንድትቀጥሉ አንብቡት፡፡ ኢትዮጵያ የአንባቢያን አገር እንድትሆን የምትወስዱት የመጀመርያው ዕርምጃ ስለሚሆን አንብቡት፡፡ አንድ ሰው እውነቱን ለማስረዳትና መልዕክቱን ለማስተላለፍ ለሚያደርገው ሙከራ ክብር ለማሳየት ስትሉ አንብቡት፡፡ እናም ሌሎች እውነት ካላቸው እንዲሁ በሥርዓት ማቅረብ እንዳለባቸው መልዕክት ለማስተላለፍ አንብቡት።
ከአዘጋጁ፡– ይህ ጽሑፍ በመጀመርያ በ‹‹Ethiopia-Insight.com›› ላይ በእንግሊዝኛ የታተመ ሲሆን፣ ይህ ትርጉም በማህሌት ልሳነ ወርቅና በሊንዳ ዮሐንስ ነው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡