Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉክቡር ምክትል ከንቲባ ከተማዋን በአግባቡ እየመራሁ ነው ብለው ያስቡ ይሆን?

ክቡር ምክትል ከንቲባ ከተማዋን በአግባቡ እየመራሁ ነው ብለው ያስቡ ይሆን?

ቀን:

በቱራ ከተማ

ክቡር ምክትል ከንቲባ ጤና ይስጥልኝ፡፡ አክብሮታዊ ሰላምታዬ ካለሁበት ይድረስዎ፡፡ እኔ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የከተማው አስተዳደር የሥራ ባልደረባ ነኝ፡፡ ጽሑፌን ሚዛናዊ ለማድረግ የሥራ ባልደረቦቼንና ወደ መሥሪያ ቤታችን የሚመጡ ባለጉዳዮችን በማነጋገር የተዘጋጀ ጽሑፍ ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ የከተማዋ ነዋሪ በመሆኔም አብዛኛው ጉዳይ ይገባኛል ባይም ነኝ፡፡ ክቡር ምክትል ከንቲባ ይህ የምጽፍልዎ አስተያየት በእውነተኛ መረጃና ራሴም በአካል ያረጋገጥኩት ለመሆኑ ቃል አገባለሁ፡፡ በቅድሚያ እየሠሯቸው ላሉት በጎ ተግባራት ከፍተኛ ምሥጋና ሊቸርዎ ይገባል፡፡ ለአብነት ያህልም በተለይ የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም፣ የትምህርት ቁሳቁስና የደንብ ልብስ ማሟላት ጉዳይን በተመለከተ ያደረጉት አስተዋጽኦ ዝንተ ዓለም የሚወደስና ሲታወሱ የሚኖሩበት ዓብይ ተግባር ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሚገኙባቸው ሃይማኖታዊ ሆኑ አገራዊ ጉዳዮች በሙሉ በተገራና ሥርዓት ባለው መንገድ የሚያደርጓቸውም ንግግሮች እንዲሁ ጨዋ ያሳደገው አሰኝቶዎታል፡፡ ሌላም በምግብ አቅርቦት፣ በዳቦ፣ በሌሎችም ሸቀጣ ሸቀጦች ለማዳረስ የሚያሳዩት ተግባር በተለይ አነስተኛ ገቢ ያለው የአዲስ አበባ ነዋሪ እንዲህ በቀላሉ ውለታዎን የሚዘነጋው አይደለም፡፡ ምንም እንኳን አንዳንዶች የተለየ ትርጉም ቢሰጡትም፡፡ ለዚህ ተግባርዎ የከተማው ወጣቶች ሽልማት አበረከቱልዎት ልበል? ይሁን ጥሩ ነው፡፡ ወጣቶቹ እነ ማን ናቸው? በምን መንገድ መጡ? ገንዘብ ከየት መጣ? የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ሽልማቱ አያንስዎትም፡፡ ክቡር ምክትል ከንቲባ በአሁኑ ጊዜ በሌላኛው ወገን የሚወቀሱበት በርካታ ጉዳይ መኖሩ ከእርስዎ የተሰወረ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በቅድሚያ የአስተዳደሩ ካቢኔ አባላትም ሆኑ በየክፍለ ከተማው ቁልፍ ቦታዎች የተመደቡ ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም የከተማው የአስተዳደር ፍርድ ቤት ሹማምንት በተመለከተ የግል ወዳጆችዎንና ጓደኞችዎን አስቀምጠዋል ይባላል፡፡ ይኼ ጉዳይ ከሐሜት የዘለለ በትክክል የፈጸሙት ተግባር ነው? አብዛኞቹ የካቢኔ አባላት እርስዎን የሚፈሩ ናቸው፡፡ በየተመደቡበት መሥሪያ ቤት የማኔጅመንት ስብሰባ፣ ሌሎችም ወሳኝ ጉዳዮች ላይ አይገኙም፡፡ የዘወትር ሥራቸው እርስዎን እንደ ታቦት አጅቦ መሄድ ነው፡፡ ይገርምዎታል የጀመሩትን ስብሰባ አቋርጠው ከንቲባው ፈለጉኝ ብለው ይዳሄሉ፡፡ እንዲያውም የተወሰኑ የግል ጥቅማቸውን ለማስቀደም የተሰበሰቡ ናቸው፡፡ ምቾታቸውን ብቻ የሚፈልጉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ብሔርን ጥላ በማድረግ ካለፈው ሥርዓት ጀምሮ፣ እስካሁን እየተሙለጨለጩና ለመጣው ባለሥልጣን ሲስቅ እየሳቁ፣ ሲያኮርፍ እየተደበቁ ዕድሜያቸውን ያራዘሙ ናቸው፡፡

ምናልባት የከተማዋም ለውጥ በአሁኑ ጊዜ የፌዴራል መንግሥት እጁን አስገብቶ በሚያከናውናቸው ተግባራት ችግሩ ተሸፍኖ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ሰው ግን እኔ በቢሮዬ ምን ሠራሁ? የሚል ሹመኛ ሕዝብ ይፈልጋል፡፡ አሁን አሁን እርስዎን በቴሌቪዥን ካየን አጠገብዎ፣ ከዚያም ቀጥሎ ማን ይቆማል? የሚለውን መገመት ቀላል ነው፡፡ የዘወትር ክስተት ስለሆነ፡፡ ክቡር ምክትል ከንቲባ ወደ እርስዎ የግል ባህሪ ስመለስም ያረጋገጥኩት ነገር አለ፡፡ ይኼውም እርስዎ ሁለት ዓይነት ገጽታ ያለዎት ሰው እንደሆኑ፣ ከዚህ ቀደም እንደ ልባችን የምንገባባት ማዘጋጃ ቤት ዛሬ መግባት ክልክል ነው፡፡ ቀጠሮ አለህ ወይ? የት ነው የምትሄደው? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች የሚያቀርቡት ገና ዋናው የጥበቃ ሠራተኞች የሚቆሙበት ቦታ ላይ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደ እኔ አመለካከት ስሙ ተቀይሮ በእርስዎ ጊዜ የአዲስ አበባ ቤተ መንግሥት ሆኗል፡፡ ለምን ቢባል የውጭ እንግዶችን የሚቀበሉበት፣ አስፈላጊ ሲሆንም የተለያዩ ግብዣዎች የሚያከናውኑበት ቦታ ነው፡፡ ከፋኝ፣ ሆድ ባሰኝ የሚል የከተማው ነዋሪ ከንቲባዬን ላናግር ቢል መግቢያም የለውም፡፡ ሌላው ቀርቶ በጋራ ቅሬታቸውን ለማቅረብ ቢፈልጉ ወደ ቅጥር ግቢው መግባት ሳይችሉ በአጥሩ ዙሪያ እንደ ቁራ ጮኸው የተመለሱት አያሌ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ሥራዎች የታይታ ናቸው፡፡

ሌላው በሙሉ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች ከግቢው እንዲወጡ ተደርጎ፣ የግለሰብ ሕንፃ በከፍተኛ ገንዘብ እየተከራዩ ሥራቸውን በማከናወን ላይ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ ከወጪው ባሻገር በሠራተኛ ሥነ ምግባር ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ፣ በራሱ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚኖረው አንድምታ ቀላል አይደለም፡፡ የኪራይ ሕንፃ ሲመረጥም ኮሚሽን ይጠይቃሉ፡፡ ክቡር ምክትል ከንቲባ ከላይ እንደገለጽኩልዎት ሕዝብ ፊት ሲቀርቡና ለብቻዎ ሲሆኑ የሚያሳዩት ተለዋዋጭ ባህሪ እንደ እኔ ቀረብ ብሎ ላስተዋለው ከበስተጀርባ ምን እየተካሄደ ነው ብሎ ቢጠራጠር አይፈረድበትም፡፡ እንደምናየው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግቢያቸውን ከፍተው ሲያስጎበኙ፣ የከተማው ነዋሪ በገዛ ከተማው የት ነው? ወዴት ነህ? መባሉ ተገቢ አይደለም፡፡ አስፈላጊውን ፍተሻ ፈፅሞ ቢፈልግ መዝናኛ ክበብ፣ ቢፈልግ ቀድሞ ወደ ነበረው ቤተ መጻሕፍት፣ ወይም እስኪ ማዘጋጃ ቤቱን ገብቼ ልየው ቢል ከልካይ ሊኖር አይገባም፡፡ እንዲያውም ቢቻል ፅዳቱ ተጠብቆ አንዳንድ የዕድሜ ባለፀጎች አረፍ ብለው የከተማውን ውበት እያዩ ሲጫወቱ ቢውሉ ምን ክፋት አለው? ከዚህ ቀደምም እነሱ ያቆዩልን ስለሆነ ክብር ይሰማቸዋል፡፡

ሌላው ልገልጽልዎ የምፈልገው ነዋሪውን እጅግ በጣም ያስመረረው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር በብዙ ዕንከኖቹ ይገለጻል፡፡ በዝምድና፣ በጉቦ፣ በባለሥልጣን ጣልቃ ገብነት ይለያል፡፡ አንድ የከተማ ነዋሪ መታወቂያ ለማውጣት የልደት ምዝገባ ምስክር ወረቀት ለማውጣት በከተማዋ ቢገኙ፣ በሁሉም ወረዳዎች ለማለት በሚያስችል ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ እንግልት ይገጥመዋል፡፡ በሌሊት ሄዶ መሠለፍ ይጠበቅበታል፡፡ ተሠልፎም አይደርሰውም፡፡ ሰው ፊት ለፊት እያየ ጉቦ የሚከፍለው ይስተናገዳል፡፡ ይህ በዓይኔ ያየሁት ክስተት ለመሆኑ በፈጣሪ ስም እምልልዎታለሁ፡፡ ይኼ ወሳኝ ኩነት በተባለ ቦታ የሚሠሩ አብዛኞቹ በቂ ዕውቀት የሌላቸው፣ ሕዝቡን የሚያስተናግዱት ደግሞ በማመናጨቅና ጉቦ በመቀበል ሲሆን ይህም የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ነው፡፡ ማንም ሄዶ ይህንን ማረጋገጥ ይችላል፡፡ ነዋሪ ላልሆነ መታወቂያ መስጠት፣ ነዋሪውን ማንገላታት፣ ለአብነት አራዳ ወረዳ 04/10፣ ቦሌ ወረዳ 10/11፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ አንድና ሌሎች፡፡ ክቡር ምክትል ከንቲባ በከተማዋ ከፍተኛ እሮሮ ከሚሰማቸው አንዱ የትራንስፖርትና የመንገድ ችግር ትልቅ መፍትሔ ይሻል፡፡ ሌላው ቢባል ቢባል መቼም የማይስተካከለው ዋነኛው መሥሪያ ቤት የመሬት ልማት ማኔጅመንትን በሥሩ የሚገኙት መሥሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ ይህንኑ መሥሪያ ቤት እርስዎ አሳምረው ያውቁታል፡፡ ከኃላፊ ጀምሮ ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች ላይ ጓደኞችዎን መድበው እያሠሩ ነው፡፡ መቼም አላደረግኩም ብለው አይዋሹም፡፡ ተሸፋፍነው ቢተኙ ገልጦ የሚያይ አምላክ አለና፡፡ ከማዕከል መሥሪያ ቤት እስከ ክፍለ ከተማ ድረስ በከተማ ፕላን ያላግባብ የመንገድ ጥናት እያወጡ፣ ቦታ እየሸነሸኑ ገንዘብ የሚደራደሩ ከፍተኛ የሆኑ ጥቅመኛ ሠራተኞች ያሉበት ነው፡፡ በመሬት ባንክና ማስተላለፍ ለሆቴል? ለፋብሪካ? ለምን አገልግሎት ቦታ ትፈልጋህ? ይህን ያህል አምጣ ይባላል፡፡ አብዛኞቹ ረዥም ጊዜ የሠሩ ኦፊሰሮች በገሃድ ጉቦ የሚቀበሉ ናቸው፡፡

ሌላው ፍፁም የባሰበት የጉቦኛ ዋሻ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ የትኛውም ባለሙያ የሠራው ፕላን ገንዘብ ካልተከፈለ ፀድቆ የማይወጣበት፣ በዚህ ላይ የሚጠየቀው ገንዘብ የትየለሌ መሆኑ፣ ከኮንስትራክሽን ማቴሪያል የበለጠ ባለጉዳዮችን ያስመረረው የግንባታ ፈቃድ ሠራተኞችና ኃላፊዎች የጥቅም ትስስር ሁኔታ ቀን ሰብስበው ማታ በየውስኪ ቤቱ፣ በየሠፈሩ ሲከፋፈሉ ሰው አይፈሩ፣ ፈጣሪን አይፈሩ፣ ኃላፊዎቹ ያለውን ለውጥ ደጋፊ መስለው ዛሬ አክቲቪስት፣ ነገ ብልፅግናን እደግፋለሁ እያሉ ፌስቡክ ይጠቀማሉ፡፡ ‹‹እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው›› ይኼን ወንበር ብቻ አይቀሙን የሚሉ የሕንፃ ሹም ዳይሬክተሮች አንድ ላይ ናቸው፡፡ አንድ ገንቢ ፕላን ሲያፀድቅ ለአራት ባለሙያ ጉቦ፣ ሰርተፍኬት ለሚፈርም ዳይሬክተር ጉቦ፣ ቦታው ላይ የሚፈርስ ካለ ለማፍረሻ ፈቃድ ጉቦ፣ ለግንባታ ማስጀመሪያ ጉቦ፣ በየደረጃው ስላቭ ሲሞላ እንደዚሁ፣ ሕንፃው ሲጠናቀቅ፣ የመጠቀሚያ ፈቃድ ሲጠየቅ ጉቦ፣ ይህን ሁሉ ጉድ የቻለ ነው እንግዲህ ሕንፃ የሚገነባው፡፡ የግንባታ ቁጥጥር በየሕንፃው እየዞሩ አምጣ፣ ስትሠራ ችግር አለበት፣ ዕንቢ ካልክ አስቆምሃለሁ፣ በዚሁ በኩል መስኮት ቀደሃል፣ ሌላም፣ ሌላም የበርካታ ሕንፃዎችን ፕላን ሲያፀድቁ፣ ሲሠሩ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ እናም የመኪና ማቆሚያው ወደ ሱቅነት ሲቀየርና ሌላም ሕገወጥ ተግባር ቢፈጸም እነሱ ምን ገዷቸው ኪሳቸው አይጉደል እንጂ፡፡

ሌላው የዚህ ክፍል አካል የሕንፃ መጠቀሚያ እጅግ የሚገርም የሥራ ሒደት እርስዎም ሌላውም ውሸታም ብሎ ይታዘበኝ፣ ምንም ዓይነት መጠቀሚያ ፈቃድ ያለ ጉቦ አይሰጥም፡፡ እርግጥ መጠኑ እንደ ግንባታ ፈቃዱ አይበዛም፡፡ እንዲህም ሆኖ የመንግሥት መኪና በራሳቸው አሽከርካሪነት ተሰጥቶዋቸዋል፡፡ ለሥራ በሾፌር ለምን አይጠቀሙም? ከዚህ ቦታ ላለመቀየር የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ደግሞም ይሳካላቸዋል፡፡ እንግዲህ ይህ ተግባር በቀጥታ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ወርዶ ላየው እንዲሁ ተመሳሳይ ነው፡፡ ልዩነቱ በጉቦ መጠን ላይ ብቻ ይሆናል፡፡ ክቡር ምክትል ከንቲባ በየስርቻው የሚፈጸመው ጉድ ብዙ ነው፡፡ ግን እዚያ ለመድረስ ቢያንስ አደባባዩን ማፅዳት ይበጃል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያየ መንገድ ይጥራሉ፣ ይለፋሉ፣ ሌላው አጋዥ መስሎ ኪሱን ያደልባል፡፡ አንዳንዱ በተለይ የመሬትና የመሬት ነክ ሠራተኛ ያጋበሰው ሀብት ቢቆጠር ምንም ያህል ነው ብሎ ለመገመት ይከብዳል፡፡

ሌላው ክቡርነትዎ በእርስዎ ዘመን ታሪክ ይቅር የማይለው ተግባር የከተማዋ የመሬት ወረራ ነው፡፡ እንዴ ምንድነው ነገሩ? በቦሌ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ለመናገር ከሚቻለው በላይ የመሬት ወረራ እየተፈጸመ ነው፡፡ ለሽፋን የሚጠቀሙበት ምትክና ካሳ ነው፡፡ በእውነት ከተማዋ ባለቤት የሌላት ሆናለች፡፡ ለዚህ ስድስት ወራት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ አንድ ብቻ 88 መሬት ተወሯል፡፡ የወረዳው ባልደረቦች ለሬዲዮ ፋና ሲገልጹ የሰማሁት ነው፡፡ በቦሌ ቡልቡላ በከተማው ያሉ ኪስ ቦታዎች ተወረዋል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ለደን የከለላቸውና አረንጓዴ ሥፍራዎች ሳይቀሩ በደላላ ጠቋሚነት ይታጠራሉ፣ ካርታ ይሰጣቸዋል፡፡ እውነት ነው የተጎዳ፣ የተቀማ ሊካስ ይገባዋል፡፡ ይኼኛው ግን መስመሩ ሌላ ነው፡፡ አንዳንዶቹ በድፍረት ያጥራሉ፡፡ የደንብ ማስከበር ሲመጣ ሰድበው ያባርራሉ፡፡ ተፅዕኖ ከበዛባቸው አርፈህ ተቀመጥ ከንቲባው ይነግራችኋል ይባላል፡፡ እናም እንደዚህ የተባሉ ቦታዎች አይፈርሱም፡፡ ታዲያ ከዚህ ሌላ ምን ማስረጃ ይምጣ? ይህን ዓይን ያወጣ የመሬት ወረራ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ካላስቆመውና የተሰጡትንም ከዚህ ቀደም በነበረው የአየር ካርታ መሠረት ዕርምት ካላደረገ ጉዳዩ በእጅጉ የከፋ ነው፡፡ ከተማዋ ወደፊት በሊዝ የምትሸጠው መሬት አይኖራትም፡፡

አሁን አሁን ከተማችን ካለባት ሥርዓተ አልበኝነት አንፃር በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አካባቢ የሚካሄደው ዘረፋ ሚዛን የሚደፋ ሆኗል፡፡ ለምን ቢባል ያለ ፍርኃት ጉቦ አምጣ ብቻ፡፡ የትም ሄዶ አቤት ማለት በማይቻልበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ አድልኦ እየተደረገብኝ ነው ወደ ሚል ድምዳሜ ያደርሳል፡፡ እዚህ ቆርቆሮ አጥርህን ግንብ አድርገሃል አፍርስ የሚል፣ እዚያ የመንግሥት መሬት ሲሸጥ ሲያይ ከማጉረምረም አያልፍል፡፡ መቼም የመዲናዋ ነዋሪ የተጋረጠበት ችግር በርካታ ነው፡፡ በመልሶ ማልማት በተባለ ፕሮግራም እጅግ ብዙ ሰዎች ለረዥም ጊዜ ከኖሩበት ሠፈር እንዲነሱ ተደርጓል፡፡ እነዚህ ወገኖች ያጋጥማቸው የነበረውን ችግር መዘርዘሩን ለእነሱው ብንተወውም፣ አሁንም ያለው እንግልት ከባድ ነው፡፡ ለሦስትና ለአራት ዓመታት እስካሁንም በተለይ የግል ይዞታ ያላቸው ተነሺዎች የሚስተናገዱበት አግባብ በከፍተኛ ደረጃ በሙስና የተጨማለቀ ነው፡፡ ለተነሺዎች ቦታ ሲሰጥ የካሳና ምትክ ሰጪ ባልደረቦች በካሳ ትመናው ላይ ሲደራደሩ፣ ቦታን በተመለከተም ክፍት ቦታዎችን አትመው በኪሳቸው ይዘው ይኼን ከፈለግህ እንደዚህ ዓይነት ክፍያ፣ ሌላም ከመረጥህ ሌላ ተጨማሪ በማለት ቤቱ ከፈረሰበት ወገን ጋር ይደራደራሉ፡፡ ካልፈለጉም በወንዝ ዳርቻዎች መንግሥት ለሌላ አገልግሎት የያዘውን ቦታ ሆን ብለው በመስጠት ለችግር ይዳርጓቸዋል፡፡ ከዚያ ሌላው በላተኛ የከተማ ፕላን ይህን ለመቀየር ለማስተካከል ያው የተለመደውን ገንዘብ አምጣ ነው፡፡

እንግዲህ ልበ እንበል እንኳን ለሰው ልጅ አብሮ ለኖረ ታማኝ ውሻና ድመት ይታዘናል፡፡ ሌላው መንግሥት የሥራ ሰዓት አይከበርም፡፡ እንደፈለጉ መግባት መውጣት ነው፡፡ ለውጡ አልወረደም የሚባለውም ታች ያለው ኦፊሰር፣ ጉቦኛው ዳይሬክተር ቡድን መሪው አልተነኩም፡፡ የተያዘው የየካውን ቦሌ፣ የቂርቆሱን ልደታ መቀየር ነው፡፡ የተከበሩ ምክትል ከንቲባ እንዲያው በዚህ አካባቢ ያለው መስተንግዶስ ቢሆን ገና ወደ ግቢው ሲመጣ የባለ ጉዳይ መኪና አይገባም፣ ሠራተኛ ያልሆነ በዚያ በኩል ይሂድ ይባልልኛል፡፡ እነ አጅሬ ዘርፈው በገዙት መኪና ተከብረው ይገባሉ፡፡ የመንግሥት መኪናም ከሆነ የያዙት እዚህ መከረኛ ሕዝብ ላይ ተጀንነው ያልፋሉ፡፡ ተገልጋዩ በጠዋት ገብቶ ወረፋ ይጠብቃል፡፡ እነሱ በፈለጉበት ሰዓት ይመጣሉ፡፡ የተፈጥሮ ጉዳይ ነውና መፀዳጃ ቤት እንኳን ባለጉዳይ ቢጠይቅ ሁሉም ቁልፍ ነው፡፡ ለመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ብቻ ይባላል፡፡ አዲስ አበቤ በከፈለው ግብር በተሠራ ሕንፃ እንዲገባም፣ እንዲፀዳዳም አይፈቀድለትም፡፡ ‹‹በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት››፡፡ እርስዎ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ‹እኔ ሥራ እንጂ ስብሰባ አልወድም› አሉ፡፡ አሁንስ? ለባለጉዳይ ረቡዕና ዓርብ ብቻ ተባለ ያም አልተተገበረም፡፡ ካስፈለግም በእነዚህም ይሁን ለሌላ ቀን ስብሰባ አለ ውጡ ብሎ ማባረር ነው፡፡ ሥርዓት ጠፍቶ የጥቅም ግንኙነት ብቻ እኮ ነው ያለው፡፡ በሥሩ ያለውን ሠራተኛ ጉቦ እንዲቀበል ይልከዋል፡፡ ‹ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር› ይባልልኛል ጉቦኛ በሙሉ፡፡ ጭራሽ የሸጠው ዕቃ ያለ ይመስል ለባለ ጉዳዩ ደውሎ ስንት ብር ነው የሰጠኸኝ? እኔን ትሸውደውኛለህ? ብሎ የሚጠይቅ ዳይሬክተር ነው እኮ ያለው፡፡ እነሱ ይህን ጽሑፍ ለማንበብ ዕድሉን ያግኙ እስኪ? አፍ አውጥተው ይህ እኔን አይገልጸኝም ይበሉ፡፡ ከራስ ህሊና በቀር ንፁህ ዳኛ የለምና እርግጠኛ ነኝ፡፡ እንዲህ የሚሉና የነገን ግፍ የሚፈሩ ካሉ ቁጥራቸው እፍኝ የማይሞሉ ናቸው፡፡  ካለም ፈጣሪ ይጠብቃችሁ ሰላሙን ያብዛላችሁ ነው የምለው፡፡

ቀበሌ፣ ክፍለ ከተማና የማዕከል መሥሪያ ቤት እንዲህ እንዳሁኑ ጊዜ በግልጽ ዘረፋ የታየበት ጊዜ አልገጠመኝም፡፡ እናም ባለው መንገድ መልካም መሥራት አለመስገብገብ ሲገባ፣ ባለፉበት ገንዘብ ልጆችን እጅግ ውድ ትምህርት ቤት ማስተማር፣ በዕረፍት ጊዜ ማንሸራሸር በላብ እንጂ በስርቆት በተገኘ ገንዘብ ሊሆን ባልተገባው ነበር፡፡ የተማሪዎች ዩኒፎርም ያለ ጨረታ እንዲሰፋ መስጠት፣ ከፍተኛ በጀት የተያዘላቸውን የከተማው አስተዳደር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በትዕዛዝ መስጠት፣ የከተማውን መሬት እንደፈለጉ ማደል የእርስዎ መለያ ባህሪ መሆናቸውን የቅርብ ሰዎችዎና ጓደኞችዎ ያሙዎታል፡፡ ክቡር ምክትል ከንቲባ ለእንዲህ ዓይነቱ ስሞታ መልስ ይኖርዎ ይሆን? ከላይ የገለጽኩት የመታወቂያ ጉዳይን በተመለከተ ከ100 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ለሚያገኙ የተለዩ ሰዎች ለመጥቀም መታወቂያ እንዲሰጥ በቃል ትዕዛዝ አስተላለፈዋል ይባላል፡፡ ያስተባብላሉ? ያምናሉ? በዚህም መታወቂያ ሲያድሉ የነበሩ ኃላፊዎች መያዛቸውን ሰምተው ‹የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ› ከማለት በዘለለ፣ በአንዳንዶቹ ወረዳዎች በአካል በመገኘት ተዋቸው ብለው መመርያ ሰጥተዋል መባሉስ እንደ ማስረጃ የሚቀመጥ አይደለምን?

ዛሬ ሁሉ ነገር ካበቃ በኋላ አንድ ሰው መታወቂያ ለማግኘት በዚያ ቀበሌ ለስድስት ወራት መኖር አለበት ተብሎ መመርያ ወጣ፡፡ የሚገርመው ሥራ አስፈጻሚዎቹ የካቢኔ አባላት 15 ቀን ለመኖራቸውም ማረጋገጫ የለም፡፡ በአጠቃላይ ክቡር ምክትል ከንቲባ ከተማዋ በብዙ ችግር ተተብትባለች፡፡ እስኪ ልጠይቅዎ ሰሞኑን የሾሟቸውን የካቢኔ አባላት እያንዳንዳቸውን በደንብ ያውቋቸዋል? አዎ ሊሉኝ አይችሉም፡፡ ከመጣው ጋር ሁልጊዜ አለን ባዮች፣ ባለፈው ጊዜ ከተማዋን ሲያምሱ የነበሩ፣ ዛሬ የካቢኔ አባላት ሆነው በምክር ቤት አባላት ሲሾሙ፣ እርስዎ በሹመቱ ስብሰባ ላይ አስተያየት ሲሰጡ ሳይ እኔ አፈርኩ፡፡ እነሱ ልማዳቸው ነውና ችግር የለባቸውም፡፡ ስለሆነም አሁንም የከተማው ነዋሪ መልካም አስተዳደር አጥቷል፡፡ ዳይሬክተር ምናምን ብላችሁ ያስቀመጣችኋቸውን ጭምር ፈትሿቸው፡፡ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ተብለው በዚህ ሥራ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ ወገኖች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች አግባብ ካለው መሥሪያ ቤት ውክልና ይዘው ጉዳይ ያስፈጽማሉ፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል በተለይ በመሬት ልማትና በሥሩ ባሉ ቢሮዎች አይወደዱም፡፡ ለምን ቢባል እነሱ ባለመብቶቹን አግኝተው መደራደር ስለሚፈልጉ ነው፡፡

በእኔ ዕይታ ሦስት ዓይነት ጉዳይ አስፈጻሚዎች አሉ፡፡ የመጀመርያዎቹ ከላይ የጠቀስኳቸው ዓይነቶች ናቸው፡፡ ከመላላክ ባለፈ ምንም ሚና የሌላቸው፣ ሁለተኛዎቹ ደግሞ የባለሙያ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ናቸው፡፡ የሠሩትን ይዘው ይቀርባሉ፣ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ግንኙነት ስላላቸው ጉቦ ያቀባብላሉ፡፡ በዚህ ረገድ አንዳንዶቹ ሙያቸውን ለድርድር አሳልፈው የማይሰጡ ናቸው፡፡ ሦስተኞቹ ደግሞ እጅግ በጣም አደገኞች ብጫቂ ወረቀት በእጃቸው አይዙም፡፡ ሠራተኛን ወይም ዳይሬክተርን የፈለጉበት ሆቴል ሆነው በስልክ ይጠራሉ፡፡ ከፍተኛ የሆነ ሕገወጥ ሥራ ይሠራሉ፡፡ የብሔር ጉዳይም ትኩረት ይሻል፡፡ ለምሳሌ በተጭበረበረ የገንቢ፣ የአማካሪና የማስረጃ ፈቃድ ያወጣሉ፡፡ የተፈለገውን ጉዳይ ያስፈጽማሉ፡፡ መሬት ያሰጣሉ፡፡ ነባር ከሆኑ የመሥሪያ ቤቱ ጸሐፊዎችና ኦፊሰሮች ጋር ቅርብ የሆነ ግንኙነት አላቸው፡፡ ጉዳዩ  ሁሉ በስልክ ነው፡፡ ለእገሌ ተመርቶልሃል፣ እንትናን ያዘው የሚሉ ከበፊት ጀምሮ ሲሽሎከሎኩ የሚውሉና በተለያየ የዕድሜ ደረጃ ላይ ያሉ፣ በዚሁ ሥራ የከበሩና በከተማው የሚታወቁ የቢሮ ደላሎች ናቸው፡፡

ሌላው ክቡር ምክትል ከንቲባ ዛሬ ባለሀብት ተብለው ከእርስዎ ጋር የሚዞሩ 80 በመቶ የአዲስ አበባን መሬት ያላግባብ በመውሰድ በመሸጥ በመለወጥ የከበሩ ናቸው፡፡ ቢመቻቸው የከተማው መሬት ሁሉ የግላቸው ቢሆን ይመኛሉ፡፡ አንዳንዱ በአራቱም ማዕዘናት ይኼ የእሱ ነው እየተባለ እንዲጠራላቸው የሚፈልጉ ናቸው፡፡ መሬት አይጠግቡ፣ ገንዘብ አይጠግቡ፣ የሚፈርስ ቤት ሆን ብለው ይገዛሉ፡፡ በሊዝ የሚሸጥ መሬት ምትክ ተብሎ ይሰጣቸዋል፡፡ ደሃን በልማት ሰበብ ያፈናቅላሉ፡፡ መሬት የመሰብሰብ ሱስ ያለባቸው ናቸው፡፡ የሚመደበውን ኃላፊ በእጅ በእግር ብለው ተዋውቀው የሚያባልጉ፣ በከፍተኛ ገንዘብ እያማለሉ የደሃውን ሕዝብ መሬት የሚዘርፉ፣ የከተማዋ ባለሀብት ተብዬዎች ዛሬም በእርስዎ ጉያ ሥር ገብተዋል፣ ይጠንቀቁ፡፡ ለነገሩ እርስዎም ከሐሜት አልዳኑም፡፡ መቼም የአዲስ አበባ መሬት ስንቱን ስግብግብ እንዳከበረው ቤት ይቁጠረው፡፡ በአገሪቱ ታሪካዊ የተባሉ ቦታዎችን ሁሉ በሪል ስቴት በሌላም ሰበብ እያፈረሱ ይወስዳሉ፡፡ ሌሎች አኩራፊ የሥራ ባልደረቦች በመሬት ልማት ቢሮ ከፍ ያለ ሥራ የተቀመጡ መኖራቸውን ልጠቁምዎ፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲገቡ ሲወጡ የሚውሉ፣ በየክፍለ ከተማው የነበሩ፣ ጥሩም ሆነ መጥፎ ሥነ ምግባር ያላቸው ነበሩና አንድ ይበሏቸው፡፡

ማጠቃለያ

ይህ ጽሑፍ ከማዕከል እስከ ወረዳ ባለጉዳይን በቅንነት የሚያስተናግዱትን፣ የሰው ችግር እንደ ራሳቸው የሚያዩትን፣ መልካም አሳቢዎችን፣ ፈጣሪያቸውን የሚፈሩትን አይመለከትም፡፡ ‹‹ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ›› ሆኖ ነው እንጂ፣ እጅግ በጣም መልካም ሠራተኞች፣ አንገታቸውን ደፍተው የተቀመጡ ጨዋ የሥራ ባልደረቦች አሉ፣ ቁጥራቸው ቢያንስም፡፡ ሁሉም ራሱን ስለሚያውቅ ተነካሁ ብሎ የሚቆጭ እንደማይኖር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስለዚህ ለውጡ ወደ ታች ይውረድ፡፡ ዳይሬክተር፣ ቡድን መሪ፣ ኦፊሰር በደንብ ይፈተሽ፡፡ ጽሑፌን በዚሁ አጠቃልላለሁ፡፡ በክፍል ሁለት ሌሎች ትኩረት የሚሹ ቢሮዎች አሉና እነሱን በመያዝ እመለሳለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...