Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትዛሬም ‹‹አገር የጋራ ነው ሃይማኖት የግል ነው››!

ዛሬም ‹‹አገር የጋራ ነው ሃይማኖት የግል ነው››!

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

በዓለማችን ከሚታየው አሳሳቢ ችግር አኳያ፣ በአገራችን እስካሁን ያለው የሃይማኖት ሰላም ምን ያህል ውድና ብርቅ ሀብት እንደሆነ መገንዘብ አይከብድም፡፡ ባለብዙ ሃይማኖት በሆነችው ኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ውስጥ በገዥዎች ምንም ተደረገ ምን፣ አባቶቻችንና እናቶቻችን ሁሉንም ችለውና ተቻችለው እያሳለፉ አብሮ በመኖር እዚህ አድርሰውናል፡፡ ይህንን በሰላም አብሮ የመኖር ቅርስ የአሁኑ ትውልድ ማስቀጠሉንና ዘላቂ መሆኑን የሚያረጋግጠው፣ ዛሬ ያለንበት የመብት ንቃት ደረጃ የሚጠይቀውን ኃላፊነትና ተግባር መሸከም ከቻለ ብቻ ነው፡፡

ይህን ይበልጥ ለማሳየት ለእንክብካቤ የሚሆን ነባራዊና ህሊናዊ ጥሪት አለን? ጉድለትስ? ብለን በመጠየቅ እንጀምር፡፡

ሀብት ወደ አንድ ወገን (አካባቢ) እየተግበሰበሰ ነው፣ ወይም ሌላው አካባቢ ከእኔ አካባቢ በሚጋዝ ሀብት እየኖረ ነው ለሚል ሐሜት የማይመች የአካባቢዎች የተመጣጠነ ልማትና ዴሞክራሲ ለሁሉም ዓይነት ሰላም የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አገራችንን የናይጄሪያ ዓይነት ከሃይማኖት ጋር የሚገናዘብ አካባቢያዊ የሀብትና የልማት ተዛነፍ ያሳስባታል አይባልም፡፡ ዕድገትና ልማት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲታይ በፌዴራልም ሆነ በክልል መንግሥታት ደረጃ በሚታቀዱ የልማት መርሐ ግብሮች ውስጥ የሚገባቸውን ያህል ትኩረት ያላገኙ ሥፍራዎች ቢኖሩም፣ የትኩረት ጉድለቶቹ ከእምነት ጋር ለተያያዘ ማሳበቢያ የሚመቹ አልነበሩም፣ አይደሉም፡፡ አንፃራዊ ቀርነት አለባቸው ለሚባሉ አካባቢዎች ልዩ ዕገዛ በማድረግ የዕድገትና የልማት ርቀትን የማጥበብ እንጂ የማስፋት አዝማሚያ አልታየም፡፡ ልማትን ከዴሞክራሲ አለያይቶ የኖረው ገዥው ክፍልም ሁሉን አካባቢ ያዳረሰ ልማት በማሳካት ዕፁብ ዝናን አፍሶ ገዥነቱን ለማርዘም የሚራወጥ ነበር፡፡

ሀብት እያካበቱ በመደርጀት ረገድም ሃይማኖታዊ የሚባል አጥር (ገደብ) አልነበረም፣ የለም፡፡ በዚህ በኩል ቅሬታ ለመፈልሰፍ የሚሞክሩ ቢኖሩ በኢኮኖሚ ሥምሪቱ ውስጥ እየታየ የመጣው የጥንቅር አዝጋሚ ለውጥና ሽግሽግ ራሱ ያሽሟጥጣቸዋል፡፡ በፖለቲካውም ረገድ፣ ከሃይማኖት ፖለቲከኛነት ውጪ፣ የፓርቲ ፖለቲካ ተሳትፎ ለየትኛው ዓይነት  ሃይማኖት ተከታይ በሩ ክፍት ሆኖ ኖሯል፡፡

መንግሥት ከየትኛውም ሃይማኖት ወገንተኛነት የተገለለ መሆኑ በሕገ መንግሥት ተደንግጓል፡፡ በኢትዮጵያ ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው›› ተብሎ የተደነገገው በኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 ድንጋጌ ነበር፡፡ አሁን ፀንቶ በሚገኘው ሕገ መንግሥት መሠረት፣ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት የሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ መርህ ሆኖ ተደንግጓል፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኖርም፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ማለት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ቃል ነው፡፡ ይህ ማለት የትኛውም ዓይነት ሃይማኖት ፖለቲካ ሆኖ፣ በኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት (ስቴት) ላይ ሊወጣና መንበረ መንግሥቱን የእምነቱ መሣሪያ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ማለትም ሃይማኖት ፓርቲ ሊሆን፣ ፓርቲም የሃይማኖት አቀንቃኝ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሲል በተለይም በሽግግሩ ወቅት ከብሔርተኛነት ጋር የተያያዘ ሃይማኖታዊ የፖለቲካ ቡድን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ተከስቶ ነበር፡፡ የተገለጸው 1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት የዚያን ዓይነቱን ቀዳዳ ደፍኖታል፡፡ ያ ቀዳዳ ክፍት ሆኖ ቢሆን ኖሮ የመንግሥት ገለልተኛነት የሚፈርስበት ዕድልም አብሮ ይኖር ነበር፡፡ በቀድሞውም አሁን ከለውጥ ወዲህ በተሻሻለውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ/ሕግ ውስጥም  ሃይማኖታዊ ድርጅቶች በፖለቲካ ፓርቲነት መመዝገብ እንደማይችሉ ተደንግጓል፡፡

መንበረ መንግሥትን ከሃይማኖት ወገናዊነት የማራቅ መነሻና መድረሻ ሃይማኖቶችን መግፋት ሳይሆን፣ የትኞቹም ሃይማኖቶች በየትኛውም ሃይማኖት የበላይነት (ጫና) ሥር እንዳይወድቁ እኩል ተከባሪነትና የህልውና መብት እንዲያገኙ መጠበቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህንን ጽንሰ ሐሳብ የቆነጠጠ፣ እምነትን በኃይልም ሆነ በማስገደድ መገድብንም ሆነ ማስቀየርን የሚከለክልና መሠረታዊ የሲቪል መብቶችን በማይሽር ሁኔታ፣ ለባህላዊና ለሃይማኖታዊ የጋብቻ ምሥረታና ዳኝነት ሥርዓቶች ቦታ የሰጠ ሕገ መንግሥት ሊያዋቅር መቻሉ ሁነኛ ጥንካሬ ነው፡፡ እናም ሃይማኖት መንግሥታዊ እንዳይሆን ወይም መንግሥት ወደ አንዱ ወይ ወደ ሌላው ሃይማኖት እንዳያጋድል መጠበቅ አንዱ ዋነኛ ተግባር ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ መሠረት የትኛውም ሃይማኖት የሌላውን ሃይማኖት ነፃነት ሳይጋፋ እምነቱን የማራመድ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ የቆሙለትን እምነት በተመለከተ ትክክለኛ አተረጓጎሙና አያያዙ ይህ ነው ብሎ መስበክ፣ የምዕመናንን ግንዛቤና የእምነት አተገባበር በማስተማር ማበልፀግ መብት ነው፡፡ በግድ መጫን ግን መብት መድፈር ነው፡፡ መስበክ መብት እንደሆነ ሁሉ መሰበክም የማይገድቡት መብት ነው፡፡ የተሰበኩትን (የተቀበሉትን) እምነት ጠበቅ አድርጎ መያዝ፣ ላላ አድርጎ መያዝ፣ ወይም መቀየርና አለመቀየር የግለሰቡ መብት ነው፡፡ ወላጆች (አሳዳጊዎች) ልጆቻቸውን በእምነታቸው ማነፅ መብታቸው ነው፡፡ የወላጅን እምነት ይዞ ለመቆየት ግን ተወላጅ አይገደድም፡፡ እነዚህን መብቶች ለመጣስ ማንም አልተፈቀደለትም፡፡ ማንኛውም ቤተ እምነት ነባር አማኞቹን ይዞ ከመቆየት ባሻገር፣ አዳዲስ ተከታዮችን ለማፍራት የማስተማር ሥራ ማካሄድን ትርጉም የሚሰጡትም እነዚህ የግል መብቶች መኖራቸውና መረጋገጣቸው ነው፡፡

ይህንን ጉዳይ ይበልጥ አፍታትተን ደግመን እናብራራው፡፡ የሃይማኖት መሪዎች ለተከታዮቻቸው በየሃይማኖታቸው ውስጥ ያሉ የአማኝነት ዕውቀቶችን፣ ሥነ ሥርዓቶችንና ግዴታዎችን ማስተማር ኃላፊነታቸው ነው፡፡ የተማሩትን አጥብቆም ሆነ አላልቶ መያዝ የተከታዮች ግለሰባዊ መብት ነው፡፡ ሁሉንም አማኝ አንድ ዓይነት ጥንካሬ ውስጥ ለማስገባት የሃይማኖት መሪዎች/አስተማሪዎች የክትትልና የማስገለል ዘዴ ቢጠቀሙ የግል መብትን በአፈና መርገጥ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ውስጥ የተንሰራፋው የእኔ እምነት ነውና ንዑሳን የሌላ እምነት ተከታዮች ለትልቁ ለእኔ ሃይማኖት ሥነ ሥርዓቶችና የበዓል አከባበር ይታዘዙ ብሎ መጫን፣ ከአፈናም በላይ የሃይማኖት ግጭት የሚጠራ ነገረኛነት ነው፡፡ እንዲህ ያለ አካባቢን የእኔ ሃይማኖት ያስተዳድር የሚል አስተሳሰብ ሲመጣ፣ እረፍ እንደ መንግሥት መሆን አይሞካክርህ ብሎ መገሰጽና የዜጎችን መብት ማስከበር የተሳነው የመስተዳድር አካል ኃላፊነቱን አልተወጣም፡፡ ጭራሽ የትልቁ ሃይማኖት ወገንተኛ ሆኖ ለዚያ አካባቢ አናሳ የሆነውን ሃይማኖት የማፈንና የማስጠቃት ተባባሪ ከሆነ፣ በየትኛውም ደረጃ ያለ የመንግሥት አካል ሃይማኖተኛ ያለ መሆን፣ ሕገ መንግሥታዊ ባህርይ የመሳት መዘዘኛ ጥፋት ሠርቷል ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ የእምነትም ሆነ የብሔረሰብ መብቶች የእኩልነት መብቶች እንጂ፣ በቁጥር መብዛትና ማነስ የሚሠፈሩ አይደሉም፡፡ እነዚን መሠረታዊ ነጥቦች አበልፅጎ በየደረጃው ባሉ የየሃይማኖቶች መሪዎችና መምህራን ዘንድ፣ በየደረጃው ባሉ አስተዳደሮችና በኅብረተሰቡ ዘንድ ማስረፅ የሁሉም ግዴታ ነው፡፡

ከመስረፅ ሥራ ጎን የቤተ እምነቶችንና የፖለቲካ ኃይሎችን ስምምነትን በተመረኮዘ አኳኃን ሃይማኖቶችንም ሆነ ማኅበረሰቦችን በማጋጨት፣ ቤተ እምነቶችን በማጥቃት በሚፈጽሙ ወንጀሎች ላይ፣ እንዲሁም በብሔር ነክ ጥላቻ በሚሰነዘሩ ጅምላ ጥቃቶችና ሰቅጣጭ አገዳደሎች ላይ ልዩ የሆነ የሽግግር ጊዜ ሕግ በቶሎ አውጥቶ ሥራ ላይ ማዋልም መጤን ያለበት አማራጭ ነው፡፡

እናም የእምነት ቡድናዊና የግል መብቶች እንዳይረገጡ መንከባከብ በሌላው ላይ ሲጓደሉ ሲያዩ እንኳ፣ ነገ በእኔ ብሎ መቆርቆር የራስን የእምነት ተቋምና የምዕመናንን መብት የማስጠበቅም ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህን መሰሎቹን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ከማስከበር ውጪ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር መወገን የሃይማኖት ተቋማት ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህንን ወይም ያንን የፖለቲካ ፓርቲ ደግፉ/ተቃወሙ/አውግዙ ብሎ ለምዕመኖቻቸው መስበክ የሃይማኖት ተቋማትን አይመለከታቸውም፡፡ ምዕመኖቻቸው የተለያየ የፖለቲካ እምነትና ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በአንድ እምነት ውስጥ የተለያየ ፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የየቤተ እምነት መሪዎች ኃላፊነታቸው ከፖለቲካ ውገና ገለልተኛ ሆኖ የሃይማኖት ተከታዮቻቸውን ያለ አድልኦ ማገልገል ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲና ሃይማኖት መወጋገን ከጀመሩ ለመንግሥታዊ ሃይማኖት መንገድ ይከፈትለታል፡፡ ፓርቲው ሥልጣን ቢይዝ ድጋፍ የሰጠው ሃይማኖትም ባለ ልዩ መብት ልሁን ባይ ይሆናል፡፡ ወደ ሥልጣን የሚያመራ ወይም ሥልጣን ላይ የወጣ ፓርቲ ለፖለቲካ ድጋፍ የሃይማኖት መድረክን ከመጠቀም መራቁና ይህም ቀጣይነት ማግኘቱ ሃይማኖት ፖለቲካን እንዳይፈተፍት ይከላከላል፡፡

ይህ ማለት ግን ፖለቲካና ሃይማኖት ጭርሱኑ አይደራረሱ ማለት አይደለም፣ ቢባልም የማይቻል ነው፡፡ ከእምነት፣ ከነፃነትና ከእኩልነት ጋር የተያየዙ መሠረታዊ መብቶች ተደፍረው ይህንን በማውገዝ መንገድ ላይ ፖለቲካ ፓርቲና ሃይማኖት ሊገናኙ ይችላሉ፡፡ የሆነ ፖለቲካ ፓርቲ አጥፊ ቅስቀሳ አድርጎ ሃይማኖታዊ አምባጓሮ ቢከሰት፣ አነሳሹ ፓርቲ ተወጋዥ ከመሆን አያመልጥም፡፡

መንግሥትና የሃይማኖት ተቋማትን የሚያገናኛቸው ብዙ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ሃይማኖታዊ ተቋማትን ወደ መንግሥት አካላት ሊወስዷቸው ይችላሉ፡፡ የሃይማኖቶች ሰላም ጉዳይ ሃይማኖቶችንና መንግሥትን ያገናኛሉ፡፡ ሃይማኖታዊ ተቋማት የሚኖራቸው የበጎ ሥራና የልማት ዕቅድ ከመንግሥት  የልማት ዕቅድ ጋር ተጋጭቶ ብክነት እንዳይሆንባቸው፣ የልማት ዕቅዳቸውን ከመንግሥት ጋር ቢያገናዝቡ አስተዋይነት ነው፡፡ መንግሥት ከሚያካሂዳቸው (ከሚደግፋቸው) የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥም የሃይማኖት ጉዳይ ተደርገው ሊምታቱ የሚችሉ (የሃይማኖት መሪዎችን ማብራሪያና የቅርብ ድጋፍ የሚሹ) ይኖራሉ፡፡ እነዚህን በተመለከተም አብሮ መሥራት ይኖራል፡፡

ከዚህ ያለፈ መጠጋጋት ግን ለመንግሥትም ሆነ ለሃይማኖት ተቋማት ጠቃሚ አይደለም፡፡ ወሰንን አልፎ በማያገባ ለመግባትም ያጋልጣል፡፡ በደርግ ዕድሜ ማብቂያ ጊዜ ላይ እነ ሕወሓት በሃይማኖት መሪዎች ‹‹ወንበዴ፣ የአገር ጠላት›› ተብለው እንዲኮነኑ የተደረገበት ጊዜ ነበር፡፡ በሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘመንም ደርግን ያስናቀና ያሰከነዳ መሰሪ ግፎች ታይተዋል፡፡

 የዚያ ዓይነት ጥፋት ዛሬም ወደፊትም ላይደገም የሚችለው በሥልጣን ላይ ያለ ገዥ ቡድን/ፓርቲ ለፖለቲካ ዓላማ የሃይማኖት ተቋማትን መገልገያ ከማድረግ ሲፆም፣ የሃይማኖት ተቋማትም መንግሥት የወደደውን መውደድ፣ የጠላውን መጥላት ይገባኛል/ይጠቅመኛል ከሚል የአስተሳሰብ ቅጥር ግቢ ሲወጡ ነው፡፡

የመንግሥት አካላትንም ሆነ የሃይማኖት ሰዎችን ሊያሟልጥ የሚችል ሌላ እውነታም አለ፡፡ ዛሬ ያለው የአገሪቱ ፖለቲካዊ ካርታ ከበፊቱ በንጉሡና በደርግ ጊዜ ከነበረው በጣም የተለየ ገጽታ አለው፡፡ ከአካባቢ አካባቢ ባለ የመንግሥት ሥልጣን ውስጥ የየአካባቢው ብሔረሰባዊ ዓብይ ጥንቅር እንደሚንፀባረቅ ሁሉ፣ የዋናዎቹ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች የክምችት ገጽታም ተንፀባርቆ ይታያል፡፡ በክልላዊ የሉዓላዊ ባለቤትነት ዕሳቤ ውስጥ ንዑሳን/መጤ ማኅበረሰቦችን የመዘንጋት ወይም እንደ ሁለተኛ ደረጃ ባለመብትና ባይተዋር የማየት ችግር እንዳለ ሁሉ፣ በሃይማኖትም መሰል ችግር ያጋጥማል፡፡ በተለይ ውጥንቅጥነት በሚሳሳባቸው ሥፍራዎች ዘንድ ባለ ማኅበረሰባዊ ይዞታና የመንግሥት  አካላት ውስጥ የአንድ ዓይነት ሃይማኖት ሰዎች ደምቀው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ በዚያ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ አስተዳዳሪዎችን የገለልተኝነት ኃላፊነት የመዘንጋት ድጥ ሊፈታተናቸው፣ ጭራሽ ሳይታወቃቸው ኃላፊነታቸው ሊጠፋባቸውም የሚችልበት ዕድል ይኖራል፡፡ በአካባቢው ዋነኛ የሆነው ሃይማኖት ተከታዮችም የራሳቸውን ሃይማኖት የአካባቢው ባለቤትና ዋና ባለመብት አድርገው ቆጥረው፣ ከዚያ ውጪ ያሉ እምነቶች መብት በእነሱ እጅና ችሮታ ውስጥ ያለ አድርገው የሚያስቡበት ስህተት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ መንግሥት ራሱ በ2006 ዓ.ም. በአሠራጫው የሥልጠና ጥራዝ አረጋግጦ እንደመሰከረው፣ ‹‹በአንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች ወይም ሠራተኞች፣ እንዲሁም በኅብረተሰቡ አባላት የሚገለጹ የሃይማኖት አድልኦ ዝንባሌዎች (ክርስቲያን ምዕመናን በብዛት ባሉበት እስልምናን የማንኳሰስ፣ የእስልምና ምዕመናን በበዙበት አካባቢ ደግሞ በተመሳሳይ … የማንኳሰስ ስህተቶች) አሁንም ጨርሰው እንዳልጠፉ የሚታወቅ፤›› ነው ተብሏል፡፡ የዚህ ዓይነቱ የበላይነት ስሜት የእብሪትም መፍለቂያ ነው፡፡ ላሽቆጥቁጥ፣ በማነስህ ልክ መብትህ አንሶ ይሰፈርልህ የሚል አፈናና መተናኮል ሊያፈልቅ ይችላል፡፡ የዚህ ዓይነቱን ሁኔታ ፅንፈኞች ይወዱታል፡፡ በአንድ ወቅት በጅማና በቤኒሻንጉል ጉምዝ አካባባቢዎች፣ በመንግሥት መረጃ መሠረት ሃዋርጃ የተባለ ፅንፈኛ አሸባሪ ቡድን የክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ ግፍ ለመፈጸም የደፈረው፣ የዚህ ዓይነት አካባቢዊ የባለቤትነት ትምክህትን መንደርደሪያ አድርጎ ነበር፡፡

የሌላውን የእምነት ነፃነት ሳይተናኮሉ እምነትን በግልም ሆነ በቡድን የማራመድ፣ የማምለክ፣ የመማርና የማስተማር መብት በቁጥር የማይገደብ፣ የማይሸረፍ እኩል መብት መሆኑ ሲዘነጋ የሃይማኖት ሰላምም ዋና ውሉን ሳተ ማለት ነው፡፡ የእምነት እኩልነትን የማስከበርና የመብት ጥሰቶችን የሚከለክል ጤናማ (ሃይጅናዊ) አመለካከት፣ ጨዋ የሃይማኖቶች ግንኙነትና የእምነት አተገባበር የማዳበር ሥራዎች መሬት መንካት ያለባቸው ለዚህ ነው፡፡ እንዲሁም በየትኛውም ደረጃ ያለ የአስተዳደር ዕርከን ሕዝብን ከየትኛውም ዓይነት ጥቃት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በዝንጉነትም ሆነ በሌላ ምክንያት ሳይወጣ ለሚደርስ ጥፋት ሊጠየቅ ይገባዋል፡፡ በየአካባቢው ወይም በአንዳንድ አካባቢዎች ደርሰው አገር ያስቆጡ ተግባራትን ያስከተሉ ‹‹አስተሳሰቦች›› በየተፈጸሙበት አካባቢ በአንድ ምሽት ብቅ አላሉም፡፡ አስቀድሞ ትኩረት ቢደረግባቸው ኖሮ ያንን የመሳሰሉ ዘግናኝ ነውሮች ለመፈጸም ባልተቻለ ነበር፡፡

ከየትኛውም ሃይማኖት፣ ከክርስትናም ሆነ ከእስልምና በኩል የሚመጣ የፅንፈኝነት ነገረኝነት የሚጀምረው ከአመለካከቱ ነው፡፡ ሌሎች እምነቶች ከእሱ አጠገብ እኩል የመኖር መብት፣ እኩል ክብር ያላቸው ሆነው አይታዩትም፡፡ በራሱ ሃይማኖት ውስጥ ሳይቀር ለዘብተኛ አማኝ ወይ ሌላ ስንጣሪ መኖር ብሎ ነገር አይቀበልም፡፡ ‹‹ትክክልና የተቀደሰ›› ከሚለው እምነት ውጪ ያለ ሁሉ የክህደት/የርኩሰት ወይም የሰይጣን ዓለም ነው፡፡ የዚህ ዓይነት አመለካከት አያኗኑርም፡፡ ‹‹የገሃነም/የሰይጣን›› ዓለምና ‹‹የቅድስና›› ዓለም እንዴት ይኗኑራል? ከሰይጣን ማደሪያ ጋር መነካካት መርከስ ወይም ከገሃነም ጋር መነካካት ይሆናል፡፡ ይህን የእርኩሰትና የዘለዓለም ሞት ሠፈር የማስወገድ፣ የማፅዳትና በቅድስና የመተካት ኃላፊነትና ተግባር ከሰማይ የተሰጠው ደግሞ ለእሱ (ለፅንፈኛው) ነው፡፡ ሲሰብክ እንኳ ድርጊቱ ሆኖ የሚታየው ማስተማር ሳይሆን፣ ከዘለዓለም እሳት/ሞት የማትረፍ ሥራ ነው፡፡ ቅድስና ከእኔ ጋር ብቻ ያለ (ሌላው ሁሉ የእርኩሰት ጎዳና) ብሎ የሚል እምነት ንዑስ እንኳ ቢሆን ሌሎቹ ሃይማኖቶች ሁሉ ተሰቅዘውለት እሱ ለመናኘት፣ የሥርዓተ ትምህርት ሰፋሪና የትምህርት ቤቶች ቃኚ ለመሆን ዕድሉን ቢያገኝ አያቅማማም፡፡ የዚህ ዓይነት ፅንፈኛ ፍላጎቶች በኦርቶዶክስ ክርስትና፣ በፕሮቴስታንት ክርስትና ፍልቃቂ እምነቶች ሆነ በእስልምና ውስጥ ያጋጥማሉ፡፡

 የዓለማዊ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት በሃይማኖት እንዲቃኝ፣ ፀሎትና ስግደት ትምህርት ቤት ውስጥ እንዲገባ መፈለግ የሃይማኖት ጭቆናንና የመንግሥትና የሃይማኖት ዝምድናን መልሶ መጥራት ነው፡፡ እንደ አካባቢው ሁኔታ ዋነኛ የሆነው ሃይማኖት ትምህርት ቤት ውስጥ ይግባ ቢባል በዚያ አካባቢ ያሉ ንዑስ ሃይማኖቶች ተጨቋኝ ይሆናሉ፡፡ አንዱ ጋ ዋና የሆነ ሃይማኖት ሌላ ቦታ ላይ ንዑስ ሆኖ ይገኛልና፡፡ ጭቆናው ለራሱም መድረሱ አይቀርም፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች በየበኩላቸው የሚሰማሩባቸው የየብቻ ትምህርት ቤቶች እንዲኖሯቸው ማሰብ፣ በመንግሥትም ሆነ በግል ሊሟላ የማይችል ቅዠት ውስጥ መግባት ይሆናል፡፡ የትምህርት ቤት ልዩነት ሳይኖር ለየትኛውም እምነት ተከታዮች የፀሎት፣ የስግደትና የእምነት ክበብ መብት በትምህርት ቤቶች ውስጥ የተፈቀደ ይሁን ማለትም የትምህርት ሥራ ይመሳቀል፣ የትምህርት ቤቶች ሰላም በእምነት ንቁሪያና መሸራደድ ይበጥበጥ ብሎ መልቀቅ ነው፡፡

ጭንቀታችን ፅንፈኛ ፍላጎት ቦታ አግኝቶ እንዲረካና እንዲያድብ ከሆነ ፅንፈኝነት አልገባንም ማለት ነው፡፡ ለፅንፈኝነት የሚታየው መብትና የመብት መጣስ ብሎ ነገር ሳይሆን ገሃነምና ገነት ነው፡፡ ፅንፈኝነት መብት አክብሮና ተቻችሎ ኗሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ገሃነም የመግባት መብትን ከማክበር ይልቅ በግድ ገነት ማስገባት ይበልጥበታል፡፡ ሃይማኖት ለወጥክ ብሎ ከዝምድና ማግለልና ካልገደልኩ ባይነት የሚከሰተው ለውጡን መብት አድርጎ ከማየት ይልቅ ወደ ቅስፈት (እርኩሰት) መግባት አድርጎ ከመቁጠር ነው፡፡ ፅንፈኝነት ባለጉልበት በሆነበት አካባቢ እምነትን በግድ ማስቀየርና ማባረር ሲከፋም ግድያ የሚያካሂደው ለዚህ ነው፡፡ በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ ያለ ከሌላው ሃይማኖት ጋር ጎን ለጎን ተከባብሮ ከመኖር ይልቅ፣ ሃይማኖታዊ አብዮት መሳይ አጥለቅላቂ ለውጥ ማምጣት የሚታየው፣ የአንዱ ወይ የሌለው እምነት ተከታይ መሆንን ከመብት የማይቆጥር፣ ከእሱ ውጪ ያለውን ሁሉ የክህደትና የቅስፈት መናኸሪያ አድርጎ የሚመለከትና አትቀላቀሉ አትነካኩ ብሎ የሚቀሰቅስ አደገኛ የፅንፈኛት ዝንባሌ ነው፡፡ በሰይፍ ከሚቀጡትና እምነት ከሚያስቀይሩት የሚለየውም በደረጃ ብቻ ነው፡፡

በትምህርት ቤቶች ውስጥ እምነቶችን የማራመድ ነገር ያሳሰበን ለመብት ማሰብ ከሆነ፣ ከትምህርት ቤት ውጪ መብቱን ማስከበሪያ መንገዶች መቼ ጠፉና? መኖሪያ ቤት፣ ቤተ አምልኮ፣ የሃይማኖት ትምህርት ቤት፣ የሃይማኖት ጋዜጣና መጽሔት፣ ወዘተ ሁሉ አሉ፡፡ ተማሪዎቻችንን፣ ልጆቻችንን በሃይማኖታዊ ግብረ ገብነት ለማነፅ አማራጮቹ ብዙ ናቸው፡፡ ዓለማዊ ትምህርትም ከሥነ ምግባር ጋር አይቃረንምና ትምህርት ቤቶች ከየትኛውም ሃይማኖት ጋር መጣበቅ ሳያስፈልጋቸው ተማሪዎችቸውን በመልካም ምግባር ማነፅ ይችላሉ፣ በደንብ ከተሰናዱ፡፡

ከትምህርት ቤቶች ባሻገር ሃይማኖታዊ ያልሆነ የሥራ ገበታን ለእምነት ማሠራጫነት መጠቀም ራሱ አደገኛ የምግባር ጉድለት ነው፡፡ የገበያና የመጓጓዣ ሠልፎችን፣ አውቶብሶችን የስብከት መድረክ አድርጎ መጠቀም፣ ወደ ሥራ የሚበር ሰውን ‹‹አንዴ ላናግርህ›› ብሎ ወይም ቤት አንኳኩቶ ልስበክህ ማለት ከትንኮሳ ቁጥር ነው፡፡ በእነዚህ ዓይነቶቹ ስብከቶች ውስጥ አልፈናል፡፡ ስድድብ፣ ንጭንጭ፣ የድብድብ ክስተቶችም አጋጥመውናል፡፡ አግባብ ባልሆነ ቦታ ልስበክ ከመባሉ ይብስ የአሰባበኩ! እምነትና ፅድቅናን ከቶ ከዚህ በፊት ሰምቶ ለማያቅ ከኃጢያትና ከዘለዓለም ሞት እኔ ላድናችሁ፣ ሌላ መዳኛ የላችሁም የሚል የዚህ ዓይነት አተያይ ‹‹እኛን ያልዳንን አድርጎ መዳቢ አንተን ማን አደረገህ? እኛ ሃይማኖት የለንም?” የሚል ቱግታን ይቆሰቁሳል፡፡ መንገድ ላይ እምነትን ማሠራጨት ቢያስፈልግ እንኳ፣ የሚሻ እንዲወስድ ጽሑፎችን በመደቀን ብቻ መቆጠብ ጨዋነትን የተላበሰ ነው፡፡

አግባብ ባለው ሥፍራና የመገናኛ ዘዴ እምነትን በመስበክ ረገድም የሌላውን እምነት በመንቀፍ ላይ መመሥረት፣ በእኛ ሁኔታና የሥልጣኔ ደረጃ ጤናማ አይደለም፡፡ በምዕራቡ ዓለም የትኛውንም ሃይማኖት ከመተቸትም ባለፈ ማሽሟጠጥም የንግግር ነፃነት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ሃይማኖት ስላልተቸንና ስላላሽሟጠጥን የሚጎድልብን የለም፡፡ ነቀፋና ሽሙጡን እንሞክር ብንል ሃይማኖትን በሃይማኖት ላይ እስከ ማስነሳት የሚሄድ ጣጣ ልንጎትት እንችላለን፡፡ ምዕራባውያኑም አሽሟጠውና ተሳልቀው የእስላማዊ ፅንፈኛ አሸባሪነት ጥርስና ጥቃት ውስጥ ከመግባት በቀር ያተረፉት ነገር የለም፡፡ ከፋይዳ ቢስ ሽሙጥ ፋንታ፣ ዴሞክራሲና የሐሳብ ነፃነታችን ለምን በፅንፈኛ አሸባሪነት ተጠመደ? ከወጥመዱስ እንዴት መውጣት ይቻላል? በሚሉና በመሰል ጥያቄዎች ላይ ቢያነጣጥሩ ፍሬው ለሌላውም የሚፈይድ ውጤት ባመጡ ነበር፡፡

የሃይማኖት መተቻቸት፣ የብሔረሰብ ጭምር ፀብ ያማዝዛል ብሎ መጠንቀቅና ትችትን በዱላና በጥይት መቅጣትን ተገቢ ብሎ መፈጸም በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ መምታታት የለባቸውም፡፡ ነቀፋና ዘለፋ፣ አምባጓሮ የመጀመር ወይም በቱግታና በጋጋታ የመቅጣት መብትን አያጎናፅፉም፡፡ የዚህ ዓይነት ዕርምጃ (በአንድ ሰው ተፈጸመ፣ በሺሕ ሰው) መብት የሚረግጥ ወንጀል ነው፡፡ እምነቴ ወይም ብሔረሰቤ ተነካ ብሎ በጋጋታና በግንፍልነት የኃይል ዕርምጃ መውሰድን ተገቢ መብት አድርጎ ማሰብ እጅግ አደገኛ ዝንባሌ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ተሠራጨ ማለት ወደ ሕግ መሄድን የጋጋታና የቱግታ ዕርምጃ እየተካ በየአሉባልታው ሁሉ ዘራፍ እንዲል መሠረት አገኘ ማለት ነው፡፡ የጋጋታ ዕርምጃ አዙሪት ውስጥ ከተገባ በሕግ የተፈቀደ መብት እስኪመስል ድረስ ሊያምስ ይችላል፡፡

የአይሁድ ሃይማኖት፣ ክርስትናና እስልምና ከፍጥረት አመጣጥ አንስቶ ብዙ የተወራረሱ ነገሮች አሏቸው፡፡ ሦስቱም ዘንድ ተመሳሳይ ጉዳዮች የመኖራቸውን ያህል እነዚያው ተመሳሳይ ጉዳዮች የተለየ አተረጓጎምና ዝርዝር እንደ እምነቱ ይዘው የሚገኙበት ሁኔታ አለ፡፡ እስልምና በራሱ አተረጓጎም ስለሙሴ፣ ስለአብርሃምና ስለያዕቆብ ልጆች፣ ስለጠቢቡ ሰለሞን፣ ስለክርስቶስና ስለማሪያም፣ ወዘተ ቢያወራ በክርስትና ውስጥ መግባቱ እንዳልሆነ ማወቅና አተረጓጎሙን ለየቤተ እምነቱ መተው ከማያስፈልግ ንቁሪያ ያድናል፡፡ ከጊዜ ጊዜ በሚቀርብ የታሪክ ማስረጃና በክርክራዊ ሎጂክ እየተመራ እምነቱን የሚያስተካክልና የሚያጣራ ሃይማኖት እስከ ዛሬ ድረስ አለመታየቱን ማጤንም ትርፍ የለሽ የሃይማኖት ክርክር ውስጥ ከመግባት ለመቆጠብ ይበጃል፡፡

የሃይማኖቶችን የእምነት ስንክሳር ለየራሳቸው ብንተውም፣ በታሪክ ውስጥ ስለነበራቸው አኗኗር ሚዛናዊና እውነታዊ ዕውቀት መያዝ ጭፍን ፈራጅ ላለመሆን ያስፈልገናል፡፡ ነባር እምነትን ተጋፍቶ ብቅ የሚል እምነትም ሆነ ሳይንሳዊ ግኝት በቀድሞ ጊዜ የህልውና ፈተናው ቀላል አልነበረም፡፡ ክርስትናም ሆነ እስልምና በየተነሱበት ወቅት መሳደድ ደርሶባቸዋል፡፡ ሁለቱም በስብከትና በሰላም መንገዶች እንደተስፋፉ ሁሉ፣ በሰይፍና በጎራዴም እየዘመቱና እየተዘማመቱ ተስፋፍተዋል፡፡ አገርና አኅጉር ለተሻገረ ዘውዳዊ ኤምፓየር መስፋፋት ክርስትና ርዕዮተ ዓለም ሆኖ እንደነበር ሁሉ እስልምናም እንደዚያ ሆኖ ሠርቷል፡፡

በቅድመ ዴሞክራሲ አገዛዞች ሁሉ ዘንድ የመንግሥትና የሃይማኖት ቁርኝት የነበረና ያለ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አስገባሪ ሥርዓት ታሪክ ውስጥ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት የአገዛዙና የገዥዎቹ ዓይንና እስትንፋስ ሆኖ መኖሩ ወቸው ጉድ! የሚያሰኝ ክስተት አይደለም፡፡ በኦርቶዶክስ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖትነት ሥር ሌሎች ሃይማኖቶች ተጨቁነው መኖራቸውም የማይመለጥ ክስተት ነበር፡፡ በኃይል ሃይማኖት ማስለወጥ፣ እንቢ ያሉትን መግደል፣ አንዱን እምነት ተናቂ ሌላውን ተከባሪ ማድረግ፣ ከሥር ማለትም ከታች በዋሉ ሃይማኖቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በመንግሥታዊው ሃይማኖትም ውስጥ በተፈጠሩ  አፈንጋጭ ዝንባሌዎች ላይ ተካሂዷል፡፡

ተጨቋኝነቱ ከእምነቶች ተፈጥሮ (ባህርይ) ጋር ግንኙነት እንደ ሌለው ሁሉ፣ ጨቋኝነቱም የጭቆና መንበር ላይ ከተቀመጠው ሃይማኖት ዓይነትነት (ማንነት) ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ የትኛውም እምነት ከላይ በተቀመጠበት፣ የመንግሥት ሃይማኖት በሆነበት ሥፍራ ጭቆናውን አስነክቶታል፣ እያስነካውም ነው፡፡ በቅድመ ዴሞክራሲ አገዛዝ ውስጥ ስለምን የሃይማኖት ጭቆና ተደረገ የሚል ቁጭት ለምን ግራር እሾህ ኖረው ብሎ የመቆጨት ያህል ከንቱ ነው፡፡ የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነትን ባለማክበሩ ያለፈውን ዘመን ለመውቀስ መነሳትም በዱሮ ጊዜ ላይ የዛሬ ፍርድ መስጠት ይሆናል፡፡ ያኔ እንኳን በሥርዓት ደረጃ፣ በግለሰብ ደረጃ እንኳን ‹‹ሃይማኖቶች እኩል መሆን አለባቸው፡፡ መንግሥት ሃይማኖት ሊኖረው አይገባም፤›› የሚል አሳቢ የሚፈጠርበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ እንደዚያ ዓይነት ግለሰብ ተከስቶ ቢሆን ኖሮ እንኳ አዕምሮው የተነካ ወይም ጋኔል የሠፈረበት የጉድ ፍጥረት ተደርጎ ከመታየት አይዘልም ነበር፡፡ ዛሬ ስለሐሳብና ስለእምነት ነፃነት እያወራን ባለንበት ጊዜ እንኳ እኩልነትንና ነፃነትን ከማክበር የሚጎትቱ ዝንባሌዎች እየተፈታተኑን ሳለ፣ የእኩልነትና የፍትሕ እሴት ያልነበረውን ዘመን ባልነበረው ግንዛቤና እሴት መፍረድ አግባብ የለሽ ከመሆንም በላይ ሙልጭ ያለ አድሎአዊነት ነው፡፡

አንድ ሃይማኖት የአገርና የመንግሥት መታወቂያ የተደረገበትን ዘመን የሃይማኖት ጫና (በደል) የሌለበት አድርጎ ማድበስበስ እንደማያግባባ ሁሉ፣ ስንት ነገር ተፈጽሞባችኋል እንካችሁ እያሉ በደል መደርደርም ከታሪክ ተምሮ ዛሬን ለማቃናትና አስማምቶ ለማኗኗር አንዳችም ድርሻ አያዋጣም፡፡ ጭቆናን ሲዘረዝሩ ጨቋኝነቱ ከመንግሥት ባለ ሃይማኖትነት የሚመጣ መሆኑን ግራ ቀኝ እያጣቀሱ ማሳየት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ዓይነት አተያይ እስካላበጁ ድረስ በክርስቲያናዊ የበላይ ገዥነት ውስጥ የተካሄደውን የውድና የግድ የክርስትና መስፋፋትና በእስላማዊ የበላይ ገዥነት ትግል በኩል የተደረገውን የእስልምና መስፋፋት በአንድ ዓይነት ሚዛን ለመረዳት እንቸገራለን፡፡ ከየሃይማኖቱ አኳያ የተወረወሩ አድሏዊ ፍርዶችንም ማቃናት ይሳነናል፡፡ የአህመድ ኢብራሂምን የበላይነት ዓመታት አንዱ የቁጣና የውርጅብኝ ዘመን አድርጎ ሲሥል፣ ሌላው የእስልምና ሃርነት ትግል አድርጎ መቁጠሩ አመለካከትን የሆድና የጀርባ ያህል እንዳራራቀ ይቆያል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ፍንክርክ ፅንፈኞች ይነግዱበታልና የታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሐፊዎች ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...