Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ትኩረት ሰጥተን የምንሠራው ኮሮና ቫይረስ ድንገት ቢገባ መተላለፍ ሳይጀምር በሽታውን መቆጣጠር ላይ ነው›› ኤባ አባተ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር 

በኅዳር ወር መገባደጃ በቻይና ውሃን ከተማ የተከሰተው ኮሮና ቫይረስ የዓለም የጤና ሥጋት ሆኗል፡፡ በቻይና ብቻ ከ48 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲጠቁ፣ ከ1,400 በላይ ደግሞ ሞተዋል፡፡ ምንነቱ ያልታወቀውና መድኃኒት ያልተገኘለት ኮሮና ቫይረስ ከአምስቱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች አንዱ ነው፡፡ የቫይረሱን ምልክት በማከም በቫይረሱ የተጠቁትን የማዳን ዕድሉ ቢኖርም፣ ሕክምናው የተሟላ የፅኑ ሕሙማን መታከሚያ (አይሲዩ) የሚፈልግ ነው፡፡ የመተንፈሻ አካላትን በመጉዳት የሰውን ሕይወት በሚነጥቀው ቫይረስ የተጠቁ ሰዎችን የማከሙ ሁኔታ ለደሃ አገሮች ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ኢኮኖሚና የተጠናከረ የጤና ሥርዓት ያላቸውንም የሚፈትን ነው፡፡ እንደ አፍሪካ ባሉ ደሃ አገሮች በሚበዙባቸው አኅጉራት ደግሞ የቫይረሱ መከሰት ጉዳቱን የጎላ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም አገሮች የራሳቸውን የቅድመ መከላከያ ሥርዓት ዘርግተው ኮሮና ቫይረስ እንዳይከሰትባቸው፣ ካጋጠመም እንዴት ማስተናገድ እንደሚገባቸው እየሠሩ ነው፡፡ ከአሥር ሺሕ በላይ የቻይና ኩባንያዎችና ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቻይናውያን በሥራ ምክንያት በአፍሪካ ይገኛሉ፡፡ አኅጉሪቷም ከቻይና ጋር ያላት የንግድ ልውውጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው፡፡ በመሆኑም ለቫይረሱ ተጋላጭነቷ የጎላ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቫይረሱ ሊገባባቸው ይችላሉ ተብለው በዓለም ጤና ድርጅት ከተቀመጡ 13 ቀዳሚ አገሮች አንዷ ናት፡፡ በመሆኑም ቫይረሱ ኢትዮጵያ እንዳይገባ፣ ከገባም ባለበት ማቆም በሚቻልበት ላይ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከጤና ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡ ኤባ አባተ (ዶ/ር) የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ምሕረት ሞገስና ታደሰ ገብረማርያም ኢትዮጵያ ቫይረሱን ለመከላከል ባላት ዝግጅት ላይ አነጋግረዋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቻይና ኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በመከላከሉ ረገድ ያለው ሥራ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ኤባ፡- የዓለም ጤና ድርጅትና የቻይና መንግሥት እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 9 ቀን 2020 ገደማ ነው በቻይና የተከሰተው ወረርሽኝ፣ የኮረና ቫይረስ አምጪ ህዋስ መሆኑን የለዩት፡፡ የመጀመርያው ተጠቂ የተገኘው ዲሴምበር 31 ቀን ነው፡፡ በተለይ ይህ ክስተት ለዓለም ሕዝብ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥጋት መጠኑን እየለካ ነበር፡፡ ወረርሽኙ አድማሱን ያሰፋል ወይስ አያሰፋም? መተላለፊያ መንገዱስ ምንድነው? ኢትዮጵያ ያላት ተጋላጭነትስ እንዴት ነው? ይህ ከሆነ ደግሞ ምን መደረግ አለበት? የሚለውን በተለያዩ መንገዶች እየገመገምን ነበር፡፡ በዓለም ላይ ያለው ሥጋት እየጨመረ ሲመጣ ሁለት ግብረ ኃይሎች እንዲዋቀሩ አደረግን፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው ብሔራዊ ግብረ ኃይል አጠቃላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ሊሳተፉ የሚችሉ መንግሥታዊ አካላትን ያካተተ፣ በአጠቃላይ ሒደቱን እየገመገመ አቅጣጫ የሚያስይዝና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ነው፡፡ ሁለተኛው ግብረ ኃይል ደግሞ ቴክኒካዊ ሥራዎችን መሬት ላይ የሚሠራ ሲሆን፣ ይህንንም ኢንስቲትዩቱ ያስተባብረዋል፡፡ እዚህም ውስጥ የተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ከሁሉም በላይ ደግሞ ድጋፍ ሰጪ የልማት አጋሮች ማለትም የዓለም ጤና ድርጅት፣ ዩኤስሲዲሲ፣ አፍሪካ ሲዲሲና ሌሎችንም በጤና ዙሪያ የሚሠሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን ያካተተ ቴክኒካዊ ቡድን ነው፡፡ የሥጋቱ ሁኔታ እየጨመረ ሲመጣ ይህንን መዋቅራዊ በሆነ መንገድ ለመመለስና በዕዝ ለመምራት፣ ኢንስቲትዩቱ የሚመራው ‹ናሽናል ኢመርጀንሲ ኦፕሬቲንግ ሴንተር› በኢንስቲትዩቱ ቅጥር ጊቢ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ይህንንም እንቅስቃሴ የመንግሥት አካላት በቅርበት ይከታተሉታል፡፡ ይህንን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) የሚመሩት ሲሆን፣ አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ የእንቅስቃሴው ሪፖርት ለከፍተኛ የመንግሥት አካል እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ዓይነቱ መዋቅራዊ ሥራ መከናወኑ አንድ ነገር ሆኖ መሬት ላይ የሚሠሩ ተግባራትን እንዴት እያከናወናችሁ ነው?

ዶ/ር ኤባ፡- በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከዚህ በፊት የምንሠራቸው ሥራዎች ነበሩ፡፡ በተለይ ኢቦላ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ከተከሰተ በኋላ የተጀመሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሥራዎች ማጠናከርና የሰው ኃይል የመጨመር ሥራ ነው የምንሠራው፡፡ 80 የሚሆኑ የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተመድበው በሦስት ሺፍት ለ24 ሰዓት ይሠራሉ፡፡ ሐኪሞችና ሌሎች የጤና ባለሙያዎች የተደራጁበት ጊዜያዊ ማቆያም አለን፡፡ በአውሮፕላን ማረፊያው የሙቀት መጠን ይለካል፡፡ ይህም ሆኖ ግን አንድ ሰው በተለያየ ምክንያት የሙቀት መለያውን ሊያልፍ ይችላል፡፡ አንቲባዮቲክ (ፀረ ተዋህስያን) ወስዶ ሙቀት ላይኖረው ይችላል፡፡ በወቅቱ ትኩሳት ሳይኖረው ሊያልፍ ይችላል፡፡ በመሆኑም ከቻይናና በሽታው ከተከሰቱባቸው አካባቢዎች የመጡ መንገደኞች በሚሞሉት አድራሻ መሠረት፣ የየዕለቱን የጤና ሁኔታቸውን ለሁለት ሳምንት ያህል ክትትል እናደርጋለን፡፡ ለዚህ ምላሽ የሚሰጥና 24 ሰዓት የሚሠራ ቡድንም አለ፡፡ ማኅበረሰቡ ውስጥ ጭምጭምታ ወይም ጥቆማ ሲኖር ጥቆማውን ተንተርሰን በሁለት ሰዓት እሱን የሚያጣራ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፡፡ ሥራው በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ወደ ክልልም እንዲወርድ እያደረግን ነው፡፡ በክልል ጤና ቢሮዎች ሥር ያሉ የበሽታ መከላከያና ቁጥጥር አደረጃጀቶች ይህንን እያስተባበሩ፣ ከኢንስቲትዩቱ የመረጃ ልውውጥና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ የተለያዩ ዜጎች በተለይ ቻይናዎች የሚሰበሰቡባቸው፣ በአንድ ጊዜ ደግሞ ብዙ ሺሕ ሠራተኞች የሚሠሩባቸው ስለሆኑ ቅድመ ጥንቃቄው እነሱንም ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ችግሮች ቢከሰቱ እንኳን ሊመልስ የሚችል አደረጃጀት ለመፍጠር የጤና ተቋማትን ማደራጀት፣ ፅኑ ሕክምና የሚፈልጉ ግለሰቦች በቅዱስ ጴጥሮስና በየካ ኮተቤ የሚታከሙበትን የማደራጀት ሒደት ከምናደርጋቸው ዝግጅቶች መካከል ይገኙበታል፡፡ ለማኅበረሰቡ፣ ለጤና ባለሙያዎች፣ ለአየር መንገድ ሠራተኞች፣ ለፀጥታ ኃይሎች፣ ለሆቴል ባለሙያዎች፣ ለታክሲ ሾፌሮች ሥልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ ይህ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ እንደ መሆኑ መጠን በአጭር ጊዜ ሁሉንም የምንጨርሰው ሳይሆን በሒደት የምናሟላው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሙቀት ምርመራው የሚደረገው ከቻይና ለሚመጡ መንገደኞች ብቻ ነው? ወይስ ከሌሎች አገሮች የሚመጡትን ያጠቃልላል? ምክንያቱም ቫይረሱ ወደ 26 የሚጠጉ አገሮችን አዳርሷልና፡፡

ዶ/ር ኤባ፡- ሙቀት መለካትን በተመለከተ ከቻይና ብቻ መሆን የለበትም፣ መስፋት አለበት፡፡ አብዛኛው ወይም 99 በመቶ ችግሩ ያለው ቻይና ውስጥ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የሚታየው ከአንድ በመቶ በታች ነው፡፡ ነገር ግን የእኛ ሙቀት ልየታ ሁሉንም ያካትታል፡፡ ቻይናና ከቻይና ውጪ የመጡ መንገደኞችን ሁሉ የሚያካትት ነው፡፡  ሁለተኛው የሙቀት ልየታችን ሁሉንም መንገደኞች የሚያካትት ነው፡፡ የመጀመርያ፣ የመጨረሻና መሀል ላይ ያለው የሙቀት ልየታ ግን ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራው ከቻይና የመጡ መንገደኞችና በሽታው ከተከሰተባቸው አገሮች የሚመጡት ላይ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በድንበሮች አካባቢ ያለው ቁጥጥርስ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ኤባ፡- የመጀመርያው ትኩረታችን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ነው፡፡ ምክንያቱም መጀመርያ የተከሰተው በቻይና ነው፡፡ ከፍተኛ ፍሰትም የሚኖረው ከቻይና ነው፡፡ ቤጂንግ ያለ ሰው በአሥር ሰዓት ውስጥ ኢትዮጵያ ይደርሳል፡፡ ስለዚህ የመጀመርያ ሩጫችን የሚሆነው አውሮፕላን ማረፊያው ጋ ነው፡፡ ያንን ስናደርግ አካባቢዎችንም ታሳቢ አድርገናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ27 በላይ በሚሆኑ የየብስ ድንበሮች ላይ የሙቀት ልኬት እናካሂዳለን፡፡ የባቡር መስመራችን ከጂቡቲ ጋር ስለሚያገናኝ ድሬዳዋ ላይ የልየታ ሥራ እየተካሄደ ነው፡፡ የሙቀት ልየታው የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ብቻ ታሳቢ ያደረገ ሳይሆን፣ የየብስ ኮሪደሮቻችንንም ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ነገር ግን አጠቃላይ ፍሰቱን ካየን አሁን ከፍተኛ ፍሰት ያለው በአየር ትራንስፖርት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አፍሪካ ውስጥ በኢንቨስትመንትና በሌሎች ሥራዎች አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ቻይናውያን ይኖራሉ፡፡ አሥር ሺሕ ያህል የቻይና ኩባንያዎችም አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ከቻይና የሚኖረው ፍሰት ከፍተኛ በመሆኑ፣ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ፈጥራችሁ እየሠራችሁ ነው?

ዶ/ር ኤባ፡- የመጀመርያ ሥራችን በቀጥታ ከቻይና የሚመጡና የጉዞ መዳረሻቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉት ላይ ነው፡፡ የአኅጉራዊ ቅንጅቱ መኖርም አግባብ ነው፡፡ ይህን የሚያደርግ የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከል ድርጅት (የአፍሪካ ሲዲሲ) ተቋቁሟል፡፡ በተለይ ምሥረታውን በተመለከተ ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና ነበራት፡፡ መቀመጫውም እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ በተጨማሪም ከ15 በላይ የሚሆኑ የአፍሪካ አገሮች እንደ ኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በየአገራቸው አቋቁመዋል፡፡ ይህንን የሚያስተባብሩ አካላት ውይይት የምናደርግበት፣ መረጃ የምንለዋወጥበት አሠራር አለን፡፡ ማስተባበሩን የአፍሪካ ሲዲሲ የሚሠራው ሲሆን፣ እርስ በርሳችን የምንነጋገርበትና መረጃ የምንለዋወጥበት አግባብም አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች የመጡ በርካታ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በስደተኞች አካባቢ ያለውን ሁኔታ እንዴት ነው ያያችሁት?

ዶ/ር ኤባ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም የመግቢያ በሮች መድረስ ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን የትኛው ነው በጣም ትኩረት የሚፈልገው የሚለው መፈተሽ አለበት፡፡ ለምሳሌ አንደኛው ትኩረታችን ስደተኞች ላይ ነው፡፡ ባለፈው በነበረው ግምገማ በተቻለ መጠን እነሱንም ታሳቢ አድርገን አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በተወሰነ መንገድ ስደተኞችን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎችን ለመሥራትና ለማስፋት ሙከራ እየተደረገ ነው፡፡ ኮሮናን በተመለከተ ግን ትኩረታችን በየብስ የሚገቡ ኮሪደሮች፣ የአየር ማረፊያና የባቡር መስመሮች ናቸው፡፡ አሁን ግን ስደተኞች አካባቢ ያለውን ሒደት የምናይበት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

ሪፖርተር፡- በሽታው ኢትዮጵያ ውስጥ ቢገባ አገሪቱ ምላሽ ለመስጠት ምን ያህል አቅም አላት? ድንገተኛ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችል መጠባበቂያ በጀት ይያዛል?

ዶ/ር ኤባ፡- ወረርሽኝ በተለያዩ መንገዶች አገር ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ትልቁ ነገር አሁን እኛ የቅድመ መከላከል ሥራችን እንዲያተኩር የምንፈልገው አቅምን መገንባት ላይ ነው፡፡ ቢገባ ያንን ሊሸከም የሚችል አቅም ፈጥረናል ወይ ስንል፣ አሁን ባሉት የጤና ተቋማት አስገንብተን አገልግሎት ለመስጠት አንችልም፡፡ ባለሙያ ሌላውን በሽተኛ ለማየት ሲገባ የለበሰውን የልብስ ዓይነት ለብሶ መግባትም አይችልም፡፡ ስለዚህ ከላይ እስከ ታች ያለውን ታሳቢ ባደረገ መንገድ ነው ሥራዎችን ስንሠራ የነበረው፡፡ ሐኪሞች የመከላከያ አልባሳትንና ሌሎችንም ተጠቅመው ሕክምና የሚያደርጉበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን መታሰብ የሚኖርበት ማኅበረሰባችን ውስጥ ከገባ በኋላ የመተላለፍ ሒደት ሳይጀምር፣ ወዲያው በሽታውን ማግኘት ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ ምክንያቶች የጤና ሥርዓታችን አውሮፓና አሜሪካ እንዳለው ዓይነት አይደለም፡፡ ደካማ ነው፡፡ ምንም እንኳን የተለያየ ለውጥ በየጊዜው እየመጣ ቢሆንም፣ የጤና ዘርፉ አሁንም ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ይህንን ታሳቢ ባደረገ ቅድሚያ የምንሰጠው ማኅበረሰቡ ውስጥ ሳይተላለፍ፣ ወዲያው ቶሎ አውቀንና ለይተን የምናስቆምበትን መንገድ መፍጠር ላይ ነው፡፡ ይኼ የሚያሳየን ብዙ ነገር አለ ብዬ  አስባለሁ፡፡

ብዙ ጊዜ ወረርሽኝ ሲመጣ ነው የጤና ሥርዓታችንን የምናየው፡፡ ይህ ግን መሆን የለበትም፡፡ ወረርሽኝ በማንኛውም ጊዜ ይመጣል፡፡ ይኼ ችግር በእርግጠኝነት ነገ ይጠፋል፡፡ ይህ ማለት ግን ወረርሽኝ ሌላ ጊዜ አይመጣም ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ምንጊዜም ወረርሽኝ ታሳቢ ተደርጎ መሠራት አለበት፡፡ የጤና ዘርፉን ማጠናከር ማለት በቀጥታ ለወረርሽኝ የሚያበቃውን ሁኔታ ማጠናከር፣ ያንን ሊሸከም የሚችል ብቃት መፍጠር ማለት ነው፡፡ ለጤና ዘርፉ የሚመደበውም በጀት እዚህ ላይ ታሳቢ መደረግ መቻል አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ለአንድ ሰው የምታወጣው የጤና ወጪ በዓመት ወደ 23 ዶላር ነው፡፡ ይህ ከዓለም አቀፉ አማካይ ጋር ሊገናኝ አይቻልም፡፡ የአፍሪካን አማካይ እንኳን ብናየው የኢትዮጵያ በእጅጉ ዝቅ ያለ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ችግሮችን ለመሸፈን ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ለጤና የምንመድበው በጀት ላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ተገቢው በጀትም መመደብ አለበት፡፡ ይህ ሲሆን መሠረተ ልማቶችና አቅም ይገነባሉ፡፡ አደጋ በሚመጣበት ወቅት ለመመለስ የሚኖረውን ሩጫ ይቀንሳል፡፡ ለጤና በተለይ ለአደጋና ለቅድመ ዝግጅት የሚመደበው በጀት ዳግም መታየት አለበት፡፡ ድንገት ለሚከሰቱ ወረርሽኞች መንግሥት ምንጊዜም መጠባበቂያ በጀት አለው፡፡ መጠባበቂያ በጀቱን በምናቀርበው ዕቅድ መሠረት የሚመደብ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሩት አጠቃላይ ግምገማ ነበር፡፡ እዚያ ላይ የተላለፈው አቅጣጫ አስፈላጊውን ወጪ አድርጎ ችግሩን መመከት ይገባል የሚል ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመንግሥት ብቻ የሚሸፈን ሳይሆን የልማት አጋሮችን ማሰተባበርንም ይጠይቃል፡፡ የተለያዩ ድርጅቶችን ማካተት ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም ጫናው በመንግሥት ብቻ የሚሸፈን አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ግንዛቤ መፍጠሩ ላይ ምን ዓይነት አሠራሮችን እየተከተላችሁ ነው?

ዶ/ር ኤባ፡- ችግሩ ቢከሰት በአፋጣኝ የእርምት ዕርምጃዎችን ለመውሰድና ለእኛም የማሳወቁን ሥራ ለማከናወን፣ የማኅበረሰቡን ንቃተ ህሊና ከፍ ማድረግና ስለበሽታው ግንዛቤ የሚጨበጥበትን ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ማድረግ የኢንስቲትዩቱ ሚና ብቻ አይደለም፡፡ በማዕከል ከእኛ ጋር የሥራ ግንኙነት ካላቸው ተቋማት ጋር አብረን የምንሠራው ነው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ አብዛኞቹን የጤና ተቋማትን የሚያስተዳድረው የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ስለሆነ፣ ከቢሮው ጋር በጥምረት እየሠራን ነው፡፡ ወደ ታች ማውረድ ላይ ግን የተወሰኑ ክፍተቶች አሉ፡፡ ጊዜ የሚፈልጉ ሁኔታዎችም አሉ፡፡ አሁን ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሚዲያ አካላት ጋር የምንገናኝባቸው ሁኔታዎችን እየፈጠርን ነው፡፡ ቢያንስ በሳምንት አንድና ሁለት ጊዜ እየተገናኘን ከሚዲያ አካላቱ ለሚቀርቡልን ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት እየሠራን ነው፡፡ በየጊዜው በኢንስቲትትዩቱና በጤና ሚኒስቴር ድረ ገጾች የምንለቃቸው መረጃዎች አሉ፡፡ ሁለተኛው ግን ራሳችን ተነሳሽነቱን ወስደን ከተለያዩ ተቋማት ጋር የባለሙያዎች ውይይት ማድረግ፣ የማኅበረሰባችንን ንቃተ ህሊና ከፍ ለማድረግ የሚረዱ ውይይቶች ባለፈው ሰኞ (ጥር 2 ቀን 2012 ዓ.ም.) ተጀምረዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር አብዛኛው ማኅበረሰባችን ምናልባት የሚዲያ ተደራሽነት ላይኖረው ይችላል፡፡ ስለዚህ እስከ ወረዳ የሚደርስ መዋቅር ስላለን በየጊዜው መረጃ እንሰጣለን፡፡ በተለይ ክልል ላይ ሥራውን የሚያከናውነው ክልሉ ነው፡፡ ስለዚህ በቅርቡ በነበረው ግምገማ የጤና ቢሮ ኃላፊዎች ብቻ ይህንን ሁኔታ ከሚመሩት፣ ከፍ ያለው የክልል አመራር እርከን እንዲመራው በቅርቡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊርማ የሚወጣና የክልል ፕሬዚዳንቶች በክልላቸው ያለውን ግብረ ኃይል የሚመሩበትና የሚያስተባብሩበት፣ ወደ ታችም የሚወርዱበት አሠራር እየተዘጋጀ ነው፡፡ ‹ስፖቶች› እየዘጋጁና እየተለቀቁ ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን በተለያየ መንገድ ማኅበረሰቡን ተደራሽ ለማድረግ እየሞከርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው ጊዜ ኢቦላ ተባለ አሁን ደግሞ ኮሮና ቫይረስ እየተባለ ነው፡፡ ማንኛውንም ወረርሽኝ ለመከላከል የጤና ሥርዓቱ አቅም ምን ይመስላል?

ዶ/ር ኤባ፡- የአሁኑ ሥራ ለዚሁ ተብሎ የተጀመረ አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2014 እስከ 2015 በአፍሪካ ኢቦላ ሲከሰት ማንቂያ ሆኖናል፡፡ በዓለም ላይ ወረርሽኝ ቢከሰት ምላሽ ሊሰጥ የሚችል አደረጃጀት አልነበረም፡፡ ሁሉም የየራሱን ነበር ሲሠራ የነበረው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2014 እስከ 15 ግን ኢቦላ ወደ 11,000 ሰው ሲጨርስና የኢኮኖሚ ተፅዕኖው ሲታይ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ እንደ አሜሪካና አውሮፓ አገሮች ሲገባ አቅም ያላቸውን አገሮች አስደነገጣቸው፡፡ አገሮች ብዙ ገንዘብ እያላቸው አፍሪካ ላይ ኢንቨስት ካላደረጉ በስተቀር፣ የሚከሰተው ችግር እነሱም ዘንድ እንደሚያንኳኳ ሲያውቁ ነው ሥርዓታቸውን ማጠናከር የጀመሩት፡፡ አገራችን ብዙ ችግሮች አሉባት፡፡ ደሃ ነች፣ የአቅም ውስንነት አለባት፣ ለጤና የሚመደበው ከጂዲፒው አምስት በመቶ ያህሉ ብቻ ነው፡፡ አቡጃ ላይ አንድ አገር የጂዲፒውን 15 በመቶ ለጤና መመደብ እንዳለበት ስምምነት ቢደረግም፣ የእኛ ግን አምስት በመቶ ነው፡፡ ወረርሽኞችን ለመከላከል ጥናትና ምርምር የሚደረግበት ላቦራቶሪ ያስፈልጋል፡፡ ኢንስቲትዩቱና ጤና ሚኒስቴር በቅንጅት ለአንድ ዓመት ተኩል ከዓለም ባንክ ጋር ሲያደርጉት የነበረው ድርድር ፍሬ አፍርቶ እ.ኤ.አ. በ2019 ማብቂያ የዓለም ባንክ ቦርድ 150 ሚሊዮን ዶላር አፅድቆልናል፡፡ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ጋር ይህንን ፊርማ የካቲት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ተፈራርመዋል፡፡ በዚህም ገንዘብ የሚከናወነው የመጀመርያው ሥራ በምሥራቅ አፍሪካ የልቀት ማዕከል የሚሆን፣ በአጠቃላይ ማንኛውም በሽታ ቢከሰት ኢቦላንም ጭምር ሊመረምርና ሊያስተዳድር የሚችል አቅም ያለው ላቦራቶሪ ከእነ ሙሉ ዕቃዎች በኢንስቲትዩቱ ቅጥር ግቢ ይገነባል፡፡ በየክልሉ 15 ተመሳሳይ ላቦራቶሪዎች ይሠራሉ፡፡ ሌላው ለወረርሽኝ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ አጋዥ የሚሆነውን ክፍል የማጠናከር ሥራ ይከናወናል፡፡ የማቆያ ማዕከል ዘላቂ በሆነ መንገድ እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ይካሄዳል፡፡ በአጭር ቀናት ውስጥ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሪፖርተር፡- የት ነው የሚገነባው?

ዶ/ር ኤባ፡- ግንባታው በኢንስቲትዩቱ ግቢ እስከ ስምንት ሺሕ ሜትር ካሬ ቦታ ላይ የሚያርፍ ይሆናል፡፡ የመተላለፍ ሒደታቸው ከፍተኛ የሆኑ በሽታ አምጪ ተህዋስያኖችን ሊይዝና ሊቆጣጠር የሚችል ላቦራቶሪ ነው፡፡ በአጠቃላይ የአምስት ዓመት ዕቅድ ነው፡፡ በተጠቀሰው ዓመት ሁሉም ነገር ይጠናቀቃል የሚል እምነት አለን፡፡ በሒደት ደግሞ መንግሥት ለጤና ዘርፉ የሚመድበው በጀት ያድጋል የሚል እምነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ላቦራቶሪው መቋቋሙ አንድ ነገር ሆኖ፣ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን ጉዳይ እንዴት ነው እያያችሁት ያለው?

ዶ/ር ኤባ፡- የዚህ ድጋፍ ከሌላው ዓይነት ድጋፍ ለየት የሚያደርገው ሁሉን ነገር ሙሉ ማድረጉ ነው፡፡ ለዚህ በጀት ተይዟል፡፡ የሚፈለገው ነገር ከውስጥም ከውጭም ተገዝቶ ይቀርባል፡፡ የተሟላ ላቦራቶሪ ይሆናል፡፡ ሌላው የሰው ኃይል ነው፡፡ የሰው ኃይል ግንባታም አለው፡፡ ለምሳሌ ከፍተኛ ሥልጠና የሚፈልጉ፣ በኤክስፐርት ደረጃ ከፍተኛ ክህሎትን የሚፈልጉ ሥራዎች ሁሉ በፓኬጆቹ ውስጥ ተካተዋል፡፡ በተረፈ ውጤቱን ወደፊት እናየዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በኮሮና ቫይረስ ሞት እየተመዘገበ ቢሆንም ድነው የወጡም አሉ፡፡ የታመሙ ድነው ለመውጣት የሚያስችሏቸው መድኃኒቶች ለመጠባበቂያ ያህል አሉ? የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ተዘጋጅቷል ወይ?

ዶ/ር ኤባ፡- ኮሮና የመተላለፊያ መንገዱ የኮሮና ዝርያ ከሆነው ሳርስ በላይ ነው፡፡ ያም ቢሆን የመግደል ምጣኔው እንደ ኢቦላ አይደለም፡፡ አንድ ሰው በኢቦላ ከተያዘ የሞት ዕድሉ ከ50 እስከ 60 በመቶ በላይ ነው፡፡ ሳርስ ወደ ዘጠኝ በመቶ ገደማ ነው፡፡ ኮሮናን ካየነው ግን ከሁለት እስከ ሦስት በመቶ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኮሮና 26 በመቶ ገደማ የፅኑ ሕሙማን (የአይሲዩ) ሕክምና ይፈልጋል፡፡ ከመድኃኒት አንፃር ግን ለዚህ ተብሎ የተዘጋጀ ፍቱን መድኃኒት የለውም፡፡ ነገር ግን ምልክቶቹን ማከም ይቻላል፡፡ ሁሉም ባይሆን አብዛኛው ሰው ከዚያ የመዳን ዕድል አለው፡፡ ለዚህም የመድኃኒት ክምችት አለን፡፡ በተለይ ትልቁ ሥራ መሠራት ያለበት መከላከሉ ላይ ነው፡፡ ሕክምናው በኋላ ላይ የሚመጣ ነው፡፡ የመከላከያ ቁሳቁሶችን በተመለከተ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችንም ለጤና ድርጅቶችና ለክልሎችም እየሰጠን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ 450,000 ማስኮች አሉን፡፡ ይህንን ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ዶ/ር ኤባ፡- የዓለም ጤና ድርጅት በየአገሩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አሉት፡፡ ኢትዮጵያም ውስጥ ብዙ ሠራተኞችን ያቀፈ ትልቅ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አለው፡፡  እንዲህ ዓይነት ችግር ሲከሰት ከእኛ ጋር በጣም በቅርበት ነው የሚሠራው፡፡ ለኮሮና ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ወረርሽኝ ትኩረት ይሰጣል፡፡ እያንዳንዱን ሥራ በጋራና በቅንጅት እንሠራለን፡፡ የመረጃ ልውውጦችን፣ ቴክኒካዊ ድጋፎችን የምናገኝበት ሁኔታም አለ፡፡ ይኼም ብቻ ሳይሆን 196 አገሮች የፈረሙበት ‹ኢንተርናሽናል ሔልዝ ሬጉሌሽን› የሚባል አለ፡፡ ኢትዮጵያም አንዷ ፈራሚ አገር ናት፡፡ እያንዳንዱ አገር ችግር በሚያጋጥመው ወቅት በ24 ሰዓት ውስጥ ለዓለም ጤና ድርጀት ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ያንን ታሳቢ ባደረገ መንገድ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ ለምሳሌ የላቦራቶሪ መመርመርያውን ኪት ለማግኘት የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛውን ድጋፍ አድርጎልናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...