Sunday, July 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ በእንግሊዝ ዕውቅና ሰጪ ኩባንያ ተሸለመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ 77 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‹‹ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ›› በተባለው ተቋም አማካይነት ምርጥ ባንክ በመባል ዕውቅና ማግኘቱን ገለጸ፡፡ የነበረበት የገንዘብ እጥረት ጊዜያዊ እንደነበርና አሁን እንደተቃለለ አስታውቋል፡፡

ባንኩ በ77 ዓመታት ታሪኩ ከውጭ ተቋም ያገኘው ሽልማት በተለያዩ ዘርፎች ከተወዳደሩ ምርጥ ባንኮች ጋር ተወዳድሮ ለሽልማት እንደበቃ ያስታወቁት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና፣ ለመሸለም ካበቁት መሥፈርቶች መካከል ለዓመታት በትርፋማነት መጓዙ፣ ተደራሽነቱን በፍጥነት ማሳደግ መቻሉ፣ የደንበኞችን ቁጥር ማስፋፋቱ፣ ለልማት ሥራዎች የሚውለውን የፋይናንስ አቅርቦት ማሳደጉ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱና ሌሎችም የባንክ አገልግሎቶችን አሟልቶ ማቅረቡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡  

ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ በ2019 ካዘጋጃቸው የመወዳደሪያ ምድቦች መካከል፣ ‹‹ምርጥ የንግድ ባንክ›› በሚለው ምድብ ተደልድሎ መሸለሙን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ከንግድ ባንክ ባሻገር በተለያዩ ምድቦች ሽልማት ያገኙ ባንኮችንም አውስተዋል፡፡ ምርጥ የኢስላሚክ ባንክ በመባል የተመረጠው የአፍጋኒስታኑ ኢስላሚክ ባንክ ኦፍ አፍጋኒስታን ነው፡፡ ምርጥ የኢኖቬሽን ባንክ በመሆን ጭምር አሸናፊ የሆነው የአርመኑ ዲጂታል ባንክ ነበር፡፡ የቦትስዋናው ኤፍኤንቢ ቦትስዋና፣ የባህሬኑ ቢቢኬም ምርጥ የንግድ ባንክ ወይም Best Retail Bank በመባል ስለመሸለማቸው አቶ ባጫ ጠቅሰዋል፡፡ ግሎባል አውትሉክ ተወዳዳሪ ተቋማትን የሚለካባቸው የማወዳደሪያ ዘርፎች የተለያዩ በመሆናቸው የግብፁ ብሔራዊ ባንክ ከአሸናፊዎች ዝርዝር ውስጥ እንደሚገኝበት በሽልማቱ ዙሪያ የቀረበው ማብራሪያ ያሳያል፡፡  

ከዚህ ቀደም የግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ሽልማት አሸናፊ ከነበሩ አገሮች መካከል ካናዳ፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ ፖርቹጋል፣ ህንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ባንኮች እንደሚገኙበት አቶ ባጫ ገልጸው፣ ሽልማቱ በግሎባል ቢዝነስ ከዚህ ቀደም ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ከአፍሪካ አገሮች የተሸለሙት የደቡብ አፍሪካና የናይጄሪያ ባንኮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ለዘመናት ባካበተው ልምድና አስተዋጽኦ እ.ኤ.አ. የ2019 ተሸላሚ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሽልማቱ ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ በሚያወጣቸው መሥፈርቶች ተመሥርቶ እንደሚካሄድ አስታውሰዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ምርጥ ባንኮችን ደረጃ እያገኘ የመጣ ሲሆን፣ ለዚህ ዓለም አቀፍ ሽልማት ሲበቃም በባንኩ ታሪክ የመጀመርያው ነው፤›› ብለዋል፡፡ የባንኩ መረጃ እንዳመላከተውም፣ ባንኩ ለሽልማት ካበቁት ጥረቶቹ መካከል ከምሥረታው ጀምሮ የሠራቸው ውጤታማ ሥራዎች እንዳገዙት አስፍሯል፡፡  

ይህ ሽልማት ባንኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ አብረውት ከሚሠሩ ባንኮች ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክር ዕድል የሚሰጠው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ባጫ፣ በሌሎች የመወዳደሪያ ዘርፎችም ተጨማሪ ሽልማት ለማግኘት የሚያነሳሳው እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችሉ ግዙፍ ሥራዎችን በግንባር ቀደምትነት በመደገፍ ላይ እንደሚገኝ ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው ብለው ከጠቀሷቸው መካከል የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት ማሳደግ ለሚያስችሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ፋይናንስ በማድረጉ ነው፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ የተጠቀሰው ባሳለፍነው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ሥራ የጀመረው የገናሌ ዳዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ነው፡፡

በጋራ ቤቶች ልማት ፕሮግራም፣ ለተለያዩ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች በተለይም እንደ ስኳርና ባቡር ያሉትን ጨምሮ ሌሎችም መስኮች ላይ ፋይናንስ በማቅረብ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

ባንኩ ለተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ መጠን ያለው ፋይናንስ እያደረገ ካለው ጥረት ባሻገር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት መድቦ የኅብረተሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ እንደቆየም አመልክቷል፡፡ እንዲህ ያሉ ተግባሮቹ ለሽልማት እንዳበቃው የሚገልጸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ይህ ሽልማት ባንኩን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪ ለማድረግ ለተያዘው ዕቅድ ስኬት የራሱ አስተዋጽኦ አለው ተብሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአጭር ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ለፕሬዚዳንቱ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል በአሁኑ ወቅት ባንካቸው የገንዘብ ችግር አጋጥሞታል የሚለው ይገኝበታል፡፡ እሳቸውም በተወሰኑ ባንኮች ላይ የተወሰነ የገንዘብ ችግር አጋጥሞ እንደነበር ጠቅሰው፣ ይህ ችግር ግን በጣም ጊዜያዊ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከሁለት ሳምንት በፊት ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንደነበር የገለጹት አቶ ባጫ፣ አሁን ግን የሚያሠጋ ሁኔታ ላይ አለመሆኑና በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ እንደሆነ በመግለጽ አጭር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ዳያስፖራን በተመለከቱ የባንኩ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ በተሰጠው ምላሽም ዳያስፖራውን ለማድረስ በውጭ አገሮች ቅርንጫፍ ለመክፈት የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጁባና በጂቡቲ ቅርንጫፎች አሉ፡፡ ሌሎችም አካባቢዎች ለመክፈት እየተደረጉ ባሉ ጥናቶች አዋጪ መሆናቸው ከተረጋገጠ በተመረጡ ቦታዎች ቅርንጫፎች ይከፈታሉ ብለዋል፡፡ በዋናነት አሁን ጥናታቸው በመጠናቀቅ ላይ ካሉ ቅርንጫፎች ይከፈትባቸዋል ተብለው ከተያዙት ውስጥ ደቡብ አፍሪካ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች፣ ሰሜን አሜሪካና ሳዑዲ ዓረቢያ ተጠቅሰዋል፡፡ በእነዚህ አገሮች የመጨረሻው አዋጪነታቸው ታይቶ ቅርንጫፎቹ የሚከፈቱባቸው እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ባንኩ ለግል ዘርፍ ከማበደር ይልቅ ለመንግሥት ስለማድላቱ በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ በ2011 ዓ.ም. ለግል ዘርፉ 22.5 ቢሊዮን ብር ማበደሩን ጠቁመዋል፡፡ በ2012 ግማሽ ዓመት ለግሉ ዘርፍ የሰጠው የብድር መጠን ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ለመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ብድር መስጠቱን አገራዊ ጠቀሜታ በማሰብ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ ባንኩ ፋይናንስ ያደረገባቸው ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረት መሆናቸውን ማጤን እንደሚገባ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ከዚህ በመነሳት ለመንግሥት ፕሮጀክቶች የሚውለው ብድር አግባብ እንደሆነ በመግለጽ የፋይናንስ አቅርቦቱ አግባብነት እንዳለው ሞግተዋል፡፡ 

እንደ እ.ኤ.አ. በ2025 ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ ባንክ ለመሆን የያዘውን ዕቅድ የሚያሳካው በደንበኞቹና በሠራተኞቹ፣ እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያዊያን አብሮነትና ድጋፍ በመሆኑ የደንበኞቹንና አጋሮቹን ድጋፍ እንደሚሻ አስታውቀዋል፡፡  

እንደ ባንኩ መረጃ በአሁኑ ወቅት ከ62 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 38 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ቋሚ ሠራተኞች ናቸው፡፡ ከ24 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ጊዜያዊና በሌሎች ቀጣሪ ድርጅቶች በኩል የሥራ ዕድል የፈጠረላቸው መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ከ1,560 በላይ ቅርንጫፎችን የከፈተው ንግድ ባንክ፣ የደንበኞቹን ቁጥርም ከ23.5 ሚሊዮን በላይ ስለማድረሱ አስታውቋል፡፡  

ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ የሆነና፣ በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢነርጂ፣ በሪል ስቴት፣ በልዩ ልዩ የንግድ መለያዎች፣ በትምህርትና በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ በማተኮር ልዩ ልዩ ትንታኔዎችና ሪፖርቶችን የሚያሳትም ተቋም ሲሆን፣ በየዓመቱም በግልና በመንግሥት የሚተዳደሩ ኩባንያዎችን ከላይ በተዘረዘሩት መስኮች ላይ ውጤታማነታቸውን እየመዘነ የሚሸልም ድርጅት ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች