ዜጎች በሰላማዊ መንገድ የአደባባይ ስብሰባዎችን ወይም ሰላማዊ ሠልፎች ለማድረግ የመንግሥትን ፈቃድ መጠየቅ እንደማያስፈልጋቸው ቢነገርም፣ የስብሰባውን ወይም የሰላማዊ ሠልፉን ዓላማ ግን በዝርዝር ጽፈው የማሳወቅ ግዴታ እንዳለባቸው የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ፡፡ አዋጁ መዘጋጀቱ የተገለጸው ቅዳሜ የካቲት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት በተደረገ ውይይት ነው፡፡
አዋጁ የተዘጋጀው ለረዥም ጊዜ አገልግሎት ላይ የቆየውንና አሁንም በሥራ ላይ የሚገኘውን፣ የሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 3/1983 ለመቀየር ነው፡፡ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር የሚመራው የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት የጥናት ቡድን የተዘጋጀው ረቂቅ እንደሚስረዳው፣ ቀደም ብሎ በሥራ ላይ የዋለው አዋጅ ቁጥር 3/1983 መሠረታዊ ክፍተቶች አሉበት፡፡
አዋጁ ዕውቅና የሚያስፈልጋቸውንና የማያስፈልጋቸውን ሠልፎች የማይለይ፣ የሰላማዊ ሠልፍ አዘጋጆችን መብትና ኃላፊነት በግልጽ የማይደነግግና በዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ገደቦች የነበሩበት መሆኑን የጥናት ቡድኑ ገልጿል፡፡
እንደ ቡድኑ ገለጻ አዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ግን፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ድንጋጌና ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋትን መሠረት በማድረግ የተዘጋጀና የነበሩትን ክፍተቶች የሚያርም ነው፡፡
የቡድኑ አባል ቃል ኪዳን ነጋሽ (ዶ/ር) የረቂቅ አዋጁን ዓላማ አስመልክተው እንዳብራሩት ዜጎች ሰላማዊ በሆነ አግባብ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግና አቤቱታ የማቅረብ መብት አላቸው፡፡ መንግሥትም ጥበቃ የማድረግ ግዴታ እንዳለበትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን ዕውን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን የቤት ውስጥና የአደባባይ ስብሰባዎች ማዘጋጀት መብቱ መሆኑንና ከመንግሥት ፈቃድ እንደማይጠየቅም አክለዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ስብሰባዎችንም ሆነ ሰላማዊ ሠልፎችን በሚያዘጋጁ ላይ ግዴታና ኃላፊነት የሚጥል ሲሆን፣ ሰብሰባው ከመደረጉ አምስት ቀናት ቀደም ብሎ ለከተማ አስተዳደሩ ወይም ለወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የስብሰባውን ዓላማ፣ ቀንና ሰዓት በጽሑፍ ማሳወቅ ግዴታ ነው፡፡
የፀጥታ ኃይሎችም የደንብ ልብስ ለብሰው ጥበቃ ማድረግ እንዳለባቸውም በረቂቅ አዋጁ ተጠቅሷል፡፡ በረቂቅ አዋጁ ዓላማና ይዘት ላይ በርካታ ጥያቄዎች እየቀረቡ መሆኑንና ተጨማሪ ሐሳቦች ሊታከሉ እንደሚገባ አስተያየቶች እየቀረቡ መሆኑም ታውቋል፡፡