Tuesday, March 5, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር የሚቻለው በአንድነት መቆም ሲቻል ነው!

ኢትዮጵያ ጥቅሟን ለማስከበር የምታደርገው ጥረት በበርካታ ፈተናዎች የተከበበ ለመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን የሚከታተሉ ዜጎች በሚገባ ይረዳሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተለይ ከግብፅ ጋር የሚደረገው ድርድር፣ ምን ያህል ከባድና ፈታኝ እንደሆነ በግልጽ ይታወቃል፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በአንድነት ማቆም ካልተቻለ፣ ፈተናው የበለጠ እየከበደ ይሄዳል፡፡ ፈተናውን ማቅለል ካልተቻለ ደግሞ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ መስጠት ውስጥ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት አሳሳቢ ሁኔታ ብርቱ ምክክር ያሻዋል፡፡ የፖለቲካ ልሂቃን በሚፈጥሩት ሽኩቻ ምክንያት ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ መከፋፈል እየተፈጠረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ዓይታው የማታውቀው ክፍፍል ሲፈጠርና ልዩነቱ ከመጠን በላይ ሲለጠጥ፣ እንኳንስ ጥቅሟን ማስከበር ቀርቶ ህልውናዋም በጣም ያጠራጥራል፡፡ ለአገራቸው ባላቸው ከፍተኛ ፍቅር ምክንያት ጥቅሟን ለማስከበር ሌት ተቀን የሚለፉ እንዳሉ ሁሉ፣ የባዕዳን ተላላኪ ሆነው ሕዝቡን በተገኘው አጋጣሚ የሚያጋጩና ጠላትነትን የሚያበራክቱም አሉ፡፡ አንገቷን አሸዋ ውስጥ እንደምትቀብር ሰጎን በደንታ ቢስነት ራሳቸውን የሚሰውሩም እንዲሁ፡፡ አሁን የሚያዋጣው ግን ልዩነትን ወደ ጎን በማድረግ ለኢትዮጵያ ጥቅም አብሮ መሥራት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከድህነት ውስጥ ለማውጣት ልጆቿ ጠንካራ ሠራተኞች መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ጥንካሬ ሊኖር የሚችለው ግን ከግላዊና ከቡድናዊ ፍላጎቶች በመላቀቅ፣ ለኢትዮጵያ በአንድነት መቆም ሲቻል ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና በወታደራዊ መስኮች የተጠናከረች አገር መሆን አለባት፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የበቁ ኢትዮጵያዊያን ያስፈልጓታል፡፡ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በፍትሐዊ መንገድ ለመጠቀም፣ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶቿን ለማልማት፣ የከበሩ ማዕድናቷን ለማውጣት፣ ወዘተ ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ ይህ ሰላም ግን ዕውን የሚሆነው ኢትዮጵያውያን በተባበረ ድምፅ በአንድነት መቆማቸውን ሲያረጋግጡ ነው፡፡ በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ምክንያት የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች እንደ እሳት የሚለመጥጥ ኃላፊነት ወስደው እየተፈተኑ ባሉበት በዚህ ጊዜ፣ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸው ጠቃሚ ምክረ ሐሳቦችን በማቅረብ ከፍተኛ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል፡፡ እነዚህ ወገኖች በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆነው እየተደራደሩ ያሉት የአገር ጥቅም ያስከብራሉ ተብሎ ስለሆነ፣ በተቻለ መጠን ከነቀፌታና ከአጉል ትችት በመታቀብ ኃላፊነትን መወጣት የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ መሆን አለበት፡፡ በሌላ በኩል በባዕዳን መደለያ የአገር ጥቅምን አሳልፈው የሚሰጡትን በተጨባጭ መረጃ በማጋለጥ፣ የዜግነት ግዴታን መወጣት የግድ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ልጆቿ እየተከፋፈሉ በረባ ባልረባው እርስ በርስ ሲላተሙ፣ የሚጠቀመው ማን እንደሆነ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ይህ ወቅት እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ትዕግሥት፣ ብልኃትና አስተዋይነት ይፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ጥቅም የሚከበረውም በዚህ መንገድ ነው፡፡

መንግሥት የኢትዮጵያን ጥቅም የማስከበር ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከኃላፊነቶቹ መካከል አንደኛው የአገሪቱን ሉዓላዊነት በማስከበር ጥቅሟንና ደኅንነቷን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህንን ተልዕኮ ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ መዋቅሮቹን ከላይ እስከ ታች ማጥራት አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ የሚያሴሩ ካሉም ተገቢውን ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ በህዳሴ ግድቡ ድርድርም ሆነ በሌሎች ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶችን ማስወገድ ግዴታው ነው፡፡ የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ሰላምና አንድነት የሚያቃውሱ ኃይሎችንም በሕግ ልክ ማስገባት አለበት፡፡ የአገሪቱን የአየርና የየብስ መግቢያና መውጫዎች በመቆጣጠር፣ ሉዓላዊነቷን የሚጋፉ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ አስቀድሞ ማምከን ይኖርበታል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም አሥጊ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖች በመለየት፣ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት መቼም ቢሆን የማይዘነጋ ተግባሩ ነው፡፡ በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚደረገው ድርድር ለሕዝብ ግልጽ እንዲሆን፣ ማብራሪያ የሚፈልጉ ጥያቄዎች ሲነሱ መልስ እንዲያገኙ፣ ጠቃሚ የሆኑ የባለሙያዎች ድምፆችና ምክረ ሐሳቦች እንዲሰሙ፣ ለሕዝብ መድረስ ያለባቸው መረጃዎች በተገቢው ፍጥነት እንዲለቀቁና ሙሉ ግንዛቤ እንዲፈጠር መትጋት የመንግሥት ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ የመንግሥት አቋምም በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ዓላማ ዙሪያ ማሰባሰብ ይቻላል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የሙያና የጥቅም ማኅበራት፣ ቤተ እምነቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አደረጃጀቶች ከምንም ነገር በፊት የአገርን ጥቅም የሚያስቀድም ተግባር ላይ ማተኮር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕዝቡን በብሔር፣ በሃይማኖትና በመሳሰሉት የሚከፋፍሉ ኃይሎች እየተበራከቱ የአገርን ህልውና እየተፈታተኑ ስለሆነ፣ ከላይ የተገለጹት አካላት በሙሉ በዚህ ወሳኝ ወቅት መተባበር አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከፊቷ በርካታ ችግሮች ተደቅነው ሰላሟ እየታወከ መዝናናት አይቻልም፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ የውጭ ኃይሎች ጫና አድማሱን እያሰፋ ሲመጣ፣ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በኅብረት ከመቆም ውጪ አማራጭ የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያን የመስዋዕት ጠቦት በማድረግ ጥቅማቸውን ለማስከበር ከሚፈልጉ ኃይሎች ጋር በተፋጠጠችበት በዚህ ወሳኝ ጊዜ፣ ኢትዮጵያዊያን ፋይዳ ቢስ የሆኑ ልዩነቶች ላይ ከተጠመዱ ጠባሳው ለልጅ ልጆች ይተላለፋል፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዘመናት የመከኑ መልካም አጋጣሚዎች ቁጭት ፈጥረው፣ በዚህ ዘመን እርማት ተደርጎባቸው አንድ ላይ መቆም ካልተቻለ የመጪውን ጊዜ ፈተና መቋቋም አይቻልም፡፡ በስህተት መንገድ ላይ ደጋግሞ መመላለስ ያተረፈው ቢኖር ጥላቻ፣ ቂም በቀልና እርስ በርስ መጠፋፋት ነው፡፡ ኢትዮጵያም ለዘመናት ድህነት ውስጥ ተዘፍዝፋ የኋላቀርነትና የተመፅዋችነት ምሳሌ የሆነችው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የሚያዋጣው በአንድነት ፀንቶ መከበር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ውርደቱ ይቀጥላል፡፡

የያዝነው ዓመት ምርጫ ይካሄድበታል ተብሎ ቀጠሮ ተይዟል፡፡ ምርጫ እንኳንስ ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ ሰላም በሰፈነበትም ሒደቱ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለአገር እናስባለን የሚሉ ወገኖች ኢትዮጵያ ከእነ ግብፅ ጋር የጀመረችውን ድርድር በውጤታማነት አጠናቅቃ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሚጥለውን ምርጫ በሰላማዊ፣ በፍትሐዊና ሁሉንም በሚያግባባ መንገድ እንድታከናውን ይተባበሩ፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር የሚኖረው ምርጫው ሒደቱ የሰመረ ሲሆንና ሁሉም ወገኖች ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ብቻ ነው፡፡ ከሒደቱ ማማር በፊት ውጤት ላይ እየተተኮረ ሴራ መጎንጎን ከተጀመረ ታጥቦ ጭቃ መሆን ይከተላል፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን ያሟላ ምርጫ እንድታካሂድ ከተፈለገ፣ ለልዩነቶች ዕውቅና በመሰጣጠት በእኩልነት ለመፎካከር የሚያስችል የፖለቲካ ምኅዳር በጋራ ማዘጋጀት የግድ ይሆናል፡፡ እልህ፣ ግትርነት፣ ሕገወጥነትና ጉልበተኝነት ከዴሞክራሲ ጋር ፀብ እንጂ ዝምድና የላቸውም፡፡ ተፎካካሪዎች በሕዝብ ድምፅ ለመዳኘት የፖለቲካ የጨዋታ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት የቤት ሥራቸውን ጨርሰው ብቻ ነው መገኘት ያለባቸው፡፡ በሴራና በመሰሪነት የሚገኘው አምባገነንነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ አምባገነንነት ሰልችቶታል፡፡ ኢትዮጵያም ድህነት ውስጥ የተዘፈቀችው የአምባገነንነት መጫወቻ ስለሆነች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በስሙ የሚነግዱና የሚቆምሩ አይፈልግም፡፡ ይህ ለአገሩ ከፍተኛ ክብርና ፍቅር ያለው ሕዝብ ጥቅሟ ተከብሮ እንዲያልፍላት ይፈልጋል፡፡ መፍትሔው የኢትዮጵያ ጥቅም እንዲከበር በአንድነት መቆም ብቻ ነው፡፡ ልዩነትን ይዞ ለኢትዮጵያ ጥቅም አንድ ላይ መቆም ይቻላል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...

ምርጫ ቦርድ ፓርላማው ያፀደቀለትን 304 ሚሊዮን ብር አለማግኘቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኔ 2016 ዓ.ም. በአራት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰብዓዊ ቀውስና በውድመት የታጀቡ ግጭቶች በአስቸኳይ ይቁሙ!

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው የሁለት ዓመቱ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተጀመረው...

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...