የሜቴክ የተከማቹ ዕዳዎችን መንግሥት እንዲሰርዝ ተጠይቋል
በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ባለመቻሉና ከዚሁ ጋር በተገናኘ የአገር ሀብት እንዲባክን አድርጓል ተብሎ የሚወቀሰው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ ‹‹ኢንተግሬትድ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን›› በሚል ስያሜ በድጋሚ ሊቋቋም ነው።
ሜቴክን በድጋሚ ለማቋቋም የተረቀቀው ማቋቋሚያ ደንብ፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ሪፖርተር ከታማኝ ምንጮች ያገኘው መረጃ ያመለክታል። ሜቴክ ‹‹ኢንተግሬትድ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን›› በሚል ስያሜ በድጋሚ እንደሚቋቋም፣ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 25/1984 መሠረት እንደሚተዳደርም ረቂቅ ደንቡ ይገልጻል።
ሜቴክ ኢንተግሬትድ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን በሚል መጠሪያ በድጋሚ ከተቋቋመ በኋላ፣ እንዲያሳካቸው የሚፈለጉ ዓላማዎችንም ረቂቅ ደንቡ ይዘረዝራል። ከተዘረዘሩት ዓላማዎች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ለማፋጠን፣ እንዲሁም የዕውቀትና የፋይናንስ እጥረትን ለመፍታት በሚያስችለው መንገድ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በአጋርነት መሥራት አንዱ ሲሆን፣ ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉትን ጨምሮ በማንኛውም ቴክኖሎጂ ላይ መመራመር፣ ማልማትና ወደ ፋብሪካ ውጤትነት መቀየር ሌላው የኮርፖሬሽኑ ዓላማ እንደሚሆን ተመልክቷል።
ኮርፖሬሽኑ የሚቋቋምበት ተጨማሪ ዓላማ፣ ‹‹በአገር ውስጥም ሆነ አገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ በሚፈጥር መንገድ በውጭ አገር ፋብሪካ የማቋቋምና የማስፋፋት፣ የማምረቻ ፕላንት መገንባት፣ መፈተሽና ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ›› እንደሆነ የረቂቅ ደንቡ ድንጋጌ ያመለክታል።
የማምረቻ ማሽኖችን፣ የካፒታል ዕቃዎችንና የፍጆታ ዕቃዎችን፣ መለዋወጫዎችን ማምረት፣ ምርትና አገልግሎትን የሚያሳልጡ ቴክኖሎጂዎችን ማምረትና መገጣጠም፣ እንዲሁም የሥራ አመራር ቦርዱን ይሁንታ ሲያገኝ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ገቢ ሊፈጥሩለት የሚችሉ ሌሎች ተዛማጅ ሥራዎችን ማከናወንም የኮርፖሬሽኑ ዓላማ ተብለው ከተጠቀሱት መካከል ናቸው።
በሜቴክ ሥር የነበሩት የጋፋት አርማመንት ኢንጂንሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የሆሚቾ አሙኒሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የደጀን አቪዬሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪና ፊዩልና ፕሮፔላንት ንዑስ ኢንዱስትሪዎች የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተብለው ከወር በፊት በፀደቀ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የተቋቋሙ በመሆናቸው፣ ሜቴክን በሚተካው አዲስ ኮርፖሬሽን ሥር አልተካተቱም።
በመሆኑም የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተብሎ በተቋቋመው ሥር ባሉ ኩባንያዎች ከታቀፉት ሠራተኞች ውጪ በሜቴክ ሥር ባሉ አምራች ኩባንያዎች ሥር ተቀጥረው በሥራ ላይ የሚገኙ ሠራተኞች፣ መሥፈርቱን አሟልተው ወደ ኢንተግሬትድ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን እንደሚዘዋወሩ ረቂቅ ደንቡ ይገልጻል።
ከሜቴክ ወጥተው በቅርቡ ወደ ተቋቋመው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተጠቃለሉትን ኩባንያዎችንና ኳሊቲ ማዕከልን ሳይጨምር፣ ሌሎቹ በሜቴክ ሥር የሚገኙ ተቋማትና ዝቋላ ስቲል ማምረቻ ፋብሪካ ጋር በተገናኘ ከዚህ ቀደም የነበሩ፣ አሁንም በሒደት ያሉ ውሎች፣ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች፣ ሥራዎች፣ ተሰብሳቢ ሒሳቦች፣ ተከፋይ ዕዳዎች፣ መዛግብት፣ ሰነዶችና ንብረቶች ወደ ኢንተግሬትድ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን የሚሸጋገሩ መሆኑንም ረቂቁ ያመለክታል። ሜቴክ ተግባርና ኃላፊነቱን ለማስፈጸም ከዚህ ቀደም ያወጣቸው መመርያዎች፣ ማኑዋሎች በሌሎች መመርያዎች ማኑዋሎች እስካልተሻሩ ድረስ ተፈጻሚነታቸው እንደሚቀጥልም ረቂቁ ይገልጻል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሥራ ላይ የሚገኘው ሜቴክ ከገባበት ቀውስ እንዲወጣና ወደ ተግባርና ኃላፊነቱ እንዲመለስ ለማድረግ ያሉበት ዕዳዎች እንዲሰረዙ፣ የባንክ ዕዳዎቹ የመክፈያ ጊዜ እንዲያራዘሙ ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
መረጃው እንደሚያመለክተው ሜቴክ በአጠቃላይ የ75 ቢሊዮን ብር ዕዳ ተሸክሟል። ይህንን ዕዳ አስመልክቶ ለመንግሥት ባቀረበው ጥያቄም ለገቢዎች ሚኒስቴር መክፈል የሚገባው 11 ቢሊዮን ብር ዕዳ እንዲሰረዝለት፣ በተመሳሳይም ለተለያዩ የክልልና የፌዴራል የመንግሥት አካላት መክፈል የሚገባው 24 ቢሊዮን ብር እንዲሰረዝለት ጥያቅ አቅርቧል።
ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መክፈል የሚጠበቅበት 13 ቢሊዮን ብር ዕዳ የመክፈያው ጊዜ በአሥር ዓመት እንዲራዘምለት፣ ቀሪው 27 ቢሊዮን ብር ዕዳ ደግሞ ወደ ካፒታል እንዲቀየርለት ዝርዝር ጥያቄ ማቅረቡን መረጃው ያመለክታል። ይህንን ጥያቄ ካቀረበ በርካታ ወራት ያለፉ ሲሆን፣ እስካሁን ግልጽ ምላሽ ከመንግሥት አልተሰጠውም።
ኮርፖሬሽኑ በ2011 ዓ.ም. ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ውስጥ ገብቶ እንደነበረ፣ ነገር ግን መንግሥት ልዩ ክትትል በማድረጉና ጠንካራ የቦርድ አመራሮችን መድቦ ተቋሙን ለመታደግ በመንቀሳቀሱ፣ ዘንድሮ ከኪሳራ ለመውጣት መቻሉን ሪፖርተር ያገኘው የሰነድ መረጃ ይገልጻል።
በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥም 114 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን የሚያመለክተው መረጃው፣ ‹‹የኮርፖሬሽኑ አመራር ግፊት ፈጥሮ በሥራ ተወዳደሪነትና ትርፋማነት ግቡን ሊያሳካ እንደሚችል አመላካች ነው፤›› ሲል አፈጻጸሙን አወድሶታል።
ይህንን ውጤት ያስመዘገበውም ያልተሰበሰቡ የቆዩ ሀብቶችን በማሰባሰብ 1.87 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ በመቻሉ፣ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ወይም የማያገለግሉ ሀብቶችን በመሸጥ ከሰበሰበው 45 ሚሊዮን ብር፣ ከኪራይ አገልግሎት፣ እንዲሁም የ342 ሚሊዮን ብር ወጪ ቅነሳ በማድረጉ እንደሆነ መረጃው ያመለክታል።