Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹በዚች አገር ፍፁም ፀረ ዴሞክራሲ አፈና ነግሷል›› ሕወሓት

‹‹በዚች አገር ፍፁም ፀረ ዴሞክራሲ አፈና ነግሷል›› ሕወሓት

ቀን:

የትጥቅ ትግል የጀመረበትን የየካቲት 11 ቀን 45ኛ ዓመት በዓሉን ምክንያት በማድረግ ሰሞኑን መግለጫ ያወጣው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)፣ በዚች አገር ፍፁም ፀረ ዴሞክራሲ አፈና ነግሷል አለ፡፡ ‹‹ፖለቲካዊ ምኅዳሩ ጠቧል፡፡ የተለየ ሐሳብ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ጋዜጠኞች ይታሰራሉ፣ ይታፈናሉ፤›› ሲልም አስታውቋል።

የተገነቡ ተቋማትን በማፍረስ፣ አገሪቱን ወደኋላ የመመለስ ጥፋቶችና ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ፣ የአገሪቱ መድኅን የሆነው ሕገ መንግሥት ተጥሶ፣ የሕግ የበላይነት ተረግጦ፣ ኅብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ በጠራራ ፀሐይ እየተሸረሸረ፣ ተጠብቆ የነበረው ሰላም ደፍርሶ፣ የሕዝቡ አንድነት ተበትኖ፣ ልማት ተኮላሽቶ፣ የአገሪቱ ክብርና ሉዓላዊነት በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ተደፍሮ አገሪቱ የትንንሽና የትልልቅ የውጭ ኃይሎች መፈንጫ ሆናለች በማለት ሕወሓት በመግለጫው አመልክቷል።

‹‹በዚህ ምክንያት የዚህች አገር ህልውና ከማንኛውም ጊዜ በከፋ ደረጃ አደጋ ላይ ወድቆ ይገኛል። በዚህ ሳቢያ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን ሲያጡ፣ አስከፊ ቅራኔና መፈናቀል ሲደርስ፣ የአገር ዘብ ሆነው ዕድሜ ልካቸውን የታገሉ ጄኔራሎች ሲቀጠፋ፣ ዩኒቨርሲቲዎች ከጥናትና ምርምር ማዕድ ወጥተው ወደ ሁከትና ግርግር ሲገቡ፣ ተማሪዎች ሕይወታቸውን ሲያጡና በወጡበት ሲታገቱ ማየት ዕለታዊ ተግባር ሆኗል፤›› በማለት አክሏል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ከዚህም አልፎ በሕጋዊ መንገድ ሥልጣን ይዞ በዚች አገር ሁለገብ ዕድገት፣ ሰላምና የሕግ የበላይነትን አረጋግጦ ይመራ የነበረው ኢሕአዴግ በፍፁም ፀረ ዴሞክራሲ፣ በሕገወጥ አካሄድና በእህት ድርጅቶች ክህደት እንዲፈርስ ተደርጓል፡፡ አዲስ ብልፅግና የተባለ ድርጅትም ተመሥርቷል። ኢሕአዴግ በምርጫ ተወዳድሮ የያዘውን ሥልጣን ጊዜው ደርሶ ለሕዝብ ሳያስረክብ በመጥለፍ በፌዴራልና በአዲስ አበባ አስተዳደር ሕወሓት ከኃላፊነት እንዲነሳ እየተደረገ ነው፤›› ሲል ሕወሓት በመግለጫው አትቷል።

አንፀባራቂ ድሎችን እያስመዘገበ የመጣው የልማታዊ ዴሞክራሲ መስመር ባለፉት ሦስት አራት ዓመታት በኢሕአዴግ ውስጥ ባጋጠመ የጥገኛ መበስበስ አደጋ በአገሪቱ ሰፍኖ የነበረው ሰላም ደፍርሶ፣ ተጀምሮ የነበረው ልማት ተስተጓጉሎ፣ የዴሞክራሲ ጥያቄ አደጋ ላይ ወድቆ ይገኛል በማለት ሕወሓት ገልጿል።

ሕወሓት ያጋጠመውን የመበስበስ አደጋ በፅናት በመታገል ዳግም ታድሶ ሥርዓቱን ለማዳን ከባድ ጥረት ቢያደርግም እንኳ፣ የኢሕአዴግ አባል የነበሩ እህት ድርጅቶች ራሳቸውን ሳያጠሩና ሳያድሱ በመቅረታቸው በኢሕአዴግ ውስጥ የተደረገው የአመራር ሽግሽግ በጥገኛው ኃይል የበላይነት ሊጠቃለል ችሏል ብሏል።

‹‹በጥገኛ መንገድ የመጣው የኢሕአዴግ አመራር የልማታዊ ዴሞክራሲ መስመርን በመተው ጠቅልሎ ወደ ጥገኛ መበስበስና ፍፁም ግለሰባዊ አምባገነናዊነት መንገድ በመግባት፣ በጥልቅ ተሃድሷችን ወቅትመደገም የለባቸውምብለን ያወገዝናቸውን ጉድለቶች አሁን በከፋ ደረጃ በመፈጸም ላይ ይገኛል፤›› ያለው ሕወሓት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዚች አገር ከባድ ጥፋቶችና ቀውሶች ተፈጥረው ዛሬ አገሪቱ ወደ ጥፋትና መበታተን መንገድ በማምራት ላይ ትገኛለች ሲል በመግለጫው አመልክቷል።

‹‹በዚህች አገር የተፈጠረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ፈታኝ ቢሆንም እንኳ ድርጅታችን ሕወሓት ገና በጠዋቱ ያነገበውን ሕዝባዊ ዓላማ ታጥቆ አሁንም በብርታት፣ በፅናትና በብስለት በመመከት ላይ ይገኛል። ከትምክህትና ከአድኃሪያን ኃይሎች ጋር ፊት ለፊት ገጥሞ በአጠቃላይ በአገሪቱ የሕግ የበላይነትና ሥርዓት እንዲከበር፣ በተለይ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ህልውናና ደኅንነት በየትኛውም ቦታና ጊዜ እንዲከበር ዛሬም እንደ ወትሮው በፅናት በመታገል ላይ ይገኛል። ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ እንዳይፈርስ፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ በዜጎች በተለይም በሕዝባችን ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ የሚያደርጉትን ያለሰለሰ ትግል ለማደናቀፍ፣ ከዚህም ከዚያ የተሰባሰቡ የትምክህት ኃይሎች ግንባር ፈጥረው ዘምተዋል።

የትግራይን ሕዝብና መሪ ድርጅቱን ሕወሓት አንገት ለማስደፋትና ለማንበርከክ ያላቸውን ኃይል ሁሉ አሟጠው እየተረባረቡ ይገኛሉ። ተሸናፊ የትምክህት ኃይሎች ያገኟትን ዕድል ተጠቀመው የትግራይን ሕዝብ ዳግም ለመጨፍለቅ ቀን ከሌት የተደራጀና የተቀናጀ ጥቃት እየፈጸሙ ይገኛሉ፤›› ሲልም አስታውቋል።

ይሁን እንጂ ያለው ሕወሓት፣ ‹‹ምኞታችንና ፍላጎታችን ብትር በነቀነቀ ላይ ብትር መነቅነቅ አይደለም። ዓላማችን ለረጅም ጊዜ በድህነት፣ በድንቁርናና በጦርነት የተጠቃውን ሕዝባችንን በልማት መካስ ነው። የትግራይ ሕዝብ ህልውናና ደኅንነት የሚከበረውም በልማት መስክ በምናስመዘግባቸው ሁለገብ ድሎች፣ በመልካም አስተዳደር መስክ በምናረጋግጠው እመርታ፣ በክልላችን በምናረጋግጠው ዋስትና ያለው ሰላምና ፀጥታ ነው። አጀንዳችን ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና በሁሉም ሕዝቦች እኩልነት ላይ የተመሠረተ፣ ለሁሉም ሕዝቦች እኩል ዕድል የሚሰጥ ሕገ መንግሥታዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት እንዳይፈርስ መታገል ነው፤›› ብሏል።

ስለሆነም የትግራይን ሕዝብና መሪ ድርጅቱ ሕወሓትን ከዚህ መሠረታዊ አጀንዳው አውጥቶ በውጥረት ውስጥ በማስገባት አንገቱን እንዲደፋና እንዲንበረከክ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ከንቱ ድካም መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ያለው ሕወሓት፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ እንኳንና ዛሬ ቀድሞም ቢሆን በጭፍጨፋና በረሃብ አልተንበረከከም። ከወጣንበት ከፍታ እየጨመርን እንሄዳለን እንጂ በፍፁም አንወርድም፡፡ ፍትሐዊ ትግል እስካካሄድን ድረስም ድላችን አያጠራጥርም፤›› ሲል አስታውቋል።

ለትግራይ ሕዝብ፣ ለሕወሓት አባላት፣ ለትግራይ ሴቶች፣ ለትግራይ ወጣቶች፣ በውጭ አገር ለሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች፣ ለክልሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራት፣ ለሕገ መንግሥታዊና ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊስት ኃይሎች፣ ለአገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ እንዲሁም ለኤርትራ ሕዝብ ጥሪ በማቅረብ ረጅሙን መግለጫ ቋጭቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...