በያሲን ባህሩ
ሰሞኑን ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የትጥቅ ትግል የጀመረበትና ድርጅቱን በይፋ የመሠረተበትን 45ኛ ዓመት እያከበረ ይገኛል። ድርጅቱ ደጋፊዎቹንና አባላቱን አነቃንቆ በዓሉን ሲያከብር ከቀደሙት ዓመታት በተለየ ሁኔታ ከአገሪቱ ማዕከል ተገፍቶ፣ በተፈጠረበት ክልል ላይ ብቻ ተወስኖ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የልዩ ኃይል ማበራከት በሁሉም ዋና ዋና ክልሎች ተጠናክሮ የሚታይ ቢሆንም፣ ሕወሓት ግን በሠራዊቱ ድምቀትና ለየት ባለ መንገድ በቡድን የመሣሪያ ትርዒት በማሳየት አድምቆት ይስተዋላል፡፡
በመሠረቱ ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ ለ17 ዓመታት ያካሄዱት መራራ የትጥቅ ትግል፣ እንዲሁም የከፈሉት ከባድ መስዋዕትነት በአገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት ለመመሥረት ግንባር ቀደም ሚናውን አበርክቷል። የክልሉ ሕዝብና ሌሎች ሕዝቦች ቀደም ሲሉ በነበሩ የፊውዳልና የደርግ ሥርዓቶች ሲደርስባቸው የቆየውን ብሔራዊ ጭቆና ለማስወገድ የትጥቅ ትግሉ ፈር ቀዳጅ በመሆን፣ ከክልሉ አብራክ በወጡ የቁርጥ ቀን ልጆች ላይ ተመሥርቶ ታግሎ አታግሏል፡፡ ምንም ያህል የመጨረሻው ፍፃሜ ውጤቱ ሌላ ቢሆንም ይኼን ውለታ መካድ አይቻልም፡፡
በረጅም የታሪክ ዘመን ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶችን ያለፈ፣ ከትጥቅ ትግል እስከ መንግሥታዊ አስተዳደር በኢትዮጵያ ፖለቲካ አየር ውስጥ ትልቅ ሚና የተጫወተም ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ኃይል በታሪኩ የሚመሠገንበት እውነት በአገሪቱ ንፁኃንን የፈጀና የእርስ በርስ ጦርነት መንስዔ የነበረ ወታደራዊ የጭቆና ቀንበር የሰባበረ፣ ከዚያም አልፎ በተለይም የብሔር ብሔረሰቦችን መብትና ታሪክ ታሳቢ ያደረገ ፌዴራላዊና ሕገ መንግሥታዊ አስተዳደር ለመመሥረት ታግሎ ያታገለ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከአጋሮቹና ከሕዝቡ ጋር በመሰናሰል የልማት ብርሃን ለመፈንጠቅም ያስቻለ ነው፡፡
በእዚያው ልክ ሕወሓት የሚወቀስባቸው በርካታ የፖለቲካ ነቁጦች ዛሬም ድረስ ለአገሪቱ መመሰቃቀል በር ከፍተዋል፡፡ በቀዳሚነት ለዘመናት የዘለቀውን የሕዝቦች አብሮነትና አንድነት በመሸርሸር፣ የአገዛዞችና የሕዝቦች በደል አደበላልቆ በተዛባ ትርክት ሕዝቦችን በማፋጠጥ፣ ለጠባብ የፖለቲካ ፍላጎቱ የሚያመች ሥርዓት መቀየዱ የሚያስወቅሰው ክስተት ነው፡፡
በዴሞክራሲ ግንባታ ረገድም አብዮታዊነት የተጠናወተውና በገደብ ላይ የተመሠረተ ስትራቴጂ ተከትሎ፣ ልዩነትን ለማስተናገድ የተቸገረና ባለ መንታ መንገድ ሥርዓት ለማንበር ሞክሯል፡፡ ከላይ ሲያዩት ዴሞክራሲያዊ ቢመስልም፣ አፋኝና የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የገደበ አካሄዱን ማስታወስ ይቻላል፡፡ የጠላትና የወዳጅ ፍረጃና የመካረር አዙሪትን ለመበጠስ መቸገሩም የሚመነጨው ከዚሁ እውነታ ነው፡፡
ከዚህ ባልተናነሰ በአገሪቱ ማኅበረ ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ገዥው ፓርቲ በሆነው ኢሕአዴግ መሪነት ቀላል ግምት የማይሰጠው ለውጥ ቢያመጣም በሙስና፣ በኢፍትሐዊነትና ሀብት በማሸሽ የታሪክ ክስረት ውስጥ በቅድሚያ የሚታማ ድርጅት ነው፡፡ ኢሕአዴግ እንደ ግንባር ወደ ገዥ ፓርቲነት በመለወጥ ላይ የነበረ ብልሹ መዋቅር ቢሆንም፣ ሕወሓት እንደ ፓርቲ አባላቱንና ደጋፊዎቹን ብቻ ሳይሆን የትግራይ ሕዝብን እንደ ሕዝብ ሊያስጠላ የሚችል ጭፍን ዘረፋና የኔትወርክ ንጥቂያ ውስጥ የተዘፈቀ ነበር፡፡ ሌላው ሁሉ ቢቀር ሜቴክ በተባለው መንግሥታዊ ኮርፖሬሽንና ኤፈርት በተሰኘው ኢንዶውመንት የተሠራውን ወደ አንድ ወገን ያጋደለ ንጥቂያ መጥቀስ ይቻላል፡፡
ለዚህ ደግሞ ብሔርን አልፋና ኦሜጋ ያደረገ አካሄዱ አመቺ መደላድል የሆነው ሲሆን፣ የእሱኑ መንገድ የሚከተሉ የፖለቲካ ኃይሎችም ተቀፍቅፈዋል፡፡ ዛሬ ባለችው ኢትዮጵያ በሕጋዊነት ከተመዘገቡት ከ100 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች 75 በመቶው የሚሆኑት የብሔር ፓርቲዎች መሆናቸው የአባባሉ ማሳያ ነው፡፡ ብሔር ተኮሮቹ ክልሎች በመካለላቸው ሚዲያ፣ ፖሊስና ልዩ ኃይል የመሳሰሉትን በአቅማቸው ልክ ብቻ ሳይሆን፣ እንዳሻቸው በመፍጠራቸውና በማዘዛቸው አጉል ፉክክር መጀምሩም ይታያል፡፡ በዚህ ላይ የፌዴራሉ መንግሥት ደከም ያለ ሲመስል መፋጠጥ ላለመምጣቱ ዋስትና የሚሰጥ አልተገኘም፡፡ የእነዚህ ነባራዊ ሀቆች የነፍስ አባታቸው ደግሞ ሕወሓት ነው ማለት ስህተት አይደለም፡፡
ቀደም ባለው ታሪካችን ምንም እንኳን በአገሪቱ የብሔር ጭቆና አልነበረም ባይባልም ሕዝቦቻችን ታሪክ፣ እምነት፣ ባህልና ቋንቋቸውን ከማስፋፋትና ከማጠናከር ባለፈ በማንነት ላይ የተመሠረተ ዕድር፣ ማኅበር፣ የንግድ አክሲዮን፣ የመኖሪያ ሠፈር፣ ወዘተ. እንዲያቆጠቁጥ እስከ ማድረግ ያበረታታው የሕወሓት አክራሪ ብሔርተኛ መንገድ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ በአንድ አገር የፀኑ የመኖሪያ ክልሎችን በብሔር ላይ መሥርቶ እንደሚያመቸው በመቀየድ፣ ለዘመናት ተሳስሮና ተዋልዶ የኖረን ሕዝብ ማንነትን በወሰንና፣ በመንደር ሀብት በማፋጠጥ አንድነትንና ኅብረ ብሔራዊነትን የሸረሸረውም የዚሁ ኃይል ፍልስፍና መሆኑን ዛሬ በግልጽ መናገር ይቻላል፡፡
እውነት ለመናገር ‹‹የአገራችን ሕዝቦች ጨዋ፣ አንድነትና መከባበርን የሚያውቁ፣ ለዘመናት በመቻቻልና በመደማመጥ የዘለቁ፣ አንዳንዱ ሕዝብም በባህላዊ ትውፊቶቹ ዴሞክራሲያዊነትንና ዕርቅን የተለማመደ፣ ወዘተ.›› እያልን ምንም ያህል ብንዘምር፣ ከአክራሪ ብሔርተኛ ፖለቲካ ካልተወጣ ሁሉም ወደ ራሱ መሰባሰቡ ብቻ ሳይሆን መገፋፋቱም አይቀሬ የሆነው ዕሳቤው ሥር በመስደዱ ነው፡፡ ይህም ኅብረ ብሔራዊ ሆነውን ሕዝብ እየገፋ፣ ያለ ጥርጥር ጠባብነትና ዘረኝነትን እያፋፋ መሄዱ የማይቀር ነው፡፡ ሁሉ ነገር ‹‹የእኔ ነው. . . የእኔ ነው. . .›› የማለቱ በስግብግብነትም ይብስ እንደሆን እንጂ ሊቀንስ የሚችል አይደለም፡፡ ስለዚህ አገር እንደሚወድ ዜጋ ሁላችንም ለአገር አንድነት ዘብ ልንቆምና አገሪቱን ከዘር ፖለቲካና የጎሳ ፌዴራሊዝም ለማውጣት ሕዝብን ያሳተፈ መፍትሔ መፈለግ ግድ የሚል ሆኗል፡፡
ይህ ማለት ግን በሕወሓት መሪነት ለ45 ዓመታት የኖረ አስተሳሰብ ከሌላውም ወገን የሚከተለው ደጋፊ አላፈራም ማለት እንዳልሆነ ጠቅሻለሁ፡፡ እንዲያውም አሁን ባለው ትውልድ ውስጥ አብዛኛው ትኩስ ኃይል ከአገራዊ አንድነት ይልቅ፣ ብሔርተኝነትን አለፍ ሲልም ጠርዘኛ ብሔርተኝነት (ጠባብነትን) እያቀነቀነ ይገኛል፡፡ በፖለቲካ ኃይል ደረጃም አገርን በአብሮነት ከመምራት ይልቅ፣ በብሔር ባርኔጣ ውስጥ ተደፍቀው ብሶት በመቆስቆስ ላይ የሚገኙ ድርጅቶች እንዳሉ ናቸው፡፡ ይህን እውነት ሁላችንም የምናውቀው ቢሆንም፣ በርካቶች በተባ ብዕር የሚተቹትና የሚያወግዙት ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ላለው ፖለቲካዊ ምስቅልቅልም መንደርደሪያው እሱ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ሒስ ከሚያቀርቡበት መካከል አንዱን ስጠቅስ አቶ ያሬድ ጥበቡ (ጀቤሳ) የተባሉ የቀድሞው ኢሕዴን (ብአዴን) ነባር ፖለቲከኛን እናገኛለን፡፡ የአዲስ አበባ ተወላጁ እኝህ ፖለቲከኛ የሚያስብላቸው እውነት ከ1960ዎቹ አንስቶ እስካሁን አክራሪ የብሔር ፖለቲካን በመቃወም፣ በፍትሕና በዴሞክራሲ ላይ የተመሠረተች የጋራ አገር እንድትኖር የሚታገሉ በመሆናቸው ነው፡፡ ‹‹የአራዳ ልጅ ብሔር የለውም›› እስከ ማለት ማንነታቸውን ለታሪካዊት ኢትዮጵያ የሰጡ መሆናቸውም የሚታወቅ ነው፡፡
እኝህ የፖለቲካ ልሂቅ ‹‹ወጥቼ አልወጣሁም›› (2010 ዓ.ም.) በሚል ርዕስ ለዓመታት በጋዜጣና በልዩ ልዩ ድረ ገጾች የተሟገቱባቸውን ጽሑፎች ሰብስበው አሳትመዋል፡፡ ካነሷቸው አንዳንድ ጠቃሚ ነጥቦች መካከል ያለፈውን ለመውቀስ ብቻ ሳይሆን፣ ለአሁኑ የለውጥ ኃይልም ሆነ ለመጭው ዘመን መሪዎችና ፖለቲከኞች ይረዳል ብዬ የማምነውንና ከዚህ ጽሑፍ ርዕሰ ጉዳይ ጋር የሚገናኘውን ጭብጥ አነሳለሁ፡፡
‹‹. . . በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቀደም ሲል ብሔርተኛ ንቅናቄዎች የነበሩት በትግራይ፣ በአፋር፣ በኦጋዴን፣ በጋራ ሙለታ፣ በሲዳሞና በቄለም ነበር፡፡ ግን የአፋሩ የዓሊ ሜራህ ንቅናቄ ዕትብቱን ከኢትዮጵያ የበጠሰ አልነበረም፡፡ ኡጉጉመ ይባል የነበረው ድርጅት ደግሞ የደርጉን ‹‹ሪጅናል ኦቶኖሚ›› ተቀብሎ ከወያኔ ጋር ስንት ፍልሚያዎችን አካሂዷል፡፡ ኦጋዴን ውስጥ የነበረው የምዕራብ ሶማሌ ነፃ አውጪ ግንባርም ከዚያድ በባሬ ጦር ጋር በደባልነት ተመትቶ ሞቃዲሾ ከገባ ዓመታት አስቆጥሮ ነበር፡፡ ባሌ የነበረው ሶማሌ አቦና የሲዳማው የወልደ ማርያም ዱባለ ንቅናቄም ተሰደው ሶማሊያ ገብተው ነበር፡፡ ጋራ ሙለታ በሼክ ጃራ የሚመራ በመቶ የሚቆጠር ደካማ ሠራዊት የነበረው ሲሆን፣ የቄለሙ የኦነግ ጦርም ከሱዳን ጠረፍ ብዙም ደፍሮ ያልገባ በቁጥሩም ደካማ ነበር፡፡
እንግዲህ ብቸኛው ድርጅትና ጠንካራ ሠራዊትም የነበረው የትግራይ ወያኔ (ሕወሓት) ነበር፡፡ እሱም በኢትዮጵያ የአልባኒያ ኮሙዩኒዚምን አነግሣለሁ የሚል ህልም ያቃዥው ስለነበር፣ በጠባብ ብሔርተኝነት ዝንባሌው ላይ ግለ ሂስ ቢጤም ሞካክሮ ነበር፡፡ . . .ኋላ ከተነሱት የኦሮሞ፣ የሲዳማ፣ የባሌ ብሔርተኞች ይልቅም የካቲት ላይ የተነሱት የተማሪው ንቅናቄ ጀግኖች የአባቶቻቸውንና የመሳፍንቱን መሬት በመንጠቅ ቆመው ያለ ርህራሔ ሲያከፋፍሉ ገባሩ ስላየ፣ እስከ ዛሬም ለተለሰነው አንድነት ዋልታ ሆኖ ቆሟል እላለሁ፡፡ ለብሔርተኛ ንቅናቄዎችም መልፈስፈስና መነጠል ዋናውን በትር አሳርፏል፡፡›› (ገጽ 130)
በእውነት አሁንም ድረስ አክራሪ ብሔርተኝነት ሰንቀው የተነሱና ‹‹አንቀጽ 39 ወይም ሞት›› የሚሉ ኃይሎች ከእነዚህ ንቅናቄዎች ጀርባ ያሉ ወገኖች ናቸው፡፡ ባለፉት 28 ዓመታት ‹‹ከእኛ ይልቅ ብሔርተኞች በሥርዓቱ ተጠቅመዋል ወይም አልተበደሉም፤›› ያሉ ዜጎች (አብን፣ ሲአን፣ ወብን፣ ሌሎችን መሥርተው) አዲስ አክራሪ ብሔርተኝነትን እንዲቀሰቅሱ የሕወሓት የማያወላዳ የጠባብ ብሔርተኝነት መንገድና በኢሕአዴግ ውስጥም ለ27 ዓመታት የተከተለው የብሔር ፌዴራሊዝም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
በመሠረቱ ቀኝ ዘመም አክራሪ የብሔር ፖለቲካ በእኛ ብቻ ሳይሆን በየትኛው ዓለም ያለና የሚኖር አስተሳሰብ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን በመሰሉ ኅብረ ብሔራዊነት በተላበሱና የተሰናሰለ ማንነት ባላቸው አገሮች ላይ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እያመዘነ ይገኛል፡፡ በእርግጥም ዛሬ የኖረ የጥላቻ መንገድና ከራር ብሔርተኝነት የወለደው የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት መፈናቀልም ይባል፣ ‹‹የእኔ. . . የእኔ. . .›› ባይነት እንዲበዛ አድርጓል፡፡ ከላይ የተነሳሱ እውነታዎችን ቸል ብሎ ይህን አካሄድ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ አለመታገል ታዲያ እንዴት ይቻላል!!
ከምስቅልቅሉ ለመውጣትና የመሀል ቤትን ለማንበር የፈለጉ የለውጥ ኃይሎችን ዛሬ አላላውስ ያለው ይህ አስተሳሰብ፣ ሕወሓት እስከ መቃብር ድረስ የያዘው መሆኑ በተለያዩ መንገዶች ተረጋግጧል፡፡ አንደኛው ለዓመታት የኢሕአዴግ ውህደትን ሲያቀነቅን ኖሮ ዛሬ ቀኑ ሲደርስ ሸርተት ማለቱ ነው፡፡ በሌላ በኩል የአስተሳሰቡ ተጋሪ የሆኑ ኃይሎችን እሱ የፌዴሬሽን ኃይሎች ቢልም፣ የኮንፌዴሬሽን አስተሳሰብ የያዙትን በማሰባሰብ የትግል ተጋሪ ለማድረግ እየሞከረ መሆኑ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተነጥሎ የማይታየው በተሃድሶ ውስጥ እንዳለፈ የገዥው ፓርቲ አካል የተጀመረውን ለውጥ እያገዙ ከውድቀት ለማዳን ከመጣር ይልቅ፣ በተቃራኒው ተሠልፎ በመፋለም ላይ በመሆኑ ነው፡፡
እንግዲህ የሕወሓት ግልጽ አሠላለፍና አቋም ይህ መሆኑ በገሀድ የሚታየው፣ አብሮነትንና በአንድነት መኖርን የሚመርጡ ወገኖች ተሰባስበው መታገል ግድ የሚላቸው ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያዊያን አገር ከመበተንም ሆነ ነጣጥሎ ከመግዛት ለማውጣት በንቃትና በሰላማዊ መንገድ የሕወሓታዊያንን አስተሳሰብ መድፈቅና ተቀባይነት ማሳጣት ነው የሚኖርባቸው፡፡ ይህን የማድረግ ጉዳይ ደግሞ ብልፅግናን ወይም ኢዜማን የመሰሉትን የመምረጥ አጀንዳ ሳይሆን፣ አገርንና አብሮነትን ጠብቆ የመቆም ርብርብ ነው፡፡
በእርግጥ ይህን ለማድረግ አሁን እንደምንመለከተው ፈተናው ቀላል አይሆንም፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያዊያን አክራሪ ብሔርተኝነትን እየተላበስን የመጣን ሆነናል፡፡ ሁሉም ብሔርና ዘሩን ፈላጊ እየሆነ በመሄዱ የዜግነት ፖለቲካ ፈተና ሆኗል፡፡ ይህ አካሄድም የጋራ ቤትና በታሪክ “የእኛ” ስንላት የኖርናትን አገር ለልጆቻችን ስለማስተላለፋችን ዋስትና የሚያሳጣ በመሆኑም ትግል ሊደረግበት የግድ ነው፡፡ ይህን በእኩልነትና ዋስትና በሚሰጥ ፍትሐዊነት አለመቀየርም የዚህ ትውልድ ውድቀትና ሽንፈት ከመሆን ውጪ አይሆንም፡፡
አሁን ማን ይሙት የሕወሓታዊያኑ መንገድ የሆነው የብሔር ፌዴራሊዝም አዋጭና ዘላቂ የአገር አንድነት የሚያስከብርና የኖረውን የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ ጥያቄ የሚፈታ ቢሆን “ተለወጥን!” እያልን ይህን ያህል አገራዊ ትርምስ በዚች ምድር ይታይ ነበር? እስኪ በጥሞና እናጢነው፣ እንመርምረው፡፡ የዘር ፖለቲካ አንድነታችንን የሸረሸረ ብቻ ሳይሆን፣ ፈጣኑን የልማት ጉዞም እየደፈቀ የመሆኑ ጉዳት እስካሁን ያልተሰማውና ዋስትና ያላሳጣው ዜጋስ ይኖር ይሆን? በጥላቻና በተካረረ መንገድ ከመጠላላት የማያስወጣ ብልሹ አካሄድ መሆኑስ ማን ሊክደው ይችላል?
በአጠቃላይ ከትግራይ ሕዝብ አልፎ የአገራችን ሕዝቦችን በወቅቱ ያማለለና በአጋርነት ያሠለፈው ሕወሓት፣ አሁንም ቢሆን ከተጣበቀበት የዘር ፖለቲካና የጠባብ ብሔርተኝነት አዙሪት የመላቀቅ ዕድሉ ዝግ አይደለም፡፡ ከጥላቻ ትርክትና በርከት ያሉ ዓመታትን ከተሻገረ የብሔር አጀንዳ ወጥቶ አገራዊና ፌዴራላዊ የፖለቲካ ትግል መሥርቶ፣ ለአዲሱ ትውልድ የማስረከብ ታሪካዊ አደራ የወደቀበት ኃይልም ነው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን፣ ተከታዮቹም መካከለኛውን ፍትሐዊ መስመር እንዲጨብጡ ታግሎ ከመታገል ይልቅ፣ በተለመደው መንገድ ብረት ነክሶ ወይም በተፅኖ አስፈራርቶ የኖረበትን መንገድ ልከተል ካለ በቀዳሚነት ውድቀቱ የራሱ ነው፡፡
ሕወሓት የመሠረተው የብሔር ጭቆናን የሚያላቅቅ የተባለ የብሔር ፌዴራሊዝምን አስተሳሰብ ዓለም እየተወው፣ የአገራችን ጠባብ ብሔርተኞች ጭቦ እንዳይሠሩበትም በፅናት መታገሉ ነው የሚጠቅመው፡፡ ይህን ካላደረገ በቀዳሚነት የትግራይ ሕዝብ፣ ሲቀጥል መላው የአገሪቱ ሕዝብ መመከትና መታገል ይኖርበታል፡፡ ሁላችንም እንደሚቆጨው ዜጋ በእዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳብ መስጠት የሚያስፈልገን፣ የችግሮቹ ሁሉ ሰንኮፍ ከዘር ፖለቲካና ከሕወሓታዊያን መንገድ ጋር የተያያዘ በመሆኑና ስለማያወጣን ብቻ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡